Saturday, 05 October 2013 09:43

ኢራፓ የነገው ሰላማዊ ሰልፍ ከፅ/ቤቱ እንዳይጀመር መባሉን ተቃወመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

                በብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ዙሪያ በነገው እለት በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፤ የሠላማዊ ሠልፉን መነሻ ብሄራዊ አካባቢ ከሚገኘው የፓርቲው ፅ/ቤት እንዳያደርግ በአስተዳደሩ መከልከሉን አስታውቆ፤ ክልከላው አግባብነት እንደሌለውና አስቀድሞ ባወጣው መርሃ ግብር የሠልፉን መነሻ ከ/ፅቤቱ እንደሚያደርግ ገለፀ፡፡ በሠላማዊ ሠልፍ መነሻና መድረሻ ጉዳይ ላይ የፓርቲው አመራሮች ከመስተዳድሩ የከንቲባ ቢሮ ሃላፊ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን ያመለከተው የፓርቲው መግለጫ፤ የሠላማዊ ሠልፉ መነሻና መቋጫ ጃንሜዳ ብቻ መሆን እንዳለበት በቃልና በደብዳቤ እንደተገለፀለት አስታውቋል፡፡

ይሁን እንጂ “ክቡር የሠው ልጅ ቀርቶ እንስሣ እንኳ ጉዞውን የሚጀምረው ከቤቱ ወይም ከመኖርያ አድራሻው ነው” ያለው ፓርቲው፤ ሠልፉን ከፅ/ቤቱ አካባቢ ከመጀመር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ገልጿል፡፡ “ሠላማዊ ሠልፈኛ ዜጐቻችን የራሣቸው መሬት በስንዝርና በጭልፋ ተለክቶላቸው የሚሠጣቸው መሆን የለበትም” ያለው ፓርቲው፤ መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሌሎች በአማራጭነት ያቀረባቸው የነበሩ ቦታዎች ከባቡር ግንባታው ጋር በተያያዘ ሣይፈቀድለት መቅረቱንና በሣር፣ በሙጃ እንዲሁም በሠንበሌጥ በተሞላው ጃንሜዳ ውስጥ ብቻ ሠላማዊ ሠልፉን እንዲያከናውን ትዕዛዝ እንደተላለፈለት አስታውቋል፡፡ የአስተዳደሩ ትዕዛዝ አግባብነት አለው ብለን አናምንም ያለው ኢራፓ፤ የሠላማዊ ሠልፉ መነሻ ብሄራዊ አካባቢ ከሚገኘው የፓርቲው ፅ/ቤት ሆኖ፣ መዳረሻው ጃንሜዳ ይሆናል ብሏል፡፡

Read 1577 times Last modified on Saturday, 05 October 2013 09:47