Saturday, 28 September 2013 14:31

የ‘ቃለ መጠይቅ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
ስሙኝማ…ሰሞኑን…አለ አይደል… ‘ስትራቴጂና ዕቅድ በመንደፍ፣ የእኔን ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርግ አካሄድ ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ መርሀ ግብር የምነድፍበትና ወደ ትግበራ ልገባ ዝግጅት በማድረግ ያለሁበት ሁኔታ’ ነው ያለው፡፡ (የአንዳንዱ ሰው ትንፋሽ ምስጋን ይግባው!)
እናላችሁ… ለ‘አቅመ ቃለ መጠይቅ’ ተደረሰም፣ አልተደረሰ…ዘንድሮ ዝም ከተባለ ተውጦ መቅረት ይመጣል! ፎቶ ‘ለአቅመ መጽሔት ሽፋን’ የደረሰ ባይሆንም፣ ድምጽ ‘ለአቅመ ኤፍ.ኤም. “ፕሮግራማችሁ ተመችቶኛል” የበቃ ባይሆንም፣ አኮሰታተርና ‘ሲርየስ’ መምሰል ለአቅመ ቴሌቪዥን “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” ባይደርስም…ብቅ ተብሎ “እዚህ ነኝ…” ካልተባለ መኖራችን የሚታወቅልን በህዝብ ቆጠራ ወቅት ብቻ ሊሆን ነዋ!
እናላችሁ…ቃለ መጠየቅ ስሰጥ…አለ አይደል…ያው ‘መፈረጅ’ ምናምን ለሁሉም ስለማይቀር ጋዜጠኛ ሆዬ ከሊጥነት አላልፍ ያለው እንጀራ ‘ማብሰያ ምጣድ’ እንዳያደርገኝ…ልጄ ጠንቀቅ ነው። (በቅንፍ የተቀመጠው በሆዴ…ይቅርታ…በውስጤ የማስበውን እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ያው እንደተለመደው “በዛሬው ዝግጅታችን እከሌ እከሌ የሚባል እንግዳ…” ምናምን ይባልና የመጀመሪያው ‘ጥያቄ’ ይከተላል፡፡
ጥ፡– ስምዎንና የመጡበትን ቢነግሩን፡፡
(የምር እኮ… ‘ዘይገርም ዘንድሮ’ የሚያሰኝ ነው። አይደለም ስሙንና የመጣበትን የተወለደ ቀን ጎረቤት የሆነ ጠበል ይጠጣ እንደነበር ለመናገር ጫፍ ከደረሰ በኋላ በድጋሚ “ስምዎንና የመጡበትን…” ምናምን ተብሎ ሲጠየቅ አያስቸግርም! እናማ እንደፈረደብኝ ‘የተጠየኩትን’ እመልሳለሁ፡፡)
ጥ፡– ለመሆኑ ምግብ ላይ እንዴት ነህ? (እንዴት ነው ነገሩ…ስለ አራት ኪሎ ይጠይቀኛል ስል ስለ ራሴ ኪሎ! አሀ…ስለምግብ መጠየቅ ያው ስለ ኪሎ መጠየቅ ነዋ!)
መ፡– ማለት፣ ምግብ ላይ ስትል…
ጥ፡– ማለት…የምግብ ምርጫህ ምንድነው?
(የምግብ ምርጫ! አጅሬ…በራስህ ተነሳሽነት አራድነትን እንደ አርቲፊሻል ጸጉር ራስህ ላይ ቀጥለህ ጎንጉነሀልና ማሞኘትህ ነው! አሀ…በስንት ነገር ፍረጃ በበዛበት በሆዴ ምን አመጣው! ነገርዬውማ የዋዛ ጥያቄ አይደለችም፡፡ “ስፓጌቲ” ካልኩ…“ይሄ ሰውዬ በግራዚያኒ መታሰቢያ ግንባታ ላይ እጁ አለበት እንዴ?” ሊባል ይችላል፡፡ “ፈጢራ” እንዳልል…“እስቲ ግብጽ ኤምባሲ አካባቢ አዘውትሮ ይታይ እንደሆነ ክትትል ይደረግበት” ሊባል ይችላል…“የበቆሎ ገንፎ” እንዳልል “ለናይጄሪያዎች ስለ አሰላለፋችን ምስጢር አሳልፎ እንዳይሰጥ ልምምድ አካባቢ ዝር እንዳይል…” ሊባል ይችላል። ልጄ ዘንድሮ የምንጠጣው የቢራ አይነት እንኳን ‘መፈረጃ’ በሆነበት ዘመን…)
መ፡– እንጀራ በወጥ…
(ልጄ…ምንም እንኳን ‘የጤፍ ተጠቃሚ ቢበዛም’… ማስፈረጅ እስክትጀምር ድረስ “እንጀራ” ማለቱ ይሻላል!)
ጥ፡– አሀ…እንጀራ ለምሳና…
መ፡– የምን ምሳ ቁርሴም፣ ምሳዬም እራቴም እንጀራ በወጥ ነው፡፡
(እፎይ! ጠያቂዬ ለምሳ ሲያስበኝ የሻይ ቁርስ አደረግሁት…)
ጥ፡– በአጠቃላይ አመጋገብህ እንዴት ነው?
(ሰውየው ምን ነካው! ከምግብ ጋር ጥብቅ የሚለው ይርበዋል እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ… ስሙኝማ…የሆነ ጊዜ አንድ አንባቢዬ ጽሁፎቼን ሲያነብ ስለ ምግብ የሚነሱ ነገሮች ቢበዙበት ለአንድ ወዳጄ ምን አለው መሰላችሁ…“ይሄ ሰውዬ… ይርበዋል!” እናላችሁ…ጥያቄዋ አስቸጋሪ ነች፡፡ ልክ ነዋ…“ቁርሴን በዚህ ሰዓት፣ ምሳ በዚህ ሰዓት፣ እራት በዚህ ሰዓት…” ምናምን ካልኩት ምን ሊባል ይችላል መሰላችሁ… “መካከለኛ ገቢ ለመድረስ ስንትና ስንት ዓመት እየቀረን ይሄ ሰውዬ በቀን ሦስቴ ሊበላ የቻለበት ምክንያት ይጣራ…” ምናምን ሊባል ይችላላ!)
መ፡– ያው በቃ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለየ አመጋገብ የለኝም፡፡
(አሪፍ ጠያቂ ቢሆን “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያልከውን ብታብራራልኝ…” ምናምን ይለኝ ነበር፡፡)
ጥ፡– በአሁኑ ጊዜ ለሚታየው የሸቀጦች ዋጋ መናር ምን የምትለው ነገር አለ?
(ኧረ! ተባለ እንዴ!… “ምን ነጋዴዎች ላይ የሚጣለው የታክስ መአት…” ምናምን ብል “የሚገዛው ዕቃ ወይም የሚገዛበት ገንዘብ ሳይኖረው መርካቶ የሚመላለሰው እኮ ነገር ቢኖረው ነው…ለቂማ ምናምን ጣል፣ ጣል ሳያደርጉለት አይቀሩም…” ሊባል ይችላል፡፡ “የዋጋ መወደድ የዕድገት ምልክት ነው…” ብዬ ‘ለጊዜው ስሙ የማይታወሰኝ ኤኮኖሚስት የተናገረውን’ ብደግም “አጅሬዋ እኮ እንደ ምስጥ አፈር ስር ነው የምትሳበው…” ሊባል ይችላል፡፡)
መ፡– እንግዲህ ለዋግ መጨመር ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመመርመር…(እያልኩ ቀብጠርጠር አደርግና ጠያቂዬም እኔም ያልኩት ሳይገባን ‘ጥያቄው ይመለሳል’፡፡)
ጥ፡– ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን ትላለህ?
(እንዴት ነው ነገሩ! ኧረ’ባክህ ስለ አራት ኪሎ…)
መ፡– ጥያቄው አልገባኝም፡፡
ጥ፡– ማለት የአገራችን ሙዚቃ አድጓል ወይስ ወድቋል ትላለህ፡፡ (ኧረ እንደው የኢትዮጵያ አምላክ ውድ…ተውኩት፡፡)
መ፡– ኮፒራይት ይከበር…
(ጨረስኩ፡፡ ደግሞ… “ከየትም፣ ከየትም የተቆረሰና የተቦደሰ ዜማ አይሉት ‘ለህዝብ የተደረገ ንግግር’… እየለጠፉ ሙዚቃችንን እንኩሮ እያደረጉት ያሉ አንዳንድ…” ምናምን ብዬ “አንዳንድ ጋዜጠኛ ተብዬዎች…” ልባል! ስለሙዚቃ ስናወራ ከዚህ በፊት ያወራናት ነገር ትዝ አለችኝማ…አንድ ወዳጄ የሆነ ዘፋኝ አልበም ባወጣ ቁጥር ምን ይል ነበር መሰላችሁ…“እንትና ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር አደረገ…” ይል ነበር፡፡)
ጥ፡– ብሔራዊ ቡድናችን ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ አሁን ያለበት በመድረሱ ምን ይሰማሀል?
(የብሔራዊ ቡድን ነገር ገና ማስፈረጅ ስላልጀመረ ቀላል ነው፡፡)
መ፡– አሪፍ ነው፡፡
ጥ፡– ስለ አገር ውስጥ ቡድኖችስ ምን ታስባለህ?
(ምንም! ልጄ…ስንት ነገር ሲባል እየሰማን…አንዳንዴ ኳስ ጨዋታ እንደ ‘ሌላ አይነት ፍልሚያ’ እየተቆጠረ…ምንም አላስብም! ይልቅ ስለ አራት ኪሎ…)
መ፡– የአገር ውስጥ ውድድር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ (ዓረፍተ ነገሮች አጠር ሲሉ አሪፍ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ጥ፡– እኔ ጨርሻለሁ፣ እርሶ የሚጨምሩት ነገር አለ? (የምጨምረውማ…የሰጠኋቸው መልሶች ለሲቪህ ይጠቅሙሀል? ልክ ነዋ…አንዳንዴ ቃለ መጠይቅ አድራጊዎች…አለ አይደል…ልክ ስኖውደንን የሚያፋጥጡ የኤፍቢአይ ሰዎች አይነት ሲያደርጋቸው ያየኋቸው ይመስለኛላ! ስሙኝማ…መልሱ እነ እሱ ለክተው፣ ቀደው እንደሰፉት ሆኖ ካልተሰጣቸው የሚቆጡ ‘ቃለ መጠይቅ አድራጊዎችን’ ልብ ብላችሁልኛል! ለምን ቢሉ…ሲቪ ይበላሻላ! እነ እንትና…አለ አይደል… “…ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” “ዓለምን እያስደነቀ ያለው ዘርፈ ብዙ ዕድገት…” “ለብዙ ሀገራት ምሳሌ የሆነው ግስጋሴያችን…” ምናምን እያሉ አልፈው ሲሄዱ ‘የበይ ተመልካች ሆኖ መቅረት’ ይመጣላ!
መ፡– የምጨምረው የለኝም፡፡ (ይልቅ አለቃህን ሂደህ “ለምንድነው ደሞዝ የማትጨምርልኝ?” ብትል አይሻልም!)
ሀሳቤን ለውጫለሁ፡፡
ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የነደፍኩት ታክቲከና ስትራቴጂ የእኔን ተጠቃሚነት ገምግሞ በመፈተሽ ልማታዊ የሆነ መፍትሄ የማይሰጥ፣ ይልቁንም ያለፈውን ናፋቂነት የሚታይበትና የተባበሩት መንግሥታትን ‘ሚሌኒየም ዴቬሎፕመንት ጎል’ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አካሄድ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ ከቀጠልኩ የትንፋሽ እጥረት ሊገጥመኝ የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 3520 times