Saturday, 28 September 2013 11:04

“ፕሬዚዳንት ግርማ፤ የታክሲ ሹፌሮችን የተቆለለ ዕዳ አሰርዘዋል”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ፕሬዚዳንቱ አልሰሩም የሚባለውን ይቃወማሉ

                               ባለፈው ሳምንት እትማችን ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በስልጣን ዘመናቸው ምን ስኬቶችና ውድቀቶች ነበሯቸው በሚል የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ ምሁራንና የፕሬዚዳንቱን አማካሪ አነጋግረን ሰፋ ያሉ አስተያየቶችን ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ አስተያየቱን ያነበቡትና ለ20 ዓመታት በታክሲ ሹፌርነት የሰሩት አቶ ወርቁ አማረ፤ ፕሬዚዳንቱ በስልጣን ዘመናቸው የሰው ችግር ለመፍታት የተጉ ስለመሆናቸው የአይን ምስክር ነኝ በማለት ለጋዜጣችን ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡ የቀድሞው የታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር መስራችና ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ወርቁ፤ ማህበሩን ለስምንት ዓመታት መርተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከታክሲ ሹፌርነት ወጥተው በመስክ መኪና ሹፌርነት እየሰሩ ሲሆን የማህበሩ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ፕሬዚዳንት ግርማ፤ የታክሲ ሹፌሮችን የ154 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዴት እንዳሰረዙላቸው ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአቶ ወርቁ አማረ ጋር በፕሬዚዳንት ግርማና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ያደረገችው ቃለምልልስ እንዲህ ቀርቧል:-

አቶ ወርቁ አማረ፤ የቀድሞ ታክሲ ሹፌሮች ማህበር ፕሬዚዳንት

እስቲ ስለ ፕሬዚዳንት ግርማ መናገር የፈለጉትን ነገር ይነገሩን… የዛሬ ሳምንት በወጣው ጋዜጣችሁ ላይ ፕሬዚዳንቱ ስኬታማ ናቸው አይደሉም በሚል ርዕስ የተለያዩ አካላትን አነጋግራችሁ ያወጣችሁት ዘገባ ነው አስተያየት እንድሰጥ የገፋፋኝ፡፡ እኔ የታክሲ ሹፌሮችን ወክዬ በምሰራበት ጊዜ የሰሩት ሥራ የማደንቀው ስለሆነ እሱን መግለጽ እፈልጋለሁ። ባለፈው ሳምንት አማካሪያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶ የሰጡትን አስተያየትም አደንቃለሁ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ምን ነበር የሰሩት? እንደነገርኩሽ ቤተ-መንግስት የገባሁት የህዝብን ጉዳይ ይዤ ነበር፡፡ በወቅቱ ታክሲ ሹፌሮች ላይ አንድ ደንብ ወጥቶ እዳ ተቆልሎባቸው ነበር፡፡ ዕዳው ወደ 154 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ታክሲ ሹፌሩ በባለንብረቶች ከሚደረግበት ጫና በተጨማሪ ደንቡ ጫና ፈጥሮበት ነበር፡፡ በ1990 ዓ.ም የወጣው ደንብ፣ መንጃ ፈቃድ እስከማስቀማት ይደርስ ነበር። አንድ ሹፌር ጥፋት ሲያጠፋ የመጀመሪያው መጥሪያ መቶ ብር ከሆነ፣ ሁለተኛው 150 ይሆናል፣ ከዚያ 250፣ 300 እያለ… እስከነወለዱ እየጨመረ፣ ሹፌሮች መክፈል እስከማይደርሱበት ደረጃ ደረሰ። ብዙዎቹ ታክሲ ሹፌሮች መንጃ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ከጫወታው ውጭ ከሆኑ በኋላ፣ የሙያው ባለቤት ያልሆኑት በዘልማድ እየገቡና እያሽከረከሩ፣ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ብዙ አደጋ ይደርስ ጀመር፡፡ ባለሙያና ባለሙያ ያልሆነውን መለየትም የሚያዳግትበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በቀጥታ ወደ ፕሬዚዳንቱ ነው የሄዳችሁት ወይስ በተዋረድ ያሉ የከተማ አስተዳደር ሃላፊዎችን አነጋግራችኋል? ወይ ጉድ ምን ያላየነው ችግር፣ ምን ያላንኳኳነው በር ነበርና! በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያላየነው ፈተና የለም፤ ግን ሃላፊዎችን ለማነጋገር ዕድሉን አላገኘንም፡፡

እናም ብዙ ተንከራተናል፡፡ አዋጁ የወጣው በ1990 ዓ.ም ነው ብለዋል። በወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አልነበሩም፡፡ መቼ ነው ቤተ-መንግስት የገባችሁት? እውነት ነው፡፡ በወቅቱ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ነበሩ፤ ደንቡ ሲወጣ ማለቴ ነው፡፡ እኛ ግን እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ትግላችንን ቀጥለን ምንም ምላሽ ሳናገኝ ተስፋ የቆረጥንበት ወቅት ነበረ፡፡ እንዳልኩሽ ብዙ ውጣ ውረድ አይተናል፡፡ ከዚያም እግዜር ፈቅዶ በ1997 ግንቦት ውስጥ ቤተ-መንግስት ገባን፡፡ ጥያቄያችሁ ደንቡን ለማስቀየር ነው ወይስ …? አንደኛ ደንቡ እንዲሻሻል ነበር ትግላችን፡፡ ሌላው በታክሲ ሹፌሮች ላይ የተቆለለው 154 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዲሰረዝ ነበር፡፡ ገንዘቡን ሹፌሮች እንዲከፍሉ ተወስኖ መንጃ ፈቃድ ሲቀሙ ግማሹ ቤተሰቡን በትኖ ጠፋ፣ ግማሹ ሌላ የማያውቀው ስራ ውስጥ ገባ፡፡ ራሳቸውን የጣሉ ሁሉ ነበሩ፡፡ ታዲያ ይሄ ነገር እስከየት ድረስ ነው የሚሄደው የሚለው ነገር ያሳስበን ነበርና በማህበሩ በኩል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመርን፡፡ ብዙ በሮችን አንኳኩተናል፤ ብዙ ውጣ ውረድ ደርሶብናል ብለዋል፡፡ ሄዳችሁ ምላሽ ከነፈጓችሁ መ/ቤቶች ጥቂቱን በስም መጥቀስ ይችላሉ? ለምሳሌ ሰራተኛ ማህበር ኮንፌዴሬሽን፣ የትራንስፖርት ቢሮዎች… ብቻ ብዙ ብዙ ቢሮዎች ሄደን መልስ ባለማግኘታችን ተስፋ ቆርጠን ነበር፡፡ ለፕሬዚዳንቱ አቤቱታ የማቅረቡ ሀሳብ እንዴት መጣ? እንዳልኩሽ ተስፋ ቆረጥንና ቁጭ አልን፤ ነገር ግን ቁጭ ብዬ ሳስብ አንድ ነገር በአዕምሮዬ መጣ። ለባልደረቦቼ “ለምን ለመጨረሻ ጊዜ ፕሬዚዳንት ግርማን እንደምንም ብለን አናናግራቸውም?” ስላቸው፣ እንደ እብድ ነበር የቆጠሩኝ፡፡ “እንኳን እሳቸዉ ጋ ሊያደርሱን የሚመለከታቸውስ መች ምላሽ ሰጡን?” በማለት ተቃወሙኝ፡፡ ጤንነቴን ሁሉ ነበር የተጠራጠሩት፡፡

እኔ በራሴ ተስፋ አድርጌ ወደ ቢሯቸው ስልክ ደወልኩ፡፡ ፀሀፊያቸው “ይህን ጉዳይ አዲስ አበባ መስተዳድር እንጂ ፕሬዚዳንቱ አያዩም” የሚል ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ “ግዴለም እኛ ብዙ ውጣ ውረድ እና እንግልት ስለደረሰብን ለፕሬዚዳንቱ መልዕክቱን ይንገሩልንና፣ የሚራሩልንና የሚያነጋግሩን ከሆነ እሰየው፤ አልችልም ካሉም ይሄም አንድ መልስ ነው” አልኳት። የፕሬዚዳንቱ ቢሮ (የቤተመንግስት) ስልክ ነበረዎት? ዶ/ር ነጋሶ ስለማውቃቸው እርሳቸው እንዲያገናኙኝ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ እናም ዶ/ር ነጋሶ የቢሮ አቸውን ስልክ ሰጡኝና ወደ ቤተ-መንግስት ደወልኩ፡፡ ከዚያስ? ከዚያማ መልዕክቱ ደረሳቸው፣ ግዴለም ቀጠሮ ያዙላቸውና ያነጋግሩኝ አሉ፡፡ በዶ/ር ነጋሶ በኩል ነው ይሄ የሆነው፡፡ ሰኞ ደወልን፡፡ እሮብ ለእኛ ተደውሎ “አርብ ቀን መጥተው ያነጋግሩኝ ብለዋል፡፡” የሚል ምላሽ አገኘን፡፡ ይታይሽ … አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ይሄ የሆነው፡፡ በዚያው ቀጠሮ መሰረት ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ገባን፡፡ ስንት ሆናችሁ ገባችሁ? ከእርስዎ ጋር እነ ማን ነበሩ? ከእኔ ጋር ሶስት ሆነን ነው የገባነው፡፡ እኔ፣ አንድ ጠንካራና ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆነ አቶ ትዕግስቱ ስብሀት የተባለ ሰው እንዲሁም መለሰ ወጂ የተባለ ግለሰብ ሆነን ነው የገባነው፡፡ ስንት ሆነን እንደምንመጣ ተጠይቀን ሶስት ነን ብለን ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቀባበላቸው እንዴት ነበር? አቀባበላቸው ከምነግርሽ በላይ አስደናቂ ነበር። እድሜና ሰውነታቸው ሳይከብዳቸው፣ በሀበሻ የእንግዳ አቀባበል ስነ-ስርዓት ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ነው የተቀበሉን፡፡

ችግራችሁን ከተናገራችሁ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ምን አደረጉ? አሁኑኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደውዬ እነግራቸዋለሁ፡፡ አንድ መፍትሄ እንዲሰጡ አደርጋለሁ አሉን፡፡ በቀጥታ ለአቶ አባይ ተክሌ ደውለው ጉዳዩን አሳወቁልን፡፡ በወቅቱ ክቡር አቶ አባይ ተክሌ በፓርላማ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ይመስሉኛል፡፡ ሀላፊነታቸውን በትክክል አላስታውስም፡፡ አምባሳደር ካሳ ገ/ህይወትም ነበሩ፡፡ ሁኔታው ወደዚያ ተመራና እኛን ጠርተው አነጋገሩን፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የተጠራችሁት? አዎ! የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገባንና አነጋገሩን፡፡ ያለንን ማስረጃ ከተቀበሉን በኋላ የአዲስ አበባ መስተዳድር የስራ ሀላፊዎችን ጠርተው አነጋገሩ። በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ አርከበ እቁባይም በነበሩበት ይመስለኛል ያነጋገሯቸው። ከዚያም ባላሰብነው ሁኔታ ስብሰባ ተጠራን፡፡ ይህ ጥሪ የተላለፈው በሬዲዮ በመሆኑ የማህበሩ አባላት አንሄድም አሉ፡፡ ከዚያም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ታክሲ ማህበር አባላትን ለስብሰባ እንደሚፈልጋቸው በሚዲያ እንደገና እንዲነገር ተደረገ፡፡ ይሄኔ አባላቱ ግልብጥ ብለው መጡ፡፡ የአዲስ አበባ ታክሲ ባለንብረት ማህበሮችም በስብሰባው ላይ ነበሩ። አቶ አርከበ እቁባይና ሌሎች የካቢኔ አባላትም ተገኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ፈለቀ ይመርም ነበሩ። በእሳቸው አማካኝነት ስብሰባው ተከፈተና “ይህ እድል ሊገኝ የቻለው የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች ማህበር ባደረገው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጋር በተደረገ ውይይት በመሆኑ፣ የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ አማረ ወደ መድረክ መጥተው ንግግር ያድርጉ” ተብዬ ተጋበዝኩና ንግግር አደረግሁ፡፡ አቶ አርከበ በንግግሬ ተገርመው ነበር፡፡

ከስብሰባው ምን ውጤት ተገኘ? ጉዳዩ ለካቢኔ ቀርቦ ውይይት ይደረግበት እንኳን ሳይባል በቀጥታ “ምህረት ተደርጐላችኋል” ተብሎ ደስታ በደስታ ሆንን፡፡ ይታይሽ … ወደ 154 ሚሊዮን ብር ገደማ የታክሲ ሹፌሮች እዳ ተሰረዘልን፡፡ ከመሀላችን በህግ መተላለፍ ጉዳያቸው የተያዘ ነበሩ፡፡ ጉዳያቸው ትንሽ እንዲቆይ ተደረገና ሌላው ተሰረዘ፡፡ በሂደት የእነዛም ሰዎች ጉዳይ አልቆ ተሰረዘላቸው፡፡ ለውዝፍ እዳ የዳረጋችሁ ደንብ እንዴት ሆነ? አንቀጿ አሁንም በስራ ላይ ናት፤ እየሰራች ነው፡፡ ታክሲ ሹፌሮች ክስ ሲኖርባቸው በ48 ሰዓት ውስጥ እየከፈሉ ነው የሚሰሩት፡፡ አሁን እርስዎ ምን እየሰሩ ነው? ከታክሲ ሹፌርነት ወጣሁና መነሀሪያ ገባሁ፣ የአገር አቋራጭ ሹፌር ሆንኩኝ፣ ከዚያ ለቅቄ ዶሎ ኦዶ ውስጥ ለአንድ የውጭ ዜጋ ሹፌር ሆኜ ነው የምሰራው፣ የመስክ መኪና ሹፌር ነኝ፡፡ ታዲያ አሁን አዲስ አበባ እንዴት መጡ? ከአለቃዬ ጋር ለስራ ነው የመጣሁት፡፡ በዚህ አጋጣሚ አዲስ አድማስን አገኘሁና ሳነብ “ፕሬዚዳንቱ ሰርተዋል አልሰሩም” የሚል የጦፈ ክርክር አየሁ። አማካሪያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶ፤ ፕሬዚዳንት ግርማን በደንብ ገልፀዋቸዋል፡፡ እኔም ይህን አጋጣሚ ተጠቅሜ የሰሩልንን ቁም ነገር፣ ያመጡልንን ትልቅ መፍትሄ መናገር ፈለግሁኝ፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ አቶ አርከበ እቁባይን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ቅን ሰው ናቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳንም ማመስገን እፈልጋለሁ። ፕሬዚዳንቱን ገብተን እንድናናግር ሁኔታዎችን አመቻችተውልናል። ዶ/ር ነጋሶ ፕሬዚዳንት በነበሩ ጊዜ ልታናግሯቸው አልሞከራችሁም? እውነት ለመናገር በጣም ጥረት አድርገናል። በተለይ እኔ በጣም ጥረት አድርጌ ነበር፤ አልተሳካም። በእርሳቸው ጊዜ አልሆነልንም። ግን ፕሬዚዳንት ግርማን እንድናገኝ ላደረጉት ጥረት አሁንም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ ለነገሩ የእኛ ፍላጐት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድም ስለሆነ ነው የተሳካልን ብዬ ነው የማምነው። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ታክሲ ሹፌሮች ማህበር ም/ሊቀመንበር የነበረው አቶ ትዕግስቱ ስብሀት፤ ጠንካራ ሰው ነው፤ ለህዝቡ ብዙ ደም የሰጠና የታገለ ሰው ነው፡፡ በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ፡፡ አቶ ኑረዲን ዲታሞም ሊመሰገኑ ይገባል። ማህበሩን መቼ መሰረቱት? እስከመቼስ መሩት? ማህበሩ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? በ1991 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ተመስርቶ መጋቢት ወር ላይ እውቅና አገኘ፡፡ በነገራችን ላይ ማህበሩን ለማቋቋም ያነሳሳኝ፣ በባለንብረቶች በኩል የነበረብን ከፍተኛ ጫና ነው፡፡

በማህበር ስንደራጅ የተሻለ አቅም ፈጥረን፣ ጫና እንቀንሳለን በሚል ነበር የመሰረትነው፡፡ ማህበሩ እንዳይመሰረትና እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ጭምር ባለንብረቶቹ ከፍተኛ እንቅፋት ሲፈጥሩብን ነበር፡፡ ፍ/ቤት እስከመከሰስ ሁሉ ደርሰን ነበር፡፡ እንቅፋቶቹ ምን አይነት ናቸው? ለምሳሌ ህገ-ወጥ ማህበር ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ ያሰራጩ ነበር፡፡ እኛ እንቅስቃሴያችን በህጉ ዙሪያ፣ በአገልግሎት ሰጪውና በተገልጋዩ መሀል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ጭምር ነበር። በባለንብረቶች የሚደርስብንን ተፅዕኖዎች መቀነስ የሚለው እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። በዋናነት ከላይ የፀደቀው ደንብ ሲወጣ፣ ህግ አውጭዎች እኛን ማወያየት ነበረባቸው፡፡ ይህን ጥያቄ በማህበራችን በኩል እናቅርብ የሚልም ሀሳብ ይዘን ነበር የተንቀሳቀስነው፡፡ ለምን ቢባል? በጊዜው የተጋበዙትና ለውይይት የተጠሩት የባለንብረቶች ማህበር አመራሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን የስራውና ደንቡ የወጣበት ጉዳይ ባለቤት አሽከርካሪዎች ነን፡፡ አሁን እርስዎ ከታክሲ ስራ ውጭ ነዎት፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል? በአሁኑ ሰዓት የታክሲ ሹፌር መብትና ግዴታውን ያወቀ አልመሰለኝም፡፡ በአቋራጭ ለመክበር አቆራርጦ መጫን እና በመሳሰሉት ሹፌርና ረዳት ሲመሳጠሩ አያለሁ፡፡ ህዝብ መከበር አለበት፤ እኔም ስሰራ ህግና ደንብን ተከትዬ፣ ህዝብ አከብሬ ነው የኖርኩት፡፡ ስንት አመት ታክሲ ላይ ሰሩ? ለ20 ዓመታት ሰርቼያለሁ፡፡ እንዴት በ20 አመት ውስጥ የራስዎ ታክሲ አልገዙም? እንደነገርኩሽ ህግና ስርዓትን ጠብቄ እሰራ ስለነበር፣ የማገኘው ገንዘብ ቤተሰብ ከማስተዳደር አልፎ ታክሲ ሊያስገዛ የሚችል አልነበረም፡፡ በ20 ዓመት የስራዎ ዘመን ውስጥ በርካት ገጠመኝዎች እንደሚኖርዎት እገምታለሁ፡፡ አንድ ሁለቱን ቢነግሩኝ … ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ነው ታክሲ መስራት የጀመርኩት፡፡ ማህበሩን ከ1991-1998 መርቻለሁ። ማሽከርከር ያቆምኩት 2000 ዓ.ም ነው፡፡ በሃያ አመት ውስጥ ታክሲ ላይ ምን የማያጋጥም አለ? የታክሲ ስራ ትልቅ መድረክ አይደለም እንዴ? አንዴ የማይረሳኝ አንድ ተሳፋሪ ከአቅም በላይ ጠጥቷል እና ወራጅ አለኝ፡፡ ከኔ ወንበር ኋላ ነው የተቀመጠው፡፡

በስካር አንደበት “ወራጅ አለ” ብሎኝ እስካቆምለት እድል ሳይሰጠኝ እኔና ጋቢና የተቀመጡት ሰዎች ላይ አስመለሰብን፡፡ ይህን አልረሳውም፡፡ ሌላ ጊዜ አንዲት ሴት መሳሪያ አውጥታ አስፈራራችኝ። የተከለከለ ቦታ ላይ አልቆምም ስላልኩኝ “የሰው ማንነት ሳታውቅ” ብላ ማጅራቴን ልትለኝ ነበር፡፡ በሽጉጥ ተመትቶ የሞተ ሹፌር አውቃለሁ፤ ፓስተር ማዞሪያ ላይ፡፡ በርካታ ገጠመኝ አለ፡፡ አንድ ሹፌር ወይም ረዳት 12 ተሳፋሪ ጭነው ሲሄዱትንሽ ጥፋት ቢፈጽሙ ከተሳፋሪዎች አንዱ እንኳን ሹፌሩና ረዳቱ ከጥፋታቸው እንዲማሩ የሚያደርግ አስተያየት ሲሰጥ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ አንድ ተሳፋሪ ቢበደል 12ቱም ሹፌሩና ረዳቱ ላይ ሲረባረቡ ይታያል፡፡ በአጠቃላይ ስራው አስቸጋሪ ነው እያሉኝ ነው? ስራው ሳይሆን የተለያየ ሰውና የተለያየ ባህሪ ማስተናገዳችን ነው አስቸጋሪው፡፡ ሙያው ክቡር ነው፡፡ ሰው ድንጋይ ተሸክሞም ኑሮውን ይመራል እኮ። ስራ ያው ስራ ነው፡፡ በ20 ዓመት የታክሲ ሹፌርነትዎ አደጋ አድርሰው፣ ሰው ገጭተው ያውቃሉ? አንድ ጊዜ አጋጥሞኛል፡፡ አዲስ ከተማ አካባቢ ሰው ገጭቼ ነበር፡፡ ጥፋተኛው ግን እግረኛው ነበር፡፡ መሀል አስፓልት ላይ ከእግረኛ መንገድ አራት ሜትር ከዘጠና ገብቶ ነው የተገጨው፡፡ ነገር ግን ህጉ ሰው ገጭተሽ ጥፋተኛም ባትሆኚ በነፃ አይለቅሽም፡፡ ሰውየው ሞተ ወይስ ተረፈ? ሰውየው ሞተ፡፡ እኔም ማግኘት የሚገባኝን ቅጣት አግኝቻለሁ፡፡ ልጆች አለዎት? አዎ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ እነሱን ለማስተማር ደፋ ቀና እያልኩ ነው፤ ይመስገነው፡፡

Read 3295 times