Print this page
Saturday, 05 October 2013 09:57

የማይወርስ ጐረቤት በሟርት ይገድላል!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(ላታ ኤኬና ሾሮይ ብት ዎሬስ) - የወላይታ ተረት

        ከዕለታት አንድ ቀን፣ ከአንድ እርሻ አጠገብ፣ አንድ ኮሳሳ ውሻ ተኝቶ ፀሐይ እየሞቀ ሳለ፤ አንድ የተራበ ተኩላ ድንገት ከተፍ ይልበታል፡፡ ከዚያም ያንን ውሻ ለመብላት አሰፍስፎ፤ “እንዳትነቃነቅ! የዛሬ ቁርሴ አንተ ነህ!” ይለዋል፡፡ ውሻውም፤ “ጌታ ተኩላ ሆይ! እኔ ባሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት ኮሳሳ ፍጥረት እንደሆንኩ ታያለህ! አሁን እኔን በልተህ ምንም አትጠቀምም፡፡ ምክንያቱም አጥንቴ የቀረ ልሞት ጥቂት የቀረኝ እንስሳ ነኝ፡፡” ተኩላም፤ “ታዲያ እንዲሁ ባዶ ሆዴን እንድውልልህ ነው የምትፈልገው?” አለ፡፡ ውሻ፤ “የለም፡፡ ሁለት ሶስት ቀን ብትታገስ፤ የእኔ ጌታ ትልቅ ድግስ ለመደገስ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ከድግሱ በርካታ ትርፍራፊ እጄ ይገባል፡፡ ያኔ ብዙውን ሥጋ፤ አጥንትና ቅባት የጠጣ ምግብ፤ ላንተ አስረክብሃለሁ፡፡ ከዛ በኋላ፤ ከፈለግህ እኔን ጨምረህ ለመብላት ትችላለህ” ይለዋል፡፡ ተኩላው፤ በጉጉት ቆበሩን እየደፈቀ፤ “ይሄ በጣም ጥሩ ዕቅድ ነው፡፡

እንዳልከው ትንሽ ቀን መታገስ አያቅተኝም” ብሎ ውሻውን ጥሎ ወደጫካው ሄደ፡፡ በሶስተኛው ቀን ተኩላው ተመልሶ ወደ እርሻው ቦታ መጣ፡፡ ውሻው ግን እበረቱ ጣራ ላይ ተኝቶ ፀሐይ ይሞቃል፡፡ “ደህና ዋልክ አያ ውሻ” አለ ተኩላ፡፡ ውሻም፤ “እንደምን ሰነበትክ፤ ሰሞኑንኮ ከዛሬ ነገ ትመጣለህ እያልኩ ስጠብቅህ ከረምኩ፡፡ ምነው ጠፋህ?” ተኩላም፤ “ሁለት ሦስት ቀን ስላልከኝ፤ ጊዜ ልስጥህ ብዬ ነው፡፡ ይኸው በሶስተኛው ቀን መጣሁ፡፡ ጌታህ ይደግሳል ያልከኝ ድግስ የታለ? በስምምነታችን መሠረት ውረዳ?” ሲል ጠየቀው፤ ምላሱን ካፉ እያወጣ፣ ከንፈሩን እየላሰ የመብላት ስሜቱን በመግለጽ፡፡ ውሻም፤ “አይ አያ ተኩላ! ጌታዬማ ድግሱን ለሚቀጥለው ዓመት አዛወረው፡፡ ከእንግዲህ እኔንም ሁለተኛ ባለፈው ያገኘኸኝ ገላጣ ሜዳ ላይ አታገኘኝም፡፡ በእጅህ የገባልህን ነገር ትተህ፣ ገና ለገና አገኘዋለህ ብለህ፣ በተስፋ የተመኘኸውን ድግስ ልትበላ ስትስገበገብ፤ ሁለት ቀን ፆምህን መዋልህ ነው፡፡ ይልቅ አሁን ጌታዬ መምጫው ስለደረሰ ከዚህ ዞር ብትል ይሻልሃል” አለው፡፡ ተኩላው እየተናደደና እየዛተ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ውሻ እየሳቀ ፀሐይ መሞቁን ተያያዘው፡፡

                                                          * * *

ፀሐይ የሚሞቅ ውሻ ሁሉ ሞኝ አይደለም፡፡ ለነገ እበላዋለሁ የሚል ጅል ተኩላ ግን ምን ጊዜም አይጠፋም፡፡ ይህን ሁሉ የሚታዘብ ህዝብ እንዳለ የሚያውቅ ካለ የብልህም ብልህ ነው፡፡ ከላይ ከተረቱም እንደምንረዳው፤ የሌሎችን ግብና አዕምሮ ማማለልንና ማዘናጋትን የሚያውቁበት ሰዎች እንዳሉ አንርሳ! ተስፋ በመስጠት እንደዳማና እንደ ቼዝ ጠጠር (ወታደር) በፈለጉት አቅጣጫ ይገፉናል፡፡ ፍላጐታችንን ያከበሩ በመምሰል ፍላጐታቸውን የሚያሟሉ ሰዎች አደገኞች ናቸው፡፡ የህንዱ ፈላስፋ ካውቲላ “በቀስተኛ የተሰደደ ቀስት፣ አንድን ነጠላ ሰው ሊገድልም ላይገድልም ይችላል፡፡ የተቀመረ ሴራ ግን እናት ሆድ ውስጥ ያለውን ህፃን ሳይቀር ሊገድል ይችላል” ይላል፡፡ በዚህ የተካኑ ሰዎችን በዐይነ - ቁራኛ ማየት ያባት ነው፡፡ ስሜትን ተቆጣጥሮ ደባና ሴራን ጠንቅቆ ማየትና በጠዋት መንቃት ተገቢ ነው፡፡ እንደ ናፖሊዮን “ጠንካራ እጅህን ከሀር በተሰራ ጓንት ውስጥ ክተት” የሚሉ እንዳሉ እንገንዘብ፡፡ ድቀትና ዝቅጠት ሲያይል አሉባልታና ጥርጣሬ ይነግሳል፡፡ አንድም፤ “ጊዜ ሲበሳበስ መሾም መሸለም እየቀለለ ይመጣል”፡፡

(ሄልሙት ክሪስት እንዳለው) በእንዲህ ያለው ሰዓት አፍ - አዊ እየበረከተ፣ ልባዊና ተግባራዊ እየሳሳ ይመጣል፡፡ ይሄኔ መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ኒቼ እንደሚለን “የአንድ ነገር ዋጋ በዚያ ተገልግለን በምናገኘው ጥቅም አይለካም፡፡ ይልቁንም ያንን ነገር ለማግኘት በምንከፍለው መስዋዕትነት ነው የሚለካው”፡፡ አገር እንገነባለን ስንል ይህን ብሂል አለመርሳት ነው፡፡ ይሆነናል የምንለውን ሰው መርጠን ስንሾምም ይህንን አለመዘንጋት ነው፡፡ ባለሙያው እያለ ስለዚያ ሙያ የሚያወራ ሲበዛ ጠንቀቅ ማለት ያሻል፡፡ “አያገባው ገብቶ አያወዛው ተቀብቶ” እንደተባለው መሆኑን ልብ ማለት ነው፡፡ መጪዎቹ የፓርላማ ጊዜያት የጠነከሩ፣ ልባዊነት የሞላባቸውና አመርቂ እንዲሆኑ እንመኝ፡፡ “ሸንጐ/አደባባይ የሰለጠነ ጦርነት ነው” የሚባለው በዋዛ አይደለም፡፡ መሪዎች የሸንጐን ጥበብ መካን አለባቸው፡፡ አደባባይ መዋል የራሱ የክት ጠባይ አለው፡፡ “ሸንጐ የሚያውቅ ሰው፤ መልኩን መቆጣጠር ይችላል፡፡ በቀላሉ ልቡን አይሰጥም፡፡ ለክፉ አድራጊዎች ዕድል አይሰጥም፡፡ ለጠላቶቹ ፈገግ ማለት ይችላል፡፡ ንዴቱን መዋጥ ያቅበታል፡፡ ወገናዊነቱን መሸፈን ይችላል፡፡ የልቡን ደብቆ እሱ በዚያች ቅጽበት ልመስል ወይም ልሆን ይገባኛል የሚለውን፤ የሚፈልገውን ስሜት ያስተናግዳል፡፡ የራሱን ቦታ፣ መሬት፤ አገር፣ ውሉን አይስትም” ይለናል፤ ፈረንሣዊው ዣን ዴላ ብሩዬር፡፡ ፕሬዚዳንት ስንመርጥ እንዲህ ያለውን ቁም ነገር አንርሳ፡፡

ህግ ብቻውን ሁሉን ጉዳይ አይጨርስልንም፡፡ አስተዋይ አመራር፣ አስፈፃሚና ተጠያቂነትን ገምጋሚ እንዲኖር ያሻል፡፡ ያ ደግሞ ግልጽነትን ልማድ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ አሉባልታ የሚቆመው ግልፅነትና መረጃ ሰጪነት ሲከበር ነው፡፡ “የፕሬዚዳንቱ ቤት ኪራይ ጉዳይ፤ የእገሊት የውጪ ባንክ ገንዘብ ጉዳይ፣ የእነ እገሌ ህንፃ… ይሄ ተሸጠ፣ ያ ተገዛ…ወዘተ” የጥርጣሬና የሟርት ዘመን ምልኪዎች ናቸው፡፡ በምንም ዓይነት ግን የፖለቲካ ትግልን እንደማይተኩልን ማሰብ ተገቢ ነው! የፖለቲካ ትግል ከሁሉም በፊት መደራጀትን፣ ተደራጅቶም መስዋዕትነትን፣ በሀገር ላይ ለውጥ የማየት ልባዊ ስሜትን ይጠይቃል! በተግባር ሳይሆን አሉባልታዊና ሐሜተኛ ማህበረሰብ እየተገነባ ከመጣ የመዝቀጥ አሊያም የመስበስ ክፉ አባዜ መምጣቱን ይጠቁማል (Decadence እንዲሉ)፡፡ ተግባራዊና የሚለውን የሚተረጉም ማህበረሰብ ካልፈጠርን ሟርት ይበዛል፡፡ “የማይወርስ ጐረቤት በሟርት ይገድላል” ይላል የወላይታ ተረትና ምሣሌ፡፡ ይሄንኑ ሁኔታ በቅጡ ሊነግረን ፈልጐ ነው፡፡

Read 3603 times
Administrator

Latest from Administrator