Saturday, 05 October 2013 10:04

ዘመኑ የሴቶች ነው? የአትሌቶች ውጤት ምን ይመሰክራል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

         እዚሁ አዲስ አድማስ፣ አንድ ፀሐፊ “ዘመኑ የሴቶች ሆኗል” በማለት አስተያየቱን እንዳካፈለን ትዝ ይለኛል። አመት ሳይሞላው አይቀርም። ያኔ በለንደን ኦሎምፒክ ማግስት መሆኑ ነው። በኦሎምፒክ ውድድሩ ከተካፈሉት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካከል፣ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የታሪክ መዝገብ ውስጥ የሚሰፍር ታላቅ ጀብድ የሠሩት ሦስት አትሌቶች አይደሉ? ሶስቱም ጀግኖች፣ ወጣት ሴት አትሌቶች ናቸው - ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና ቲኪ ገላና።
የአዲስ አድማሱ ፀሐፊ ይህንን የሴት አትሌቶች አስደናቂ ገድል ሲያይ ነው፣ ዘመኑ የሴቶች እየሆነ ነው ብሎ የፃፈው። በከፍተኛ ትምህርት፣ በዘመናዊ የሙያ መስኮች፣ በቢዝነስ ሥራም እንዲሁ፣ ሴቶች በየቦታው ብቅ ብቅ ማለት ብቻ ሳይሆን ጎላ ጎላ እያሉ መምጣታቸውንም ታዝቧል። ይሄውና ዘንድሮም፣ ያንን ሃሳብ የሚያጠናክር እንጂ የሚያስቀይር ነገር የተፈጠረ አይመስልም።
በእርግጥ፣ በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ወንድ አትሌቶችም ጥሩ ውጤት አምጥተዋል። ወንድ አትሌቶች አንድ ወርቅ፣ ሶስት ብር እና አንድ ነሐስ አምጥተዋል። ሴት አትሌቶች ደግሞ ሁለት ወርቅና ሶስት ነሐስ። ተቀራራቢ ውጤት ነው። ብሄራዊ ቡድኑም በጥቅሉ፣ በሞስኮ ቆይታው ሶስት የወርቅ ሶስት የብር እና አራት የነሃስ በድምሩ አስር ሜዳልያዎችን በማግኘት ከአለም 6ኛ ከአፍሪካ 2ኛ በመሆን ሻምፒዮናውን አጠናቋል።
በአዲሱ አመት ዋዜማ በሞሪሽየስ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ግን፣ ሴት አትሌቶች የሚቀመሱ አልሆኑም። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከተጎናፀፏቸው 7 የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል፣ 6ቱ በሴት አትሌቶች የተገኙ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም። በውድድሩ ከተገኙት ሰባት የብር እና ስምንት የነሐስ ሜዳሊያዎች መካከል አብዛኞቹ፣ በሴት አትሌቶች ውጤት ናቸው። ለዚያውም፣ ካሁን በፊት በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድ እምብዛም ባልተለመዱት፣ በመቶ ሜትርና በሁለት መቶ ሜትር የሩጫ ውድድሮች የተካፈለች አትሌት፣ ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አጥልቃለች። በአራት መቶ ሜትር የመሰናክል ሩጫ የብር ሜዳሊያ፣ በሌላ የአራት መቶ ሜትር ውድድር ደግሞ የነሐስ ሜዳሊ አግኝተዋል - ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴት አትሌቶች። ከ1500 ሜትር በላይ ባሉት ሩጫዎችማ፣ ወርቅ በወርቅ ሆነዋል።
ይሄን ይሄን ስናይ፣ እውነትም ዘመኑ የሴቶች ነው ያሰኛል።

አንዳንዴ ግን ጉዳዮች ሰፋ፣ ነገሮችን ራቅ አድርጎ መቃኘት ያስፈልጋል። ለዚህም ነው፤ ወደ ኋላ መለስ ብዬ የሃምሳ እና የአርባ አመታት የኢትዮጵያ አትሌቶች አለማቀፍ ውጤቶችን ለማነፃፀር የሞከርኩት።
እናስ ምን ተገኘ በሉኝ። ትክክል ነው። የሴት አትሌቶች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየገነነ መጥቷል። እስከ 1984 ዓ.ም፣ በኦሎምፒክ አደባባይ ድል ለመጎናፀፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሙሉ ወንዶች ናቸው - አምስት ወንድ አትሌቶች። ምሩፅ ይፍጠር፣ ሁለት ወርቅና አንድ ነሐስ፤ አበበ በቂላ ሁለት ወርቅ፣ ማሞ ወልዴ ደግሞ አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና አንድ ነሐስ ተቀዳጅተዋል። መሀመድ ከድርና እሸቱ ቱራ ደግሞ ነሐስ።
በ1984ቱ የባርሲሎና ኦሎምፒክ ግን፣ የአበበ በቂላ ታሪክ በሴቶች ተደገመ። ደራርቱ ቱሉ፣ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት የኦሎምፒክ ጀግና ለመሆን በቃች። ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ፣ የፋጡማ ሮባ ወርቅ እና የጌጤ ዋሚ ነሐስ ተጨመረበት። በሲዲኒው ኦሊምፒክ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ ሜዳሊያ ስትደግም፣ ጌጤ ዋሚ የብርና የነሐስ ባለቤት ሆነች። ከዚያ በኋላማ የሚያቆማቸው አልተገኘም። በጥቂት አመታት ውስጥ የሴቶቹ ድል ከወንዶቹ አትሌቶች ጋር ተቀራራቢ ለመሆን ከመቻሉም በላይ፣ ብልጫ ወደ ማሳየት ተሸጋገረ።
በአለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናም ላይ፣ የሴት አትሌቶች ውጤት በአስገራሚ ፍጥነት ተመንጥቋል።
እንዲያም ሆኖ፤ የወንዶቹ ውጤት እዚያው በነበረት አልቀረም። ከሞላ ጎደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል። በየጊዜው ከፍ ዝቅ ማለቱ ባይቀርም፣ በጥቅሉ ሲታይ፣ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት ባለፉት 30 እና 40 አመታት አድጓል፤ ተመንድጓል። የሴት አትሌቶች የስኬት ፍጥነት ግን አጃኢብ ያሰኛል።
በእርግጥ፣ የሴቶች እንቅስቃሴ በጨመረ ቁጥር፣ መንፈስን የሚያነቃቁ የጀብዱና የስኬት ታሪኮች የመበራከታቸው ያህል፣ በተወሰነ ደረጃ አስደሳች ያልሆኑ ቀሽም ታሪኮች መፈጠራቸውም አልቀረም። የትንቢት መልክተኛዋ ጀማነሽንና “የቢግብራዘርዋ” ቤቲን መጥቀስ ይቻላል። ደግነቱ፣ ወደፊት ሳይረሳ የሚቀጥለው ዘመን የማይሽረው ታሪክ፤ የነጥሩነሽ ዲባባና የነመሰረት ደፋር ታሪክ ነው።

Read 1381 times