Saturday, 05 October 2013 10:17

የአበሻ ወንዶች ኑሮ በሳዑዲ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

              …ወደ ሳውዲ ያቀናሁት ለአንድ ድርጅት በሾፌርነት ለመቀጠር በመጣልኝ ቪዛ ነው። እዛ ከገባሁ በኋላም በሥራዬ አጋጣሚ ከብዙ አበሾች ጋር ለመገናኘትና ለመተዋወቅ በቃሁ፡፡ አብዛኛዎቹ ወደ ሳውዲ ከገቡ ከሦስት ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል። ኑሮአቸው እጅግ የተደላደለና የቅንጦት ነው፡፡ እኔ ተቀጥሬ የምሰራበት ድርጅት ባለቤት የሚያሽከረክረውን አዲስ ሞዴል መኪና እነሱም ያሽከረክራሉ፡፡ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ቢሰሩ ነው ኑሮአቸዋውን አሸንፈው ለዚህ ሁሉ ሀብት የበቁት እያልኩ በጣም እገረም ነበር። የሚሰሩትን ሥራና ሞያቸውን ስጠይቃቸው፤ አንድም ቀን አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተውኝ አያውቁም። እጅግ ከሚያማምሩ አበሻ ሴቶች ጋር በየምሽቱ ሲዝናኑ አያቸዋለሁ፤ በየመዝናኛው ሥፍራ የሚመዙትን ሪያድ ስመለከት እደነግጣለሁ፡፡

እኔ ወር ሙሉ ሰርቼ የማገኘውን ደመወዝ እነሱ ለአንድ ምሽት ግብዣ ሲያወጡ ማየቱ ምንኛ ያስደነግጣል መሰለሽ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ የሚሰጣቸው ከበሬታ ልዩ ነው፡፡ አበሻ ሴቶች እነዚህን ወንዶች ለማጥመድ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ልጆቹ ምን እንደሚሰሩ ደረስኩበት፡፡ በሳውዲ በሚኖሩ አበሾች ዘንድ እጅግ የከበረ ስምና ዝና ያላቸው ሌቦች ናቸው። ልጆቹ ወደ ሳውዲ የገቡት እኔ በመጣሁበት መንገድ እንደነበርና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሌብነት መግባታቸውንም ተረዳሁ፡፡ ሳውዲ ውስጥ ተመችቶህ ለመኖር ከፈለግህ ወይ ስረቅ ወይ ንጠቅ ብለው ቁርጤን ነገሩኝ። እኔ ኑሮዬን ለማሸነፍ ወር እስከ ወር ለ18 ሰዓታት እየሰራሁ ስኳትን፣ እነሱ ሰፊ ጊዜያቸውን ለመዝናኛ አውለው የሚኖሩት የቅንጦት ኑሮ አጓጓኝና ከእነሱጋር መቀራረብ ጀመርኩ፡፡

ከእነሱ ጋር ይበልጥ እየተቀራረብኩ ስሄድ፣ ወር እስከ ወር ለፍቼ የማገኛትን ሪያድ ጨርሶ እንድንቃት አደረገኝ፡፡ እንደነሱ ለመሆንም አስመኘኝ። እናም ቀስ በቀስ ወደ እነሱ ሥራ ገባሁበት። የተቀጠርኩበትን ድርጅት ለቀቅሁ ሌብነቱን ጀመርኩ፡፡ ትዝ ይለኛል ሥርቆት የጀመርኩት ለሐጅና ዑምራ ወደ መካ በመጡ ምዕመናን ነው። በዚህ ወቅት ከተለያዩ የዓለም አገራት በርካታ ምዕመናን ወደ መካ ስለሚመጡ በጣም አሪፍ “የሥራ” ጊዜ ነው፡፡ አብዛኞቹ ወደ መካ የሚመጡ ምዕመናን የሞላ ኑሮ ያላቸው ሀብታሞች ናቸው፡፡ ምዕመኑ ልቡንና ሃሳቡን ወደፈጣሪው አድርጐ ፀሎት በሚያደርስበት ጊዜ ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶችና የገንዘብ ቦርሳውን በቀላሉ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የሚለብሱት ሽርጥ በመሆኑ ሥራችንን እጅግ ቀላል ያደርግልናል። ገና በመጀመሪያ የሌብነት ሙከራዬ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት ማግኘቴ “ሙያውን” የበለጠ እንድወደውና እንድገፋበት አደረገኝ፡፡

ከዛ በኋላ እኔም እንደ ጓደኞቼ ሆንኩ… ወድ መኪና ማሽከርከር፣ እንደልቤ መዝናናት ጀመርኩ፡፡ በሌብነት ለአራት አመታት ያህል ሰርቻለሁ። ብዙ አበሻ ወንዶች ሳውዲ ውስጥ በሌብነት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በተለይ በሀጅና ዑምራ ወቅት የሌቦቹ ቁጥር እጅግ ይጨምራል፡፡ አበሾቹ ከሌሎች ከተሞች እየለቀቁ ወደ መካ የሚመጡት በዚህ ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ባዋዲ የሚባል ሰፊ የገበያ ቦታ አለ። እዚህ የገበያ ሥፍራ በርካታ አበሾችን ታገኛለሽ፡፡ አብዛኛዎቹ ወደ ገበያ ሥፍራው የሚሄዱት ለሸመታ ከሚመጡ የአረብ ሴቶችና ወንዶች ለመዝረፍ ነው። የቦርሳ ንጥቂያ፣ የሞባይል ቅሚያ ሁሉ የሚታየው እዚህ ነው፡፡ የጠፋብሽን አበሻ ሁሉ ባዋዲ ውስጥ ታገኛለሽ፡፡ ወንዱ ለዘረፋ፣ ሴቷ ደግሞ አበሻ ሌቦቹን አጥምዶ ባል ለማድረግ ወደዚህ ይመጣሉ፡፡ ሌባ አበሻን ባል ማድረግ የቻለች ሴት በሣውዲ ባሉ አበሻ ሴቶች ዘንድ የተከበረች ነች፡፡ ገንዘብ እንደልቧ የምትመነዝር በመሆኑ ሁሉም ጓደኛ ሊያደርጓት ይፈልጋሉ፡፡ ሌላው ባዋዲ የሚመረጥበት ጉዳይ በዛ ሥፍራ ሁሉንም ነገር በቅናሽ መገኘቱ ነው። አረብ ሴቶች ለገበያ ወደዚህ ሲመጡ ተሸፋፍነው በመሆኑ ለሩጫ አያመቻቸውም፤ ስለዚህ ሥፍራው ለቦርሳ ነጣቂዎችም የተመቸ ነው። የሚገርምሽ ሣውዲ ውስጥ ካሉ ሥፍራዎች ሁሉ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረገውም እዚህ ቦታ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ሌቦች አዘውትረው የሚመላለሱበትና እንጀራቸውን የሚያገኙበት ሥፍራ ነው፡፡

በጣም የሚያሣዝንሽ ሞራልሽንና ህሊናሽን ሁሉ ሸጠሽ የምታገኚውን ገንዘብ ይዘሽ ወደ አገርሽ መመለስ አለመቻልሽ ነው፡፡ አበሻ ወደ አገሩ ለመመለስ የመውጫ ቪዛ ሲጠይቅ፣ በስሙ ወደ አገሩ የላከው የገንዘብ መጠን ይጣራል፡፡ የላከው ገንዘብ በርከት ያለ ከሆነ ከአገር እንዲወጣ አይፈቀድለትም፡፡ ፖሊስ “ገንዘቡን ከየት አምጥተህ ላክ” የሚል ማጣሪያ ይደረግበትና ወደ እስር ቤት ሊወረውረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ያለን አማራጭ በጣም ለሚታመኑ ሰዎች ወደ ሌላ አገር መላክ ወይም በህገወጥ መንገድ ከአገር ማውጣት ብቻ ነው፡፡ ሁለቱም ካልተቻለ በዘረፋ የተገኘውን ገንዘብ በትኖ መጨረስ ነው፡፡ ሌላ አገር ሰው ያላቸው አበሾች ግን በቀላሉ ገንዘባቸውን ወደ ሌላ አገር ይልኩታል፡፡ ለአራት አመታት የቆየሁበትን የሌብነት ሥራ ትቼ ወደ አገሬ የመጣሁት፣ እህቴ ከፈረንሳይ ወደ ሳውዲ መጥታ ገንዘቤን ይዛልኝ ስለወጣች ነው። አሁን በአገሬ የተከበረ ሥራ እየሰራሁ የተከበረ ኑሮ እኖራለሁ፡፡ ደግሜ ወደ ሳውዲ የመመለስና ወደዛ ቆሻሻ ህይወት ተመልሼ የመግባት ሃሳብ ግን ፈፅሞ የለኝም፡፡ ይህን ታሪክ ያጫወተኝ የዓመታት የሳውዲ ኑሮውን ትቶ ከወራት በፊት ወደ አገሩ የተመለሰና በሞባይል ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡

ወጣቱ የአገሩ ልጅ ከሆነው ጓደኛው ጋር ኑሮአቸውን በአገራቸው አድርገው ሰርተው ለመኖር ወስነው ከመጡ ወራት ተቆጥረዋል። አሁን በመርካቶው ይርጋ ኃይሌ ሕንፃ ውስጥ በከፈቱት የሞባይል መሸጫ ሱቃቸው ውስጥ በጋራ እየሰሩ ነው፡፡ ጥብቅ ሀይማኖታዊ መመሪያ ባላት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ወንዶች በአብዛኛው የሚታወቁት በሌብነት፣ በሴት ድለላና በህገወጥ ተግባራት ነው፡፡ ሸሪካ እየተባለ በሚጠራው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ለአረብ ወንዶች በማቃጠርና በማገናኘት ተግባር ላይ ተሰማርተው ኮሚሽን የሚሰበሰቡ አበሻ ወንዶችም በርካቶች ናቸው፡፡ እስማኤል ቃሲም (ስሙ የተቀየረ) በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ለአመታት ሠርቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት የሚሰሩት በድብቅ በመሆኑ የሸሪካዎቹ (የሴት አገናኝ ደላላዎቹ) ተግባር ፈታኝ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግራ ቀኙን አገናኝተውና ደልለው ጠቀም ያለ ኮሚሽን እንደሚቀበሉ እስማኤል ይናገራል።

“ቤት ተከራይተን የምናስቀምጣቸውና ለአረብ ወንዶች እያገናኘን ጠቀም ያለ ኮሚሽን የምናገኝባቸው አበሻ ሴቶች ብዙ ናቸው፤ ገንዘብ በቸገረንና በፈለግን ጊዜ ሁሉ አበሾቹ ይሰጡናል፡፡ አብዛኛዎቹ አበሻ ሴቶች ፈቃድ የሌላቸው በመሆኑ የጠየቅናቸውን ከማድረግና ከመታዘዝ ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም የጠየቅነውን ሁሉ ካላደረጉልን ያሉበትን ቦታ ለፖሊስ ጠቁመን እናስይዛቸዋለን፡፡ ይህን የምትፈልግ አበሻ በድፍን ሳዑዲ ውስጥ አትገኝም።” እስማኤል ይህ አይነቱ የሳዑዲ ኑሮ አንገሽግሾት ወደ አገሩ መመለሱንና በአገሩ ልጆች ላይ የሰራው ግፍ አብዝቶ እንደሚፀፅተው ይናገራል፡፡ የአበሻ ወንዶች ኑሮ በሳውዲ ህገወጥነት የተሞላበት፣ በፖሊስ ዓይን የጐሪጥ የሚታይበት ቢሆንም የቅንጦትና እጅግ የተንደላቀቀ እንደሆነ ወደ አገራቸው የተመለሱት የሳዑዲ ነዋሪ የነበሩ አበሾች ይገልፃሉ፡፡ አበሻ ወንድ በሳውዲ የሚኖረው ኑሮ የተንደላቀቀ፣ በቅንጦት የተሞላ ይሁን እንጂ ሰቀቀን የበዛውና የህሊና ነፃነት የሌለው እንደሆነም እነዚሁ ወጣቶች አልሸሸጉም፡፡

Read 4969 times