Saturday, 05 October 2013 10:14

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(4 votes)

                    ባለፈው ሳምንት ስለነክፍሌ ዕድር (ቁጥር 5 ቅዱስ ገብርኤል መረዳጃ ዕድር) እየተረኩላችሁ ነበር ያቆምኩት፡፡ በሰበብ አስባብ ይሁን እንጂ የወንጂ ከረሜላ ጉብኝቴ ትዝታ እንዴት እንደተቀሰቀሰብኝ ላወጋችሁ ነው፡፡ ዱሮ አፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት እንደእኔ ኤሌሜንታሪ የተማረ ሁሉ የማይረሳው ነገር አለ፡- ጋሽ “ተስፋዬ ብጉር”ን (የሥዕል አስተማሪያችንን)፣ ጋሽ አወል አማንን (የሂሳብ አስተማሪያችንን)፣ ጋሽ ግርማ ቄንጦን (ፀጉረ ሉጫውን የእንግሊዝ አስተማሪያችንን)፣ ጋሽ ደሱን፣ በተለይ “My name is ከተማ ሙሣ I came from ጨፌ ደንሣ” ብሎ (መስከረም 18 ት/ቤት ሲከፈት) ራሱን የሚያስተዋውቀንን፤ ጋሽ ከተማ ሙሳን፤ ሁልጊዜም ሳስታውሰው እኖራለሁ፡፡ የልጅነት የት/ቤት ትዝታ መቼም አይረሳም! ባለፈው ሣምንት “ልጅነቴን ያስታወሰኝ ዕድር” ብዬ ንዑስ ርዕስ የሰጠሁት ትረካ ዋናው ሰበቡ ተማሪ ሳለን ወንጂ ስኳር ፋብሪካና ከረሜላ ፋብሪካን እንጐበኝ እንደነበር እንዳስብ ያደረገኝ ሁኔታ ነው፡፡

ከላይ የጠቀስኩት ዕድር ማህበር ፀሐፊ፤ “የአካባቢ ፋብሪካዎችን፣ ተቋማትን፣ ት/ቤቶችን ፕሮግራም ይዘን ልጆቹን በማስጐብኘት ልምድ እንዲያዳብሩ እናደርጋለን” አለኝ፡፡ “እኛምኮ በኃይለሥላሴ ጊዜ ወንጂ ለጉብኝት ሄደን፤ የወንጂ ስኳር ባለዝሆን ከረጢት፣ ደስታ ከረሜላ ይሰጠን ነበር፡፡ የእኛ ጊዜ “አገርህን ዕወቅ” ነበር መሰለኝ መንፈሱ፡፡ የእናንተስ ለምንድነው?” አልኩት፡፡ “እኛ ትምህርታዊና ጥናታዊ ጉብኝት፣ ብለን፤ ትራክተር ፋብሪካ፣ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ፣ ወረቀት ፋብሪካ፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲ፤ ወዘተ ተዘዋውረው እንዲያዩ እናደርጋለን፡፡ የግቢው መንፈስ (atmosphere) ስነ ልቦና፣ አስተሳሰብና ዕውቀት፤ የሚፈጥርባቸው የሥራ ተነሳሽነት ቀላል አይደለም። በወደፊት አስተዳደጋቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያደርጋል” አለኝ፡፡

(ይህ ነገር በመላው አገሪቱ ምነው የተለመደ በሆነ አልኩ በሆዴ) ቀጠለና “ይሄ እንግዲህ አንዱ ሥራችን ነው፡፡ 2ኛው/ ስለህፃናት እንክብካቤ ዘዴ በባለሙያ ሥልጠና አማካኝነት ግንዛቤ መፍጠር፣ ልጆች በዱላና በቁጣ ሳይሆን በሥነስርዓት እንዲያድጉና የተሻለ የትምርት አቀባበልና የኑሮ ዝንባሌ እንዲኖራቸው፤ እንዴት እንደሚኮተኮቱ ግንዛቤ መስጠት 3ኛው/ለቤተሰብ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ወደ ራስ መቻል እንዲያመሩ ማድረግ 4ኛው/ የቁጠባ ባህልን ማዳበር፤ 5ኛ/የንግድ አዋጪነትን ሥርዓት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ባለሙያና የንግድ ተቋማት በሥልጠና የተደገፈ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ በመጨረሻም ጧሪ ለሌላቸው አረጋውያንና በላያቸው ላይ ቤት ፈርሶ ችግር ለበዛባቸው አዛውንቶች የቤት ጥገናና እንክብካቤ እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው” አለኝ፡፡

ከውይይታችን እንደተረዳሁት፤ “የዘላቂነት ነገር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አባላት ለዕድሩ ከሚያዋጡት ገንዘብ፤ ለህፃናት በወር ሁለት ሁለት ብር ተቀማጭ በማድረግ ፕሮጀክቱ ቢቆም ማስቀጠያ ይደረጋል። ወደፊት የብሎኬት ማምረቻ ማቋቋምም በታሳቢ የተያዘ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ስናጠቃልልም ህዝቡ ወደኛ እሚመጣው ለጆቹን ብሎ ነው፡፡ በመደጋገፍ ተአምር ሊሰራ እንደሚችል ስለገባው ነው፤ የሚለውን ሃሳብ አሰመርንበት፡፡ ‘ሁልጊዜ ስለ ችግር ከማውራት ሠርተን መለወጥን መርጠናል’ የሚለው መሪ መፈክር ለትውልድ መተላለፍ ያለበት ነው። ለዚህ ደግሞ የእየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና ሚና መጫወቱን በኩራት ማውሳት እንወዳለን”፤ ብለውኝ፤ ጉዳዬን ጨርሼ “ኧረ ናዝሬት ናዝሬት ረባዳ መሬት” ታበቅያለች አሉ ሸጋ እንደሰንበሌጥ”ን እያዜምኩ የመጨረሻ አዳሬን በቢራ አጅቤ፤ ፊቴን ወደ ነገ አዙሬ ተኛሁ፡፡

======================

  •      የደብረ ዘይትና የአዋሳ የጉዞ ማስታወሻዬ “ማህበረሰብን ከያዙ ለመሥራት የማይቻል ነገር የለም!”
  • “ግንዛቤ ብቻውን ዳቦ አይሆንም!”

                   ደብረ ዘይት በስልሳዎቹ መጀመሪያ ግድም፣ ልዕልት ተናኘ ወርቅ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምሬአለሁ - 9ኛ ክፍል፡፡ እነ አስካለ ነጋ፣ እነ ይስሃቅ (አሁን ዶክተር)፣ እነ ወንድማገኝ ማሞ (አሁን ዶክተር)፣ እነ ግርማ ቦንዳ ወዘተ ትዝ ይሉኛል፡፡ ደብረዘይት የአየር ኃይልና የአየር ወለድ አገር ሆና ነው የማውቃት፡፡ ዛሬ ዘመኑ ቢለያይም መሠረታዊው ሐዲድ አይጠፋኝም፡፡ አሁን የምጐበኘው “ንጋት የማህበረሰብ ልማት ማህበርን ነው፡፡ ሰብሳቢው አቶ ፍቃዱ ደመቀ ናቸው፡፡ ወፍራም፤ አንደበተ-ቀናና ጠንከር ያለ ንግግር ያላቸው ሰው፡፡ ም/ሰብሳቢው አቶ መሳይ ታደሰ፤ ፀሀፊዋ አይናዲስ አስረሳኸኝ ናት፡፡ ፍልቅልቅ ስሜት የሞላው አቀባበል ነው ያደረጉልኝ! አንዳንድ ሰው ሲናገር የተፃፈ የሚያነብ ነው የሚመስለው አቶ ፍቃዱ እንደዛ ናቸው፡፡

“ማህበራችን የተቋቋመው በ2001 ዓ.ም መጨረሻ ነው፡፡ ትኩረት የሚያደርገው ህፃናትን፤ ሴቶችንና ወጣቶችን ማገልግል ላይ ነው! ታሪካዊ አመጣጡ፤ ቀደም ሲል የእየሩሳሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት ፕሮጀክት ቀርፆ እዚህ አካባቢ ይንቀሳቀስ ነበርና ጊዜውን ጨርሶ ሲወጣ፤ ጀምሯቸው የነበሩት የልማት ሥራዎች፤ ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ማህበረሰቡ የራሱን ማህበር አቋቁሞ በራሱ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ከሴቶች ጉዳይና ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ማኅበራችን የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር አለው፡፡ አዳራሽ አለው። ካፌ አለው፡፡

መጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣል፡፡ መፃህፍት ቤት አለው፡፡ ባለጋሪ ነው፡፡ የቆሻሻ መውሰጃ ትራክተርም አለን፡፡ የአካባቢው ገበሬ ገበያ ውሎ ሲመለስ የሚያርፍበት ካፌ ከፍተናል፡፡ መላውን ህ/ሰብ በማንቀሳቀስ የአካባቢው ንፅህና ላይ እንሠራለን (ቦይ ጠረጋ፣ ቆሻሻ መቃጠል ላይ እንዘምታለን፡፡ የሚገርምህ ስንጀምር ፕሮጀክት እንዴት እንዳሚቀረፅ እንኳ አናውቅም ነበር፡፡ ዕድሜ ለኢየሩሳሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት ዐይናችንን ከፈተልን! አቶ መሳይ ሲናገር ስሜት የሚያጥለቀልቀው ኰበሌ ነው፡፡ እንዲህ አለኝ፡፡ “ግንዛቤ ብቻውን ዳቦ አይሆንም፡፡ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ልማትና እርዳታ ይለያያል፡፡ ልማት ቁጭት ይፈልጋል፡፡

እልህ ይፈልጋል፡፡ ያ ካለ መልማት ይቻላል - የተረጅነት ስሜትን ማስወገድ ይቻላል፡፡ እየሩሳሌም መነሻ ሆነን፡፡ ጥሩው ነገር ተቋም መኖሩ፣ ከፍተህ የምትገባበት ቢሮ መኖሩ … ከዛ ራስህ ትቀጥላለህ … ዱሮ እኛ እየሩሳሌም (ጄክዶ) ላይ ተስፋ እንጥል ነበር - አሁን እየሩሳሌም በእኛ ላይ ተስፋ ጥሏል … ይሄ ነበር የሚፈለገው! እኛ ቦይ ውስጥ የቀሩ ልጆች ት/ቤት መግባት አለባቸው ብለን ተነሳን፡፡ የራሳችንን ሥራ ጊዜ ለይተን፣ ሌሊትም ቢሆን ሠርተን ይህን ሁኔታ መለወጥ አለብን አልን! ለራሳችን ቃል ገባን! አርኪ ሥራ ሠራን … ልጆቹ ዩኒፎርም ለብሰው ት/ቤቱ ሲገቡ ሳያቸው አልቅሻለሁ! እግዚአብሔርን አልቅሻለሁ! በጐ-ፈቃደኝነት የገንዘብ ጥቅም የምታገኝበት አይደለም “አንዲት ምስኪን እናት፤ እግዚአብሔር ይመስገን ልጄ ት/ቤት ይሄዳል” ስትል ስትሰማ ትረካለህ! ያ ነው ጥቅሙ፡፡ … ቀን ቴሌ ሣንቲም እየዘረዘረች እየተማረች፣ ማታ በቆሎ እየጠበሰች፣ ተምራ - ከቤት ኪራይና ከራስ በማያልፍ ገቢ የምትኖር ተማሪ ረድተህ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ስትደውልልህ የሚሰማህን ደስታ ያህል ከየት ታገኛለህ?...” የማህበሩ ፀሐፊና የመጻህፍት ቤቱ ኃላፊ ዐይናዲስ፣ የጠንካራ ሴት ናሙና ትመስለኛለች፡፡ ቀጭን ናት - ስትናገር እንዝርት የምታጠነጥን ትመስላለች፡፡

ቃላቱን በወጉ ታዳውራቸዋለች፡፡ “ይሄ ቀበሌ ከደሀም ደሀ የወረደ ደሀ፤ የመኖሪያ አካባቢው ያልፀዳ፤ ተመርጦ የተቀመጠ የድህነት ቦታ ይመስልሃል! ብዙ ለውጥ አመጣ - በራሱ ኃይል፡፡ የህዝቡን ተነሳሽነት፣ የልጆቹን ት/ቤት መሄድ፣ ለስምንት አባ-ወራ አንድ ሽንት ቤት ተሠራ … ፅዳት አየን፡፡ በበኩሌ የማየው ለውጥ ደስ ስለሚለኝ ደከመኝም ብዬ አላውቅም፡፡ ለውጥ ስታይ አይደክምህም! አምስት ልጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፡፡ ለቀሪው ትውልድ ብለው የተማሩባቸውን፣ መፅሀፎቻቸውን ሰጥተው ሄደዋል - ምን ትፈልጋለህ? … በጦርነት የተጐዱ ሰዎችን ለመርዳት ነበር ጄክዶ (Jeccdo) የመጣው በ1979፡፡ አሁን የትና የት ደርሷል! እኔ እንደ ጄክዶ መሆን እፈልጋለሁ - ደሞ እችላለሁ! እግዚሃር ይርዳን እንጂ እንደኢየሩሳሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት የማንሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም!” ያለችውን እንደምታደርገው ፊቷ ላይ ያለው ጠንካራ መንፈስ ይናገራል፡፡ የህዝብ የባለቤትነት ስሜት ከዚህ በላይ ምን አለ?! (ጉዞዬ ይቀጥላል)

Read 1825 times