Saturday, 05 October 2013 10:10

“ፀሐይ በስተምሥራቅ ከመውጣቷ ጀርባ የእነማን እጅ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

                      መስከረም ‘ፉት’ አለ አይደል! ይበል፣ የራሱ ጉዳይ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ድሮ፣ ድሮ እንዲህ የከፋን፣ ነገሩ ሁሉ ጨለመለም ያለብን ጊዜ «ጦሳችንን ይዞ ይሂድ!» የምንለው ነገር ነበረን፡፡ ዘንድሮ ግን…አለ አይደል…. ‘ጦስ ይዞ ከሚሄድ’ ይልቅ ‘ጦስ ይዞ የሚመጣው’ ስለበዛብን ነው መሰለኝ እንደዛ ማለት ትተናል፡፡ ተተኪ አባባል ይፈጠርልንማ! ስሙኝማ…«የመረጃ ዘመን ነው» የሚባል ነገር አለ አይደል… እውነትም የዓለምን ነገር ስታዩ በእርግጥም የመረጃ ዘመን ነው፡፡ መረጃ በምን ያህል ፍጥነት ከአንዱ የዓለም ጥግ ወደሌላኛው እንደሚደርስ ስታዩ የምርም ዓለም እየተለወጠች ነው ትላላችሁ፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ…እኛ ዘንድ ሲደርስ! ነገርዬው ሁሉ መቶ ሀምሳ ስፍራ እየተተለተለ…መረጃ እንደ ምንጩ ምናምን ሳይሆን እንደ አቅራቢው ሆኖላችኋል፡፡ የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…. ‘አፍንጫችንን ተሰንገን’ ፈረንካችንን ቁጭ ለምናደርግባቸው አገልግሎቶች፣ አይደለም ትክክለኛውን መረጃ የሚሰጠን፣ ሊሰጠን የሚያስብ ጠፍቶ ተቸግረናል፡፡

ከማበሳጨት አልፎ ‘ማስቀወስ’ ደረጃ ላይ ከደረሰው የኃይል መቆራረጥ ጀርባ ያለው ‘እውነተኛ መረጃ’ ምነው የማይነገረንሳ! ይሄን ያህል ጂ… ምናምን ጂ… እየተባለ የሚወራለትና ተቃቅፈን እያለን እንኳን «የፈለጓቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…» የሚለንን፣ ገና «እንደምን አደርክ…» ምናምን ተባብለን የእግዜሐር ሰላምታ ተለዋውጠን ሳንጨርስ መሀል ላይ ድርግም እያለ ወሽመጣችንን ብጥስ ከሚያደርገን፣ አንድ የድረ ገጽ አድራሻ ለመክፈትና አንድ በቆሎ ለመጥበስ የሚፈጀው ጊዜ እየተቀራረቡበት ካለው የኔትወርክ ነገር ጀርባ ያለው ‘እውነተኛ መረጃ’ የማይነገረንሳ! ትውልድ አስደንጋጭና አሳሳቢ በሆኑና ማህበራዊ መሰረቶችን ሙሉ ለሙሉ በሚያናጉ ልማዶች እየተዘፈቀ ስለመሆኑ እየተነገረ፣ እየተጻፈ፣ እየታየ ባለበት ሰዓት… «ያገባኛል…» ባይ ጠፍቶ ‘እንዳላዩ ከሚታለፍበት’ ምክንያት ጀርባ ያለው ‘እውነተኛ መረጃ’ የማይነገረንሳ! እናላችሁ…እንደ ሁሉም ነገር የመረጃ ጽንሰ ሀሳብ እኛ ዘንድ ሲደርስ ‘ድርጅታዊ’… ‘ክልላዊ’… ’ጎሳዊ‘… ‘አበልጃዊ’… መልክ እየያዘ ተቸግረናል፡፡

እናማ ሁላችንም የምናገኘውን ‘ዓለም ያወቀውን፣ ፀሐይ የሞቀውን’ መረጃ ‘በልካችን እየሰፋን’…አለ አይደል…ሁለትና ሁለት አራት ቢሆንም እንኳን «አራት ከመሆኑ ጀርባ ባሉ ምክንያቶች…»… «የምልህን ካልተቀበልክ ውርድ ከራሴ» አይነት ነገረ እየተባባልን ነው፡፡ ታዲያላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እኛ ሚዲያ ውስጥ ያለን ሰዎችም ብንሆን «አንዳንዴ» ሊባል ከሚችል ጊዜ በላይ መረጃን ለእኛ በሚመች መልኩ ቅርጽ አውጥተን፣ ‘ፋውንዴሽን’ና ‘ፓውደር’ ነስንሰን፣ ‘ፔዲዩርና ማኒኪዩር’ አድርገን ‘አለስልሰን’ ነው የምንበትነው፡፡ ድሮስ የዚቹ ዓለም ክፍል ልጆች አይደለን! የምር ግን…«ፀሐይ በስተምሥራቅ ትወጣለች…» የሚለው መቶ አንድ ትርጉም ሊሰጠው የሚችለው እኛ ዘንድ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ…ከዚህ መረጃ በኋላ የሚከተለው ጥያቄ…«ፀሐይ በስተምሥራቅ ከመውጣቷ ጀርባ የእነማን እጅ አለበት…» የሚል ይሆናላ! (ስሙኝማ…እዚሀ አገር መሀል ላይ ያለው ትልቅ ግራጫ ስፍራ ጠፍቶ…አለ አይደል… ሁሉም ነገር ‘ወይ ጥቁር፣ ወይ ነጭ’ ከሆነ ከራረመ፡፡ «ወይ ከእኛ ጋር ነህ፤ ወይ ከአነሱ ጋር ነህ…» «ወይ ደጋፊ ነህ፣ ወይ ተቃዋሚ ነህ…»፣ «ወይ ‘ትራስንፎርሜሽን’ ነህ፤ ወይ ናፋቂ ነህ…»፣ «ወይ ባለራዕይ ነህ፣ ወይ ባለቀቢጸ ተስፋ ነህ…» የዚች አገር የማያልቅ ትራጄዲ እንዲህ፣ እንዲህ እያለ ይቀጥልላችኋል፡፡) እናላችሁ…ሚዲያ ውስጥ ያለን አንዳንዶቻችን እንክት አድርገን ነው…ዜናና አስተያየቱን ሚስቶ እያደረግን የምናቀርብ፡፡

ስንትና ስንት ሺህ ሰው የተገኘበትን ሰልፍ ምናምን ነገር ላይ… «ከሁለትና ሦስት መቶ የማይበልጡ…» ከአሥርና ከአሥራ ምናምን ሺህ የማይበልጥ ሰው የተገኘበትን «በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ…» ምናምን የሚለው የጎንደር ጠጅ ቤት ጠጅ ቀጂ ሳይሆን እኛ በዚህና በዛ ጎራ ያለን የሚዲያ ሰዎች ነን፡፡ ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታም አይደል ..ዘንድሮ እነማን ያሳዝኑሀል ብትሉኝ…ህዝብ ግንኙነቶች (ይቅርታ…የኢንፎርሜሽንና የኮሚኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤቶች…)፡፡ የሁሉንም ‘ጉድ’ ተሸክመው ዓይኖቻቸውን ‘በጨው ማጠብ‘ ያለባቸው እነሱ ናቸዋ! የምርት ክፍል ሀላፊው አረቄውን እየጋተ፣ ሠራተኞቹ የሚመራቸውና የሚቆጣጠራቸው አጥተው ምርቱ በአፍ ጢሙ እየተደፋ….የአስተዳዳር ሀላፊው በየሰበቡ እንትናዬዎችን «እነሆ በረከት ካላልሽ ዓመድ እንደነፋብሽ ትኖሪያታለሽ…» እያለ…(እኔ የምለው…እነሆ በረከት ካልተባለ… «ዕድገት አታገኚም»፣ «የስልጠና ዕድል አታገኚም» «ከ‘ኤፍ’ ሌላ አታገኚም»… ምናምን የሚባለው ነገር… እነሆ በረከቱ ‘ኮላተራል’ መሆኑ ነው? ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…ባንክስ ቢሆን «ኮላተራል ካለቀረብክ ብድር አታገኝም…» ምናምን አይደል የሚለው!) ሥራ አስኪያጁ ከሚገባበት የማይገባባት ጊዜ በልጦ ፊርማ ፈላጊ ሰነዶች ጠረዼዛው ላይ ተከምረው…ህዝብ ግንኙነት ሆዬ መድረክ ይቀርብና…«ከማኔጅመንት ጀምሮ እስከ ተላላኪና የጥበቃ ሠራተኞች ድረስ በከፍተኛ ቅንጅት እየሠራን…» ለማለት ይገደዳል። እንጀራ ነዋ…ልጄ! ‘ተጠቃሚዋ በዝቶ’ ዋጋዋ የየተወደደውን ጤፍ ማግኘት እኮ መከራ ሆኗል፡፡

ስሙኝማ…የመረጃን ነገር ካነሳን…ምን ኮሚክ ነገር አለ መሰላችሁ…አንዳንዱ አባወራ እንትናዬውን ከመገናኘታቸው በፊት የነበሯትን፣ ወይም ነበሯት ብሎ የሚያስባቸውን እንትናዎች እያሰበ ይንጫረራል፡፡ ልክ እኮ…አለ አይደል…እንደ ተወለደች «ይቺ ልጅ ስታድግ የእንትናና የእንትና ብቻ ትሆናለች… ይህንን ያፈረሰ ውጉዝ ከመአርዮስ ይሁን!» ምናምን የሚል ጽሁፍ ያለበት ክታብ የታሠረላት ያመስመስለዋል፡፡ የምር… አንዳንዱ አባወራ እንትናዬውን ስምንተኛ ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ በ‘ኪሲንግ ያጦፋትን’…(እንደ ማብራሪያ…‘ኪሲንግ ማጦፍ’ የልምድ ውጤት ሲሆን…ለጀማሪዎች ግን ‘ኪሲንግ መለቅለቅ’ ነው የሚባለው፡፡ ምን አለፋችሁ…መጀመሪያ ላይ እንደ ብራዚል ጫካ እርጥበት በእርጥበት ይሆንላችኋል…) እያስታወሰ የሎካል ብራንዲ ፍጆታውን የሚጨምር ሞልቷል፡፡ እናላችሁ….«ትናንትና ሠርግ ላይ የተቃቀፋችሁት ሰውዬ የትምህርት ቤት ቦይ ፍሬንድሽ ነው፣ አይደል!» አይነት ‘የመረጃ ነጻነት’ ቅሽም ያለ ነው፡፡ እሺ… «አዎ፣ ነው…» ብትለው ምን ሊሆን ነው! አገር ቤተ ዘመዶቹ ዘንድ ሄዶ «እንደው አያቴ ያስቀመጡት አልቤን ይኖራችሁ ይሆን?» ሊል ነው! ወይስ የእሷን የድሮ እንትናዎችና የእሱን የድሮ እንትናዬዎች አሰባስቦ…«የተቀማመሱት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ» ምናምን ‘ሊቦተልክ’ ነው! ቂ…ቂ…ቂ… (‘እንደ ሀሳብ’ ለዓለም አዲስ የ‘ቦተሊካ’ አቅጣጫ መጠቆም አይመስላችሁም!) እናላችሁ…ስለ ስምንተኛ ክፍል የኪሲንግ ኤ.ቢ.ሲ.ዲ. ስላስተማሯችሁ ቦይፍሬንዶች ለምትጠየቁ እንትናዬዎች ጥቆማ…እናንተም እንክት አድርጋችሁ ጠይቁ፡፡

እናላችሁ… ከምትጠይቋቸው ጥያቄዎች መሀል እንደው ለመንደርደሪያ ያህል…. ዶሮ ማነቂያ ቀይ ቀለም ያለው የሎተሪ ቲኬት አሳይቶ «አሥር ብር ነው…» በማለት ሌሊቱን ሙሉ ‘ኳስ ሜዳ’ ሲፈነጭ (ቂ..ቂ…ቂ…) ያደረበትን፣ ጣልያን ሰፈር ለቡና ብር ተሰባ አምስት ሰጥቶ ‘ሄዶ መልስ’ ይልበት የነበረውን፣ እሪ በከንቱ ‘ክራይቴሪያው’ አለ አይደል ‘ሚዛንና ክብደት’ ‘ቂ…ቂ…ቂ….) በሆነበት ቦታ የከፈተውን በር ሳይዘጋ በዛው «ለዚችስ…» ተብሎ የተባረረበትን … ሁሉ እያነሳችሁ ጠይቁት፡፡ ደግሞላችሁ… በር ተንኳኩቶ «ሰዓት ሞልቷል፣ ውጡ…» ሲባል «እጨምራለሁ!» ብሎ ትንፋሽ እያጠረው የጮኸበትን…ምናምን ሁሉ ጠይቁ፡፡ ያኔ ልክ ይገባላችሁና ታርፋላችሁ፡፡ እምቢ፣ አሻፈረኝ ካለ «ተጨማሪ ጥቆማዎች ይዘን በሌላ ጊዜ እንመለሳለን…» ልክ ነዋ…እንትናዬዎቹ ብቻ በምን ዕዳቸው! እናላችሁ…አንዳንዱ የሚፈልገው መረጃ ግርም የሚላችሁ ነው፡፡ ስሙኝማ….ዘንድሮ መቼስ ሁላችን ‘ልባችን ተሰቅሎ’ መረጃ እየተጠያየቅን አይደል…እናላችሁ «ስማ የአጅሬዎቹ ነገር እንዴት ነው?» ብለን ተንኮስ እናደርጋለን፡፡ (‘አጅሬዎቹ’ የሚለውን ላለማብራራት ምንጭ ያለመንገር መብቴን እንደተጠቀምኩ ይከተብልኝማ!) እና…የሚሰጠው መረጃ ብዛቱ የምናወራው ስለ አንዲት አገር ብቻ ሳይሆን ስለኮመንዌልዝ አባል አገራት ምናምን ነው የሚመስለው፡፡ ንጹህ መረጃ የምንለዋወጥበትን ዘመን ያፋጥልንማ! «ፀሐይ በስተምሥራቅ ከመውጣቷ ጀርባ የእነማን እጅ አለበት!» ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5272 times