Saturday, 28 September 2013 13:38

ሰሜን ወሎ:- ከቡሄ እስከ መስቀል

Written by  ከዮሐንስ ገ/መድህን
Rate this item
(0 votes)

የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ ወደሆነችው የወልድያ ከተማ ነሐሴ አጋማሽ ላይ አቀናሁ፡፡ በየዓመቱ ቡሄ በመጣ ቁጥር የልጅነት ትውስታዬ የሆነው የዚያ አካባቢ የተለየ የቡሄ አጨፋፈርና የመስቀል አከባበር በሬዲዮ ወይም በፕሬስ ውጤቶች ላይ ቀርበው አይቼ አላውቅም፡፡ አሁን ከሌላ ከምጠብቅ ለምን ራሴ አላቀርበውም ብዬ የተነሳሁት፡፡ የወልድያ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን አቶ አያሌው ገዳሙን እህሳ? አልኳቸው፤ እንዲህ አወጉኝ፡-
“ሆያ ሆዬ የቡሄ ሶለላ አሆ ሰለሌ አስገባኝ በረኛ” የሚባል አለ፡፡ ቡሄ ጨፋሪው እከሌ እከሌ ቤት እንሂድ ብለው ይሰባሰቡና ወደመረጡት ቤት ሲሄዱ
አስገባኝ በረኛ አሃሃ አሆሆ አስገባኝ በረኛ
በጊዜ እንድተኛ አሃሃ አሆሆ አስገባኝ በረኛ
እየተባለ ከበር ላይ ሆኖ ይጨፈራል፡፡ ከቤቱ በር እንደደረሱም
በሕብረት
አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ጨረቃ ድመቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ኮከብ ተሰለቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ ኧረ እማማ እንትና አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
አሆ ሰለሌ የሴቶች አረቂ አሆ ሰለሌ አሆ ሆዬ በል
እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ ሌላው ቀበል ያደርግና:- ዜማውን ወደ ሆያ ሆዬ ይቀይረዋል (ዜማውን እንዴት ልፃፈው?)
ሆያ ሆዬ ሆ
የኔማ ጌታ ሆ
የሰጠኝ ብር ሆ
ሁለመናዋ ሆ
የምታምር ሆ
እንዲህ ሲጨፍሩ ከቤት ውስጥ አንድ ሰው ወጥቶ የሚሰጠውን ይሰጣል
በሕብረት
እሆይ ናሃሃ እሆይ ናሃሃ
እንዳባባ እከሌ መስጠትን ማን አውቆ አሆይ እሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይ ናና
ባላገር ይሞታል በድሪቶ ታንቆ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
አሆይ እንደቸርዮ አሆይ አሆይናና
አሆይ እንደሚዛኑ አሆይ አሆይናና
ሚዛኑ ሚዛኑ ሚዛኑ ዘለቀ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
እንደሰማይ ኮከብ እያብረቀረቀ አሆይ
አሆይ ናና አሆይ አሆይናና
ቸሩ ሆዬ አሆ
ቸሩ ሆዬ አሆ
እንዳንበሳ አሆ
ምድር ብሳ አሆ
እያሉ ወደቀጣዩ ይሄዳሉ፡፡ የሚሄዱበት ቤት ራቅ ያለ እንደሆን :-
ሽቦ ኧረ ዋርዳው ሽቦ ሃሃ ሃሃዋ
ሽቦ ኧረ ዋርዳው ሽቦ ሃሃ ሃሃዋ…
እያለ ከቦታው ሲደርስ
አስገባኝ በረኛ አሆሆ አሃሃ አስገባኝ በረኛ
በጊዜ እንድተኛ አሆሆ አሃሃ አስገባኝ በረኛ…
እያሉ ወደቤቱ ይጠ/oና
በሕብረት
የቡሄ ሰለላ የቡሄ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ከፈረስ አፍንጫ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ይውላል ትንኝ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ኧረ አባባ እከሌ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ጤና ይስጥልኝ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ እንኳን ደህና መጡ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ከሄዱበት አገር የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ጠላቶችህ ሁላ የቡሄ ሰለላ የቡሄ
የቡሄ ሶለካ ይቅር ብለው ነበር የቡሄ ሰለላ የቡሄ
እየተባለ ይጨፈራል፡፡
ወዲያው የሚሰጥ እየሰጠ፣ ሌላውም ለመስቀል ገንቦ ጠላ፣ ድፎ ዳቦ ወይም ሰላሣ… ሃያ እንጀራ እሰጣለሁ እያለ ቃል እየገባ ይሸኛቸዋል፡፡
ከ16 ኪዳነ ምሕረት ጀምሮ፤ እስከመስቀል ድረስ ይጨፈራል፡፡ ሆያ ሆዬ ሲል የሰነበተው ጐረምሳም፤ ህፃናትም ያገኘውን ሁሉ በየአለቃው ያዥነት ገንዘብ ያጠራቅምና መስቀል አንድ አራት ቀን ሲቀረው በግ ይገዛል፡፡
የመስቀል ዕለት፤ ወላጆች ትንሽ ትልቁ አዛውንቱ መስቀልን ለማክበር ለሊት ደመራ ተደምሮ ባደረበት ቦታ ልክ ከለሊቱ አስር ሰዓት፣ እያንዳንዱ ችቦውን አብርቶ በመያዝ ከቤቱ እንዲህ እያለ በመጀመር፡-

ዳብር ዳብር ዳብር
የጐመን ምንቸት ውጣ
የሥጋ ምንቸት ግባ…እያለ ይወጣል፡፡
የጤና ግዜ፣ የሰላም ጊዜ፣ የደስታ ጊዜ… የማግኘት ጊዜ ያድርግልን እያሉ… ለከርሞ በሰላም የምንደርስ ያድርገን፣ ዳብር ዳብር እያለ… በየቤቱ፣ በየሙሃቻው፣ ሊጥ በተቦካበት ድህነት ውጣ ሀብት ግባ፣ ጐመን ውጣ ሥጋ ግባ… እያለ መስቀል መለኮሻው ላይ ይሰባሰባል፡፡ ከዚያ ደመራውን እየዞረ
እዮሃ መስቀል ነሽ
ሳይሞት ያግኝሽ
እዮሃ እዮሃ
እየተባለ ሶስት ጊዜ ይዞርና ደመራው ይለኮሳል፡፡ አንዲት ከደመራው መሃል የተተከለች ረጅም እንጨት በመጨረሻ ላይ ስትወድቅ ያቺ እንጨት የወደቀችበትን አቅጣጫ ተመልክተው “ዘንድሮ በዚህ አካባቢ አዝመራ ይዟል” ይባላል፡፡ ይህ ከተባለ በኋላ፤ ቡሄ ሲጨፍሩ የነበሩ ወጣቶች በየቡድናቸው የገዟቸውን በጐች ያቀርባሉ፡፡
“አባቶቻችን እንግዲህ በሰጣችሁን ገንዘብ በግ ገዝተን አበርክተናል” ይላሉ፡፡ ሃያ በግ ቀርቦ እንደሆነ አምስቱን ይወስዱና፡- “የተቀረውን ለእናንተ መርቀናል፤ እናንተ አርዳችሁ ብሉ” ይሉና ቡሄ ለጨፈሩት ይሰጧቸዋል - ዕልልታው ይቀልጣል፡፡ ሽማግሌ ተነስቶ ይመረቃል፡፡
“ዓመት አውዳመት ያድርሳችሁ፡፡ (አብሮ ያድርሰን) ከርሞ ይኸን ጊዜ ደግሞ የሌለው አግኝቶ ያለውም ጨምሮ የምንሰጥ እግዚአብሔር ያድርገን” ተብሎ ይመረቃል፡፡ ከዚያ ቡሄ ጨፋሪዎቹ የተመረቀላቸውን በግ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ማለዳ፤ በጉ ሁላ ይታረድና ገንቦ ጠላ፣ አንድ ሙጌራ ሃምሳ እንጀራ ወይ ሰላሳ እንጀራ ለመስቀል ሊሰጥ ቃል ወደገቡት ሰዎች ቤት ገንቦ እየተያዘ ይዞርና፣ በጉ በታረደት ቤት በጋንና በበርሜል ይቀመጣል፡፡ ምግቡ ይሰናዳና ሁሉም ይበላል፤ ይጠጣል፡፡ ይደሰታል፡፡
በነጋታው ተማሪው ወደ ትምህርቱ፣ እረኛው ወደ ኩበቱ፣ ገበሬው ወደ እርሻው ይሄድና፤ ማታ ለመብላት እንደገና ይሰበሰባል፡፡ ይበላል፤ ይጠጣል ይጨፈራል፡፡ ከዚያም የተዘጋጀው ሲያልቅ… “ለከርሞ ያድርሰን” ተባብሎ፣ ተመራርቆ ይበተናል፡፡
የጤና፣ የሰላም፣ የደስታ ጊዜ ያድርግልን! ለከርሞ በሰላም ያድርሰን! ቸር እንሰንብት!

 

Read 2532 times