Saturday, 21 September 2013 11:09

ያላለቀ ድርሰት

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(4 votes)

     “ኧረ ይብቃህ ደጀኔ!... አራት ሰዓት ሞላኮ!...” አሉ እትየ ስንዱ፣ መጋረጃውን ገለጥ አድርገው ከወደ ጓዳ ብቅ እያሉ፡፡ “አንቺ ግን ለምን ሰላም አትሰጪኝም!?...” ደጀኔ አቀርቅሮ ከሚጽፍበት ቀና በማለት በንዴት ጦፎ እስክርቢቶውን ወረወረ፡፡ “ስንቴ ልንገርሽ አክስቴ!?… በውስጤ የታመቀውን የደራሲነት ስሜት መተንፈስ እንጂ፣ የኮሌጅ ትምህርት አጠናቆ መመረቅ አይደለም የህይወቴ ጥሪ!” እየተንቀጠቀጠ ተናገረ፡፡ “የዛሬውስ የተለየ ነው!... ገና በማለዳ ንትርክ ጀመራችሁ?” የእማማ በለጡ ድምጽ በስተቀኝ ያለውን የኮምፔርሳቶ ግድግዳ አልፎ ተሰማ፡፡ ከጉዳይ የጣፋቸው አልነበረም፡፡ “ተው እንጂ ደጀኔ… ደህና ሂደህ ሂደህ አንድ አመት ሲቀርህ አትሰላች!” በትህትና መለሱለት፡፡ “አንቺኮ ችግርሽ ይሄ ነው!... የጀመርኩትን ትምህርት እንጂ፣ የጀመርኩትን ድርሰት ስለመጨረሴ አትጨነቂም!” ከተቀመጠበት ብድግ አለ፡፡ ሁለት አንቀጽ ጅምር አጭር ልቦለድ የጻፈባትን ወረቀት ከጠረጴዛው አንስቶ በፍጥነት ወደ ጓዳ አመራ፡፡

“እኔኮ ላንተ ብየ ነው!... ደሞም’ኮ አትጣፍ አላልኩህም፡፡ ከኮሌጅ ስትመለስ መጨረስ ትችላለህ” አሉት አክስቱ በትህትና ፈገግ ብለው፡፡ የአክስቱ ትህትና የገነፈለ ስሜቱን በረድ አደረገለት፡፡ እንደወትሮው አልተቆጡትም፡፡ እንደሌላው ጊዜ ልብ የሚሰብር ነገር አልተናገሩትም፡፡ “ደሞ አንተን ብሎ ደራሲ!... የአስር ሳንቲም ሻይ ቅጠል የማይገዛ እንቶፈንቶ መሞንጨሩን ትተህ፣ ትምህርትህን ብታጠና ይሻልሃል!” ብለው አልተሳለቁበትም፡፡ ወደ ጓዳ የጀመረውን ጉዞ ገታ አደረገና ዘወር ብሎ ተመለከታቸው፡፡ አክስቱ ፊት ላይ ባዕድ ፈገግታ ተመለከተ፡፡ ጥቂት አሰብ አደረገና በእጁ የያዘውን ወረቀት በተስፋ መቁረጥ ወደ ጓዳ ወረወረው፡፡ “ማንም ተጠያቂ አይደለም…” ብሎ ጀምሮ፣ ሁለት አንቀጽ ከተጓዘ በኋላ ሳይቋጭ የቀረው የደጀኔ ጅምር አጭር ልቦለድ፣ እየተውለበለበ ወርዶ ጓዳ የተቀመጠ መክተፊያ ላይ አረፈ፡፡ ደጀኔ ከአክስቱ ቤት ወጥቶ ወደ ኮሌጅ ሄደ፡፡

ደጀኔ ከኮሌጅ ወጥቶ ወደ አክስቱ ቤት ተመለሰ፡፡ ከላይ ባሉት ሁለት አረፍተነገሮች መካከል ብዙ ነገር ተከናውኗል፡፡ “ስንዴ ቡናው ፈልቷል” ብለዋል እማማ በለጡ፡፡ ደጋግመው ተጣርተዋል… ምላሽ አጥተዋል፡፡ ወደ እትየ ስንዱ ቤት መጥተዋል፡፡ “የት ገባች ይቺ ሴትዮ?” ጠይቀዋል - ስንዱን ከሳሎን ሲያጡ፣ ወደ ጓዳ እያዩ መጋረጃውን እየገለጡ፡፡ “እሪሪሪሪሪ!!!!!” ብለዋል በፍርሃትና በድንጋጤ እየተንቀጠቀጡ፣ መንደሩን በጩኸት እያቀለጡ፡፡ እትዬ ስንዱ ተፈጽመዋል፡፡ በእንስራ ገመድ ራሳቸውን አንጠልጥለዋል፡፡ መንደርተኛው በለቅሶ ሲናወጥ፣ ዙሪያ ገባው በዋይታ ሲቀወጥ፣ ልጅ አዋቂው በእንባ ሲራጭ… ይህ ሁሉ ሲሆን ከቆየ በኋላ ነው፣ ደጀኔ ከኮሌጅ ወደ መንደሩ የተመለሰው፡፡ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ - ደጀኔ የሆነውን ሁሉ ሲሰማ፡፡ “አክስቴን… ስንዱዪን!... ምነው ምን አረግኩሽ!?... ለማን ትተሽኝ ሄድሽ?... እኔ ልሰቀልልሽ!...” እያለ መሬት ላይ ወድቆ ተንከባለለ፡፡ ጎረቤት ተባብሮ ከመሬት ሲያነሳው ደግሞ፣ ለመሮጥ ሞከረ፡፡ ወዴት?... ወደ እማማ በለጡ ውሃ ጉድጓድ!... ለምን?... ራሱን ለማጥፋት! “የኔ ጉድጓድ የማንም እርኩስ መደበቂያ ነው እንዴ?!” አሉ እማማ በለጡ ነገሩን ሲሰሙ፡፡ ደጀኔ ሴትዮዋ “መደበቂያ” የሚለውን ቃል ያለነገር እንዳልተጠቀሙት የገባው ዘግይቶ ነው። ጎረቤቶቹ አረጋግተው ካስቀመጡትና የሆነውን ሁሉ ከነገሩት በኋላ ነው ነገሩ የተገለጠለት፡፡

ፖሊስ ነገሩን ሊያጣራ መጥቶ እንደነበርና መረጃ ሰብስቦ እንደሄደ ከጎረቤት ሰማ፡፡ እማማ በለጡ ፖሊሶች ከሄዱ በኋላ የእሱን ስም እየጠሩ አጉል ነገር ሲናገሩ እንደነበር ተነገረው፡፡ “ጧት ስንዱና ደጀኔ ሲጨቃጨቁ ሰምቻለሁ፡፡ እሱ ከሄደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ቡና ጠጪ ልላት ስሄድ ተንጠልጥላ አገኘኋት፡፡ እሱ ነው አበሳጭቶ ያለጊዜዋ የደፋት” ሲሉ ነበር አሉት፡፡ ስለዚህ ደጀኔ በአክስቱ ሞት ተጠርጣሪ ነው። ለምርመራ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ከተወሰደው አስከሬን ጋር የሄደች አንዲት ሴት “ፖሊሶቹ ስንዱ ከመሞቷ በፊት የጻፈችውን ኑዛዜ አግኝተዋል” የሚል አዲስ መረጃ ይዛ መጣች፡፡ ይህ ነገር ብዙዎችን አስደነቀ፡፡ ‘እሱ ነው አቃጥሎ የገደላት’ ብለው፣ ደጀኔን ውስጥ ውስጡን ሲያሙ የነበሩ ሁሉ ተገረሙ፡፡ ደጀኔም ቢሆን ወሬውን ሲሰማ ግራ መጋባቱ አልቀረም። አክስቱ መጻፍ እንደሚችሉ አያውቅም ነበር። ይሄም ሆኖ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርገው የአክስቱ ኑዛዜ በመገኘቱ ተጽናና፡፡

በዚህ መሃል ነው መርማሪው ፖሊስ ከተፍ ያለውና ከደጀኔና ከቅርብ ሰዎች ጋር መወያየት የጀመረው፡፡ ተገኘ የተባለው ጽሁፍ በሌላ ሰው ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ አለመሆኑንና እርግጥ ሟቿ የጻፉት እንደሆነ ለማረጋገጥ፣ ሌላ ከዚህ በፊት የጻፉት ጽሁፍ ካለ እንዲቀርብለት አዘዘ ፖሊሱ፡፡ ያልተበረበረ ቁምሳጥንና ሻንጣ የለም፡፡ ደጀኔ ወደ ጓዳ ገብቶ የአክስቱን የእጅ ጽሁፍ መፈለግ ጀመረ፡፡ የአክስቱ የእጅ ጽሁፍ ጓዳ የለም። የአክስቱ ብቻ ሳይሆን የእሱም የእጅ ጽሁፍ የለም፡፡ “ማንም ተጠያቂ አይደለም…” ብሎ ጀምሮ፣ ሁለት አንቀጽ ከተጓዘ በኋላ ሳይቋጭ የቀረው ጅምር አጭር ልቦለዱ፣ ጧት ላይ ተናዶ ወደ ጓዳ የወረወረው የእጅ ጽሁፉ! ደጀኔ ነገሩ ተገለጠለት፡፡ የለቀስተኛ ድምጽ እየረበሸው፣ ጓዳ ተደብቆ የሆነ ነገር ለመጻፍ ሞከረ… የሆነ ነገር… በቃ… አለ አይደል… ለፖሊሶቹ የሚሆን… ከጓዳ ያገኙትን የአክስቱን ኑዛዜ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሚረዳ የአክስቱ የእጅ ጽሁፍ…

Read 4846 times