Saturday, 05 October 2013 10:26

“የብርሃን ፈለጐች”ን ተከትለን ስንጓዝ

Written by  ከጲላጦስ
Rate this item
(4 votes)

              መነሻ

             ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የበኩር ሥራው የሆነውን “አጥቢያ” ለአንባብያን ካደረሰበት ከ1999 ዓ.ም በመነሳት፣ ስምንተኛ በረከቱ አድርጐ ባለፈው ነሐሴ ወር እስካቀበለን “የብርሃን ፈለጐች” ድረስ የጊዜ ቆጠራ ብንይዝ፣ ስድስት ዓመታት በመካከሉ ተዘርግተው እናገኛለን፡፡ ስምንት መጽሐፍት በስድስት ዓመታት አንብቦ የጨረሰ ለማግኘት ፍለጋው አድካሚ እየሆነ ለመምጣቱ በርካታ ትችቶችና አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየነፈሱ፣ ትውልዱን በሚገልቡበት ዘመን፤ አለማየሁ ማህፀኗ ለምለም እንደሆነች ሴት (አንዳንዶቹን በመንታ ሂሳብ) ስምንት ደርሰውለት ስመለከት ስለመንፈሱ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ስለመሰጠቱም ጭምር አድናቆቴን እቸረው ዘንድ ግድ ይለኛል፡፡ ይኸ አድናቆቴ ሽቅብ እየጨመረ እንዲሄድ የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ደራሲው ከድርሰት ምጡ የተረፈ ትንፋሽ መሰብሰቢያ ጊዜውን ሳያቋርጥ ለሚጽፋቸው የጋዜጣና የመጽሔት ኪናዊና ማኅበራዊ ሀተታዎችና ትችቶች የማዋሉ እውነታ ነው፡፡

እነዚህ የጋዜጣና የመጽሔት መጣጥፎችም ቢሆኑ ጠንካራ የብዕር ሰው መሆኑን የሚያረጋግጡልን የተመረጡ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትችቶች ከመሆን ባሻገር፣ በአንድ ጥራዝ “ኢህአዴግን እከስሳለሁ” በሚል ርዕስ ስድስተኛ ልጁ አድርጐ ተገላግሎ አቅርቦልናል፡፡ የዚህ በዋነኛነት በግል አስተያየትና ምልከታ ላይ ተመስርቶ የቀረበ ጽሑፍ ዓላማ፣ የደራሲውን ቀደምት ሥራዎች የመገምገምም ሆነ የመቃኘት አቅጣጫን የተከተለ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከአንድ ወር በፊት ለንባብ የበቃውን “የብርሃን ፈለጐች” የተሰኘ መጽሐፉን አንኳር ሃሳብ (ጭብጥ) በራስ ብርሃን ታግዞ ለመፈተሽና እግረ መንገድ ትውልዱን በአደባባይ እየገለበ ለሀፍረት እየዳረገው የሚገኘውን ከንባብ የመጣላት ትችት በዚህ መጽሐፍ እንዲያለዝብ ለማበረታታት ነው፡፡

በተለይም እንዲህ እንደዛሬው የኑሮ ዳገት መውጣትና የማኅበራዊ ሕይወት ፈተናችን ሽቅብ፣ ሽቅብ በሚያስተነፍሰን ሰዓት ላይ ቆመን፣ ደራሲው እንደቀደሙት ሁለት መጽሐፍቱ (አጥቢያ እና ቅበላ) የዚህች ሀገር እውነተኛ መገለጫ ከሆኑት ከምንዱባን ዜጐቿ ሕይወት እየቆረሰ መራብ፣ መታረዝ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ መባከን እና የመሳሰሉትን በቃላቱ ኃይል አብስሎ ካቀረበልን ማዕድ ሳንቋደስ ብንቀር፣ ራስን በመካድ ጠኔ ለመሰቃየት የመፍቀድ ያህል ይሆንብናል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ “የብርሃን ፈለጐች” ይሁን እንጂ የደራሲውን ቀደምት ሁለት ልብ ወለድ ሥራዎች ከግምት የከተተ አንድ መሠረታዊ ጉዳይ በዚህ መነሻ ሥር አስቀምጦ ማለፍ ደግሞ የተገባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ይኸውም ከደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የስድስት ዓመታት ስምንት መጻሕፍት መካከል የረዥም ልብ ወለድ ባህርያትን ይዘው የቀረቡልን ሦስት ሲሆኑ ደራሲው በእነዚህ ሦስት መጻሕፍቱ ዋነኛ የታሪክ መሽከርከሪያ አድርጐ የሚያስነብበን ጭብጥ የሚፈልቀው ከድሀ ኢትዮጵያውያን ሕይወትና ከድህነት መንደራቸው የተቆረሰ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የደራሲው ምጥ ስለ ድሆች በመቃተት የተያዘና ብዕሩም በእነሱ ደም ሞልቶ በወረቀቱ በማፍሰስ የተገላገለው ይመስላል፡፡ ለዚህ አባባል ማስረጃዬን ከሦስቱም መጻሕፍቱ አንድ ሰበዝ እየመዘዝኩ ላቅርብ፡- የደራሲ አለማየሁ የበኩር ልጅ የነበረችው “አጥቢያ” የታሪክ ምስረታ አራት ኪሎ እንዲህ እንደዛሬው ባድማ ከመሆኗ በፊት ከምትታወቅበት ሥጋ ቤቶቿ ጀርባ አንስቶ ቁልቁል እስከባሻ ወልዴ ችሎትና እንዲሁም በዙሪያው ለረዥም ዓመታት ኑሮውን መስርቶ እስከቅርብ በነበሩ ዓመታት የዘለቀውን ኢትዮጵያዊ ድሀ ማንነትና ምንነት አንባቢው በግርምት እስኪዋጥ በብዕሩ ያስቃኘበት ነበር፡፡

የከመረውን ምግብ ሲንድ፣ ያሻውን መጠጥ ሲያማርጥ፣ በለበሰው ጨርቅ ሲበላለጥ፣ በሚነዳው ተሽከርካሪ ሲደናነቅ ውሎ በሚያድረው የአዲስ አበቤው አንድ ዓለም መካከል “አጥቢያ” መከራና ችግር ያደቀቃቸው ነፍሶች የሚኖሩባትን ሌላ ዓለም እየመዘዘች፣ በየፈርጁ ስታቀርብልን፣ እምነት የለገሰችንን የገነትና ገሃነም ሁለት ዓለምነት ሽራ፣ በአንዲቷ ከተማችን የሚገኙ ሁለት አጥቢያዎች የመሆናቸውን እውነት እስከመቀበል አድርሳን ነበር። የአጥቢያ ታሪክ የተመሰረተበት መንደር በደራሲው ብዕር እንዲህ ተስላለች፡- “…የኛ ሰፈር ልጆች እንደዛፍ ዕድገት ወይም እንደንጋትና ውድቅት ድንበራቸውን ሳትለይላቸው አድገው፣ ጐርምሰውና በስተመጨረሻ ወድቀው ታያቸዋለሽ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ካልተለዩዋቸው ለውጣቸው ልብ ሳይባል ነው የሚከናወነው፡፡ አንድ ቀን ተወልዷል፣ አንድ ቀን አድጓል፣ አንድ ቀን አስፋልት ወጥቷል፣ አንድ ቀን ሰክሮ ታይቷል፣ አንድ ቀን ጫት ቅሞ ተስተውሏል፣ አንድ ቀን ታስሯል፤ አንድ ቀን ችግር ጠንቶበት ታይቷል፤ አንድ ቀን ታሞ ተጠይቋል፣ አንድ ቀን ሞቷል…ይሄ የአብዛኛው የሰፈራችን ልጆች አጭር የሕይወት ታሪክ ነው፡፡” (ገጽ 35) መንደር ሰው ነው፡፡

መንደር የነዋሪው ማንነትና ምንነት መገለጫ ነው፡፡ መንደር የሰው ልጅ በሕይወቱና በኑሮው ተውኔት የሚሰራበት መድረክ ነው፡፡ ደራሲው ደግሞ ይኸን እውነታ በሚገባ ከሚያውቃት አንዲት መንደር በመነሳት፣ ለዓመታት በመከራቸው ከገነቧት ሰዎች ሕይወት አንፃር የስዕል ያህል አስቀምጦ አሳየን፡፡ ድህነት የፈጠራቸው ሽርሙጥና፣ ስካር፣ ረሃብ፣ እርዛት፣ ሐሜት፣ ጭካኔ፣ ጥላቻ…የነዋሪዎቿ “ጌጥ” የሆኑባትን መንደር የታሪኩ ማጠንጠኛ በማድረግ፣ ብዕሩን ያሟሸው ደራሲ አለማየሁ፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ቀጣዩን መጽሐፉን “ቅበላ”ን ይዞልን ሲመጣም እንዲሁ ምርጫው ያደረገው ሌላዋን የድህነት እምብርት ጨርቆስን ነበር፡፡ “መንደራችን በዛ መሬት ላይ ስለተቆረቆረች ልምላሜ አጥቶ እንደተንቀፈረረ ሠፊ የወይን እርሻ እርጥበትና ድምቀት የሸሿት ናት፡፡ በዋል ፈሰስ የሆኑት የውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ ከሕይወት የተፋቱ የወይን ሀረግ ይመስላሉ፡፡ የቤቶቹ ክዳኖች ችምችም ብለው በመካከላቸው የሚታዩት ክፍተቶች ቀጭንና ጥልቅ ሆነው የመሬት ንቃቃት ያስታውሳሉ። ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ ዓይን የሚሰብ እንቅስቃሴ የለበትም፡፡

ረሃብ ገብቶ ሁሉም ደጃፉን ለመክፈት እንደየክቴ አቅም ያጣ እየመሰለኝ ይጨንቀኛል። ህይወት የተረታች፣ የሰው ልጅ ያበቃለት ያህል ስለሚሰማኝ የሁሉንም ደጃፍ እየቆረቆርኩ የሞትን አዚም መረበሽ ያሰኘኛል፡፡” (ገጽ 7) ደራሲ አለማየሁ፤ የድርሰቱ ታሪክ የኋለኛ ጉዞ ወደየትኛውም አቅጣጫ ይጓዝ የገፀ ባህርዩ መነሻና አስተሳሰብ እንዲሁም እምነት (በአጭሩ ስነ ልቦናዊ አቋም በማለት ልንገልፀው እንችላለን) መፍለቂያ ምንጩ ግን ከአንድ እውነት እንዲሆን አስቦና ተጨንቆ ለመድከሙ እርግጠኛ መሆን የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ይኸ እውነት ደግሞ ድህነት ነው። ደራሲው በ”ቅበላ” ውስጥ እንደቀደመ ሥራው መንደሩን በነዋሪዎቿ ማንነት ላይ መስርቶ ከመግለጽ ይልቅ የወደቀና የፈረሰ ግዑዙን አካሏን እያስጐበኘን፣ ነዋሪዎቿን ደግሞ ለእኛ የምናብ ምስል የተወልን ሆኗል፡፡ መንደር ሰው የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው፡፡ በአለማየሁ ብዕር የተቀረፀችው የጨርቆስን መንደር በወጉ ለጐበኘ፣ የውስጧ ነዋሪዎች የሕይወት እውነት ላይ መድረስ የሚከብደው አይሆንምና፡፡ ይኸ እውነት ደግሞ ድህነት ነው፡፡

ደራሲ አለማየሁ “ቅበላ”ን በ2001 ዓ.ም ካበረከተልን በኋላ በሌላ የረዥም ልብወለድ ሥራ ተመልሶ ብቅ ያለው እንግዲህ አራት ዓመታትን ተሻግሮ ባለፈው ነሐሴ ወር 2005 ዓ.ም በ”የብርሃን ፈለጐች” ነበር፡፡ ደራሲው በዚህ አዲስ ሥራውም ቢሆን የታሪኩ መሠረት እንዳለፉት ሁሉ የተጣለው በደሀና ድህነት ላይ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከቀደሙት ሁለት ሥራዎቹ የዚህኛውን የሚለየው የታሪኩ ማጠንጠኛ ሁለት መንደሮች መሆናቸው ነው እንጂ (ግንፍሌ እና ሞጆ) በተቀረ አሁንም ደሀና ድህነት ለደራሲ አለማየሁ ብዕር የቅርብ ወይም የተመረጡ የሕይወት እውነታ ከመሆን አላመለጡም፡፡ በ“የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ዋነኛው ገፀ ባህርይ የሆነው መክብብም ሆነ ሌሎቹ ገፀ-ባህሪያት አፍላ የልጅነት ሕይወታቸው የተቀረፀበትን የግንፍሌን መንደር ደራሲው በምልሰት ሲያስቃኘን ይኸው የድህነት እውነት አፍጥጦ ይመጣል፡፡ የድህነት እውነት የከበበውን የልጅነት ዘመን በ “ብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ደራሲው መለስ ብሎ ሲያስቃኘን እንዲያስታውስ ያደረገው “ዘመናዊዋና መሀል አዲስ አበባ ያለችውን ግንፍሌ ሳትሆን ገጠሬዋ እና ኋላቀሯ ግንፍሌ” የመሆኗ ጉዳይ በአንፃራዊም ደረጃ ቢሆን የተሻለ ለሚመስለው የከተማዋ የአኗኗር ዘይቤና ደረጃ ብዕሩን ፆመኛ ለማድረግ የቆረጠ አስመስሎታል፡፡

“እኛ እንግዲህ የእነዚህ ገጠር ናፋቂ የግንፍሌ ሠፋሪ ልጆች ነንና ገጠሬነት በግድ ተጭኖብን አድገናል፡፡ ለጮቃችን፣ ለሙጃሌያችን፣ ለቀጭአችን፣ ለፎረፎራችን፣ ለላሻችን፣ ለቆረቆራችን፣ ለጭርታችን፣ ለእከካችን፣ ለፎከታችን…ወላጆቻችን መፍትሔ አድርገው የሚያቀርቡት ከወላጆቻቸው የወረሱትን ባህላዊ የህክምና ዘዴ ነው፡፡ እንቅፋት ሲመታን የሸረሪት ድር እንደመድማለን፣ ሆዳችንን ሲቆርጠን የበር ፍቅፋቂ በውሃ ተበጥብጦ እንጠጣለን (ወይም አረቄ በስኳር)፣ እራስምታት ሲያጣድፈን መሬት እየጠቆምን የወጋንን ቦታ ነካ ነካ በማድረግ “ቀደምኩ” እንድንል እንመከራለን፣ ጉሮሮአችን ሲታመም አር ላይ ስለተፋን በመሆኑ “አር ማረኝ” በሉ እንባላለን፡፡ ጉሮሯችንን እንቧጠጣለን፣ ግጋችንን እንነቀላለን፣ ወሸላችንን እንገረዛለን፣ እንጥላችንን እንቆረጣለን፣ አይናችንን እንቆራለን፣ ቅንድባችንን እንበጣለን…የመድኃኒቱ ብዛት ስሩ፣ ቅጠሉ፣ ሃረጉ፣ ፍሬው…እንስላል፣ ጡንጁት፣ ምች መድኒት፣ ድንገተኛ፣ ግራዋ፣ ሬት፣ አመድ፣ ጋዝ፣ ቤንዚን…” (ገጽ 42) መንደር ሰው ነው፡፡ መንደር በውስጧ በሚገኘው የሰው ልጅ ሕይወት፣ አኗኗር፣ እምነት፣ ፍላጐት፣ አቅም…ተቀርፆ የምትታይ ብቻ ሳትሆን እሷም በተራዋ በውስጧ የሚበቅሉትን እምቦቃቅላዎች፣ የቀደሙት በቀረፁት ማንነቷ ልክ ሰርታ የምታሳይ ዓለም ነች፡፡

መነሻውን “ግንፍሌ” በማድረግ የታሪኩን ቀጣይ ሥፍራ “ሞጆ” ላይ የሚያጠነጥነው “የብርሃን ፈለጐች”፤ ሰፊው የታሪክ ጉዞ የተመሠረተባት ሞጆም ብትሆን እንዲሁ በነዋሪዎቿ የድህነት ሕይወት ከመገለጥ የዘለለች አልሆነችም፡፡ የታሪኩ ዋና ገፀባህርይ (መክብብ) በሞጆ የተሻለ የሚባልና ከድህነት ያመለጠ የአክስቱ ቤት ሕይወት ቢጠብቀው እንኳን እሱ ግን የውሎና አዳሩ ምርጫ ያደረገው ከመንደሪቱ ምንዱባኖች ጋር ነበር፡፡ ግንፍሌ በድህነት ማንነቷ የቀረፀችው ነውና በሞጆም የተለየና አዲስ ማንነት ሳያበቅል፣ ከድሆች ጋር መንደሮቿን በዚሁ መንፈስ ያስሳል፡፡ እነ ጦጤ፣ ጠኔ፣ ንዳዴ፣ ናፍቆት፣ እና ሌሎቹ የሞጆ ፍሬዎች ከመክበብ ጋር ሆነው መንደሪቱን ሲያሳስሱን ከግንፍሌዎቹ ጋሙዳ፣ ጋንጩር፣ መስፍን ሴንጢ፣ ወይም ከማናሉ እና ከይጋርዱ ቂጦ የቀጠሉ የድህነት መንፈሶች ሆነው ይመጡብናል፡፡ እንግዲህ የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የፈጠራ ድርሰቶች የሆኑት ሦስቱ ሥራዎቹ በዋነኛነት የተመሠረቱበትንና የሚያመሳስላቸውን አንድ እውነታ ለመነሻ ይሆነን ያህል እንዲህ ከመዘዝን በቂ ይመስለኛል፡፡

ደራሲው በልብ ወላጆቹ ውስጥ እንዲህ ደህና ድህነት ላይ የተመሠረተ ሕይወት በዋነኛነት ማጠንጠኛው ያድርገው እንጂ የዚያኑ ያህል የማይካድ አንድ እውነት ደግሞ ስለእሱ አስቀምጦ ማለፍ ይቻላል፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ስሜት አጨፍግጐና አኮፋትሮ እንዲህ መራርነት የሚፈጥረው ድህነት፣ በአለማየሁ ብዕር ተዋዝቶ ሲቀርብ በሐዘን ውስጥ ደስታን፣ በእንባ ውስጥም ሳቅን የመፍጠር ኃይል መላበሱ ነው፡፡ ገፀባህርያቱ ድሆች ቢሆኑም ትወዳቸዋለህ እንጂ አትጠላቸውም፤ ታከብራቸዋለህ እንጂ አትንቃቸውም፡፡ ከኢትዮጵያዊው ማንነት ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱና የሚወክሉ ናቸውና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ እኛነታችንን እንድናገኝባቸው አንቸገረም፡፡ በ“የብርሃን ፈለጐች” ውስጥ ለመጓዝ ስንነሳም የመንገዳችን ስንቅ አድርገን የምንቋጥረው ይህን ዘመንና ትውልድ በአንድ መልኩ የተመለከትንበትን የደራሲውን ምናብ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ (ይቀጥላል)

Read 2562 times