Saturday, 26 November 2011 08:23

በስደት ያሉ ዜጐቻችንን ደህንነት የሚከታተለው ማነው?

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

ከአገራችን እድሜ ጠገብ ባህላዊ ዘፈኖች አንዱ እንዲህ የሚል ግጥም አለው፡-  
ካገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ፣
ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ፡፡
ከአገሩ ወጥቶ በሰው ሀገር በስደት የሚኖርን ሠው፤ ፈተናና እንግልት ያለ ብዙ ማብራሪያ በቀላሉ የሚያስረዳ ስንኝ ነው፡፡ የሠው ልጆች በልጅነትም ሆነ በአዋቂነት ዘመናቸው ሊሆኑ የሚመኙትን አይነት ሠው ሆነው የእድሜ ዘመናቸውን ተወልደው ባደጉበት ሀገራቸው ውስጥ ማሳለፍ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ፍላጐት የበለፀጉት የአውሮፓውያንና የአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን ከፍ ባለ የጉስቁልና ኑሮ የሚኖሩት የታዳጊ ሀገራት ህዝቦችም ፍላጐት ነው፡፡ ስደት የሠው ልጆች ወደ ስምና ሀገር አልባነት የሚቀየሩበት አስከፊ የህይወት እጣ እንደሆነ፣ ይህ አስከፊ እጣ ደርሶአቸው ፈተናውን ከእነ ገፈቱ ያጣጣሙት ይመሰክራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ሠዎች በሀገራቸው ሠርተው ለመኖር እንዳይችሉ በሚያደርግና ከአቅማቸው በላይ በሆነ ሀይል ሲገፉ አሊያም ደግም በሀገራቸው ውስጥ የእለት ጉርሳቸውንና የአመት ጨርቃቸውን ለመሸፈን የሚበቃ ስራ ሠርተው ለመኖር የሚያስችል እድልና ተስፋ ሲያጡ፣ አስከፊ ነው የምንለውን ስደት አይናቸውን ሳያሹ ይመርጡታል፡፡ እናም የተሳካለት በቦሌ ያላለለት ደግሞ አሳልፍላት ይሆናል ብሎ የተመኘላትን ነፍሱን የአሳና የውሀ ሲሳይ የሚያደርግን ጉዞ ሳይፈራ፣ ባህር አቋርጦ በረሀን ሠንጥቆ እድሉ ወደመራቸው ይሠደዳል፡፡ የስደት አድባር የተቀበለችው በደረሠበት ሀገር አንድ ቀን የቻልኩትን ያህል ጥሪት ቋጥሬ፣ አገሬ እገባለሁ በሚል ተስፋ ያሠባትን ጥሪት እስኪቋጥር ድረስ “ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ” ሆኖ የስደት ኑሮውን ሲገፋ፤ አድባሯ ፊቷን ያዞረችበት ደግሞ ካሠበው ሳይደርስ የባህር አሳና የበረሀ አሸዋ ሲሳይ ሆኖ እንደወጣ ይቀራል፡፡ ይህን በዘመናችን ሁሉ እያየን ስንታዘብ ኖረናል፡፡ ዛሬም እንዲሁ፡፡ 
መንግስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሠባትና ስምንት አመታት አለምን ሁሉ ጉድ ያስባለ ተከታታይ ባለ ሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የህዝቦችን የኑሮ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ እንደቻለ፤ ከሁሉም በላይ ደግም ሀገሪቱ መንግስት መስርታ እንደ ሀገር ከቆመችበት ዘመን ጀምሮ ጨርሶ ያልታየ ሚሊዬነር አርሶ አደር ማፍራት መቻሉን ነጋ ጠባ ይደሰኩረናል፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን አገራችን በተባበሩት መንግስታት የምዕተ አመቱ የልማት ግቦች፣ የተቀመጡትን ግቦች ከታዳጊ ሀገራት ቀድማ ማሳካት እንደምትችልና ኢትዮጵያ ራሷ እንደገመተችው ሳይሆን ከዚያ በጣም ባጠረ ጊዜ (በሚቀጥሉት አስር አመታት ውስጥ) ብቻ ባለመካከለኛ ገቢ ሀገር መሆን ትችላለች ተብሎ በአለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ እንደተመሠከረላት፣ እሱም ሳይሰለች እኛንም ይሰለቻሉ ብሎ ሳይጨነቅ ሲያስረዳን ቆይቷል፡፡
ሁነኛና ተገቢውን የመንግስት ጆሮ ማግኘታችንን በእርግጠኝነት አናውቀውም እንጂ በሚሊዮን የምንቆጠረው እኛ ደግሞ መንግስት የሚጠቅሳትንና ሌሎችም የመሠከሩላትን ኢትዮጵያ ፈልገን ማግኘት እንዳልቻልን፣ ከዚያ ሁሉ አለምን ያስደነቀ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ አንጀታችንን የሚያርስ ጠብ ያለልን ነገር እንዳጣን፣ ይልቁንስ አንደኛውን ቀን ከሁለተኛው ቀን ለማገናኘት የገጠመን የኑሮ ፈተና ጀርባችንን እንዳጐበጠው መናገራችንን ዛሬም ድረስ አልተውነውም፡፡
ህይወታችንን አስቸጋሪና መራራ ያደረገውን የእለት ተዕለት የኑሮ ቀንበር ጉተታ ያልታከተው ሲቀጥል፣ እጁን የሠጠው ደግሞ አይኑንና ልቡን በውጭ ሀገራት ስደት ላይ አድርጐ ቀኑን ይጠባበቃል፡፡ በሀገራቸው የሚኖሩት የጉስቁልና ኑሮ አልገፋ ያላቸው በርካታ ሠዎች፣ ከአመታት በፊት ይናገሩት የነበረውን “ከዚህ ሀገር የሚብስ ሀገር ጨርሶ የለም” የሚል የብሶትና የተስፋ መቁረጥ ንግግር ዛሬ በብሶትና በምሬት ሲናገሩት መስማት የተለመደ ነው፡፡ እናም ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ የቻለው በቦሌ፣ ያልቻለው ደግሞ ነፍሱን ሸጦ በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ባህርን በሰባራ ጀልባ እያቋረጠ ይሠደዳል፡፡
በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሚሠደደውን ለጊዜው ትተን እንዲያው ህግና መንግስት አውቆት ወደ ውጭ ለመውጣት የሚሞክረውን ህዝብ መጠኑን ለማወቅ ከእሁድ በቀር ከእለታት በአንዱ ቀን ካዛንቺስ በሚገኘው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ብቅ ብላችሁ ማየት ብቻ ይበቃል፡፡
ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ውጭ ሄደው ለመስራት የሚያስችላቸውን የጉዞ ፕሮሰስ ለመጨረስ በየእለቱ ረጅም ሠልፎች ሠርተው ሲጋፉ ከሚውሉት በርካቶች ውስጥ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሚያህሉት ሴቶች ሲሆኑ ምናልባት መቶ በመቶ በሚያስብል ሁኔታ ሁሉም መሄድ የሚፈልጉት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራትና የሚቀጠሩበት የስራ መስክም የቤት ሠራተኛነት እንደሆነ ብዙም ሳያቅማሙ ይናገራሉ፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት፣ ከፓኪስታንና ከስሪላንካ የሚመጡ የቤት ሠራተኞችን መቅጠር ስላቆሙ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከኢትዮጵያ የሚሄዱት የቤት ሠራተኞች ተፈላጊነት እንደጨመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከወራት በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ በሳኡዲ አረቢያ የስራ ጉብኝት አድርገው እንደተመለሱ በጉብኝታቸው ስላስገኙት ድል ለመንግስት ጋዜጠኞች ሲገልፁ፤ ሳኡዲ አረቢያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችንና ሾፌሮችን እንደምትፈልግ እንደ ነገሯቸው ጠቅሰው፤ ይህም ለኢትዮጵያውያን ታላቅ የስራ እድል እንደሆነና ለሀገሪቱም ትልቅ ጥቅም ማስገኘት እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡
ኢትዮጵያም ቀስ እያለች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጐቻቸውን በቤት ሠራተኛነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚልኩት ግንባር ቀደም ሀገራት ተርታ ለመሠለፍ ዳዴ እያለች ነው፡፡ አሁን ያለው እውነታ ይህ ነው፡፡ ነገርዬው እንዲህ ከሆነ መንግስት የዜጐችን ስደት ማቆም ይችላል ወይ ብለን ብንጠይቅ፣ የምናገኘው መልስ ቀላልና አጭር ነው፡፡ አይችልም! ስደትን ያህል ከባድ ጉዳይ ለመመኘትና ለመሠደድ እንዲሁም ህይወትን መስዋዕት ለማድረግ ከመቁረጥ የሚታደግ ተስፋን ለመፍጠር መንግስት ብዙ መጓዝ ይቀረዋል፡፡
እንዲህ ከፍ ባለ ቁጥር በቤት ሠራተኛነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚሠደዱት ዜጐች፤ የመሰደድና ከስደት በሁዋላ ባለው ሂደት የሚገጥማቸው ፈተና ዳፋው ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለቤተሠብም ለሀገርም ጭምር ነው፡፡
“ካሠቡት ሀገር በህይወት ይደርሳሉ?” “ለቤተሠባቸው ቀድሞ የሚመጣው የላኩት ዶላር ነው ወይስ አስከሬናቸው?” የተሠደደውንና እዚህ የቀረውን ቤተሠቡን እኩል የሚያስጨንቁ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በሁዋላ የሚከተለው ጥያቄ ዋናና መሠረታዊ ነው፡፡ ስደተኛው ዜጋ በስደት ስራ ላይ እያለ የሚደርስበትን የተለያዩ ችግሮች እንዲቋቋምና በየጊዜው ለቤተሠብ የሚላከውን አስከሬን ለመቀነስ እንዲቻል፣ መንግስትና ሀገርም በውጭ ሀገር በስራ ከተሠማሩ ዜጐች ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችሉ ምን ማድረግ ይገባል? ጥያቄው ይህ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ በየመስኩ የዳበረ ልምድ ካላቸው ሀገራት ምንም እንኳ ክፉ ክፉውን እየመረጠም ቢሆን የመኮረጅ ልምድ ያካበተው መንግስት፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ልምድ ካላት ፊሊፒንስ አሪፍ ልምድ መቅሠም ይችላል፡፡
በመላው አለም ዜጐቿን በቤት ሠራተኛነት በአሜሪካ፣ በካናዳና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በመላክ ፊሊፒንስን የሚፎካከር ሀገር የለም፡፡ የሚርያም ዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት፤ ኢትዮጵያን የረሀብ መፍቻ ምሳሌ አድርጐ በማቅረቡ እኛን እርር ትክን እንደሚያደርገን ሁሉ፣ በ2005 ዓ.ም የታተመው ይሄው መዝገበ ቃላት፤ የፊሊፒንስ ሴት ለሚለው ሀረግ መፍቻ፣ ገረድ ወይም ለስለስ ባለ አነጋገር የቤት ሠራተኛ አድርጐ በማቅረብ መላ ፊሊፒንሳውያንን ቆሽታቸውን ልጦታል፡፡
በፊሊፒንስ በየአመቱ አንድ መቶ ሺ የሚሆኑ ዜጐች በአገልግሎት ኢንዱስትሪው ለመሠማራት ወደ ውጭ ሀገራት ይጓዛሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስ ነበሩ የሀገራቸው ኢኮኖሚ እንዲያንሠራራና እያሻቀበ የመጣው የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ በሚል በ1974 አ.ም ዜጐችን ወደውጭ ለስራ መላክ የጀመሩት፡፡ በዚሁ አመትም 35ሺ ፊሊፒንሳውያን ወደ ውጭ ሀገራት በመሄድ ስራ ማግኘት ቻሉ፡፡
ያኔ ታዲያ ፊሊፒንሳውያንን ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት የመላክ ስትራተጂ እድሜው አጭር ነው ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡
ያኔ ሲጀመር ቶሎ እንደሚደርቅ ትንሽዬ የምንጭ ውሀ ተገምቶ የነበረው ስትራተጂ፤ ከሠላሳ አምስት አመታት በሁዋላ ታላቅ ጐርፍ መሆን ችሏል፡፡
ዛሬ 8.5 ሚሊዮን ፊሊፒንሳውያን በውጭ ሀገራት በአገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪው ውስጥ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ በአብዛኛው ሴቶችን የያዘው ይህ ቁጥር፤ ከፊሊፒንስ ጠቅላላ የህዝብ ብዛት አስር ከመቶ ያህሉን፣ ከጠቅላላው እድሜው ለስራ ከደሠረው ህዝብ ቁጥር ደግሞ 22 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል፡፡
የአለም ባንክ አመታዊ ሪፖርትና በያዝነው አመት የታተመው የ ”Migration and Remittance Fact Book” መረጃ እንደሚያስረዳው፤ ፊሊፒንስ ባለፈው አመት ብቻ በውጭ በስራ ከተሠማሩት ዜጐቿ 21.3 ቢሊዮን ዶላር የሬሚታንስ ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ ይህ ገንዘብ የፊሊፒንስን አመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) አስራ ሁለት በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል፡፡
በውጭ ሀገር በስራ ከተሠማሩ ዜጐቻቸው የሚላክ ከፍተኛ የሬሚታንስ የውጭ ምንዛሪ በማግኘት ከአለም ፊሊፒንስን የሚበልጧት ሶስት ሀገራት፡- ቻይና ህንድና ሜክሲኮ ብቻ ናቸው፡ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ፊሊፒንሳውያን በከፍተኛ ቁጥር ለስራ የተሠማሩባቸው ሀገራት ደግሞ አሜሪካ፣ ካናዳና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ናቸው፡፡
የፊሊፒንስ መንግስት ምንም እንኳ የሀገሪቱ ሴቶች በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ለገረድ ቃል መፍቻ ምሳሌነት መቅረባቸው ቢያናድደውም፣ ወደ ውጭ ሀገራት ለስራ ከሚያሠማራቸው ዜጐቹ የሚያገኘው ጥቅም፣ ከፍተኛና ምትክ የለሽ መሆኑን ጠንቅቆ ተገንዝቦታል፡፡ እናም በውጭ ሀገራት በስራ የተሠማሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐቹ በተሠማሩበት ሀገር ለጉዳትና ለእንግልት የመዳረጋቸውን እድል ለመቀነስና የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማሠብ “Super maid” የተባለ ልዩ የስልጠናና የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ቀርጾ በተግባር ላይ ማዋል ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም አማካኝነትም በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው፣ በውጭ ሀገራት በስራ ለሚሠማሩ ዜጐች በዲፕሎማ ደረጃ የሚሠጥ፣ ተቀጥረው የሚሄዱበትን ሀገር በዋናነት መሠረት ያደረገ የቋንቋ ትምህርት፣ የህዝቦችን የአኗኗር ባህል፣ የምግብና የመጠጥ አሠራርና አቀራረብ፣ ዘመናዊ የቤት ንጽህና አያያዝ ዘዴ፣ የህፃናትና የአረጋውያን አያያዝና እንክብካቤ፣ የስነ ምግባር ትምህርት፣ የመጀመሪያ እርዳታ አሠጣጥና መሠረታዊ የግል ንጽህናና ጤና አጠባበቅ ዘዴ፣ የቀላል ተሽከርካሪዎችና የመኪና ማሽከርከር ትምህርት፣ የቤት ውስጥ ዘመናዊ የምግብ ማብሠያና የንጽህና መስጫ መሳሪያዎች አጠቃቀምና ቀላል ጥገና ስልጠናዎች ይሠጣሉ፡ ብቃታቸውን በሚገባ ለማረጋገጥም የሚሠጠው ፈተናም በጣም ጥብቅና ፈታኝ እንደሆነ ተምረው ያለፉት ፊሊፒንሳውያን ይናገራሉ፡፡ በእነዚህ ተቋማት ገብቶ ለመማር በመቀነታቸው ሁለት መቶ አስራ ሁለት ዶላር መቋጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሙያ ስልጠና ትምህርቱ የሚሠጠው በፊሊፒንስ መንግስት ብቻ ሳይሆን እዚህ እኛ ሀገር ኤጀንሲ እያልን በምንጠራቸው አስቀጣሪ ድርጅቶችም ጭምር ነው፡፡ የለብ ለብ ትምህርት ሠጥተው ዜጐችን ለችግር እንዳይዳርጉብኝ በሚል የፊሊፒንስ መንግስት ከእነዚህ አስቀጣሪ ድርጅቶች ላይ አይኑና ጆሮውን ለአፍታም እንኳ ከድኖ አያውቅም፡፡
የሙያ ስልጠናው በውጭ ሀገራት በቤት ሠራተኛነት ተቀጥረው ለሚሄዱት ፊሊፒንሳውያን ወደር የማይገኝለት አቅምና የተሻሉ አማራጮችን እንዲያፈላልጉ እድል ሠጥቷቸዋል፡፡ የሊዎናራ ሳንቶስ ታሪክ ይህን እውነት በሚገባ ያስረዳናል፡፡
37 አመት ወጣት የሆነችው ሊዎናራ ሳንቶስ፤ በሠሜን ፊሊፒንስ በምትገኘው የሉዞን ከተማ ተወልዳ ያደገች የሶስት ልጆች እናት ነች፡፡ የቴሌግራም መልእክቶችን በልዩ ኮድ በመፃፍና ኮዶችን ፈቶ በመገልበጥ የቴሌኮሙኒኬሽን የመረጃ ሙያ በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡ በዚህ ሙያ በመንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ተቀጥራ ለጥቂት አመታት ብትሠራም የሚከፈላት ክፍያ የሶስቱን ልጆቿን የትምህርት ቤት ክፍያ ሸፍኖ፣ ሁለት ዳቦ በቀን ለመግዛት እንኳ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ምንም እንኳ የባሏ ደመወዝ ከቤታቸው ሌማት ዳቦ እንዳይጠፋ ማድረግ ቢችልም፤ የልጆቿ ትምህርት ነገር ሁሌም እንዳስጨነቃት ነበር፡፡ በፊሊፒንስ የትምህርት ቤት፣ በተለይ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍያ በጣም ውድ ስለሆነ ወላጆችን ከባድ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ያስገድዳቸዋል፡፡ እናም ልጆቿ የጀመሩትን ትምህርት ሳያቋርጡ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡላት የምትመኘው ሊዎናራ፤ ይህን ምኞቷን ለማሳካት ወደ ውጪ ሀገር ሄዳ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥሮ ከመስራት ሌላ አማራጭ እንደሌላት ስታውቅ ጉዳዩን ለባለቤቷ አማከረችው፡፡ “እንዲያው የልጅ ቤት ነው አንዳቸውን እንኳ ቢያማቸው ምኑን ከምን አደርገዋለሁ” በሚል ለክፉ ቀን ቆጥቦና ደብቆ ያስቀመጠውን ገንዘብ አስይዞ ወደ ማሠልጠኛ ተቋም ላካት፡፡
ከማሠልጠኛ ተቋሙ በተለያዩ የቋንቋና የሙያ መስኮች በዲፕሎማ ተመረቀች፡፡ ከዚያ የትምህርት ማስረጃዋን ለተለያዩ አስቀጣሪ ድርጅቶች በማቅረብ፣ የሚያመጡትን የውጭ ሀገር የስራ እድል መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሠባት አስቀጣሪ ድርጅቶች በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተገኙ ሠባት የስራ እድሎችን አቀረቡላት፡፡ አንዱንም መምረጥ አልፈለገችም፡፡ ለምን ቢባል? ሊዎናራ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መሄድ አልፈለገችም፡፡ ከባለቤቷና ከልጆቿ በቀር ጓደኞቿና ዘመድ አዝማዶቿ ያገኘችውን እድል ተጠቅማ እንድትሄድ ቢገፏፏትም በጄ አልል አለች፡፡ የሊዎናራ ሳንቶስ ዋነኛ ፍላጐት ወደ አሜሪካና ካናዳ አሊያም ወደ ሆንግ ኮንግ መሄድ ነበር፡፡ በተገናኙ ቁጥር ለምን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አትሄጂም እያለ ለሚጨቀጭቃት ወንድሟ “እየውልህ ወንድማለም፤ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መሄድ የማልፈልገው ለቤት ሠራተኞች የሚከፈለው ክፍያ በጣም ትንሽ ስለሆነ ነው፤ በዛ ቢባል በወር ከሶስት መቶ ዶላር አይበልጥም፡፡ ለዚህ ብዬ ባሌንና ልጆቼን ጥዬ አልሠደድም፡፡ እዚህ መንግስት በወር ከሚከፍለኝ ጋር ያለው ልዩነት እኮ በጣም ትንሽ ነው፡፡ እኔ መሄድ የምፈልገው ወደ አሜሪካና ካናዳ፤ ይህም ካልሆነ ወደ ሆንግ ኮንግ ነው፡፡ ለምን መሠለህ? በሆንግ ኮንግ በትንሹ በወር 650 ዶላር ማግኘት እችላለሁ፡፡ እንዴ … እዚያ ሄዶ መስራት የሚያስችል ተገቢ ትምህርት ተምሬ ተመርቄአለሁ እኮ! ተፈላጊነቴን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ከሌሎች የተሻለ የስራና የገቢ እድል ለማግኘት እንዲያስችለኝም አረጋውያንንና ህፃናትን የመያዝና የመንከባከብ ልዩ ተጨማሪ ስልጠናን ወስጃለሁ፡፡ ታዲያ ትንሽ ታግሼ ለምን እንዲህ አይነት እድሌንን አልጠብቅም?” በማለት ልታስረዳው ሞክራለች፡፡
ሊዎናራ የሌሎችን ግፊት በመቋቋም፣ በሀሳቧና በውሳኔዋ ፀንታ ለአንድ አመት ያህል ታግሳ ቆየች፡፡ በመጨረሻ ትዕግስቷ ፍሬ አፍርቶ በሆንግ ኮንግ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥሮ ለመስራት እድል አግኝታ፣ ከሀገሯ ፊሊፒንስ በሁለት ሰአት የአየር በረራ ወደምትርቀው ሆንግ ኮንግ አመራች፡፡ በተቀጠረችበት ቤት ካሠበችው በላይ በወር ስምንት መቶ ስልሳ ዶላር የወር ደመወዝ ይከፈላታል፡ የአሠሪዋ ባለቤት ቤታቸዉ ውስጥ እንድታድር እንጂ እንድትመገብ ስለማይፈልግ፣ ለምግቧ በወር ተጨማሪ አንድ መቶ አርባ አራት ዶላር፣ ሁለቱን ህፃናት ልጆች በተለየ ለምትጠብቅበትና ለምትንከባከብበት ደግሞ ሌላ ተጨማሪ አንድ መቶ ስልሳ ስምንት ዶላር ክፍያ ታገኛለች፡፡ ይህ ክፍያ ለሊዎናራ ህልሟን በሚገባ የሚያሟላ ሲሆን አውሮፓዊ ለሆኑት አሠሪዎቿ ደግሞ እንደ ሊዎራና አይነት አገልግሎት ለሚሠጥ ሠው ከሚከፈለው ክፍያ በጣም ያነሠ በመሆኑ ወጪያቸው ርካሽ ነበር፡፡
ሊዎናራ የተማረችው የቋንቋ፣ የሙያና የስነ ምግባር ትምህርት፣ ከአሠሪዎቿ ጋር ላላት ግንኙነት ምን ያህል እንደረዳት ግማሽ ፈረንሳዊና ግማሽ ቤልጅየማዊ የሆነችው የአሠሪዋ የቤትሪስ ምስክርነት በሚገባ ያስረዳናል፡፡ ቤትሪስ ሌኒ እያለች በቁልምጫ ስለምትጠራት የቤት ሠራተኛዋ ሊዎናራ ስትናገር “ሌኒ ታታሪ ሠራተኛ ነች፡፡ መስራት ያለባትን ነገር ጥንቅቅ አድርጋ ታውቃለች፡፡ ይህን ነገር እንዲህ አድርገሽ መስራት አለብሽ ብለህ እንድታዛት ጨርሶ እድል አትሠጥህም፡፡ የልብ አውቃ ናት፡፡
ከህፃናት ልጆች ጋር ያላት መግባባት ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ልጆቹ ከእኔ ከእናታቸዉ ጋር ከሚሆኑ ይልቅ ከእሷ ጋር መሆንን ይመርጣሉ፡ እንዴት አድርጋ እንደምትንከባከባቸውና እንደምታጫውታቸው ሳይ፣ ለካስ ህፃናቶችን ከወላጅ እናታቸው አስበልጠው የሚወዱና የሚንከባከቡ ሞግዚቶች አሉና እያልኩ እገረማለሁ፡ ሌኒ ለልጆች የሚሆን ጨዋታና ተረት እንዴት እንደማያልቅባት ይገርመኛል፡፡ ያጫወተቻቸውን ጨዋታና የነገረቻቸውን አስቂኝ ተረቶች በእንቅልፍ ልባቸው እያሠቡት ሲስቁ ብዙ ጊዜ ሠምቻቸው አውቃለሁ፡፡
የሌኒን ጉዳይ በአንድ አረፍተ ነገር አጠቃለሽ ተናገሪ ከተባልኩ ሌኒን በቤት ሠራተኝነት ብቻ ሳይሆን እንዲሁ እንደ ሰውም ቢሆን ስላገኘናት እጅግ በጣም እድለኞች ነን፡፡” ነበር ያለችው፡፡
ለፊሊፒንስ መንግስት በውጭ በስራ የተሠማሩ ዜጐችን ጉዳይ መከታተል ለነገ የማይባል ጉዳዩ ነው፡፡ እናም በውጭ ሀገራት በተለይም በአሜሪካ፣ በካናዳና በመካከለኛው ምስራቅ ወክሎ ያሠማራቸው አምባሳደሮቹ ዋነኛ ስራቸው በዚያ የሚገኙ ዜጐቻቸውን ጉዳይ ከንጋቱ እስከ ቀጣዩ ንጋት ድረስ በንቃት መከታተልና መደገፍ ነው፡፡
ለፊሊፒንስ የውጭ ሀገር ስራ አስቀጣሪ ድርጅቶችም ቢሆኑ ወደ ውጭ የሚልኳቸውን ሠራተኞች ጉዳይ ቢያንስ የስራ ኮንትራታቸው እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ዋና ነገሬ ብሎ መከታተል ምለው የተገዘቱበት ሀላፊነታቸው ነው፡፡ የስራ ኮንትራት በማስፈረምና ቪዛ በማስመታት ብቻ በሺ የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብሎ ጭጭ ማለት እዚያ የለም፡፡
የፊሊፒንስ ተሞክሮ ከዚህ በላይ ያየነውን ይመስላል፡፡ አሁን ሁለተኛውን አብይ ጥያቄ እናንሳ፡ የሀገራችን ሁኔታስ ምን ይመስላል? የሳምንት ሠው ይበለንና እንዲሁ እንጫወታለን፡፡

 

Read 3623 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:28