Saturday, 28 September 2013 11:10

በአንድ ሃይማኖት እያመኑ፣ “የሰይጣን መልእክተኛ!” እያሉ ይሰዳደባሉ

Written by 
Rate this item
(25 votes)

ደቂቀ ኤልያስ፣ ማህበረ ቅዱሳን፣ ተሀድሶ … እርስበርስ ይናከሳሉ

ወሃቢያ፣ ሰለፊያ፣ አህበሽ … አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ይናጫሉ

የአዲሱን አመት አዝማሚያ ታዝበን እንደሆነ፣ እንደአምናው ዘንድሮም “ከሃይማኖት ጣጣዎች” በቀላሉ እንደማንላቀቅ ያስታውቃል። ግን ብዙም አሳሳቢ የሆነብን አይመስልም። ከአወሊያ ትምህርት ቤት እና ከእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምርጫ ጋር ተያይዞ ባለፉት ሁለት አመታት እየተባባሰ የመጣው ችግር ስጋት ቢፈጥርብንም፣ የአደጋው መጠንና ስፋት ያን ያህልም በግልፅ አልታየንም። ወይም ለማየት አልፈለግንም። ለምሳሌ፣ “ነብይ ኤልያስ ዓለምን ሊፋረድ በእሳት ሰረገላ መጥቷል” በማለት እነ ጀማነሽ ሰለሞን በሚያካሂዱት ስብከት ላይ የተፈጠረው ውዝግብ ብዙም አላስጨነቀንም። “መስቀል ከሰማይ ወረደ” ተብሎ በተጀመረው እንቅስቃሴ ዙሪያ የተከሰተው እንካሰላንቲያ ያን ያህልም አያሳስበንም። ነገር ግን፣ በጊዜ ካላሰብንባቸውና መፍትሄ ካላበጀንላቸው፣ ክፉ መዘዝ ማስከተላቸው አይቀርም።

የዛሬ ፅሁፌም፣ “ደቂቀ ኤልያስ፣ ማህበረ ቅዱሳን፣ ተሀድሶ…” በሚሉ ጎራዎች እየተለኮሱ የሚቀጣጠሉ የሃይማኖት ጣጣዎች ላይ ያተኮረ ነው። የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ተከታይ መሆናቸውን በሚገልፁት በእነዚህ ጎራዎች መካከል የተጧጧፈው የውግዘትና የውንጀላ ውርጅብኝ ይዘገንናል። በከፊል እየቀነጨብኩ አቀርብላችኋለሁ። የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ መሆናቸውን የሚናገሩ ሰዎችም ውስጥ፣ ወሃቢያ፣ ሰለፊያ፣ አህበሽ… በሚሉ ጎራዎች ተቧደነው፣ አንዱ በሌላው ላይ የሚያዘንቡት የውግዘትና የውንጀላ ዶፍ ያሰቅቃል። ትችቶቻቸው እንደ እሬት የመረሩ፣ ክርክሮቻቸውም እንደ እሳት የሚጋረፉ መሆናቸው አይደለም የሚያስፈራው። በሰዎች መካከል የሚደረግ የሃሳብ ክርክርትና ትችት ከልኩ አያልፍም። “ካልደረሰብህ ጫፉን አትንካ” የሚባል የመብትና የነፃነት ድንበር ይበጅለታላ። የሃይማኖት ተከራካሪዎች ግን፣ የሃሳብ አለመግባባትን የፍፃሜ ጦርነት ያስመስሉታል። ለዚያውም ጦርነቱ “ተራ የሰዎች ግጭት” አይደለም። ፈጣሪና ሰይጣን የሚፋለሙበት ጦርነት ነው! ተሸፋፍኖ የቆየውና አስፈሪው የሃይማኖት ጣጣም፣ በዚህ ምናባዊ የፈጣሪና የሰይጣን ጦርነት አማካኝነት በግልፅ መታየት ይጀምራል። እንዴት ቢባል፤ …በጦርነቱ መሃል፣ የሰው ልጅ ከእንሰሳትና ከእፀዋት የተሻለ ክብር አይሰጠውም።

በቃ፣ እንደ አህያ ጭነው የሚነዱት የጋማ ከብት፣ እንደ ቀርከሃ መልእክት የሚያስተላልፉበት ቱቦ ሆኖ ያርፈዋል። የሰው አእምሮ ጥልቅና ረቂቅ እውነቶችን የማወቅ አቅሙ ኢምንት ነው ተብሎ ሲሰበክ አልሰማችሁም? የጊዜያዊ ስሜትና የብልጭልጭ ነገሮች እስረኛ ስለሆነ ለራሱ የሚበጀውንና የሚጠቅመውን ነገር አጥርቶ መለየት አይችልም፤ ያለ እረኛ ተስፋ የለውም ተብሎ ሲሰበክስ አላደመጣችሁም? “ሰውማ ምን አቅም አለው? ደካማና ከንቱ ፍጡር!” የሚል ፅሁፍስ አላነበባችሁም? ብዙውን ጊዜ በሃይማኖት ስብከት ውስጥ፣ የሰውን ልጅ የሚገልፁት እንደ ምርኮኛ ወይም እንደ ባሪያ አድርገው ነው። ሁሉንም አለመግባባትና ውዝግብ፣ “የፈጣሪና የሰይጣን ጦርነት” ሆኖ የሚታያቸውም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። አንደኛ ነገር፤ የሰው ልጅ፣ በአእምሮው አገናዝቦ እውነትንና ሃሰትን የማወቅ አቅም የሌለው ቀልበ ቢስ ፍጡር ከሆነ፣ የፈጣሪን ወይም የሰይጣንን ቃል በጭፍን ተቀብሎ ከማመን ውጭ ምንም ማድረግ አይችልም።

ሁለተኛ፤ የሰው ልጅ፣ በአእምሮው አመዛዝኖ ጥሩና መጥፎውን ለይቶ የመምረጥና የመወሰን አቅም የሌለው ዱካ ቢስ ፍጡር ከሆነም፣ የፈጣሪ ወይም የሰይጣንን መመሪያዎች በታዛዥነት ከመከተል ውጭ አማራጭ አይኖረውም። ሦስተኛ ነገር፤ ሰው ሲባል በጥቅሉ፣ እውነትን አገናዝቦ በማወቅና መልካምነትን አመዛዝኖ በመምረጥ ስኬታማ ሕይወትን የመቀዳጀት አቅም የሌለው፣ ጎደሎና መናኛ፣ ደካማና ክብረ ቢስ ፍጡር ከሆነ፣ እጣፈንታው ምን ሊሆን ይችላል? የሰይጣንን ቃል ተቀብሎ በተላላኪነት የሚያገለግል ምርኮኛ ወይም የፈጣሪን ቃል ተቀብሎ በታዛዥነት የሚያገለግል ባሪያ! አሃ፤ ከአህያና ከቀርከሃ የተሻለ ክብር ለሌለው ፍጡር፣ መብትና ነፃነት ማክበር የሚባል ነገር ሊነሳ አይችልማ። “የሰይጣን መብትና ነፃነት” ብሎ ነገር ይኖራል እንዴ? “ሰይጣን ለሚጋልበው አህያስ”፣ መብትና ነፃነቱን እናከብርለታለን? አያችሁ! የሃይማኖት ክርክር ድንበር የለሽ ነው። ልክ ሊበጅለት አይችልም። አንደኛው ጎራ ሌላኛውን፣ “የሰይጣን መሳሪያ!” እያለ ሲያወግዝ በጣም ሊያሳስበን የሚገባውም በዚህ ምክንያት ነው። “አንተ የዲያብሎስ መልእክተኛ! አንቺ የአውሬው ቅጥረኛ!” እየተባባሉ መወነጃጀል ሲበራከት፣ መስጋት አለብን። ውዝግባቸውን በጣም አለዘብኩት መሰለኝ።

ቃል በቃል ክርክራቸውንና ንግግራቸውን ባቀርብ ይሻላል። በሌላ ጊዜ፣ “ወሃቢያ፣ ሰለፊያ፣ አህበሽ…” በሚል የሚወራወሩትን ውንጀላና ውግዘትን ለማሳየት መሞከሬ ባይቀርም፣ ለዛሬ ግን ከላይ እንደጠቀስኩት “ደቂቀ ኤልያስ፣ ማህበረ ቅዱሳን፣ ተሃድሶ…” በሚለው ዙሪያ ላይ ነው የማተኩረው። ነብይ ኤልያስ አለምን ሊፋረድ በእሳት ሰረገላ መጥቷል በማለት የሚሰብኩት እነ ጀማነሽ ሰለሞን፣ “ማህበረ ሥላሴ ደቂቀ ኤልያስ” በማለት ራሳቸውን ሰይመው ያሰራጩትን ፅሁፍ በመጥቀስ ልጀምር። “እነሆ ለዘመናት የተጠበቀው ትንቢት ተፈጽሞላት፣ ኢትዮጵያ ዓለምን በተዋህዶ የምትገዛበት ሰአት ላይ ቆመን ይህንን ታላቅ አስፈሪ የቅዱስ ኤልያስ ምስጢር ስናውጅላችሁ በታላቅ ደስታና ሐሴት ነው። … ዓለማችንን እየገዛ ካለው አውሬ ይታደገን ዘንድ ቅዱስ ኤልያስን የላከልን… የኢትዮጵያ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። … ይህ ጹሑፍ ለአመጸኞች የሚያቃጥላቸው… እንደመብረቅ የሚያስደነግጣቸው ሊቋቋሙት የማይቻላቸው እሳት ነው” ጽሑፉ ከፈጣሪ እንጂ ከሰዎች የመነጨ እንዳልሆነ በመግለጽ አንባቢዎችን ሲያስጠነቅቅም፣ “…ከልዑል መለኮታዊ መንበር የታዘዘና የተላለፈ ኃይለ ቃል ነው። ስለዚህ ማንም ቢሆን በትህትና… የቅዱስ ኤልያስን መርህ መከተል ይገባዋል” ይላል።

ለምን? ፅሁፉ ምላሽ ይኖረዋል። ቅዱስ ኤልያስ ሁሉንም ነገር ሊያፀዳ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ይዞና ሌሎችንም አሰልፎ ነው በእሳት ሰረገላ የመጣው። የሆነ ሆኖ፣ “ማኅበረ ሥላሴ ዘደቂቀ ኤልያስ” ጳጉሜ 1 ቀን ያሰራጨው ጽሑፍ በዚህ ማስጠንቀቂያ ወደ ዋና ፍሬ ነገሮች ይቀጥላል። በቤተክርስትያኗ ስም ላይ፣ “ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል በሰይጣን ተንኮል የተጨመረ ስለሆነ መወገድ እንዳለበት የሚገልፀው ይሄው ፅሁፍ፣ የሰንበት በዓል መከበር ያለበት በቅዳሜ እለት እንጂ በእሁድ መሆን እንደሌለበት ያሳስባል። የሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ማህበረ ቅዱሳን የተሰኙት ተቋማትም የሰይጣን ስራዎች ስለሆኑ መፍረስ እንዳለባቸው ፅሁፉ ያስጠነቅቃል። ቤተክርስትያኗ በአለም አብያተ ክርስትያናት ማህበር ውስጥ በመግባት በሰይጣንና በአውሬው ሴራ ውስጥ ተካፋይ ሆናለች በማለት እያወገዘም፣ ከማህበሩ እንድትወጣ ያሳስባል። እንግዲህ አስቡት። ነብይ ኤልያስ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ይዞ በእሳት ሰረገላ እንደመጣ “ደቂቀ ኤልያስ” ነግረውናል። እውነት መሆኑን አምነን እንድንቀበልም ይጠብቃሉ።

ለምን? የሰው አእምሮ በራሱ አቅም እውነትን የማወቅ አቅም የለውም። ስለዚህ የፈጣሪን ቃል ተቀብሎ ማመን የግድ ነው። “ከፈጣሪ የመነጨ ቃል” ሲባል፣ በሌላ አነጋገር ከእነ ጀማነሽ የሰማነውና ያነበብነው ቃል ማለት ነው። የነሱን ቃል አምነን ካልተቀበልን፣ የሰይጣንን ቃል የምንከተል ርጉማን እንሆናለን። “እሁድን ሳይሆን ቅዳሜን አክብሩ፣ ያኛው ማህበር ይበተን፣ ከዚያኛው ውጡ…” የሚሉ መመሪያዎችን ሲያቀርቡም፣ “ለምን አላማና በምን መነሻ? ጥቅሙና ጉዳቱስ? በምን መመዘኛ?” ብሎ መመራመርና መፈተሽ አይኖርብንም፤ በሰው አቅም አይቻልማ። ከአቅመ ቢሱ የሰው ልጅ ሳይሆን ከፈጣሪ የመነጨ መመሪያ ስለሆነ በታዛዥነትና በትህትና መከተል ይገባል ብለዋል ደቂቀ ኤልያስ። በሌላ አነጋገር፣ በደቂቀ ኤልያስ የተሰራጨውንና ያነበብነውን መመሪያ በታዛዥነት መከተል ይጠበቅብናል ማለት ነው። እነሱ የነገሩንን በእምነት ለመቀበል እና መመሪያቸውንም በታዛዥነት ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆነ ሰውስ? በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ተብሎ በፅሁፉ ውስጥ የተጠቀሰው ነገር፣ ለእንዲህ አይነቱ “የሰይጣን አገልጋይ አመፀኛ ሰው” መፍትሄ ይሆናል በሚል ሃሳብ ይመስላል። በጭካኔ ጭፍጨፋ ፈፅማለች ተብላ የምትጠቀሰው “ዮዲት ጉዲት”፣ ቤተ መቅደስ ላይ ተሹመው ይሳለቁ የነበሩትን ካህናት ከመጻህፍቶቻቸው ጋር ቤተ መቅደሳቸውን ያፈራረሰችና ያጠፋች ቅደስት ሴት ናት በማለት ያደንቋታል - ደቂቀ ኤልያስ። እንዲህ አይነቱ ውዳሴ አስገራሚ ሊሆንባችሁ ይቻላል። ነገር ግን፣ “የምንነግራችሁን ነገር በጭፍን አምናችሁ ተቀበሉ።

የምሰጣችሁን መመሪያ በታዛዥነት ተከትላችሁ ፈፅሙ” ብሎ የሚጀምር ስብከት፣ ዞሮ ዞሮ አፈናን፣ ጭካኔንና እልቂትን ወደ ማወደስ ማምራቱ አይቀሬ ነው። በዚህ ካልተስማማችሁ፣ ይህን ጥያቄ መልሱልኝ። ዮዲት፣ ከሃይማኖት ወጥተዋል ወይም አፈንግጠዋል ያለቻቸውን ሰዎች ከነንብረታቸው ካጠፋቻቸው፣ እንዴት ቅድስት ተብላ ትወደሳለች? ድርጊቷ እንደ ወንጀል ሳይሆን እንደፅድቅ ተቆጥሮ በአድናቆት ሲሞገስ ምን ትላላችሁ? ነውጠኛነት ነው። ደቂቀ ኤልያስ ባሰራጩት ነውጠኛ ፅሁፍ ላይ ከየአቅጣጫው በርካታ ትችቶችና ወቀሳዎች፣ ከዚያም አልፎ ውግዘቶችና ውንጀላዎች መሰንዘራቸው ላይገርም ይችላል። አሳዛኙ ነገር፣ አብዛኛው ትችትና ውግዘት የተሰነዘረው “በፅሁፉ ነውጠኛነት” ላይ አይደልም። መምህር ምህረተአብ አሰፋ፣ ደቂቀ ኤልያስን ባወገዙበት ስብከታቸው፣ ነብይ ኤልያስን እንዲህ ሲሉ በአድናቆት ገልፀውታል - “በቂሶም ወንዝ 450 የባዕድ ነቢያትን ያሳረደ፣ ስለ እግዚአብሄር ክብር የቆመ ነብዩ ኤልያስ!”።

እንግዲህ በተሳሳተ መንገድ ይሰብካሉ የሚባሉትን ሰዎች ማስገደል ለሙገሳ የሚያበቃ ከሆነ፣ ከሃይማኖት አፈንግጠዋል ያለቻቸውን ካህናት በመግደሏና ንብረታቸውን በማውደሟ፣ “ቅድስት ዮዲት” ብትባል ምን ይገርማል? ለማንኛውም፣ በ“ደቂቀ ኤልያስ” ከተሰራጨው ነውጠኛ ፅሑፍ ጥቂት ልጨምርና፣ መምህር ምህረተአብ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዲሁም በማህበረ ቅዱሳን መፅሄት ወደ ታተሙ ምላሾች ልሻገር። “ኦርቶዶክስ” የሚለው ስያሜ ከሰይጣን ተንኮል የመጣ ነው በማለት የውግዘት ውርጅብኝ የሚያዘንበው የደቂቀ ኤልያስ ፅሑፍ፤ “…በግሪክ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ውስጥ፣ ‘ቀጥተኛ ሃይማኖት’ የሚል ፍቺ ቢሰጠውም፣ በዓለም ሕብረተሰብእ ዘንድ ግን ‘አክራሪ፣ አውቃለሁ ባይ፣ ጊዜው ያለፈበት፣ የቆየ’ … የሚል አሉታዊ ትርጉም ያለው ቃል ነው” ይላል። “…ኦርቶዶክስ የሚለው ስያሜ ለቤተ ክርስቲያናችን መቼ፣ እንዴት፣ በእነማን፣ ለምን አላማ ሊሰጣት ቻለ የሚሉትን መጠይቆች ስንመረምር… በቤተክርስቲያን ላይ ሰይጣን የቀመመው መርዛማ ተንኮል፣ አውሬው ያቀናበረው ስውር ደባ መኖሩን እናስተውላለን። …የሮም መናፍቃን ለራሳቸው ‘ካቶሊክ’ (ማለትም አንዲት፣ ሐዋርያዊት፣ ዓለምአቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን) የሚል ስያሜ ወስደው፣ ከእነሱ የተለዩትን ምስራቅ አውሮፓውያንን ለመንቀፍ የተጠቀሙበት ስያሜ መሆኑን እናስተውላለን።

…ኦርቶዶክስ የመናፍቃን ስያሜ ነው። እመቤታችንን የሰው እንጂ የአምላክ እናት አይደለችም በሚለው የንስጥሮስ… መንገድ፣ ክርስቶስ ሁለት ባህርይ ነው ብለው ክደው፣ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን ያሳደዱ የምስራቅ አውሮፓ፣ የግሪክ፣ የሩስያ… መናፍቃን ስያሜ ነው። ታዲያ… እኛ [ላይ እንዴት] ኦርቶዶክስ የሚል ስያሜ ሊለጠፍብን ቻለ ቢሉ፣ ጠላታችን ዲያብሎስ በአውሬው ላይ አድሮ የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ የተጠቀመው ረቂቅ ተንኮል መሆኑን እናስተውላለን። …አውሬው፣ እረኞችን ከተኩላ፣ ስንዴን ከእንክርዳድ ለመቀላቀልና ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ለማጥመድ ባዋቀረው ተንኮል፣ ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክስ በሚል ስያሜ ስትጠራ ኖራለች” በደቂቀ ኤልያስ የተሰራጨው ፅሑፍ፣ አብዛኛውን ነገር የሚያወግዘው፣ “የሰይጣን መርዝ፣ የዲያብሎስ ተንኮል፣ የአውሬው ሴራ”… የሚሉ ውንጀላዎችን በማዥጎድጎድ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማህበር የተቋቋሙት፣ በሰይጣንና በአውሬው ተንኮል ነው በማለት ይኮንናቸዋል። “ቤተክርስቲያን፣ ከልዑል እግዚአብሔር ያገኘችውን፣ ከነቢያን ከሐዋርያት የተረከበችውን ንጹህ ቃለ እግዚአብሔር በጥንቃቄ አዘጋጅታ ልጆችዋን መመገብ ሲገባት፣ መርዛማ ጥርጥር ከሚነዙ መናፍቃን ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለመጻፍ ማኅበር መግባትዋ፣ ለብዙዎች ማሰናከያ ወጥመድ ሆኑዋል።

… መናፍቃንን ገስጸ የሰው ልጆችን ሁሉ ወደ ተዋህዶ እቅፍ እንዲገቡ ማድረግ ሲገባት፣ በገንዘብ ፍቅር ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት ከመናፍቃን ጋር መመስረቷ፣ ለብዙዎች መውደቅና በአውሬው መማረክ ምክንያት ሆኗል” አለምን የሚገዛ አውሬ፣ የዓለም መንግስታትንና የቤተክርስቲያን መሪዎችን ለመቆጣጠር “የረቀቁ ተንኮላዊ ስልቶችን” እንደሚጠቀም የሚያትተው የደቂቀ ኤልያስ ፅሁፍ፣ ማህበረ ቅዱሳን እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች በሰይጣን ተንኮል ለአውሬው ስውር አላማ የተቋቋሙ ናቸው ሲል ያወግዛል። እግዚአብሄር ስድስት ቀናትን ሠርቶ ያረፈባት ሰባተኛዋ ቀን ቅዳሜ ሰንበት ተብላ እንድትከበር እንዳዘዘ ጽሑፉ ጠቅሶ፣ በቅዳሜ ፋንታ እሁድ (የፀሐይ ቀን) ሰንበት ተብሎ እንዲከበር የተደረገው የፀሐይ አምልኮን በመከተል ነው ይላል። ደቂቀ ኤልያስ ያሰራጩት ፅሁፍ እንደሚተርከው ከሆነ፣ ሰይጣን ያልሰራው ነገር የለም። ቅዱስ ኤልያስም ሁሉንም ነገር ሊያፀዳ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ይዞ ሌሎችንም አሰልፎ መጥቷል ይላል። የሰይጣን መልእክተኞች፣ የዲያብሎስ ታዛዥ፣ የአውሬው አገልጋይ በማለት ያወገዟቸውን ነገሮች ለማጥፋት መሆኑ ነው። እንግዲህ፣ ከዚህ በኋላ የሚቀረን፣ ደቂቀ ኤልያስ ላይ የተሰነዘረውን ትችት ማቅረብ ነው። ትችት ብቻ ሳይሆን ውግዘትና ውንጀላ ጭምር ነው የዘነበባቸው - ደቂቀ ኤልያስም በተራቸው “የሰይጣንን ቃል የሚሰሙ፣ በሰይጣን ቅናት የሚመሩ፣ ሰይጣናዊ ስውር አላማ የያዙ፤ ቤተክርስትያንን ለማጥፋት የሚያሴሩ ጠላቶች” ተብለው ተኮንነዋል። ለሳምንት እናቆየው።

Read 8698 times