Saturday, 05 October 2013 09:59

የአሜሪካ መ/ቤቶች መዘጋታቸው ለጤና ነው

Written by 
Rate this item
(8 votes)

“የአሜሪካ መንግስት ተዘጋ፤ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በር ተከረቸመ” የሚለው ሰሞነኛ የውዝግብ ዜና፣ እውነት ቢሆንም የተጋነነ ነገር አለው። አዎ፤ አብዛኞቹ መሥሪያ ቤቶች ተዘግተዋል። ነገር ግን ሁሉም አልተዘጉም። እንደ ኤፍቢአይ የመሳሰሉ የፍትህ አካላት፣ እንደ ሲአይኤ የመሳሰሉ የስለላ ተቋማት በከፊል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አልተዘጉም። የመከላከያ ሃይል ተቋማትም ስራቸውን አላቋረጡም። በርካታ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከሞላ ጎደል ተከርችመዋል። ከዚሁ ጋርም፣ 800 ሺ ገደማ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች፣ ደሞዝ የማይከፈልበት እረፍት እንዲወስዱ ተነግሯቸው ስራ ፈትተዋል፤ ወደ ስራ ተጠርተው እስኪመለሱም ድረስ የመተዳደሪያ ገቢ አይኖራቸውም። በእርግጥ “የመንግስት ሠራተኛ ድሮስ መቼ ሠርቶ ያውቃል?” ብለው በቢሮክረሲው ዝርክርክነት የሚያሾፉ ሰዎች ደግሞ፣ “ሳይሰራ ደሞዝ ይከፈለው ነበር፤ አሁን ግን ሳይሰራ ገንዘብ አለማግኘትን ደግሞ ይሞክረው!” ማለታቸው አልቀረም። በእርግጥም፤ የመሥሪያ ቤቶቹ ሰሞኑን የተዘጉበት የውዝግብ መነሻ፤ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው - ከመንግስት ወጪና ባጀት ጋር።

ዋናዎቹ አወዛጋቢ ጉዳዮች ሶስት ናቸው፣ ከአመት አመት የሚያብጠው የመንግስት በጀት፣ በጊዜ ወደ ጊዜ የሚቆለለው የመንግስት እዳ እና “ኦባማኬር” የተሰኘው አስገዳጅ የጤና ኢንሹራንስ። ተወዛጋቢዎቹስ እነማን ናቸው? በአንድ ወገን፣ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና መቶ መቀመጫዎች ባሉት ሰኔት ውስጥ አብላጫውን ወንበር የተቆጣጠሩ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጮች አሉ። በሌላኛው ወገን ደግሞ፣ 435 መቀመጫዎች ባሉት ኮንግረስ ውስጥ፣ አብላጫውን ወንበር የተቆጣጠሩ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች አሉ። በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል ላለፉት ሶስት አመታት እየተካረረ የመጣው ውዝግብ፣ ሰሞኑን መፈናፈኛ ወዳልተገኘለት አጣብቂኝ ስለተሸጋገረና በበጀት ጉዳይ ላይ ሊስማሙ ባለመቻላቸው ነው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተዘጉት።

ታላቋ የነፃነት አገር አሜሪካ፣ ባለፉት መቶ አመታት ነገረ ስራዋ እየተበላሸ መምጣቱን ከሚመሰክሩ ነገሮች መካከል፣ የሰሞኑ አጣብቂኝ እንደ አንድ ምልክት ሊታይ ይችላል። ውዝግብና አጣብቂኝ መፈጠሩ፣ አልያም የመንግስት መሥሪያ ቤቶች መዘጋታቸውና ሠራተኞች እረፍት እንዲወጡ መደረጋቸው አይደለም ችግሩ። እነዚህ ነገሮችማ፣ አሜሪካ ገና ከሁሉም አገራት የተሻለች የነፃነትና የሕግ አገር መሆኗን የሚጠቁሙ የጤንነት ምልክቶች ናቸው። ይልቅስ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንግስት ወጪ እየተለጠጠና በጀቱ እያበጠ መምጣቱ ነው፣ ትልቁ የበሽታ ምልክት። በጀት ማሳበጥ፣ መዘዞች አሉት። ወጪውን የሚሸፍን በቂ ገንዘብ እንደ ልብ አይገኝማ። እናም መንግስት ወጪውን ለመቀነስ ከመጣጣር ይልቅ፣ በየአመቱ እየገዘፈ የሚመጣውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን፣ በቦንድ ሽያጭ ገንዘብ ይበደራል። ለምሳሌ ባለፉት መንግስት ሶስት አመታት ከ3 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ስለተበደረ፣ በድምሩ የመንግስት እዳ ከ16 ትሪሊዮን ዶላር አልፏል።

በእርግጥ፣ የመንግስት ወጪዎችንና በጀቶችን ለመቀነስ መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ከዚህም ጋር የብድር ጣሪያን የሚገድቡ ህጎች በተደጋጋሚ ታውጀዋል። ነገር ግን፣ የብድርና የእዳ አዙሪቱ አልተበጠሰም። እንዲያውም በአዳዲስ ተጨማሪ ወጪዎች፣ ነገሩ ሁሉ እንደ አውሮፓውያኑ የግሪክ እና የስፔን አይነት ተስፋ ቢስነት እንዳያመራ የሚሰጉ አሉ። ለምሳሌ ከውዝግብ ጋር ተገጣጥሞ፣ ማክሰኞ እለት ስራ ላይ የዋለው አስገዳጁ የጤና ኢንሹራንስ ህግ (ኦባማኬር)፣ በየአመቱ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ተጨማሪ ወጪዎችን የሚያስከትል ነው። በዚያው መጠንም የበጀት ጉድለቱና የእዳ ክምሩ ይባባሳል። የዘንድሮውን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን ብቻ መንግስት፣ ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ብድር ያስፈልገዋል።

ነገር ግን፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ በገንዘብ ሚኒስትራቸው በኩል ለ“ኦባማኬር” እና ለሌሎች የመንግስት ወጪዎች ያሰኛቸውን ያህል በጀት የመመደብና የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ያሻቸውን ያህል ገንዘብ የመበደር ስልጣን የላቸውም - ከኮንግረስ ይሁንታ ካላገኙ በስተቀር። የአሜሪካ ውበት ያለው እዚህ ላይ ነው። የመንግስት ስልጣን በሕግ የተገደበ ነው። የመንግስት ወጪ በግማሽ ትሪሊዮን ዶላር ለመቀነስና “ኦባማኬር”ን ለማስወገድ ከመሞከር ያልቦዘኑት ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው፣ ህጉን ለመሻር 40 ያህል አዋጆችን አርቅቀው ቢያፀድቁም፣ በፕሬዚዳንቱና በሰኔቱ ተቀባይነት ስላላገኙ ውድቅ ተደርጎባቸዋል። አንዱ የመንግስት አካል፣ ለሌላኛው የመንግስት አካል ልጓም ይሆንለታል። እንግዲህ፤ በአንድ በኩል ኮንግረሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሰኔቱና ፕሬዚዳንቱ ለበርካታ ወራት እንደተፋጠጡ፣ “መስከረም ጠባ”። የዘንድሮው መስከረም እንደሌላው ጊዜ የበጀት ውዝግብን ብቻ አስከትሎ አልመጣም፣ ሌሎች ሁለት ውዝግቦችንም ጨምሮበታል። እንደተለመደው፣ መስከረም 21 ቀን (ኦክቶበር 1 ቀን)፣ አዲስ የበጀት አመት የሚጀመርበት ቀን ስለሆነ፣ የበጀት ውዝግብ መፈጠሩ አይገርምም።

ውዝግቡ መካረሩና በቀላሉ ስምምነት ላይ አለመደረሱ ነው፣ የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው። አዲስ በጀት ካልፀደቀ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በራቸውን ይዘጋሉ። አወዛጋቢውና በሪፐብሊካኖች ዘንድ የማይወደደው “ኦባማኬር” የተሰኘው አስገዳጅ የጤና ኢንሹራንስ፣ በይፋ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረውም በዚሁ እለት መሆኑ፣ የሁለቱን ወገኖች ውዝግብ አወሳስቦታል። ከሁለት ሳምንት በኋላ (ኦክቶበር 17) ደግሞ፣ የመንግስት የእዳ ክምር በህግ የተቀመጠለትን ጣሪያ ይነካል ተብሎ ይጠበቃል። እናም የብድር ጣሪያ ለመገደብ ከሁለት አመት በፊት የፀደቀው ህግ ካልተከለሰ፣ መንግስት ወጪዎቹን ለመሸፈን ተጨማሪ ብድር ማግኘት አይችልም። የመንግስት አማካይ የሳምንት ወጪ 60 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ቢሆንም፣ አማካይ ገቢው ግን 45 ቢ. ዶላር ገደማ ነው። በየሳምንቱ በአማካይ 15 ቢሊዮን ዶላር ብድር ካላገኘ አመቱን ሊዘልቅ አይችልም። ተንገራግጮ ይቆማል።

እናም፣ በተጨማሪ ብድር አመቱን ለመዝለቅ፣ የእዳ ጣሪያው ከ16.7 ትሪሊዮን ወደ 17.5 ትሪሊዮን ገደማ መስተካከል ይኖርበታል። ግን እስከመቼ እዳ እየተቆለ ይቀጥላል? እንደምታዩት፣ የፍጥጫው አስኳሎች እነዚሁ የበጀት፣ የእዳ እና የ“ኦባማኬር” ውዝግቦች ናቸው ማለት ይቻላል። ፕሬዚዳንት ኦባማ እና አብላጫውን የሰኔት ወንበር የያዙ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጮች፣ የሚያጨቃጭቅ ነገር የለም ባይ ናቸው … “የመንግስት መስሪያ ቤቶች መዘጋት ስለሌለባቸው እንደ አምናው በጀት ሊመደብላቸው ይገባል፤ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈንም የእዳ ጣሪያው መስተካከል አለበት። ይሄ አከራካሪ ሊሆን አይገባውም። ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የበጀት ጉድለትን ለማስወገድና የእዳ ክምችትን ለማቃለል፣ መወያየትና መደራደር እንችላለን። ነገር ግን፣ የመንግስት ስራዎች መቋረጥ አይኖርባቸውም” ይላሉ። በኮንግረስ ውስጥ አብላጫውን ወንበር የያዙ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተመራጮች ግን በዚህ አይስማሙም። አምርረው ይቃወሙታል እንጂ። “የመንግስት ወጪ እየተለጠጠ፣ የበጀት ጉድለት እየሰፋና የእዳ ክምችት እየተቆለለ መምጣቱ ሳያንስ፣ ‘በኦባማኬር’ ሳቢያ ችግሩን ይበልጥ የሚያባብስ ግዙፍ ወጪ ሊጨመርበት አይገባም። የእዳ ጣሪያውን በማንሳት ለተጨማሪ ብድር በር ከመክፈታችን በፊት አሁኑኑ የረዥም ጊዜ መፍትሄ ማበጀት ይገባናል። ቢያንስ ቢያንስ፣ ኦባማኬር ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ለአንድ አመት ስራ ላይ እንዳይውል ማዘግየት ያስፈልጋል” ይላሉ። በዚህ አቋም ላይ በመመስረት፣ በኮንግረስ የሪፐብሊካኖች መሪ የሆኑት አፈጉባኤ ጆን በይነር ምን አደረጉ? ለአስር ሳምንታት ገደማ የሚያገለግል ጊዜያዊ የበጀት አዋጅ ያዘጋጁትበይነር፣ “ለኦባማኬር ምንም በጀት አይመደብለትም” የሚል ተጎታች ከአዋጁ ጋር በማዳበል የኮንግረስ አባላት ድምፅ እንዲሰጡበት አቀረቡት። አሜሪካ የነፃነት አገር ነውና፣ የፓርቲ መሪዎችን ተከትለው ድምፅ የማይሰጡ የኮንግረስ አባላት መኖራቸው አይገርምም። አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖችና 20 ያህል አፈንጋጭ ዲሞክራቶች፣ ባለተጎታቹን የበጀት አዋጅ በመደገፍ ድምፅ ሰጥተዋል።

አብዛኞቹ ዲሞክራቶችና ጥቂት አፈንጋጭ ሪፐብሊካኖች ደግሞ ተቃውመውታል። በድምሩ በ230 ድጋፍ አዋጁ በአብላጫ ድምፅ ፀድቆ ወደ ሰኔት ተላከ። ሰኔቱ ይህንን ባለ ተጎታች የበጀት አዋጅ ቢያፀድቀው፣ ወደ ፕሬዚዳንቱ ነበር የሚሄደው። ነገር ግን፣ እዚያ አልደረሰም። በሴኔት ውስጥ አብላጫውን ወንበር የያዙት ዲሞክራቶች፣ የመጣላቸውን ባለተጎታች አዋጅ ተቀብለው፣ “ለኦባማኬር በጀት አይመደብለትም” የሚለውን አንቀፅ በመሰረዝ ሌጣውን ካስቀሩት በኋላ ሴናተሮች እንዲከራከሩበት አቀረቡት። ድምፅ ይሰጥበት ከተባለ ሌጣው አዋጅ እንደሚፀድቅ አያጠራጥርም - በ54 ዲሞክራት ሴናተሮች ድጋፍና በ46 ሪፐብሊካን ሴናተሮች ተቃውሞ። ነገር ግን፣ ዲሞክራቶች፣ በሰኔት ውስጥ አብዛኛውን ወንበር ስለያዙ ብቻ፣ በቀላሉ አዋጁን ማፅደቅ ይችላሉ ማለት አይደለም። አንድ እንቅፋት ማለፍ አለባቸው - በቅድሚያ የሰኔት ውስጥ የሚደረገውን ክርክር መቋጨት ይኖርባቸዋል።

ምክንያቱም በሰኔት ውስጥ፣ ነገ አራት ሰዓት ላይ ድምፅ ይሰጥበታል ተብሎ የተጀመረው ክርክር፣ በተባለው ሰዓት ላያበቃ ይችላል። ለምን? ሴናተሮች ልዩ መብት አላቸዋ። ተራው ደርሶ መናገር የጀመረ ሴናተር፣ ያለማቋረጥ የቻለውን ያህል ሰዓት ንግግሩን መቀጠል ይችላል። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እለት፣ ‘ኦባማኬር’ እንዲወገድ የሚፈልጉ ቴዲ ክሩዝ የተባሉ ሪፐብሊካን ሴናተር፣ ሌጣውን አዋጅ በመቃወም ለ21 ሰዓታት ያለማቋረጥ የሴኔቱን መድረክ ይዘው ነበር። በአዋጁ ላይ ድምፅ ይሰጥበታል የተባለው ሰዓት ካለፈ፣ ማሸጋሸግ ብሎ ነገር የለም። እንደገና እንደ አዲስ የውይይትና የድምፅ አሰጣጥ ፕሮግራም ይወጣል። ነገር ግን አሁንም፣ ያለ ገደብ ለበርካታ ሰዓታት የሚቀጥል አንድ ሴናተር፣ እንደገና የድምፅ አሰጣጥ ፕሮግራሙን በማዛባት ያስተጓጉለዋል።

በዚህ መንገድ፣ አዋጅ እንዳይፀድቅ ማሰናከል፣ ‘ፍሊበስተር’ ተብሎ ይታወቃል። የሴናተር ንግግርና ክርክር ሊቋረጥ የሚችለው፣ 60 ሴናተሮች የሰዓት ገደብ ለመጣል ከተስማሙ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በሰኔቱ ውስጥ 54 ወንበር ያላቸው ሴናተሮች፣ ብቻቸውን የውይይት ሰዓት ገደብ እንዲበጅለት መወሰን አይችሉም። ቢሆንም፣ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ “በፓርቲ ትዕዛዝ ሰጥ ለጥ ብሎ መመራት” ብሎ ነገር ስለሌለ፣ ዲሞክራቶቹ ከሪፐብሊካን ሴናተሮች መካከል የተወሰነ ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ። በመጨረሻም የሪፐብሊካኑ ሴናተር የቴድ ክሩዝ ረዥም ንግግር እንዲያበቃ የሚፈልጉ ሴናተሮች ቁጥር 60 ስለደረሰ፣ ሲናገሩ ውለው ያደሩት ቴዲ ክሩዝ ከ21 ሰዓት ተኩል ገደማ በኋላ ንግግራቸው ለመቋጨት ተገደዋል።

ከዚያማ ሌጣው ሕግ ላይ ድምፅ ተሰጥቶ 54 ለ46 በሆነ ድምፅ ፀደቀና ወደ ኮንግረስ ተመልሶ ተላከ። በኮንግረሱ ውስጥ የሪፐብሊካኖች መሪ ሆነው በአፈጉባኤነት የሚሰሩትበይነር፣ በሰኔት ለከልሶ የመጣውን አዋጅ በኮንግረስ አባላት ድምፅ እንዲሰጥበት አላደረጉም - “ለኦባማኬር በጀት አይመደብለትም” የሚለው ተጎታች ስለተሰረዘ። በዚያ ምትክ ሌላ አዋጅ አርቅቀው አቀረቡ - ለ10 ሳምንታት ገደማ የሚያገለግል ጊዜያዊ በጀትና ኦባማኬር በከፊል ለአንድ አመት እንዲዘገይ የሚደነግግ አዋጅ። አዋጁ ፀድቆ ወደ ሰኔት ሲሄድ ግን፣ ተመሳሳይ እጣ ገጠመው። “ኦባማኬር፣ በከፊል ለአንድ አመት ይዘገያል” የሚለው አንቀፅ ተሰርዞ 54 ለ46 በሆነ ድምፅ ወደ ኮንግረስ ተመለሰ። እንዲህ እንዲህ እያለ፣ በጀት ሳይፀድቅ የበጀት መዝያ እለት ደረሰ - ሰኞ ሴፕተምበር 30። በማግስቱም በጀት አልፀደቀም። ያለበጀት መስራት ስለማይችሉ ለጊዜው እንዲዘጉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መቼ እንደሚከፈቱ አይታወቅም። ለምን? ውዝግቡ መቼ እልባት እንደሚያገኝና መቼ በጀት እንደሚፀድቅ ስለማይታወቅ! ሁለት ሶስት ሳምንት ሊቆይ እንደሚችል ነው የሚገመተው።

Read 2484 times Last modified on Wednesday, 09 October 2013 12:26