Saturday, 05 October 2013 10:21

የወርቃማው ዘመን አመለካከት

Written by  ቱዋ (ጋርጋንቱዋ)
Rate this item
(2 votes)

                   አንድ አማራጭ አፈታሪክ ስለ ወርቃማው ዘመን እንዲህ ይላል፡- “እግዜር በራሱ እጅ የፈጠራቸው ሰዎች ወርቃማው ዝርያ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ሞት የሚያሸንፋቸው (mortal) ቢሆኑም፤ ኑሯቸው ግን እንደፈጣሪያቸው ያለ ሀዘን እና ስቃይ… ሰርክ በደስታ ነበር፡፡ የህይወት ውጣ ውረድ የሌለባቸው፣ ለመኖር መልፋት የማያሻቸው ነበሩ፡፡ አፈሩ ያለ እነሱ አፈር መግፋት በራሱ ፍሬ ያፈራል፡፡ ትርፍ ፍሬ፡፡ ከብት እና የጋማ እንስሳት የበዙላቸው በሁሉም ረገድ በረከት ያላቸው ነበሩ፡፡ የሞታቸው ሰአት ሲደርስ የሚለብሱት አፈር ወደ ንፁህ መንፈስ የሚለውጣቸው የሰው ዘር ተጠሪ ነበሩ” ነገር ግን፤ የእነዚህ የወርቃማ ዝርያዎች ፈጣሪ፤ በወርቅ እጁ በሰራው ነገር ረክቶ መቀመጥ አልፈለገም፡፡ ከወርቅ ቀጥሎ በተለያዩ ረከስ ባሉ ብረታ ብረት ቀጣይ ትውልዱን እየቀጠቀጠ መስራት ጀመረ፡፡

ከወርቅ ወደ ብር፣ ከብር ወደ መዳብ…ከመዳብ ወደ ብረት፡፡ በደረጃ ዝቅ እያደረገና እየለዋወጠ፡፡ የብር ዘመን ፍጡራን ከወርቁ በጣም ያነሱ ነበሩ፡፡ የማሰብ ብቃታቸውም የደከመ ነው፡፡ እርስ በርስ ከመጐዳዳት ሊቆጠቡ የማይችሉ በመሆናቸው… ዘመናቸው ሲጠናቀቅ ከምድር መዝገብ ላይ ተፋቁ፡፡ መንፈሳቸውም ከሞታቸው በኋላ ህያው ሆኖ መኖር አልቀጠለም፡፡ ከብር ተከትሎ የመዳቡ ትውልድ መጣ። የመዳቡ ትውልድ፤ በአካል በጣም ጠንካራ፣ በመንፈስ ግን ደካማ በመሆኑ ከጦርነት የበለጠ የሚወደው ነገር አልነበረውም፡፡ ጭካኔ መገለጫቸው ነበር፡፡ ጭካኔያቸው ለመተላለቃቸው ምክንያት ሆናቸው፡፡ ግን “ለበጐ ነበር” ከመዳቡ ዘመን እና ትውልዱ በኋላ፤ ለአጭር ጊዜ ተከስቶ የነበረ ትውልድ የተሻለ ተስፋ እንዲታይ መንገድ ከፈተ፡፡

ይህ ለአጭር ጊዜ ተከስቶ የነበረ ትውልድ እንደፈጣሪያቸው በግብር እና በመንፈስ የተመሳሰሉ ነበሩ፡፡ በጀግንነት የተሞሉ ናቸው፡፡ ጀግንነታቸው ግን መልካምን ለመደገፍ፣ መጥፎን ለመቅጣት እንጂ ለክፋት የሚተባበር አልነበረም፡፡ ትውልዱ በጊዜው ሲያልፍም ዘመኑ ላይ የነበረ በሙሉ፣ ከፍ ካለው ስፍራ ተባርኮ እንዲቀመጥ ሆኗል (ይላል አማራጩ አፈ-ታሪክ) አምስተኛው ትውልድ የብረት ልጆች ናቸው። ተፈጥሮአቸውም ሆነ ዘመኑ የረከሰ በመሆኑ ከእርኩስ ተግባር ውጭ ቢፈልጉም ሊፈጽሙ አይችሉም፡፡ የልፋታቸውም ውጤት ሁሌ ሀዘን የሚፈጥርባቸው፣ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ ነበሩ፡፡ የእነሱም ትውልድ አለፈ፡፡ ካለፈም በኋላ ዘመን ዘመንን ሲተካ የሚመጣው ውጤት በአንድ አጭር አረፍተ ነገር ለሁልጊዜም እንዳይቀየር ሆኖ ተፃፈ:- “ትውልድ መጥቶ ትውልድ ሲሄድ ኋለኞቹ ከፊተኞቹ የባሱ ይሆናሉ፤ ልጆችም ከአባቶቻቸው ዝንተ አለም የተሻሉ አይሆኑም” የሚል እርግማን መሰል ህግ፡፡ ይህንን አፈ - ታሪክ ተንተርሼ ወደ አሁን እና ዛሬ ወይንም ወደራሴ ልመለስ፡፡ ልመለስና በዚሁ መንደርደሪያ ስለወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ ምንነት ላሰላስል፡፡ የራሴ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ልሞክር፡፡

ከላይ የቀረበው አፈታሪክ ከግሪክ አፈታሪክ አማራጭ ትርክቶች አንዱ ነው፡፡ ታሪኩ ከሌሎች ሀይማኖታዊ ወይንም ሐሪሶታዊ አመለካከት ጋር ቅርርብ ቢኖረውም፤ በዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ግን ታሪኩን የሚወስደው እንደ ተረት ነው፡፡ “ለምሳሌ” የሚሆን ተረት፡፡ ወርቃማው ዘመን የሚወክለው የሰው ልጅን “ምልዑነት” ነው፡፡ ሙሉነት ድሮ ላይ ቀረ ወይንስ አሁንም አለ? አሊያም ወደፊት ይደገማል? በሚል የጥያቄ አቅጣጫ ጉዳዩን መመልከት ነጥቡን ወደዘመንኛ ፍለጋችን ወይንም ፍላጐታችን እንዲጠጋ ማድረግ ነው፡፡ ሁላችንም የሚያስማማ አንድ ነጥብ ግን አለ። ይኸውም ማንም ትውልድ ወይንም በማንም ትውልድ ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ እንደ ወርቃማው ዘመን የሚቆጥረው የድሮ ታሪክ አለው፡፡ ግለሰቡ ከህይወት ዘመኑ አንዱን ወቅት እንደ “ሙሉነት” አድርጐ የሚቆጥረው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፤ የወጣትነት ዘመኑን እንደ “ወርቃማው ጊዜ” ይቆጥረዋል፡፡

ወይንም ከወጣትነቱ ውስጥም (ለምሳሌ ዘፋኝ ከሆነ) “የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙን” የለቀቀበትን ጊዜ፣ ወይንም ሚስቱን ያወቀበትን ጊዜ፣ ጥሩ ትንፋሽ ያለው ሯጭ የሆነበትን ጊዜ…ወዘተ… ዋናው ነገር ግን በግለሰቡ የህይወት ዘመን ውስጥ ወርቃማው ጊዜ ሁሌ “እዚህ እና አሁን” ላይ ወይንም ወደፊት ላይ የሚገኝ ሳይሆን፤ ትላንት ወይንም ድሮ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ልክ በአፈ ታሪኩ ላይ ልጆች ሁልጊዜ ከአባቶች ያነሱ ናቸው እንደሚለው… ለግለሰቡ ደግሞ… ዛሬ ሁልጊዜ ከትላንት ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው፡፡ ይህ ትላንትን የተሻለ አድርጐ በመቁጠር ዛሬን የሚያሳንስ ስሜት ወይንም አስተሳሰብ “የወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ” ተብሎ ይጠራል። አስተሳሰቡን የሚያራምደው ሰውም “የወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ (Delusion) ተጠቂ” ይባላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ግን በታመመ ወይንም አመለካከቱ በተቃወሰ ሰው ላይ ሳይሆን በተለይ ጤነኛ ነን በሚሉት ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ የአመለካከት ቀውሱ እንደ ጤናማ አመለካከት ይቆጠራል፡፡

ይሄንኑ አመለካከት በማንፀባረቅ ባለቅኔዎች፣ የማህበረሰብ አይን ገላጮች፣ የሥነ ምግባር መርህ አስተማሪዎች…የወርቃማውን አመለካከት ያግዙታል፡፡ እገዛውን የማይፈልግ ትውልድ የለም፡፡ ሁሉም ነጠላ ግለሰብ፣ በግለሰቦች ጥርቅም የሚሰራ ማህበረሰብ ወይንም በዘመን ሂደት ግለሰብ እና ማህበረሰብን ከቀድሞው ወደ አዲሱ የሚያሸጋግር የትውልድ መዘውርም የሚሰሩት “በወርቃማው ዘመን” አስተሳሰብ ነው፡፡ የልጅነት ዘመን ወርቃማ የማይሆንበት ማንም የለም፡፡ ወርቃማ የሚሆነው ግን ልጅየው በልጅነት ዘመኑ ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ አይደለም፡፡ የራስ ወጣትነትም ወርቃማ ቀለም ማምጣት እንደጀመረ የተሰማው የእድሜው ባለቤት ካለ… ከወጣትነት እየወጣ መምጣቱን ማወቅ ይገባዋል፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን የሚኖር ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤ ወርቃማው ዘመን ለኢትዮጵያ ታሪክ የቱ እንደሆነ ቢጠየቅ… በእርግጠኝነት “የእምዬ ምኒልክ” ወይንም አሁን የቆምኩበት አይልም፡፡ አሁን የቆመበትን ድሮ ተቁሞበት ከነበረው ጋር ነው የሚለካው፡፡

ሲለካው ደግሞ በመሠራት ላይ ያለው ታሪክ ተሠርቶ ካለቀው ጋር አይመጣጠንም፡፡ “ልጅ አባቱን መቼም እንዳያክል ሆኖ ተረግሟል” እንዲል አፈ - ታሪኩ፡፡ ግን ልጅ የአባት ፈጣሪ ነው፡፡ ልጅ ባያድግ አባት አይፈጠርም፡፡ የ“ወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ”ን በትውልዶች መሀል እንፈልገው ካልን የምናገኘው አዳም ላይ ነው…አዳም እና የኤደን ገነት ቆይታው የወርቃማው ጊዜ እኩያ የለሽ መወከያችን ነው፡፡ በግለሰብ የህይወት ስንዝር ርዝመት ውስጥ ወርቃማውን ፈልጉ ስንባል “ህፃንነት ብቻ ነው ሊስተካከል የሚችለው” ማለታችን አይቀርም፡፡ የዋህነቱ፣ ለእውቀት መጓጓቱ፣ ግልጽነቱ፣ እውነትን ያለ ምክንያት ሆኖ መገኘቱ፣ ደስታው…ወዘተ፡፡ ግን ህፃንነትንም ከእናት ማህፀን ቆይታ ጋር ካነፀርነው ወይንም ካወዳደርነው …ወርቃማው ጊዜ የእናት ማህፀን ሆኖብን ቁጭ ይላል፡፡ የእናት ማህፀንን እንደ ገነት ቅጽር የሚያዩት አሉ፡፡ አዳም የወርቃማው ዘመን ሰው ከሆነ፣ የገነትን ቅጽር እንደ ጨቅላው መውለድ ትቶ ከወጣ በኋላ የሚያመራው በተቃራኒ አቅጣጫ እስከሆነ ድረስ… ድሮን መልሶ ሊያገኘው አይችልም፡፡ አዳም ከወርቃማው እየራቀ ወደ ብሩ እያደገ… ከብሩ ወደ መዳቡ እየተሸጋገረ… ብረት ላይ ይደርስና…ከዛም ቀጥሎ ይጓዛል፡፡ እስከሞቱ ድረስ።

እስከተወለደ ድረስ መሞቱ አይቀርም። ከገነት ባይባረር ኖሮ አይሞትም ነበር፡፡ ገነት ድሮውኑ ያረገዘው… ሊወልደው ፈልጐ ነው፡፡ አዳም አሁን የሆነውን… ከድሮው ጋር እስካነፃፀረ ድረስ፤ የሀዘን፣ የስቃይ እና የመሳሰሉት የመውረድ እና የመዝቀጥ ስሜቶች ይፈራረቁበታል። ከእነዚህ ለመሸሽ ያለው እድል “ወርቃማውን ዘመን” እያመለከ መቆየት ነው… የወርቁን ዘመን አስተሳሰቡን ይዞ አዳም በትውልዶች ውስጥ ሳይቀየር መቀጠሉ ይገርማል። ዘመኑ እንጂ እሱን ሲቀይር የሚታየው፣ እሱ ዘመኑ ላይ ምንም አቅም ያለው አይመስልም፡፡ አቅም ቢኖረውማ “ወርቃማውን ዘመን” ከማለም… ህልሙን ወደ እውነታ ይቀረው ነበር፡፡ በዛው የአማራጭ አፈታሪክ ውስጥ የወርቃማውን ዘመን እንዳይደገም ያደረገው፣ ፈጣሪ በወርቃማው ዘመን ሴቶችን ስላልፈጠረ ነው። በቀጣይ በመጡት (የመዳብ፣ ድንጋይ…ወዘተ) ዘመናት ሴቷ ከአዳም ጋር ነበረች (ተፈጥራለታለች/በታለች)፤ ይላል ትርክቱ። (ይህም አመለካከት የወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ መሆኑን አትዘንጉ፡፡ ወንድ ብቻውን ይነግስ እና ይገስስ የነበረበት ዘመን ውስጥ የሴቷ ቦታ ኢምንት ወይንም ባዶ የሆነበትን ጊዜ መመኘቱ እና ባለማግኘቱ የተሰማው የቁጭት አይነት ነው!” የወርቃማ ዘመን አስተሳሰቡ፤ አምስት ዶሮን በአምስት ሳንቲም በድጋሚ የሚገዛበት ወርቃማ ዘመን እንዲመጣለት ቢያስመኘውም…ወቅታዊው የብር ዘመን አስተሳሰብ… ብር እንዲሰራ እና ዘመኑን እንዲመስል ያደርገዋል፡፡

የብረት ዘመን አስተሳሰቡ ደግሞ በብረት የተሰሩ ማሽን እና ኢንዱስትሪ እንዲያቋቁም ያስገድደዋል፡፡ የድንጋይ ዘመን አስተሳሰቡ፣ ድንጋይን እንደወርቅ አቅልጦ ግዙፍ ሃውልቶች እንዲያቆም እንዳደረገው ሁሉ…የዲጂታል ዘመን አስተሳሰቡ ደግሞ በኮምፒውተር አማካኝነት ህይወቱን እንደአስፈላጊነቱ ወይንም አስገዳጅነቱ እንዲቀርጽ ይጠይቀዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን አብዮቱ ግራ ያጋባው፣ የግብርና አብዮት ዘመን እይታ ወደ ድንጋይ ወይንም የመዳብ ዘመን የእናቱ ማህፀን መመለስ ባይችልም…በምኞት መመለስ እንዲችል የወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ ስንቅ ይሆነዋል፡፡ …በመጨረሻም “የወርቃማው ዘመን አስተሳሰብ” የአመለካከት ስህተት ተደርጐ መወሰድ የለበትም፤ እኔ እላለሁ፡፡ “የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” እንዲሉ (ጐልዲሎካዊያን)፤ እኔ ደግሞ “የኋላው ላይ የሙሉነት ምሳሌ ከሌለ የወደፊቱ ላይ ሙሉነትን ለመፈለግ መጓዝ አንችልም” እላለሁ፡፡ ምናልባት ወደፊት የሄድን መስሎን…የኋላውን ፍለጋ ብንወጣም…ያረጋገጥነው መድረሳችን በእርግጠኝነት ሊካድ የማይችለው… እና በእጃችን በእርግጠኝነት የጨበጥነው “አሁንን” ብቻ ነው፡፡

Read 2842 times