Saturday, 05 October 2013 09:42

በጉራጌ የአበሽቲ ወረዳ የመሰናዶ ተማሪዎች ከትምህርት ተስተጓጐሉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

            “ይማሩ የተባሉበት አዲስ ትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶችን አላሟላም” ወላጆች በጉራጌ ዞን አበሽቲ ወረዳ የዳርጌ ቀበሌ የመሰናዶ ተማሪዎች በት/ቤቱ መሰረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጐላቸውን የተማሪዎቹ ወላጆች ተናገሩ፡፡ ከአንድ እስከ 10ኛ ክፍል በዳርጌ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ 11ኛ ክፍል ያለፉት ከ170 በላይ ተማሪዎች አዲሱ መሰናዶ ት/ቤት ገብተው ካልተማሩ የትም ሄደው መመዝገብ እንዳይችሉ ተደርገዋል ሲሉ የተማሪዎቹ ወላጆች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “ከዚህ በፊት በዳርጌ ት/ቤት አስረኛን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አስራ አንደኛ ሲያልፉ ወልቂጤ ከተማ የሚገኘው መሰናዶ ት/ቤት ውስጥ ይማሩ ነበር” ያሉት አንድ ወላጅ፤ በአሁኑ ሰዓት የተሰራው “ኮሌ” የተሰኘው መሰናዶ ት/ቤት ከመብራት በስተቀር እንደ ውሀ፣ ትራንስፖርት፣ የሚከራይ ቤት፣ እስኪሪብቶ ቢያልቅና ቢጠፋባቸው ወጥተው የሚገዙበት ሱቅም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶች ስላልተሟሉለት ልጆቻቸውን ልከው ማስተማር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ከዳርጌ ቀበሌ በ30 ኪ.ሜትር ከወልቂጤ ከተማ ደግሞ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ የተገለፀው አዲሱ የመሰናዶ ት/ቤት፤ ተማሪዎቹ ከወልቂጤም ሆነ ከዳርጌ በእግር ተመላልሰው ለመማር ሩቅ መሆኑን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለውና ት/ቤቱ በሚገኝበት ቦታ የሚከራይ ቤት ባለመኖሩ ተማሪዎቹ በአማራጭ ማጣት እየተጉላሉ ነው ተብሏል፡፡

“ወልቂጤም ሆነ ወሊሶ ወስደን ልጆቻችንን ልናስመዘግብ ስንል ከዳርጌ ቀበሌ ከመጣችሁ አንመዘግብም እየተባልን ተቸግረናል” ብለዋል ወላጆች፡፡ “ችግራችንን ለሚመለከታቸዉ አካላት በተዋረድ አቤቱታ አቅርበናል” ያሉት አንድ ወላጅ፤ ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞንም እስከ ክልል ድረስ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ ሰዎች ተወክለው ቢሄዱም ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውንና ልጆቻቸው የትምህርት ወቅቱ እየባከነባቸዉ መሆኑን በምሬት ገልፀዋል። የአካባቢው ሰው በራሱ ተነሳሽነት 500ሺ ብር አዋጥቶ አንድ ባለ አራት ክፍል ብሎክ ገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ ቢገኝም የዞኑም ሆነ የወረዳው ት/ቢሮዎች አዲሱ መሰናዶ ት/ቤት ገብተው ካልተማሩ በስተቀር ወላጆች በገነቡት ት/ቤት ውስጥ ልጆቻቸዉን ማስተማር እንደማይችሉ እንደገለፁላቸው ወላጆች ተናግረዋል፡፡ የአበሽቲ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን አበበ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ምላሽ በመስጠት ላይ እያሉ ስልካቸው የተቋረጠ ሲሆን በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ከአገልግሎት ውጭ በመሆኑ ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡

Read 1732 times Last modified on Saturday, 05 October 2013 09:47