Saturday, 21 September 2013 10:59

የጀግና አሟሟት

Written by  አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(11 votes)

ምዕራፍ አንድ፡- አጼ ቴዎድሮስ እና ሞት

አትጠገብ የምትባል ሴት ከ195 አመታት በፊት ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ወይዘሮ አትጠገብ ሀይለ ጊዮርጊስ ከሚባል ውድ ባለቤቷ ካሣ የሚባል ልጅ ወለደች፡፡ ልጁ ካሣ ሀይሉ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ካሣ ሲያድግ ንጉስ መሆን አማረው፡፡ ካሣ በተወለደበት ዘመን ተራ ሠው አይነግስም፡፡ ነገሥታት የሚሆኑት የሠለሞን ዝርያ ያላቸው፣ በእግዚአብሔር የተመረጡ እና የተሰየሙ እናም የነዚህ ሠዎች ዝርያዎች ነበሩ፡፡ ካሣ ግን ንጉሥ መሆን አማረው፡፡ ሲያስብ እንዲህ እያለ ነበር ፡- “የነገስታቱ ዝርያ አይደለሁም፡፡” “እና ባልሆንስ?!” “አትቆጣ?!” “መቆጣት አይደለም፡፡” “እና ታዲያ;!” “ንጉሥ መሆን አምሮኛል!” “እና ንጉሥ መሆን የምችል ይመስልሃል?!” “Yes, I can” ብሎ ተነሳ፡፡ የአሜሪካው ንጉስ ባራክ ኦባማ `Yes, we can` የሚለውን የምርጫ መወዳደሪያ መፈክር የኮረጀው ከካሳ ሀይሉ ነው፡፡ የምናውቅ እናውቃለን፡፡

ካሳ ጉረኛ አልነበረም፤ በተወለደ በሰላሳ ሰባት አመቱ፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ በደረስጌ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ንጉሰ ሆኖ ተቀባ፡፡ ካሳ ተራ ንጉስ አልነበረም፤ ሀገሩን በጣጥሰው ሲገዙ የነበሩትን ቅርብ ሀሳቢ መሳፍንት አስገብሮ ንጉስ ነገስታቸው ሆነ፡፡ ያልተረጋጋች እና ያልሰለጠነች ኢትዮጵያን ለማረጋጋት እና ለማሰልጠን ጣረ፤ ለአስራ ሶስት አመታት ነገሰ፤ ባከነ፡፡ ከንግስናው እለታት አንድ ቀን መሞቻህ ይሁን ሲለው፣ እኩያው አድርጎ ለሚያስባት የእንግሊዝ ንግስት የቴክኒክ ድጋፍ የሚጠይቅ ደብዳቤ ፃፈ፤ ፅፎም ካሚሮን ለሚባል እንግሊዛዊ፣ እንዲያደርስ ላከው፡፡ መልእክተኛው ግን የቁራ መልእክተኛ ሆነ። ካሜሮን የተላከውን መልእክት ሳያደርስ፣ በዚያም ላይ ግብፅ ምናምን ሲዞር ከርሞ መጣ፤ በወቅቱ የግብፅ ሰዎች ከቴዲ ጋር አሪፍ ጓደኞች አልነበሩም፡፡ ካሜሮን መጣ፡፡

“እህሳ ነጫጭባው! መልእክቴን ለንደን አደረስሽ?” “አላደረስኩም ነብሴ፤ ግን እንዲደርስ በሌሎች ልኬያለሁ፡፡” “እኔ እኮ መልእክቱን አንቺ እራስሽ ለንደን ወስደሽ ለንግስቲቷ በእጇ እንድታስረክቢ ነው የላኩሽ፡፡” “ፍሬንድ እኔ እሱ መች ጠፋኝ፤ አለቆቼ እኛ በምናደርሰው መንገድ እናደርሰዋለን አሉኝ እንጂ፡፡” “እና ይህን ሁሉ ጊዜ ምን ስታደርጊ ከርመሽ መጣሽ?!” “ግብፅ ምናምን ለአንዳንድ ጉዳዮች ሄጄ ነበር፡፡” “እንዲህ ነኝና መይሳው!” አለ ንጉስ ቴዎድሮስ፤ በጣም ተናዷል ፡፡ “ይህችን ነጫጭባ አስገባት፡፡” ካሜሮን እስር ቤት ገባ፤ ታሰረ፡፡ የካሜሮን አቢሲኒያ ውስጥ መታሰር ለንደን ተሰማ፡፡ እንግሊዝ ካሜሮንን ለማስፈታት ራሳም የሚባል ሰውዬ ላከች፤ ቴዲ እሱንም ጭፍራዎቹንም አሰራቸው፡፡

ቴዲ ሳይታወቀው አንገቱ ላይ ገመዷን እያጠበቀ ነበር፡፡ ቴዎድሮስ የታሪካችን ፈርጥ፣ የስነ-ፅሑፋችን ጌጥ ነው፡፡ እስከአሁን ካነበብኳቸው የአማርኛ መፅሐፍት የብርሃኑ ዘርይሁንን “የታንጉት ምስጢር” የሚያክል የለም፡፡ ቴአትር ብዙ አላየሁም፣ ካየኋቸው ግን የፀጋዬ ገብረ መድህንን “ቴዎድሮስ” የሚስተካከል የለም፡፡ ምዕራፍ ሁለት፡- እኔና ሞት የአንድ ሠው የህይወት ዘመን ሶስት ክፍሎች ናቸው ያሉት፡፡ አንድ፡- ጅማሮ፤ ሁለት፡- ኑሮ፤ ሶስት፡- ሞት፡፡ ሶስቱም እኩል ዋጋ አላቸው፡፡ ቴዎድሮስ ከህይወቱ አጀማመር እና አኗኗር በጣም ጎልቶ የሚነገረው አሟሟቱ ነው፡፡ የጀግና አሟሟት ተምሳሌት ተደርጎ ሁሌ ነው የሚወራው፡፡…. እኔ ደግሞ ብዙ ጊዜ ያልተሳኩ እራስን የማጥፋት ሙከራዎች አድርጌያለሁ፤ እንደ ሲልቪያ ፕላዛ። ሲልቪያ ፕላዛ ሶስት የከሸፉ እራስን የማጥፋት ሙከራዎች አድርጋ፣ በሶስት መክሸፍ አንድ የተሳካ ግጥም ፅፋለች፡፡ የከሸፉ እራስን የማጥፋት ሙከራዎች ትዝ ባሉኝ ጊዜ (ሁሌ ነው ደግሞ ትዝ የሚሉኝ) ቴዎድሮስ ትዝ ይለኛል፡፡ እራስህን ማጥፋት የምር እየፈለክም ላይሳካልህ ይችላል፡፡ ቴዎድሮስ ደፋር ብቻ ሳይሆን እድለኛም ነበር። ሁሌ ስለ ቴዎድሮስ አስባለሁ፤ ሁሌ ትዝ የሚልህ ምርጥ መጽሐፍ “የታንጉት ምስጢር” ከሆነ፤ ያው ቴዎድሮስ ነው ትዝ የሚልህ፡፡ አንድ ቀን ስለህይወት ከንቱነት እያሰብኩ፤ (ቀጣዩን ራሴን የማጥፋት ሙከራዬ የመግቢያ ሀሳብ ነው፤ ከልምድ አውቃለሁ) የሚገርም ነገር ተከሰተ፡፡ የቴዎድሮስ አይነት የክብር አሟሟት ተከስቶ አየሁ። የሚገርመው ደግሞ ብዙ ሠው ተሰብስቦ በነበረው ባር ድርጊቱን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻ ስከታተል የነበርኩት እኔ ነኝ፡፡ ለኔ የተላከልኝ መለኮታዊ መልእክት ይመስለኛል፡፡ ቴሌ ባር የሚባል ቤት ውስጥ የመቅደላ ታሪክ ሲደገም፤ ሙሉ(!) ታሪኩን ያየሁት እኔ ብቻ ነበርኩ። ታሪክ መፃፍ አለበት፤ በተለይ እንዲህ አይነቱ፡፡ የክስተቱ ሙሉ ተመልካች (ነበርኩ) ነኝ ብያለሁ። አሁን የምፅፍላችሁ ግን ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ ስለ ሠዎቹ ያጠናከርኩትን አካትቼ ነው፡፡

                                                         * * *

ሲልቪያ ፕላዝ እራሷን እንስቲቷ አልአዛር እያለች ነው የምትጠራው፤ ብዙ ጊዜ ከሞት ተርፋለች፤ ተነስታለች፡፡ እራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረው የዳኑ ሠዎች ከሞት እንደተረፉ ሳይሆን ከሞት እንደተነሱ ነው የሚሰማቸው፡፡ የምናውቅ እናውቃለን፡፡ ሲልቪያ ፕላዝ Lady Lazarus በሚለው ግጥሟ ላይ እነኚህ ስንኞች አሉ፡- I have done it again One year in every ten I manage it… Soon, soon the flesh The grave cave ate will be At home on me --- I am only thirty And like the cat I have nine times to die. This is Number three What a trash To annihilate each decade --- The first time it happened I was ten It was an accident The second time I meant To last it out and not come back at all I rocked shut Dying Is an art, like everything else I do it exceptionally well. I do it so it feels like hell I do it so it feels real I guess you could say I’ve a call. ሲልቪያ ፕላዛ በአራተኛ የተሳካ ሙከራዋ፤ በ31 አመቷ ሞተች፡፡ ጠፋች፡፡

እራሷን አጠፋች፡፡ ምዕራፍ ሶስት፡- ዘመናዊው አጼ ቴዎድሮስ እንደተለመደው ጠዋት ከእንቅልፌ ነቃሁ፡፡ አምሽቼ ተኝቼ በጠዋት ነው የምነቃው፡፡ እንቅልፍ አይወደኝም፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ሞት የሚጠላኝ። በሁለት ታክሲ ወደ ሰንጋተራ ሄድኩ፣ ወደ አረቄ ቤት፡፡ የአረቄ ቤት የጠዋት ጓደኛዬ አስፋው ቀድሞኛል፤ ቁርስ አብረን ነው የምንበላው፤ ማታ ማታ አስር አስር ብር አዋጥተን ለአረቄ ቤቱ ባለቤት እንሰጣለን፤ ጠዋት ጉበት ገዝቶ፤ ከትፎ፣ ቀምሞ ይጠብቀናል፤ አብረን እንበላለን፡፡ ዛሬ ሠኞ ነው፡፡ ሰኞ ይደብራል፡፡ (አጼ ቴዎድሮስ የሞተው ሰኞ ቀን ነው፤ በፋሲካ ማግስት፡፡) ዛሬ ሠኞ ነው፡፡ ዛሬ ቀፎኛል፡፡ (የዛሬው ቁርስ ከአስፋው ጋር የመጨረሻችን ይሆናል፤ አስፋው በንጋታው ይሞታል፡፡ አስፋውም ቀፎታል፡፡ በቅርቡ እንደሚሞት እንደታወቀው ያስታውቃል፡፡) ቁርሴን ከነ አስፋው ጋር በልቼ፣ አንድ አረቄ ጠጣሁ፡፡ አካሄዴ የተለመደ ነው፡፡ ጠዋት ቁርስ እበላለሁ፣ አረቄ እጠጣለሁ፣ ከዚያ ውሃ ያስፈልገኛል (ጠላ ወይ ድራፍት) ማለቴ ነው፡፡ ዛሬ ብር አለኝ፤ ድራፍት መጠጣት እችላለሁ፡፡

ወደ ቴሌ ባር ወረድኩ፡፡ በነገራችን ላይ በ dehydration እራስን ማጥፋት ይቻላል፤ በየእለቱ dehydrate የሚሆን ሰውነቴ ጠዋት ሁሌ ውሃ ይለኛል፡፡ ውሃ መጠጣት አልችልም፤ ጠላ እና ድራፍትን እንደውሃ ነው ሠውነቴ የሚጠቀማቸው፡፡ በ dehydration እራስን ማጥፋት ይቻላል፡፡ ከሰውነታችን ሰባ ከመቶው ውሃ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ አስራ አምስት በመቶ ብናጎል እንሞታለን፡፡ (ምናልባት ቀጣዩን ራሴን የማጥፋት ሙከራ የማደርገው በ dehydration ይሆን ይሆናል። ሌላም አማራጭ አለ፤ የከሰል ጭስ፤ ለምሳሌ ዘንድሮ ብቻ በከሰል ጭስ አዲስ አበባ ውስጥ አስራ አንድ ሰው ሞቷል፤ ስለዚህም አስብበታለሁ፡፡) ወደ ቴሌ ባር ሄደኩ፡፡ ውሃ ፍለጋ፡፡ የመጠጫ፣ የመጫወቻ፣ የመተከዣ፣ የመደንዘዣ፣ የማንበቢያ፣ የመፃፊያ ... የተለመደች ቦታ አለችኝ፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ልቀመጥ ስል እልፍ ብሎ ያለው ወንበር ላይ ተአምር አየሁ፡፡ ውብ ሴት! ሌላ ገለፃ አያስፈልግም፡፡ ውብ ሴት፡፡

የተቆጣች ፀይም ውብ ሴት! ከሰው ጋር ናት፡፡ ወይ ከባሏ ጋር፣ ወይ ከጓደኛዋ ጋር፣ ወይ ከፍቅረኛዋ ጋር ናት፡፡ በሱ ነው የተቆጣችው፤ እሱን ነው የምትቆጣው፡፡ የተለመደ ቦታዬን ትቼ እነሱ አጠገብ ያለውን ወንበር ስስብ አንድ እጅ አብሮኝ ወንበሩን ሳበ፡፡ ሁለታችንም ልጅቷን እያየናት ስለነበር አልተያየንም፡፡ ወንበሩን አጥብቄ ያዝኩት። ልጅዬው በልመና አይነት አየኝ፡፡ በቁጣ አየሁት፡፡ አይኑን ቢያንከራትት ልጅቷ አጠገብ ምንም ወንበር የለም፡፡ ፈልጎ ሊያገኝ የቻለው ልጅቷ ፊት ለፊት ራቅ ብሎ ያለ ወንበር ነው፡፡ ወደዚያ አመራ፡፡ ከዚያ ትታየዋለች፤ ትርቅበታለች እንጂ ትታየዋለች፡፡

ልክ ልጅዬው ወንበሩን ለቅቆልኝ ሊሄድ ሲል፡- ልጅቷ እንዲህ ስትል ሰማናት፡- “እንዴት እንደዛ ታደርጋለህ;! የገዛ እህቴን;! እራሴ አልጋ ላይ;!” ወንበር እየተሻማኝ የነበረው ሰው ከርቀት ልጅቷን ሊያሳየው የሚችለው ወንበር ሊያዝበት ሲሆን እየሮጠ ሄደ፡፡ እውነት እሮጧል፡፡ “እህስ;” አለችኝ አለም አስተናጋጇ፤ የምንኖርባት አለም ብታስጠላኝም ይህቺ አስተናጋጇ አለም ግን ደስ ትለኛለች፤ እወዳታለሁ፡፡ “ድራፍት፡፡” አለም ድራፍቱን ልታመጣ ሄደች፡፡ ፊልም ላይም፣ መጽሄት ላይም፣ ምድር ላይም ይህችን የተቆጣች ጠይም የምትመስል ቆንጆ አይቼ አላውቅም፡፡ የተናገረችውን ስሰማ ግን ማመን አቃተኝ፡፡ አሁን የገረመኝ አብሯት ያለው ሠው ነው፤ እሷ አይደለችም፡፡ ምን አይነት ጀግና፣ ወይ ሠይጣን፣ ወይ መልአክ ቢሆን ነው ይህቺን ሴት ትቶ አልጋዋ ላይ እህቷን የሚዳራው;! አሁን ደግሞ አብሯት ቁጭ ብሎ እያወራ ነው፡፡ አየሁት፡፡ ግድየለሽ ነው፤ የእግዚአብሔር ግድ የለሽነት ይታይበታል፡፡ እያጨሰ ነው፤ እንደ ሰይጣን ነው የሚያጨሰው፡፡ (ይቀጥላል)

Read 6145 times