Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 26 November 2011 08:10

4ኛው የአረቦች አምባገነን ወደቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አስራ አንደኛ ወሩን የያዘው የአረቦች አብዮት፤ ረቡእ እለት የየመኑን አብዱላህ ሳላህ ከስልጣን እንዲወርዱ በማስገደድ ቀጥሏል። የመንን ለ33 አመታት የገዙት አብዱላህ ሳላህ፤ በነሳውዲ አረቢያ አደራዳሪነት፤ ስምምነት ተፈራርመው ከስልጣን ቢወርዱም፤ ብዙዎቹ የየመን ወጣቶች በዚህ እርካታ አልተሰማቸውም። የተፈረመውን ስምምነት፤ ጨርሶ አልወደዱትም። በስምምነቱ መሰረት፤ አብዱላህ ሳላህ ካሁን በፊት በፈፀሙት ማንኛውም ጥፋት እንዳይከሰሱ ዋስትና ተሰጥቷቸዋል። የክብር ፕሬዚዳንት የሚል ማእርግም ይኖራቸዋል። ይህ ነው፤ ለብዙ የመናውያን ያልልተዋጠላቸው። 
በእርግጥ፤ በድርድሩ ላይ በመሳተፍ ስምምነቱን የተፈራረመ አንድ የተቃውሞ ድርጅት፤ ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረዳቸው ምክንያት፤ በሰንአ አደባባይ የደስታና የድጋፍ ሰልፍ አካሂዷል።

ነገር ግን የድጋፍ ሰልፉ ወደ ተቃውሞ ሰልፍ ለመቀየር ጊዜ አልፈጀበትም። ላለፉት ወራት ተቃውሞ ሲያሰሙ የከረሙ በርካታ ዜጎችና ቡድኖች፤ ከነጭራሹ ድርድሩ ተቀባይነት የለውም በማለት የአደባባይ ተቃውሟቸውን ለመቀጠል ወስነዋል። በዚያው አለት ከፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት አምስት ሰዎች መሞታቸውን የዘገበው ዘ ጋርድያን፤ ከአስከሬናቸው ማየት እንደሚቻለው ሟቾቹ ወጣቶች ናቸው ብሏል። “በየጎዳናውና በየአደባባዩ፤ በመንግስት ሃይሎች የፈሰሰው የዜጎች ደም አልደረቀም” በማለት ቁጣቸውን የገለፁ የየመን ወጣቶች፤ አብዱላህ ሳላህ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወደ ቤት አንመለስም ብለዋል - ለወራት በከተሙበት አደባባይ ተሰባስበው።
የየመን ወጣቶችን ያስቆጣቸው፤ “አብዱላህ ሳላህ አይከሰሱም” መባሉ ብቻ አይደለም። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣናቸው ቢወርዱም፤ ፓርቲያቸው ከነስልጣኑ ይቀጥላል። በዚያ ላይ፤ በርካታ ሚኒስትሮችና የጦር አዛዦች፤ የአብዱላህ ሳላህ ቤተሰቦችና የቅርብ ዘመዶች ናቸው። እውነትም፤ አብዱላህ ሳላህ ከስልጣን መውረዳቸው በተነገረ ማግስት፤ የቤተመንግስት ጦር የተቃዋሚ ቡድኖችን ካምፕ በመድፍ ሲደበድብ አርፍዷል። በማን ትእዛዝ? የአብዱላህ ሳላህ ልጅ፤ የቤተመንግስት ጦር ዋና አዛዥ ነው። በሰንአ “የለውጥ አደባባይ” አመፁን ለመቀጠል የወሰኑ የመናዊያን፤ ቁጣቸው ቢበረታ ምኑ ይገርማል?
አብዱላህ ሳላህ ብቻ ሳይሆኑ፤ በስልጣን ላይ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው፤ እንዲሁም የፓርቲ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ከስልጣን መውረድ አለባቸው በማለት የሚጮሁ የመናዊያን፤ ለፍርድ ይቅረቡልን ብለዋል። አመፁ ቀጥሏል። የፖሊስና የፀጥታ ሃይሎች ጥቃትም ቀጥሏል። የመናዊያንም እየሞቱ ነው። ከሊቢያና ከሶሪያ ጋር ሲነፃፀር የከፋ ባይሆንም፤ በየመንም ላለፉት ወራት በርካታ ሰዎች ሞተዋል። በመስከረምና በጥቅምት ወር ብቻ መቶ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
ግን እስከ መቼ? ከአስር ወራት በላይ ባስቆጠረው ተቃውሞና አመፅ ውስጥ፤ ስልጣናቸውን የሙጢኝ ይዘው የቆዩት አብዱላህ ሳላህ እና መንግስታቸው ወደ መጨረሻቸው እንደተቃረቡ ሳይገነዘቡት አልቀረም። ኒውዮርክ ታይምስ እንዳለውም፤ ፕሬዚዳንቱ አሁን ከስልጣን ለመልቀቅ ፍቃደኛ የሆኑት፤ እንደ ሙአመር ጋዳፊ ቱቦ ለቱቦ ሲሸሹ ከመገደል ይልቅ፤ በጤና ስልጣን መልቀቅ ይሻላል ብለው ስላሰቡ ሳይሆን አይቀርም።
በእርግጥ፤ የፕሬዚዳንቱና የመንግስታቸው መውደቅ፤ ለየመን ፈጣን ሰላም ያመጣል ተብሎ አይታሰብም። ለተቃውሞ የተሰለፉት ቡድኖች በበርካታ ጉዳዮች የሚለያዩና የሚቀናቀኑ ናቸውና።
በዜጎች ነፃነት ላይ የተመሰረተ፤ ከሙስና የፀዳ የኢኮኖሚና የቢዝነስ አሰራር፤ የፓርቲዎች ፉክክርን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ስርአት እንዲሰፍን የሚፈልጉ የመናዊያን ጥቂት አይደሉም። ለምሳሌ፤ “ነፃ ወጣቶች” ብለው ራሳቸውን የሰየሙና ተቃሟቸውን ለመቀጠል የወሰኑ በርካታ የመናዊያን፤ ወደዚህኛው ጎራ ያዘነበሉ ናቸው።
ነገር ግን የዚያን ያህሉ፤ ተቃራኒ አስተሳሰቦችን የያዙ ሰዎችና ቡድኖች አሉ - ወደ ሃይማኖት ያዘነበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በጎሳ ላይ የተመሰረቱ ቡድኖች፤ ከመንግስት ባፈነገጡ ጄነራሎች የተደራጁ ወገኖች ወዘተ...። ሰሜንና ደቡብ ሱዳንን ለመገንጠል የሚጣጣሩ ታጣቂ የጎሳ ቡድኖች እንዲሁም፤ የለየላቸው የሽብር ድርጅቶች ሲጨመሩበት፤ የየመን አብዮት ገና ብዙ ፈተና እንደሚቀረው መገንዘብ አይከብድም።

የግብፅ ሁለተኛ ዙር አብዮት?
በአስራ ስምንት ቀናት አመፅ ሆስኒ ሙባረክን ከስልጣን ያስወገደ የግብፅ አብዮት፤ ከ10 ወራት በኋላ፤ ዛሬም ገና ከፈተና አልወጣም። “ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ጊዜያዊ ስልጣን ይዣለሁ” በማለት አገሪቱን ተቆጣጥሮ በሚገኘው ወታደራዊ መንግስት ላይ የተቆጡ ግብፃዊያን፤ ባለፈው ቅዳሜ እንደገና ወደ አደባባይ ወጥተዋል - ወደ ታህሪር አደባባይ።
“ወታደራዊው መንግስትና የፀጥታ ሃይሎች ግፍ እየፈፀሙ ነው” በማለት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ግብፃዊያን፤ ለወራት ታግሰው ብንቆይም አሁን ትእግስታችን አልቋል በማለት ቁጣቸውን ገልፀዋል። በሚቀጥለው ሰኞ የሽግግር ዘመን የፓርላማ ምርጫ እንዲካሄድ የታቀደ ቢሆንም፤ “ከዚያ በፊት ወታደራዊው መንግስት፤ በተለይ ደግሞ ዋነኛው መሪ ፊልድ ማርሻል ሁሴን ታንታዊ ከስልጣን ይውረዱልን” ብለዋል - እነዚሁ ግብፃዊያን።
ፖሊስ ደግሞ፤ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ከታህሪር አደባባይ ለቅቀው እንዲወጡ ይፈልጋል። በዚሁ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት አምስት ሰዎች መሞታቸውን ኤፒ ዘግቧል። የቀድሞው ግጭትና ሞት አይበቃም? ወታደራዊው መንግስት ኮስታራ ለመሆን ሞክሯል - ማክሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ፤ የሰኞ ምርጫ በተያዘለት ፕሮግራም እንደሚካሄድና የተቃውሞ ሰልፈኞች ወደ የቤታቸው መመለስ እንዳለባቸው አስጠንቅቆ ነበር። ማስጠንቀቂያው ግን፤ ግጭቱን ይበልጥ አባባሰው እንጂ መፍትሄ አልሆነም።
ፖሊስ፤ በተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ላይ በርካታ “የአስለቃሽ ጭስ አይነቶችን” እንደተጠቀመ የገለፀው ኒውዮርክ ታይምስ፤ አደባባዩ በጭጋግ መሰል ጭስ ተሸፍኖ ነበር ብሏል። በፖሊስ የተረጨው አስለቃሽ ኬሚካል በጣም ከመብዛቱ የተነሳ፤ ከጊዜ በኋላ በንኖ አልጠፋም። የተወሰነ ያህል ኬሚካል ከመሬት አሸዋ ጋር ተቀላቅሏል። በነፋስና በእርምጃ አሸዋው አቧሯ ሲነሳ፤ ኬሚካሉም ብናኝ እየፈጠረ የሰዎችን የመተንፈሻ አካል ይከረክራል፤ ያስነጥሳል ብሏል ኒውዮርክ ታይምስ። ፖሊሶች ኬሚካሉን ሲረጩ በትኩሱ ሲሆንማ አደገኛ ነው - ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ስተው ወድቀዋል፤ አንዳንዶቹም እየተንቀጠቀጡ ተርገፍግፈዋል። እንዲያም ሆኖ፤ የተቃዋሞ ሰልፉ አልተበተነም። በርካታ ተቃዋሚዎችም ተቀጣጣይ ነዳጅ የያዙ ጠርሙሶችን ሲወረውሩ ታይተዋል።
ከዚህ በኋላ ነው፤ ወታደራዊው መንግስት ትንሽ የተለሳለሰ መግለጫ ለመስጠት የወሰነው። በግጭቱ አምስት ሰዎች መሞታቸው እንዳሳዘናቸውና ተጠያቂዎቹን ለህግ እንደሚያቀርቡ የገለፁ ጄነራል መኮንኖች፤ ግብፃዊያን ማተኮር ያለባቸው የአደባባይ ሰልፍ ላይ ሳይሆን የሰኞው ምርጫ ላይ ነው ብለዋል። የግብፃዊያን አብዮት ወደ ግቡ ለማድረስ ጊዜያዊ የሽግግር ሃላፊነትና ስልጣን ተሸክመናል ያሉት ጄነራሎች፤ “ስልጣን ከፍተኛ ሸክም ነው፤ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሳይሆን ወደ ካምፓችን ለመመለስ እንፈልጋለን” ብለዋል። ለጊዜው ግን፤ ምርጫ እስኪካሄድና አዲስ ህገመንግስት ተዘጋጅቶ በአንድ አመት ውስጥ እስኪፀድቅ ድረስ ግን... ከስልጣን ለመውረድ ፍቃደኞች እንዳልሆኑ ተናግረዋል - ጄነራሎቹ።
ወታደራዊው መንግስት፤ የተለሳለሰ ቢመስልም፤ በታህሪር አደባባይና በዋና ዋና የተቃውሞ ጎዳናዎች ዙሪያ፤ ከሮቡእ ወዲህ ተጨማሪ ወታደሮችንና የጦር መኪኖችን አሰማርቷል። ወታደሮች አካባቢውን በሽቦ እያጠሩ፤ በኮንክሪት አጥር ሲያጠናክሩ መሰንበታቸው፤ “አመፁ ለረዥም ጊዜ ሊቀጥል ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላቸው ይመሰክራል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፤ የሰኞው ምርጫ ለተወሰኑ ቀናት ሊራዘም እንደሚችል ተገምቷል። ምናልባትም ነገርዮው ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ፤ ሁለተኛው ዙር የግብፅ አብዮት ሊሆን ይችላል።

የሶሪያው አብዮት - “የሊቢያ መንገድ”
የአረብ አገራት አብዮት፤ እንደየአገሩ የተለያየ መልክ የያዘ ቢሆንም፤ የአንዳንዶቹ ይመሳሰላል። የግብፅ አብዮት ከቱኒዚያው ጋር የመመሳሰሉን ያህል፤ የሶሪያው ደግሞ ከሊቢያ ጋር ይመሳሰላል - ተቃዋሚዎች በታንክና በመድፍ፣ በአውሮፕላንና በሄሊኮፕተር የሚጨፈጨፉበት ሆኗልና።
ምንም እንኳ የበሽር አል አሳድ መንግስት፤ በየከተማውና በየገጠሩ የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰሙ ዜጎችን ዝም ለማሰኘት በርካታ ሺ ዜጎችን ቢገድልም፤ አመፁ አልበረደም። እንዲያውም እየሰፋና እየተወሳሰበ መጥቷል። የተወሰኑ የጦር ክፍሎችና ወታደሮች፤ አልአሳድን በመቃወም ከመንግስት ጦር በማፈንገጣቸው፤ አገሪቱ ወደለየለት የእርስበርስ ጦርነት እያመራች ነው የሚል ግምት ተፈጥሯል። በያዝነው ሳምንትም፤ “አፈንጋጭ ጦር መሽጎባቸዋል” የተባሉ በርካታ የገጠር አካባቢዎች በመንግስት ጦር ሲደበደቡ ሰንብተዋል። የሶሪያና የሊቢያ ተመሳሳይነት ይህ ብቻ አይደለም።
በሊቢያ እንደታየው ሁሉ፤ የአረብ ሊግ አባል አገራት የሶሪያውን መንግስት አውግዘዋል፤ ማእቀብ ለመጣልም ወስነዋል። ከዚህም በተጨማሪ፤ እንደ ሊቢያው ሁሉ፤ “ሲቪል ሶሪያዊያንን ከመንግስት ጦር ጥቃት መታደግ አለብን” የሚል ሃሳብ መነሳት ጀምሯል። በተለይ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡእ እለት በሰጡት መግለጫ፤ “ሶሪያ ውስጥ የፀጥታ ቀጣና መከለል ያስፈልጋል” ብለዋል። ሲቪል ሶሪያውያን ይጠለሉበታል ወደ ተባለው የፀጥታ ቀጣና፤ የሶሪያ መንግስት ጦር እንዳይዘምት ማን ከልካይ አለው? ምናልባት በሊቢያ እንደታየው፤ የኔቶ የጦር አውሮፕላኖች ይሰማሩ ይሆን?

የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ - “ስራአጥ ተመራቂ”
ከላይ እንደተጠቀሰው የየአገሩ አመፅ ልዩ ልዩ ገፅታዎች ቢኖሩትም፤ ዋነኛ ባህሪያቸው ግን ይመሳሰላል። ለምሳሌ፤ የየመናዊያን አመፅ መነሻ ከቱኒዚያንና ከግብፅን አብዮት፤ ከሶሪያና ከሊቢያ አመፅ መነሻ ጋር ተመሳሳይ ነው - የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ችግር። በእነዚሁ አገራት ውስጥ የነበሩ መንግስታትን ተመልከቱ።
“ለብቻዬ ስልጣን ካልያዝኩ አገር ጤና አያገኝም። እድሜ ልክ ካልገዛሁ፤ አገር አይለማም፤ አገር ሰላም አይሆንም” የሚሉ መሪዎችና ፓርቲዎች ከ20 አመት በላይ በገናናነት ስልጣን ላይ ቆይተዋል። አንዳንዶቹማ፤ ተቃዋሚዎችን እያሰሩና እያሳደዱ ወይም እያዋከቡና እያዳከሙ፤ ስልጣን ላይ ከ30 እና ከ40 አመት በላይ አስቆጥረዋል - ምሁራንን፣ ጋዜጦችንና ዜጎችን እያፈኑ።
አንዱ አምባገነን፤ የሌላው አምባገነን “ኮፒ” ይመስላል። “ለአገርና ለህዝብ እንሰራለን” በማለት፤ ተቃዋሚዎችና ዜጎች ላይ የተለያዩ ስሞችን እየለጠፉ ያስፈራራሉ - “ፀረልማት፤ ፀረመንግስት፤ ከሃዲ፤ አሸባሪ፤ የውጭ ሃይሎች ተላላኪ፤ የአሜሪካና የአውሮፓ ቅጥረኛ” በማለት። የቱኒዚያውን ቤን አሊ፤ የግብፁን ሆስኒ ሙባረክ፤ የሊቢያውን ሙአመር ጋዳፊና የየመኑን አብዱላህ ሳላህ፤ እንዲሁም የሶሪያውን በሽር አልአሳድ መጥቀስ ይቻላል። ለተቃውሞ የተነሱ ዜጎች ላይ ያዥጎደጎዱት የውንጀላ መአት እና የውግዘት አይነት ሲታይ፤ አምባገነኖቹ አንድ አይነት የመዝገበ ቃላት መፅሃፍ የሚጠቀሙ ይመስላሉ - “ከሃዲዎች፤ እብዶች፤ የውጭ ሃይል ተላላኪዎች፤ ሰላዮች...” እያሉ ዜጎችን ይሰድባሉ፤ ያስፈራራሉ።
ፕሮፓጋንዳቸውም ይመሳሰላል። ነፃ የጤና አገልግሎት በማቅረብና ለዜጎች ድጎማ በመስጠት ድህነትን ቀርፈናል የሚሉት የአረብ መንግስታት፤ የስራ እድል ለመፍጠር ወይም ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ በጀት እንደሚመድቡና ትምህርት በማስፋፋት ወደ መቶ ፐርሰንት ሽፋን እንዳደረሱ ይገልፃሉ - እድሜ ልክ በስልጣን ላይ ለመቆየት። “የሚሌኒየም የልማት ግቦችን አሟልተናል፤ ተቃርበናል” እያሉም ይደሰኩራሉ።
ነገር ግን የትም አገር ውስጥ እንደሚታየው፤ “ለስራ ፈጠራ”፤ “ድህነትን ለማቃለል”፤ “ህዝቡን ለመደጎም”፤ “ለትምህርትና ለጤና ሽፋን” በሚሉ ሰበቦች ከፍተኛ በጀት የሚመድቡ መንግስታት፤ ኢኮኖሚውን በቁጥጥራቸው ስር በማስገባት ሁለት ጥፋቶችን ይፈፅማሉ።
አንደኛ፤ ከፍተኛ የበጀት ወጪያቸውን ለመሸፈን ከባድ ቀረጥ ወይም ታክስ እየጫኑ የዜጎችን ኪስ ያራቁታሉ። ለምሳሌ፤ “ትምህርት አስፋፋለን” ይላሉ፤ ግን በዚያው መጠንም ዜጎች ይደኸያሉ። ኢንቨስትመንትና ምርት (በአጠቃላይ ቢዝነስ) እየተዳከመ፤ የስራ እድል ይጠፋል።
ሁለተኛ፤ የመንግስትን በጀት በማሳበጥ፤ በታክስ አማካኝነት ከዜጎች የሚዘርፉትን ገንዘብ በሙስናና በእርባና ቢስ ፕሮጀክት ያባክኑታል። ለምሳሌ “ትምህርት አስፋፋን” ይላሉ፤ ነገር ግን በዚያው መጠን ሙስናው ይስፋፋል። ለአመታት ወደ ትምህርት ቤት ሲመላለሱ የነበሩ ወጣቶችም፤ በቅርበት ሲታዩ ማንበብና መፃፍ አይችሉም። ለኑሮ የሚጠቅም እውቀትና ሙያ የላቸውም። ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለስራ ፈጠራ እየተባለ በመንግስት ከሚመደበው በጀት ውስጥ፤ ግማሹ እንዲህ ይባክናል። በራሳቸው ጥረት አማካኝነት፤ እውቀትና ሙያ ለመያዝ የቻሉ ወጣቶችም፤ በቀላሉ ቢዝነስ ለመጀመር ወይም ስራ ለማግኘት አይችሉም - መንግስት በስፋት የተቆጣጠረው ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ መዳከሙ አይቀርምና - በሙስናና በብክነት።
በአጭሩ፤ በመንግስት እጆች ሲጨማለቅ የከረመው የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ፤ ለበርካታ አመታት ተሸፋፍኖ ሲጠራቀምና ሲንከባለል የቆየው የ”ቅይጥ ኢኮኖሚ” ግርግር፤ በዘመናችን ያገጠጠና ያፈጠጠ ቀውስ ወደመሆን ደርሷል - ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁና ኑሯቸውን ማሻሻል የማይችሉ ድሃ ወጣቶች የበዙበት ዘመን ሆኗል።
ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር የገባ የሶሻሊዝም ኢኮኖሚ፤ ከአመት አመት በውድቀት እየተቃወሰ እንደፈራረሰው ሁሉ፤... ለስም ያህል ብቻ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ተብሎ እየተጠራ፤ መንግስት በስፋት የሚቆጣጠረው ቅይጥ ኢኮኖሚም ቀስ በቀስ ከፍተኛ የቀውስ ደረጃ ላይ ደርሷል። የአረብ አገራት አብዮት የዚህ ቀውስ አንድ ትልቅ ምልክት ነው። ደግሞ... የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማምለጫ የለም - ወደተሟላ የነፃ ገበያ ስርአት (ወደ ካፒታሊዝም) ለመራመድ ጥረት ካልተደረገ በቀር ማምለጫ የለም።

 

Read 2732 times Last modified on Saturday, 26 November 2011 08:23