Saturday, 28 September 2013 13:58

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

(ካለፈው የቀጠለ)
“አንኳኩ ይከፈትላችኋል”
ከአዳማ ዕድሮች፣ የእንረዳዳ ዕድሮች ማህበር፣ ሰብሳቢ ከአቶ ታምራት አስፋው ጋር መወያየት ላይ ሳለሁ ነበር ባለፈው ጽሑፌን ያቋረጥኩት። የማህበሩ ሰብሳቢ ባለ ሁለት እርከን ፎቅ በገቢ ምንጭነት ለመሥራት እንዳቀደ፤ የተለያዩና ተያያዥ አካላትን በር እንዳንኳኳ ነገረኝ፡፡
በተለይ ከሃይማኖት ድርጅቶች ጋር በጥብቅ ትስስር እንደተግባቡ አወጋኝ፡፡
“ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ትልቅ መድረክ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰባቱ ወንጌሎች ተጋብዘው ሌሎችም ምዕመናን በተገኙበት ትልቅ ጉባዔ አድርገን፣ ከፍተኛ ድጋፍ ተገኘ” አለኝ። “ምን ብላችሁ ተናግራችሁ ነው?” አልኩት። አቶ ታምራት የሚገርም መልስ ነው የሰጠኝ፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆቻቸውን ስላጡ ህፃናት ምን ይላል? ህብረተሰቡ ምን ሊያደርግላቸው ይገባል? ምንድነው ግዴታው? ይህንን በተመለከተ አባት መምህራንና ካህናት ለምዕመኑ አስተማሩልን፡፡ የደከሙ አረጋውያንን ስለመርዳት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ምዕመናንስ ምን ይጠበቅባቸዋል? አስረዱልን አልን፡፡ ትልቅ ትልቅ ትምህርት ሰጡልን” ምዕመናኑ፤ ምን ያህል ይሆናሉ ብዬ ጠየኩት፡፡ “ከ10ሺ በላይ” አለኝ በኩራት፡፡
አሁን ደግሞ እንደዚሁ ከሙስሊሞቹም ጋር ተግባብተናል፡፡ አንድ መድረክ ሊፈጥሩልን ነው፡፡ ከካቶሊኮች፣ ከፕሮቴስታንቶችም እንደዚያው ብቻ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል ነው ሚስጥሩ፡፡ ለሥራህ ራስህን መስጠት ነው፡፡ አሳታፊ ዓይነት አሠራር ካለ የማይከፈት በር የለም፡፡
ከዚያ ሠሌዳ ላይ ያሉ ፎቶዎች አሳየኝ። “ምንድናቸው?” አልኩት፡፡ “ባለሀብቶች” አለ ኮራ ብሎ፡፡ “አላማችንን ተረድተው በሙያም፣ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም ድጋፍ የሰጡን ናቸው። ከብፁዕ አቡነ ጐርጐሪዮስ የምሥራቅ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ጀምረህ፤ የክሊኒክ ባለቤት በል፣ የሆቴል ባለቤት በል፤ የዩኒቨርሲቲ መምህር/ወጣት (ባለቀይ ክራቫት፣ መምህር የበጐ ፈቃድ አገልጋይ) እነዚህ ሁሉ ህፃናትን በነፃ በማከም፣ በየወሩ ለዕድሜ ልክ የገንዘብ መዋጮ በመስጠት፣ አረጋውያንን በመደገፍና ልጆችን በማሳደግ ስኮላርሺፕ በመስጠት ከፍተኛ ትብብር እያሳዩን ነው፡፡ ሌላውን ተወውና፤ ለህፃናት 25ሺ ለአረጋውያን 25ሺ እና በዓመት ግማሽ ሚሊዮን የሰጠን ሰው አለ፡፡ ያበረታታናል ባለሀብቱ፡፡
“ይቺ በር ማንኳኳት በጣም ጥሩ ናት እ”? አልኩት፡፡
“መጽሐፉ ነዋ ያለው! ለምን እንቆጠባለን፡፡ አለዚያ ትዕዛዝ ማፍረስኮ ነው!”
በኦሮሚያ ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት በኩል ከአምናው ማስ ስፖርት 326,955.55 ብር አግኝተናል” አለኝ፤ አሁንም በሥራ እርካታ፡፡ ሌላ የተደረደሩ ፎቶዎች አየሁና “እነዚህስ?” አልኩት፡፡ “እነዚህ አረጋውያን ናቸው፡፡ የምንረዳቸው ናቸው፡፡ ቀይ መስቀል ወጣቶችን አስተባብረን ግቢያቸው ይፀዳል፡፡ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሲታመሙ እናሳክማቸዋለን፡፡ በዓመት በዓል ቀን ሥጋ ቋጥረን በባጃጅ እንልክላቸዋለን፡፡ ጐረቤት እንዲያጐርሳቸው እናስተባብራለን”፡፡
በምን መረጣችኋቸው? አልኩት፡፡ “መመዘኛ አለና! አምስት መስፈርቶች አሉ” ለአሳዳጊዎች ብድርና ቁጠባ አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ፋይናንሱን በሂሳብ ህግ በባለሙያ ነው የምናስተዳድረው፡፡ ግልጽ አሠራር ነው ያለን፡፡ ካልሆነ ነገ አለመታመን ይመጣና ያ ሁሉ ግርማ ሞገስ ይሟሽሻል፡፡ ዓላማው ሟሸሸ ማለት ነው፡፡ ምስክርነት ካጣን ማህበር የለም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደድሮ ልጃገረድ የምንጠነቀቀው!!
ቀጥዬ፤ “አሁን እንደእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ያሉት አብረዋችሁ የሚሠሩ ድርጅቶች ቢለዩዋችሁ እንዴት ትቀጥላላችሁ?” አልኩት፡፡ “በጭራሽ አትጠራጠር፤ ራሳችንን ችለናል። ለወጣቱ መዝናኛ ማዕከል ዘርግተናል፤ የባለሁለት ፎቁ ገቢ አለ፣ ዘመናዊ ቀብር ማስፈፀሚያ አቅደናል፣ ፎቶ ኮፒ ማዕከል ልናቋቁም ነው፤ ምኑ ቅጡ! ዘላቂነታችን አስተማማኝ ነው፡፡
ከታምራት ጋር ሻይ ቡና ብለን ተለያየን፡፡
* * *
ቁጥር 5 የቅዱስ ገብርኤል መረዳጃ ዕድር - “ልጅነቴን ያስታወሰኝ ዕድር”
“ካፒታላችን ህዝባችን ነው!”
- የዕድሩ ሰብሳቢ
ናዝሬት (አዳማ) አገሬ ነውና ከእንረዳዳ ማህበር ቀጥዬ ካራመራ ሆቴል ጀርባ ወደሚገኘው ቁጥር 5 የቅዱስ ገብርኤል መረዳጃ እድር አመራሁ፡፡ የናዝሬት ፀሐይ ማቃጠል ጀምሯል፡፡ የጥንት የጠዋት የአዳማ ልጅ ብሆንም አልማረችኝም፡፡ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ” ነው መሰለኝ የናዝሬት ፀሐይ መርህ!
“ነባር ዕድር ይመስላል” አልኩት፤ ለዕድሩ ሰብሳቢ ለአቶ ክፍሌ፡፡
“ይሄ ዕድር እኔ ከቤተሰብ የወረስኩት ነው” አለኝ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያለ የሚመስለው ጠይሙ፤ አጠር ያለው መሪ - አቶ ክፍሌ፡፡ ፀሐፊውና ፕሮጄክት ሃላፊው፤ የሥራ ባልደረቦቹ አጠገቡ አሉ፡፡ “ዕድራችን፤ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ የተቋቋመ ነው፡፡ ደርግ ሲመጣ ቤቶቹን ወረሰ፡፡ ከሚከራዩት ቤቶች ማህል እስካሁንም ያልተመለሱ አሉ” አለ ክፍሌ በቁጭት፡፡ ከአዳማ እጅግ ነባር ዕድሮች ውስጥ ምናልባት አንደኛ ነው በሚባለው ቅፅር ግቢ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ (62 ዓመት ያህል ሆኖታል፤ 1937 ዓ.ም ስለተመሠተ) ክፍሌ ሲናገር በቁጭት ነው፡፡ “ዕድሩ ቤት ተቸግሯል፡፡ ሌላው ይጠቀምበታል፡፡ ዞሮ ዞሮ እስከደርግ ማብቂያ ድረስ የዕድሩ የልማት ሀሳብ ተቀዛቅዞ ቆየ፡፡ ከ417 በላይ አባላት የነበሩት አንጋፋ ዕድር፤ ግማሹ - አገር እየቀየረ፣ ግማሹ እያረጀ፣ ከፊሉ እየሞተ፤ አሁን ወደ 340 ግድም አባላት አሉት፡፡ በዚህ ዘመን እንግዲህ የልማት አቅጣጫዎች ቀርበዋል፡፡ መንግሥትም ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡”
“ዕድሩ እንዴት የልማት አቅጣጫ ያዘ?”
“በድሮ ጊዜ የነበረው ባህላዊ የመረዳዳት መንፈስ ብቻ ሳይሆን፣ ለምን ወደ ልማት አንገባም? አልን። ገባን፡፡ መንግሥት በዚሁ ከተማ 680 ካ.ሜ ቦታ ሰጠን፡፡ ባለ 4 ፎቅ ት/ቤት ሠርተን-ሥራ ጀምሯል፡፡ አቅጣጫው፤ ላይ ወደ መድሐኒዓለም ነው!”
“በምን ገንዘብ ነው የምትንቀሳቀሱት?” አልኩት።
“የህብረተሰቡን መዋጮ በመጠቀም ነው። ይሄ ህ/ሰብ ሁሉን ያሟላል፡፡ በቂ ደሀ አለው፡፡ መካከለኛና ከፍተኛ ሀብታም አለው፡፡ በዕውቀትም ከመጨረሻ ወለል እስከ ላይ ድረስ አለው፡፡ በጋራ ይሠራሉ። ለምሣሌ ምህንድስናውን የያዙልን አባላት አሉን። በጎ-ፈቃደኞች ማለቴ ነው። የሚገርምህ ቦታውን ስንጠይቅ የተጠየቅነውን ጥያቄ ነው ያነሳህልኝ-“በምን ገንዘብ ትሠሩታላችሁ? ካፒታላችሁን አሳዩን?” አሉን፡፡ ካፒታላችን ህዝባችን ነው፣ ነበር ያልናቸው፡፡ ዕውቀት ያለው፣ ገንዘብ ያለው ህዝብ አለን! በሃሳቡ ተስማሙ፡፡ በደስታ ሰጡን። ት/ቤቱ ዛሬ በወር 17ሺ ብር ያስገባል፡፡ በዚህ አላቆምንም። በየጎዳናው ላይ የሚወድቀውን፣ ረዳት ያጣውን፣ ከኑሮ ወለል በታች የወደቀ ድሀ እንርዳ ብለን ተነሳን፡፡ ያን ጊዜ እየሩሣሌም ህፃናትና ማ/ሰብ ልማት ድርጅት እንዲህ ያለ የተቀደሰ ተግባር የሚያካሂዱ ዕድሮችን ያፈላልግ ስለነበር፤ እኛን ያገኘናል፡፡ ሁሉንም ጠይቆን ፕሮጀክታችንንና ዓላማችንን ከተረዳ በኋላ፤ በገንዘብ ሊደግፈን ፈለገ፡፡ ርዳታ ሰጠን፡፡ እኛም በሚገባ ተግባራዊ አደረግን፡፡ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ድጋፍ ሰጠን፡፡ ለአሳዳጊዎቹ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ሰጠን፡፡ አደጉና ራሳቸውን ቻሉበት፡፡ ለህፃናት የት/ቤት ቁሳቁስ ከላጲስ እስከ ዩኒፎርም ልብስ፣ ቦርሳ፣ መደበኛ ልብስ፣ ጫማ ስናደርስ ቆየን፡፡ ይሄ አንደኛው ፌዝ (Phase) ነበር፡፡ ቀጠልን፡፡ በሁለት፣ ሦስት መርሀግብር ተራ (Phase) 200 ህፃናትንም በትምርት አቅርቦት በኩል ምንም ሳይጐልባቸው እንዲማሩ ወላጆቻቸውና አሳዳጊዎቻቸው ራሳቸውን እንዲለውጡና ራሳቸውን እንዲችሉ ብድር ሰጥተን አጠነከርናቸው፡፡ ህፃናት፤ ከህክምና ማዕከል ጋር እየተነጋገርን እንዲታከሙ አድርገናል፡፡
(ሌሎቹ የዕድሩ አባላት የሰጡት አንኳር አንኳር አስተያየት በሚቀጥለው ሣምንት ከደብረ ዘይትና ከአዋሳ ጉዞ ማስታወሻዬ ጋር ይቀርባል!)
(ይቀጥላል)

Read 2705 times