Saturday, 28 September 2013 13:28

ዴንጌሣት

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ዴንጌሣት - የልጅ እሳት
ዴንጌሣት - የልጅ መብራት…
የባህል ችቦ መቀነት
ከዘመን ዘመን ማብሰሪያ፣የመስቀል ብርሃን “ኬር” በሥራት፡፡
“በእሳት አትጫወት” ይላል አበሻ ልጁን ሲያሳድግ
ዴንጌሣትን ባያውቀው ነው፤ የጉራጌን ባህልና ወግ
ገና በጥንስስ በጭሱ፣ መስቀልን እንደሚታደግ
በችቦ ማህል ተወልዶ፣ ንግዱን እንደሚያንቦገቡግ
በእሳት አልፎ እሳት ሲሆን
አላየውም ጉራጌውን
ዴንጌሣት ነው የዚህ እርከን!
ጉራጌ የላቡን ሠርቶ
ዓመቱን በንግዱ ገፍቶ
በፍቅሩ ልጆቹን አይቶ
የለማው በፊናው ለፍቶ
የተገፋውም ተገፍቶ፤
ላንደኛው አዱኛ በርቶ
ያንዱ መክሊቱ ከስቶ
ያም ሆኖ በቀኑ ተግቶ
መስቀሉን በዕድሜው አብርቶ
የልጅ - እሳት፣ የዴንጋ - እሳት፤ ለምለም ጨረር ይዞ መጥቶ
ይሄው በመስቀል ወር ጥቢ፣ ኬር! ይላል የዓመቱን ንጋት
ኬር! ይላል የዓመቱን ብሥራት
ፍሬው በስሎ፣ ቅርሱ ሲያብብ፤ ማየት ነው ያገሬው ኩራት
ዴንጌሣት የልጆች ምትሃት
ጐርፍ ላይ የሚሄድ እሳት
ዓመቱን እንደብጤቱ፣ ሰው መቼም አቅሙን ለክቶ
እንደየርምጃው ነውና፣ የሚሄድ ብርሃን አይቶ
እንደዘመን እንደ ዓመሉ…ነግዶም አርሶም አምርቶ
ወይ ጀግኖ አሊያም ፈርቶ
ወይ ሸሽቶ ወይ ዝቶ ኮርቶ
ወይ ተኮራርፎ ወይ ታርቆ
ወይ ከስሮ ወይ አንሰራርቶ
አትርፎ ወይ “ፓሪ” ወጥቶ
በጋን እንደበጋ ፀሐይ፣ ክረምትን እንደዶፍ ዝናብ
ሁሉን ችሎ ሁሉን አዝሎ፣ ሁሉን የንግድ አጀብ ወጀብ
ተቀብሎ ታግሎ፣ ጥሎ፤
አቀርቅሮ ቀና ብሎ
የተስፋ ጐሁን በችቦ፣ ቀዶ በዴንጌሣት ፍካት
በዝናብ ውጋገን እሳት
የመስቀል ደመራ ዜማ
ያውዳመት ሆታ ዋዜማ
የልጆች ርችት ማማ
አገር ሲታጠር በአበባ
የኮከቦች ሳቅ ሲተባ
የማይሞት የማይነቀል
ኗሪ የጉራጌ ባህል፤
እንደህፃን ፍልቅልቅ ፊት፣ እነደመስክ ብርሃን ወለል፤
መስከረም ወር ፍንትው ሲል፣
ገጠር ከተማውን ዳብሶ፣ ዴንጌሣት ዙሪያ ይሞላል!
ዴንጌሣት የፍቅር እሳት
የልጅ መቅሰስ ያዋቂ እራት
ነግ እንዲያበራ ይህ ልማድ፣ መስቀል - ወፍ እንድትዘምረው
ምራቅ የዋጥን፣ ልማድ ያቀፍን፤
አሻግረን እንለኩሰው
ለአገር ልጅ እናስረክበው
ጐዶሏችንን እንሰብስብ፣ ሙሉማ አለ በጃችን
ዘለዓለምን ለማሸነፍ፣ ብርሃን ነው መሣሪያዎችን !
ሁሌም ዴንጌሣት ለማየት፣ አሁን ያለን እንበቃለን፡፡
ይህን የልጆች ህብር እሳት፣ እጅ በእጅ እንለኩሰው
ወትሮም በእፍኝ ጭራሮ ነው፣ አገር - ምድሩ የሚበራው
ባህል የሚኖር እንዲህ ነው፣ ትውልድ የሚጫር በዚህ ነው!
አገር ማለት ዴንጌሣት ነው!
ኬር እንሁን ኬር እናርገው!
የጉራጌ ብርሃን ህልም፣ እዚህ ጋ ነው ትርጉም ያለው፡፡
ዴንጌሣት የልጅ አገር ነው፤
አገር ማለት ዴንጌሣት ነው፡፡
መስከረም 14/2006
(ለዴንጌሣት በዓልና ባህሉን ለሚያከብሩ)

 

Read 3870 times