Saturday, 28 September 2013 11:25

ስድራ ኢንተርናሸናል-ቡቲክ ሆቴል በ35 ሚሊዮን ብር የተዘጋጁ ልብሶች ኢንዱስትሪ ሊገነባ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ወደ መገናኛ ሲጓዙ ለም ሆቴል አካባቢ መስቀለኛ መንገድ አለ፡፡ ከ22 አካባቢ መጥተው መስቀለኛው ጋ ደርሰው ወደ ቀኝ ሲታጠፉ፣ በአንበሳ አውቶቡስ ዋና መ/ቤት (አንበሳ ጋራዥ) ወደ መብራት ኃይልና ወደ የረር አካባቢ የሚያደርስ መንገድ አለ፡፡ በዚያ አስፋልት፤ ከመስቀለኛው በግምት 400 ሜትር እንደተጓዙ በስተግራ አንድ ባለ 7 ፎቅ ሕንፃ ያገኛሉ-ስድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል፡፡ ሆቴሉ እስካሁን በአገራችን ከለመድናቸው ሆቴሎች ትንሽ ለየት ይላል - ቡቲክ ወይም ቢዝነስ ሆቴል መሆኑ፡፡ “ቡቲክ ሆቴል ደግሞ ምንድነው?” እንደምትሉ እገምታለሁ፡፡ ትንታኔውን ላቆየውና ሌላውን ላስቀድም፡፡ ስድራ አሁን እውን ይሁን እንጂ ሐሳቡ ከተጠነሰሰ 10 ዓመት ሆኖታል ይለናል፤ የስድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወጣት ዮናስ ሀጎስ፡፡

ታዲያ 10 ዓመት ሙሉ ለምን ዘገየ? ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ እነዮናስ ሞባይልና መለዋወጫዎች ለማምጣት ወደ ተለያዩ አገሮች ሲጓዙ የሚያርፉባቸውና የሚያዩዋቸው ሆቴሎች ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉ ናቸው፡፡ እነሱ ሥራ በጀመሩበት 1994 ዓ.ም አዲስ አበባ ያሏት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ጥቂት ነበሩ፡፡ እኛስ በውጭ አገራት የምናያቸው ዓይነት ሆቴሎች ለምን አይኖሩንም? በማለት ቁጭትና መንፈሳዊ ቅናት አደረባቸው፡፡ “ችግሩ ገንዘብ ነው እንጂ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች መገንባት ይቻላል” ብለው አሰቡ። ግን ገንዘብ ስላልነበራቸውም ሃሳባቸውን ወዲያው እውን ሳያደርጉት ቀሩ፡፡ ዮናስ ሀጎስ፣ አዲስ አበባ ነው ተወልዶ ያደገው። የ33 ዓመቱ ወጣት በትምህርት 12ኛ ክፍል አጠናቋል። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ፣ ሥራ ወደ እሱ እስኪመጣ አልጠበቀም-እሱ ወደ ሥራ ሄደ’ንጂ፡፡ መርካቶ አካባቢ “አየር ባየር” መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡

ያኔ ካፒታሉ “እዚህ ግባ” የማይባል ከእጅ ወደ አፍ ነበር፡፡ ቁጥሩን በትክክል አያስታውሰውም፤ ግን ከ15ሺህ ብር እንደማይበልጥ ይናገራል፡፡ የናቲ ሞባይል ባለቤት የእህታቸው ልጅ ነው። አየር ባየር እየሠራ ከቆየ በኋላ፤ ካፒታሉ ትንሽ ከፍ ሲልለት፤ እሱና ወንድሞቹ፣ የቤተሰብ ቢዝነስ በሆነው ናቲ ሞባይል መሥራት ጀመሩ፡፡ እዚያ እየሠሩ ከቆዩ በኋላ ሰው (ገበያው) የሚፈልገውን በደንብ አጠኑ፤ አወቁ፡፡ ይኼን ጊዜ ወደ ውጭ አገራት እየሄዱ ሞባይልና መለዋወጫዎችን እያመጡ መነገድ ጀመሩ፡፡ በዚህ ዓይነት እየሠሩ ከቆዩ በኋላ ገንዘቡ ትንሽ ጠርቀም ማለት ሲጀምር፣ ከ10 ዓመት በፊት ወደ ውጭ አገራት ሲመላለስ የተፈጠረበትን ስሜት አስታወሰ፡፡ ከዚያም ወደ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በመግባት ቁጭቱን ለመወጣት ወሰነና በ2000 ዓ.ም የስድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል ግንባታ ተጀመረ፡፡ ስድራ ማለት ምን እንደሆነ የማታውቁ አንባብያን “የምን ቃል ነው? ምን ማለት ነው? …” ብላችሁ ሳትመራመሩ እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ፡፡ ስድራ፤ የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛ፣ የአረብኛ፣ የቻይንኛ፣ … ቃል አይደለም፡፡ የአገራችን ቋንቋ ከሆነው ከአንዱ የተወሰደ ነው፡፡ ስድራ፣ በትግርኛ ቋንቋ ቤተሰብ ማለት እንደሆነ ዮናስ አጫውቶኛል፡፡

ስድራ ኢንተርናሽናል ከግለሰብ በተገዛ 400 ካ.ሜ ቦታ የተሠራ ሆቴል ነው፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ወደ ውጭ መውጫና ለመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አግኝቷል፡፡ ሆቴሉ 41 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው 26 ክፍሎች አሉት፡፡ አንድ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል የሚያሟላቸውን ነገሮች ይዟል፡፡ ሆቴሉ ዴሉክስ፣ ደብልና ሱት ክፍሎች አሉት፡፡ ሁሉም ክፍሎች ቁምሳጥን፣ ቲቪ፣ ስልክ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ሚኒባር፣ ካዝና፣ ጭስ መጠቆሚያ፣ በረንዳ (ባልኮኒ)፣ … አላቸው፡፡ ሱት የተባለው ክፍል ለየት ያለ አልጋ፣ ሳውና ባዝ፣ … አለው፡፡ ይህ ክፍል ከመኝታው ቤቱ ሌላ ሚዜዎችን መያዝ የሚችል ሰፊ ሳሎን ስላለው፣ በተለይ ለሙሽሮች ምቹ ነው ይላል ዮናስ፡፡ በእያንዳንዱ ክፍል መታጠቢያ ቤት በሆቴሉ ስም የተሠራ ሳሙና፣ የጥርስ ቡሩሽ፣ ሎሽን፣ (ቅባት) የሴቶች ፀጉር ማድረቂያ፤ በቁምሳጥኑ ውስጥ ደግሞ ስድራ በሚል የተዘጋጀ ልብስ መስቀያ፣ … አለ። ከዚህም በተጨማሪ፣ ሆቴሉ በአንድ ጊዜ ስድስት ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ስቲም ባዝና ጃኩዚ፣ ከ35-40 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ፣ በግል፣ በቡድንና በቤተሰብ መጥተው የሚታሹበት ማሳጅ ክፍልና ማረፊያ፣ የሴቶች የውበት ሳሎን፣ ሁለት ባርና ሬስቶራንት፣ የእንግዶች ስፖርት መስሪያ ጂምናዚየም፣ … አለው፡፡ መጨረሻ ፎቅ ያለው ቴራስ ባር ሰፊ ሲሆን ማታ ነው የሚከፈተው፡፡ የምሽቱን አየር እየሳቡና ዙሪያ ገባውን እያዩ የሚዝናኑበት ነው። ቴራስ ባሩን ሲጐበኙ ከነበሩ ሰዎች አንዱ “ይኼ ባር፣ ሙሽሮችን ከነሚዜውና አጃቢው ማዝናናት ይችላል” ሲል ሌላኛው ቀበል አድርጐ፣ “26ቱንም ክፍሎች ተከራይቶ ሲጨፍሩ ማደር ነው እንጂ” አለ፡፡

ስድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል ቡቲክ ወይም ቢዝነስ ሆቴል ነው፡፡ ቡቲክ ወይም ቢዝነስ ሆቴል ምንድነው? ላላችሁ አንባብያን ባለቤቱ ዮናስ ሲገልጽ፤ ሆቴሉ ትልቅ ያለመሆኑን ጠቅሶ፣ “ቡቲክ ወይም ቢዝነስ ሆቴል፣ በትንሽ ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ፣ የተለያየ አማራጭ ያለው ሆቴል ማለት ነው” ሲል አስረድቷል፡፡ ሆቴሉ በዚህ አያበቃም-የማስፋፊያ ሥራም አለው፡፡ በማስፋፊያው፤ መዋኛ ገንዳ፣ ዘመናዊ አዳራሽ፣ ተጨማሪ ክፍሎች፣ … ለመገንባት ከጐን ያለውን ቦታ ጠይቋል፡፡ ዮናስ፣ ቀደም ሲል፣ ቀበሌውም ሆነ መስተዳደሩ ጥሩ ድጋፍ እንዳዳረጉለትና ለጥያቄዎቹ ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው አመስግኖ፤ አሁንም መልካም ምላሽ ይሰጡኛል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡ የስድራ ሆቴል ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ የስኬቱ ምክንያት ደስተኛ ሆኖ ጠንክሮ መሥራትና ችግሮችን በብልሃት መወጣት እንደሆነ ይናገራል። “ቀደም ሲል አራትና አምስት ሆነን ነበር የምንሠራው። አሁን በሆቴላችን ለ85 ሰዎች በሌላው ንግዳችን ደግም ለ18 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፡፡ ከምንም በላይ ትልቁ ስኬት ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡

በዚያም ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡ ዮናስ ከዚህ ስኬት የደረሰው ያሰበው ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆኖለት አይደለም፡፡ በኮንስትራክሸን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ለማግኘት ችግር ነበረበት። በዚህ ምክንያት ነው ግንባታው አራት ዓመት የፈጀው፡፡ ሌላው ደግሞ የገንዘብ ችግር ነው፡፡ የባንክ ብድር ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ነበረበት፡፡ እሱ ብድር በጠየቀበት ጊዜ ብድር መስጠት ቆሞ ነበር፡፡ የባንክ ብድሩን ያገኘው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የሆቴሉ ግንባታ ማለቅ ከነበረበት ጊዜ በአንድ ዓመት ዘግይቷል፡፡ ሆቴሉ የዛሬውን መልክ የያዘው በእሱ ዲዛይን መሆኑን ይናገራል፡፡ ዮናስ በትምህርት ደረጃ፣ የምህንድናስ ወይም የአርክቴክትነት ሙያ የለውም። የሆቴሉን አርክቴክት ሌላ ባለሙያ ቢሆንም የውስጡን ዲዛይን ቅርፅ ያስያዘውና ያሳመረው ራሱ መሆኑን ይናገራል፡፡

ይህን ማድረግ የቻለው ውጭ አገራት ሲመላለስ ከሚያያቸው ማስዋቢያዎች ጥሩና የሚያምሩትን በመውሰድ እንደሆነ ገልጿል። የሆቴሉን ቀለም የመረጠው፣ ጥራት ያላቸውን ዕቃዎች መርጦ ከቻይና የገዛው፣ … ራሱ ነው። “ምርጫዬን ሰዎችም ስለወደዱልኝ በጣም ደስ ብሎኛል፤ አመሰግናለሁ፡፡ ከውጭ አገር የመጡ እንግዶች ሁሉ ሲያዩት ከሚገምቱት በላይ ነው የሚሆንባቸው፡፡ በዚህም በጣም ደስተኛ ናቸው” ብሏል፡፡ በሆቴሉ የሚያርፉ እንግዶች፣ ሌሎች ሆቴሎች ከሚበዙበት ስፍራ ወጣ ማለቱንም አልጠሉትም። “ከተማ መሃል ሲሆን ጫጫታና የመኪና ድምፅ ይኖራል፡፡ በዚህ የሚረበሹ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የእኛ ፀጥ ማለቱ፤ ጥሩ መስተንግዶ መስጠታችን… ለብቻ መሆንና ረዥም ጊዜ መቆየት የሚፈልጉ፣ … ይመርጡናል፡፡ ስለዚህ የገበያ እጦት ስጋት አይኖርብንም” በማለት አስረድቷል፡፡ ዮናስ በሆቴል ሥራ ላይ ብቻ አልተወሰነም፡፡ የጋርመንት (የተዘጋጁ ልብሶች) ምርት ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ቃሊቲ አካባቢ ቦታ ወስዶ በ2007 ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በ35 ሚሊዮን ብር የሚቋቋመው ፋብሪካው፤ ከ270 ለሚበልጡ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለው፡፡ ቀጣዩ ፕሮጀክት ይህ ሲሆን ሌላውም እንደሁኔታው ይቀጥላል ብሏል፡፡

Read 4347 times