Saturday, 05 October 2013 09:48

ኢዴፓ፤ የተቃዋሚዎች ሰልፎች ግብ የላቸውም አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ቀጣዩ ምርጫ ሲቃረብ ጠንካራ ሰልፎችን ለማድረግ አቅዷል

             ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚደረጉ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ተከልክሎ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት መፈቀዱን ውጪ የሚያሳኩት ግብ የላቸውም ሲል ኢዴፓ ገለፀ፡፡ የኢዴፓ ያለፉት ሁለት አመታት የትግል አካሄድና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያካሄዱትን የተቃውሞ ሰልፎች መገምገማቸውን የጠቀሱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የተቃውሞ ሰልፎቹ ኢህአዴግ የሚያውቃቸውን የተለመዱ ጥያቄዎች አደባባይ ይዞ በመውጣት የታፈኑ ድምፆችን ከማሰማት ያለፈ በስርአቱ ላይ ጫና የመፍጠር አቅም አልተንፀባረቀባቸውም ሲሉ ተችተዋል። “የሰልፎቹ አላማ ድምጽን ማሰማትና ጥያቄ ማቅረብ ብቻ ከሆነ፣ ውጤቱ ዲሞክራሲያዊ መብትን እንደገና መለማመድ ብቻ ይሆናል፤ ይህም ኢህአዴግ ከፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ጋር ተያይዞ ለሚነሱበት ጥያቄዎች ማዳፈኛ ይሆነዋል” ብለዋል፤ አቶ ሙሼ፡፡

የተቃውሞ ሰልፎቹ አላማ ኢህአዴግ ላይ ጫና መፍጠር ከሆነም የተሳታፊው ቁጥር በምርጫ 97 የቅንጅት ሰልፍ ላይ ከተሳተፈው ጋር ተመጣጣኝ መሆን ነበረበት ያሉት አቶ ሙሼ፤ ፓርቲያቸው ቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ሲቃረብ ምርጫውን ግብ ያደረጉ ጠንካራ ሠላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማድረግ ማቀዱን ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢዴፓ በነገው እለት 6ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሂድና፣ ፓርቲውን ለቀጣይ ሁለት አመታት የሚመሩ አዳዲስ አመራሮችን እንደሚመርጥ አቶ ሙሼ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ምንም እንኳ የፓርቲው ህገደንብ አንድ ግለሰብ በሁለት ዙር ምርጫዎች ለተከታታይ አራት አመታት ፓርቲውን የመምራት እድል የሚሰጥ ቢሆንም፣ አቶ ሙሼ በነገው ምርጫ ድጋሚ መመረጥ ስለማይፈልጉ ከወዲሁ ከፕሬዚዳንት እጩነት ራሳቸውን እንዳገለሉ አስታውቀዋል፡፡

Read 2801 times