Saturday, 21 September 2013 11:19

ዝምተኛው ገዳይ! (Silent Killer)

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(7 votes)
  • የደም ግፊት መነሻዎች፣ ምልክቶችና ጥንቃቄዎች
  • ወንዶች ከሴቶች የበለጠ በደም ግፊት የመያዝ ዕድል አላቸው በአገራችን የደም ግፊት ህሙማን ቁጥር 30 ሚ. ይደርሳል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በሽታው እንዳለባቸው እንኳን አያውቁም

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቆ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የተደላደለ የሰውነት አቋም ነበረው፡፡ ጤናማና ንቁ የ26 ዓመት ወጣት በነበረበት ወቅት ምኞቱና ህልሙ ትምህርቱን መቀጠልና በተሰማራበት የሥራ መስክ ስሙን ሊያስጠራ የሚችል ተግባር ማከናወን ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ይህን ህልሙን ማሳካት እንደሚችልም እርግጠኛ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ራሱን ከተለያዩ ሱሶች ጠብቆ ትምህርቱን ለመቀጠል የሚያስችለውን ገንዘብም ማጠራቀም የጀመረው፡፡ ምንም ዓይነት የህመም ስሜት ስለማይሰማው ጤናማነቱን ተጠራጥሮት አያውቅም፡፡ “እንኳን እሱ እራሱ እኛም የከፋ በሽታ ቀርቶ ጉንፋን እንኳን ጠንከር ብሎ ይይዘዋል ብለን አናስብም ነበር” ይላል ታናሽ ወንድሙ ዳንኤል ታደሰ፡፡ ሆኖም የዚህን ወጣት የረጅም ጊዜ ህልምና ምኞት የሚያጨልምና ከህይወት ሩጫው የሚያስተጓጉል አጋጣሚ በአንዲት ክፉ ቀን ገጠመው፡፡

“የዛን ዕለት ቀኑን በሥራ አሳልፎ ወደቤቱ የተመለሰው በሠላም ነው፡፡ ወንደላጤ ስለሆነ ምሽቱን የሚያሳልፈው በላፕቶፑ ላይ በሥራ ተጠምዶ ነው። ብቻዬን ከምሆን ብሎ እኔን ከወላጆቼ ቤት እሱ ጋ ሲወስደኝ ሠላሙንና ፍላጐቱን መጠበቅና ማክበር እንዳለብኝ አስጠንቅቆኝ ስለነበር ሥራ ከጀመረ በኋላ በምንም አይነት ሁኔታ አልረብሽውም፡፡ የዛን ዕለት ምሽትም እራታችንን ከበላን በኋላ አጠገቡ ድርሽ አላልኩም፡፡ እስከሌሊቱ አጋማሽ ድረስ ላፕቶፑ ላይ ሲሰራ አምሽቶ ወደመኝታው ሲሄድ፣ በሰመመን ሰምቸዋለሁ፡፡ ንጋት ላይ ከወትሮው በተለየ ከአልጋው ላይ ሳይነሳ መቆየቱ እንግዳ ነገር ሆነብኝ። ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ የተረፈውን ሥራ ንጋት ላይ አጠናቆ፣ በማለዳ ወደ ሥራው ነው የሚሄደው፡፡ የዛን ዕለት ግን ከመኝታው ሳይነሳ ሰዓቱ ረፈደ፤ ሁኔታው ግራ አጋብቶኝ ልቀስቅሰው ወደ ክፍሉ ስገባ፣ ከአልጋው ወድቆ ወለሉ ላይ እጥፍጥፍ ብሎ አየሁት፡፡ በድንጋጤ እሪ ብዬ ጮህኩ፡፡ ሰዎች ደርሰው ስናየው ትንፋሹ አለች፤ ይዘነው ወደ ሆስፒታል በረርን፡፡” ሲል ታናሽ ወንድም በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

ወጣቱ ቀደም ሲል መኖሩን እንኳን የማያውቀው የደም ግፊት በሽታ ባስከተለበት መዘዝ ሳቢያ፣ የደም ቧንቧዎች መዘጋት ችግር (ስትሮክ) ገጥሞት ሰውነቱን መቆጣጠር አቃተው፡፡ መነጋገርና ሽንትና ሠገራውን መቆጣጠር የማይችል ሰው ሆነ፡፡ የዚህ ወጣት አሣዛኝ ህይወት አሀዱ ብሎ የተጀመረው እንዲህ ነው፡፡ ገና ሮጦ ባልጠገበበት፣ የረዥም ጊዜ ህልሙን ሰንቆ ከህይወት ጋር ግብ ግብ በጀመረበት የአፍላነት ዕድሜው፣ ከአልጋው ላይ ያለሰው ድጋፍ መነሳት የማይችል ህመምተኛ ሆነ፡፡ በጥቁር አንበሣ ሆስፒታል በተደረገለት የህክምና እርዳታ ህይወቱ ሊተርፍ ቢችልም በህይወት ዘመኑ ሁሉ አብሮት የሚኖር የአካል ጉዳት ገጠመው፡፡ ቤተሰቦቹ ህይወቱን ለማትረፍና ወደ ቀድሞው እሱነቱን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉለትም አልተሳካላቸውም፡፡ ረዘም ባለ የህክምና ክትትል በሰው ድጋፍ መንቀሣቀስ፣ ሽንትና ሠገራውን መቆጣጠር ቢችልም ዛሬም ወደ ሥራው መመለስና ሃሳቡን እንደልቡ በንግግር መግለፅ አልቻለም። ወጣቱን ለንግግር የሚረዳ ህክምና (Speech Therapy) በአገሪቱ በብቸኝነት በሚሰጥበት የካቲት 12 ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን በሆስፒታሉ ህክምናውን ለማግኘት ተመዝግበው ረዥም ቀጠሮ ከሚጠባበቁት ህሙማን መካከል አንዱ ነው፡፡

ህክምናውን በአገራችን ውስጥ የምትሰጠው ባለሙያ አንዲት ብቻ ስትሆን ህክምናውን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ለረዥም ጊዜ ተራ መጠበቅ የግድ ሆኗል፡፡ ባላሰበውና ባልጠበቀው ሁኔታ የ26 ዓመቱን ወጣት አልጋ ላይ ያዋለው የደም ግፊት በሽታ፤ አሁን አሁን በአገራችን በስፋት የሚታይና የተለመደ በሽታ ለመሆን እንደቻለ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአሜሪካ ብቻ ከ45 ሚሊዮን በላይ የደም ግፊት ህሙማን አሉ፡፡ ዘመኑ የተራቀቀ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን መጠቀም የሚያስገድድበት ጊዜ በመሆኑ፣ ሰዎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ማድረጉና የጣፋጭና ፈጣን ምግባች ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ እንዲሁም የሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት በውጥረትና በጭንቀት የተሞላ እየሆነ መምጣቱ በደም ግፊት በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጐታል፡፡ በአገራችንም በአግባቡ የተደረገ ጥናትና ቆጠራ ባይኖርም የደም ግፊት ህሙማን ቁጥር ከሃያ አምስት እስከ ሰላሣ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የሚናገሩት የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ተስፋሁነኝ ታዴ፤ የኑሮ ውጥረቱ፣ ጭንቀትና የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲበራከት ምክንያት መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ በሰውነታችን ውስጥ ጤናማ የሚባለው የደም ግፊት መጠን የታችኛው ዲያስቶሊክ (Diastolic) 80፣ የላይኛው ሴስቶሊክ ደግሞ ከ120-130 ድረስ ሲሆን ነው የሚሉት ዶ/ር ተስፋሁነኝ፤ የታችኛው ከ90 በላይ፣ የላይኛው ደግሞ ከ140 በላይ ከሆነ ከፍተኛ የደም ግፊት መኖሩን ጠቋሚ እንደሆነና ሰውየው (ሴትየዋ) አደጋ ላይ መሆናቸውን እንደሚያመላክት ይገልፃሉ። ዝምተኛው ገዳይ (silent killer) እየተባለ የሚጠራው የደም ግፊት በሽታ፤ ይህንን ስያሜውን ያገኘው ያለአንዳች ማስጠንቀቂያና ምልክት ለህልፈተ ህይወት በመዳረጉ ነው፡፡ የደም ግፊት ህመም (hyper tension) በደም ቧንቧዎች መጥበብ ወይም በግድግዳዎቹ እንደልብ መለጠጥ አለመቻል ሳቢያ የሚከሰት ህመም ሲሆን ምልክቶቹ ከባድና ድንገተኛ ራስ ምታት፣ ትኩሳት፣ ማጅራትን ጨምድዶ መያዝ፣ ጭንቅላት ላይ የማቃጠል ስሜትና የልብ ድካም ናቸው፡፡

የደም ግፊት በሽታ ከያዛቸው ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚጠጉት በሽታው እንዳለባቸው እንኳን የማያውቁና ህክምና የማይከታተሉ ናቸው፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የደም ግፊት መከሰቻው በውል የማይታወቅ ሲሆን በበቂ ምክንያቶች የሚከሰተው የደም ግፊት ከአስር በመቶ በታች ነው። ለደም ግፊት መከሰቻ ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የዘር ውርስ፣ የኩላሊት በሽታ፣ የነርቭና የልብ ሥርዓት መቃወስ፣ የሆርሞን መዛባት፣ በጣፋጭና በቅባት የተሞሉ ምግቦች፣ የማያንቀሳቀስ ስራ፣ የዕድሜ መግፋት፣ ጨው በብዛት መመገብ፣ ጭንቀትና ውጥረት ይገኙበታል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በህክምና እርዳታም ሆነ በሌሎች መንገዶች በቁጥጥር ስር ያልዋለ የደም ግፊት፣ ግፊቱ እየጨመረ ሄዶ በደም ስሮች ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር፣ ደም ስሮቹ እንዲደድሩና ደም እንደልብ እንዳይዘዋወሩባቸው ያደርጋል፡፡ ይህም ለከፋ የጤና ችግርና ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ የጤና ችግሮች መካከል ደም በሚፈለገው መጠን ወደ ኩላሊት እንዳይገባ በማድረግ ኩላሊት የተለመደ ተግባሩን በአግባቡ እንዳያከናውን ማዳከም፣ ደም በአንጐል ውስጥ እንዲፈስ ማድረግ፣ የልብ የደም ቧንቧዎችን መዝጋትና ማጥበብ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ማንኛውም የደም ግፊት ያለበት ሰው መድሃኒት መውሰድ እንደሚገባው የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር፣ ክብደትን በመቀነስና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ብቻ ደም ግፊትን ማስቀረት ወይም ማጥፋት ይቻላል የሚለው ግምት የተሳሳተ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፤ ክትትል ያልተደረገለትና መድሃኒት ያላገኘ የደም ግፊት በድንገት ለከፍተኛ ችግርና ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፡፡

የደም ግፊት መድሃኒትን በመውሰድ በግፊቱ ሳቢያ የሚከሰተውን ሞት 13 በመቶ፣ ከደም ግፊቱ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የስትሮክ (በአንጐል ውስጥ ደም የመፍሰስ ችግር) 42 በመቶ፣ የልብ ድካምን ደግሞ 28 በመቶ ማስቀረት እንደሚቻል ዶ/ር ተስፋሁነኝ ይናገራሉ፡፡ የደም ግፊት በሽታ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ በስፋት እንደሚታይ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ወንዶች በተፈጥሮአቸው ከሴቶች የበለጠ የቁጡነት ባህርይ ስላላቸውና በጭንቀት በቀላሉ ስለሚጠቁ ሲሆን የወንዳወንድነት ሆርሞን በደማቸው ውስጥ በብዛት መኖሩና ይህም ባህርይን የመለወጥ አቅም ስላለው ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በከፍተኛ ደም ግፊት የመያዝ ዕድል እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የደም ግፊት ችግሮችን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል ሲጋራን ማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ በዘር ወይም በቤተሰብ በደም ግፊት በሽታ የተጠቃ ሰው መኖር፣ የጣፊያ ወይም የስኳር በሽታ፣ ጨው በብዛት መመገብ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ጨውን አብዝቶ መመገብ የደም ግፊትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያባብስ ከመሆኑም በላይ የደም ግፊት መድሃኒቶች በአግባቡ እንዳይሰሩም ያደርጋል፡፡ ቡና መጠጣት ለደም ግፊት ህሙማን የማይመከርና በሽታውን ለማባባስ አስተዋፅኦ እንዳለው በተደጋጋሚ ቢነገርም ይሄን እውነታ የሚያረጋግጥ መረጃ በቅርቡ አለመውጣቱን ጥናቶቹ ጠቁመዋል፡፡

የደም ግፊት በሽታ ከመከሰቱ በፊት ሊደረጉ ከሚገባቸው ጥንቃቄዎች መካከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ በየጊዜው የጤና ምርመራዎችን መከታተል፣ ራስን ከጭንቀትና ውጥረት ማላቀቅ፣ ክብደትን መቀነስና ጣፋጭና ቅባት ነክ ምግቦችን ማስወገድ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላም ህመምተኛው ክብደቱን በመቀነስ፣ የእግር ጉዞ እንቅስቃሴዎችን በማድረግና ጨውና ቅባት አልባ ምግቦችን በመመገብ የደም ግፊትን ለማስወገድና በግፊቱ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉትን አደጋዎች ለመቀነስ ይችላል፡፡ ፖታሺየም ለደም ግፊት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ንጥረ ነገር ሲሆን ፖታሺየም በአብዛኛው በሙዝ፣ በቲማቲምና ቅጠላቅጠሎች ውስጥ በስፋት ይገኛል፡፡ ስለዚህም የደም ግፊት ህሙማን ፖታሺየም ያላቸውን ምግቦች ቢመገቡ ግፊቱ እንዲወርድና ጉዳት እንዳይደርስ በማድረግ ሊከላከሉት ይችላሉ፡፡ ከልክ ያለፈ ፖታሺየም መመገብም ለከፍተኛ አደጋና ለጉዳት ሊዳርግ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ ባልታሰበ ጊዜና ሰዓት ለአካል ጉዳተኝነትና ለሞት ሊዳርግ የሚችለው የደም ግፊት በሽታ፤ ዛሬ የዓለማችን ሁሉ ሥጋት ሆኗል፡፡ እናም ይህንን አስከፊ በሽታ ለመከላከል የጤና ምርመራ ማድረግና በሽታው እንዳለብን ባወቅን ጊዜም ተገቢውን ህክምና በመከታተል ልንቆጣጠረውና በእሱ ሳቢያ ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡

Read 6678 times