Saturday, 21 September 2013 10:43

አንበሳ ግቢና የሰራተኛው አሰቃቂ ሞት

Written by 
Rate this item
(11 votes)

የአንበሶቹን ያህል ለሠራተኞቹ ጥንቃቄ አይደረግም - ሰራተኞቹ ቸልተኝነቱ ከቀጠለ ሌላም ሰው ሊሞት ይችላል - አስተያየት ሰጪዎች አደጋው የደረሰው አንበሶች በምግብ ስለተጐዱ አይደለም- ዋና ዳሬክተር ለአንበሳ ስጋ በዓመት ከ1.5ሚ ብር በላይ ወጪ ይደረጋል

             ባሳለፍነው ሰኞ ማለዳ ስድስት ኪሎ በሚገኘው አዲስ ዙ ፓርክ (አንበሳ ግቢ) ውስጥ በአንድ የግቢው ሰራተኛ ላይ የተከሰተው አስደንጋጭ አደጋና አሰቃቂ ህልፈተ ህይወት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በእለቱ ተራቸውን ጠብቀው የአንበሳውን ማደርያ ለማፅዳት ወደ ውስጥ የዘለቁት አቶ አበራ ሲሳይ የተባሉ ሰራተኛ፤ በጥቂት መዘነጋት አንበሳውን ወደ መዋያው አስገብተው በር ባለመዝጋታቸው፣ በአንበሳው ማጅራታቸውን ተይዘው፣ ለ20 ደቂቃ ያህል ሲሰቃዩ ቆይተው መሞታቸው እጅግ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን የሟች ባልደረባ አቶ ምትኩ ጭብሳ ይናገራሉ፡፡

ምንም እንኳን አደጋው “በጥቂት መዘነጋት” እንደደረሰ ቢነገርም ይህ አይነት አደጋ የመጀመርያው እንዳልሆነና የመጨረሻውም ሊሆን እንደማይችል ነው የአንበሳ ግቢ ሠራተኞች የሚናገሩት፡፡ ከዚህ በፊት በአንበሳ ተበልተው የሞቱ አንድ ሰራተኛ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ሰራተኞቹ፤ ተነክሰው ከሞት የተረፉም እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡ አሁን ባለው ቸልተኝነት ከቀጠለም ሌላ ሰው መሞቱ አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በ1940 ዓ.ም ለቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ፤ ከኢሊባቡር ጐሬና ከሲዳማ በመጡ አራት ትላልቅ እና ሶስት ደቦል አንበሶች የተመሰረተው አዲስ ዙ ፓርክ፤ ላለፉት 60 ዓመታት አንበሶችንና ሌሎች እንስሳትን አካቶ ለጐብኚዎች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለንጉሱ የመጡት እነዚህ ሰባት አንበሶች በጊዜ ሂደት በመራባት በአሁኑ ሰዓት በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩት አንበሶች ቁጥር 15 ደርሷል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ ሀይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሰረት፣ ጥሩነሽና እጅጋየሁ በሚሉ የታዋቂ ጀግኖች አትሌቶች ስም የተሰየሙ ሲሆን ሌሎቹም ላይሽ ተረፈ፣ ሰለሞን ጠንክር፣ መኮንን ተጋፋው፣ ወርቁ ገረመው፣ በሻዱ ጫላ፣ ቃኘው ወርቁ ወዘተ በሚል ስም ይጠራሉ፡፡ በተለይ ጠንክር የተባለው አንበሳ ከሁሉም አንጋፋው ሲሆን በ1984 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡

ቀነኒሳ በቀለ ወርቁ፣ ሀይሌ ገ/ስላሴ ወርቁና መሰረት ደፋር ወርቁ ወንድምና እህትና አንበሶች ናቸው፡፡ ወንድማማቾቹ ሀይሌና ቀነኒሳ በአንድ ማደሪያና መዋያ ቢያድጉም በጊዜ ሂደት ግን መስማማት አለመቻላቸው ብዙዎችን ያስጨንቅ እንደነበር የፓርኩ አስጐብኚ ይናገራሉ። በተለይ ቀነኒሳ ከወንድሙ ሀይሌ ጋር በየቀኑ መደባደብ ልማዱ ነበር፡፡ “በዚህም የተነሳ ሀይሌና ቀነኒሳን በተለያየ ኬጅ ውስጥ ለማዋልና ለማሳደር ግድ ሆኗል” ብለዋል - አቶ ምትኩ ጭብሳ። በነገራችን ላይ መጀመሪያ ከሞላ ጋር የመጣው ሉሉ የተባለው አንበሳ፤ በጃንሆይ የውሻ ስም የተሰየመ ሲሆን ሞላ የተባለው የመጀመርያው አንበሳም ሚስቱን በመግደሉ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት እንደተገደለ ይነገራል፡፡ የአንበሶቹ አያያዝ በአሁኑ ወቅት በግቢው ውስጥ የሚኖሩት አንበሶች የሚመገቡት ስጋ በቀጥታ ከቄራ ተመርምሮ የሚመጣ ሲሆን ለእያንዳንዱ አንበሳ በቀን ከ5-7 ኪሎ ንፁህ ስጋ ይቀርባል፡፡ ለአንድ ኪሎ ስጋ 55 ብር ከ20 ሳንቲም እንደሚወጣና በቀን እስከ 120 ኪሎ የሚደርስ ንፁህና የተመረመረ ስጋ እንደሚቀርብ የፓርኩ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሴ ክፍሎም ተናግረዋል፡፡

አንበሶቹ በግቢው ውስጥ የራሳቸው ቋሚ ሀኪም ያላቸው ሲሆን ለውስጥ ጥገኛ ተውሳኮች ከምግብ ጋር መድሀኒት እንደሚሰጣቸውና ምርመራም እንደሚደረግላቸው ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀውልናል፡፡ የአቶ አበራን በአንበሳው ተነክሶ መገደል ከአንበሶች በቂ ምግብ አለማግኘትና መጎሳቆል ጋር የሚያገናኙ ወገኖች እንዳሉ የተገለፀላቸው ዳይሬክተሩ፤ጉዳዩ መሰረተ ቢስ አሉባልታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ አንበሶቹ በአመጋገብና በጤና በኩል አንዳችም ጉድለት እንደሌለባቸው የገለፁት ዶ/ር ሙሴ፤ አቶ አበራ ላይ የደረሰው አደጋ ከአንበሶቹ ምግብ ማጣትና ጉስቁልና ጋር እንደማይገናኝና አንበሶቹ በተፈጥሯቸው መላመድ የማይችሉ በመሆናቸው እንዲሁም በሩ ባለመዘጋቱና ከአንበሳው ጋር ፊት ለፊት ስለተገናኙ ለአሰቃቂው የህልፈት አደጋ መዳረጋቸውን አብራርተዋል፡፡ የአንበሶችን የምግብ አቅርቦት በተመለከተም፣ “የዚህ ፓርክ ትልቁ ወጪ የአንበሶች ምግብ ነው፤ በአመት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ለስጋ ይወጣል።

ችግሩ የተፈጠረው አንበሳው ከማደሪያው ወደ መዋያው ከገባ በኋላ ሁለቱን ቦታዎች የሚያገናኘው በር ባለመዘጋቱ ነው፡፡ አንበሶች ምግብ አያገኙም ተጐሳቁለዋል እየተባለ የሚወራው ስህተት ነው” ብለዋል፡፡ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት የነበሩት የ52 ዓመቱ አቶ አበራ ሲሳይ፤ ጠንካራና ታታሪ ሰራተኛ እንደነበሩ የጠቆሙት ዶ/ር ሙሴ፤ ወደ መጋቢነት እና ጽዳት ሰራተኝነት ከገቡ አንድ አመት ቢሆናቸውም በግቢው ውስጥ በሌላ የስራ ዘርፍ ለረጅም አመታት መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ “በዚህ ግቢ ውስጥ ሰው በአንበሶች ሲገደል የመጀመርያው አይደለም፤ ከዚህ ቀደም የተነከሰ ሠራተኛ አለ፤ ታዲያ ይህን ለመከላከል የዚህ ግቢ ሃላፊዎች ለምን ቅድመ ዝግጅት አያደርጉም?” ሲሉ ይጠይቃሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጪ፡፡ በዚህ ቸልተኝነት ከቀጠለ ሌላም ሰው ሊሞት እንደሚችል ስጋታቸውን የገለፁት ሌላው የፓርኩ ሰራተኛ፤ ለግንባታ ሰራተኞች ሄልሜት እና ሌላ የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች የሚሰጡ ሲሆን ለአንበሳ መጋቢዎችና ጽዳት ሰራተኞች ግን ምንም አይነት መከላከያ እንደሌለ ተናግረዋል። “ሌላው ቀርቶ የዋና ገንዳ ባለባቸው ቦታዎች ህይወት አድን ሰራተኛ (Life saver) ይዘጋጃል” ያሉት እኚሁ ሰራተኛ፤ አንበሳን ከሚያክል እንስሳ ጋር ለሚሰሩ ግን ምንም አይነት አደጋ መከላከያ እንደሌለ ገልፀው፣ ህይወት አድን ሰራተኛ ቢኖር ኖሮ ባልደረባቸው ከሞት ሊተርፉ ይችሉ እንደነበር በቁጭት ተናግረዋል፡፡

“ደሞዛችን እንኳን ከ600 ብር አይበልጥም፤ እኔ እዚህ ግቢ መስራት ከጀመርኩ 10 ዓመት አልፎኛል፤ ስራው ከባድ ክፍያው ግን አነስተኛ ነው” ያሉት ሌላው የግቢው ሰራተኛ፤ መንግስትና የፓርኩ ሃላፊዎች የሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግና መሟላት ያለባቸውን ነገሮች በአስቸኳይ ማሟላት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ “ያለበለዚያ እኔ በአንበሳ ተንገላትቼ ስሞት ያየ ሌላ ሠራተኛ፣ ወደዚህ ግቢ ገብቶ ለመስራት እግሩን አያነሳም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ የሰራተኞቹን የህይወት ዋስትና በተመለከተ የፓርኩ ዳይሬክተር ሲናገሩ፤ “ስራው ከባድና ከአንበሳ ጋር የሚሰራ እንደመሆኑ ሁሉም ሰራተኞች ኢንሹራንስ መግባት አለባቸው” ያሉ ሲሆን ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢንሹራንሱ ፕሮሰስ ተጀምሯል ብለዋል፡፡ “አንበሳውን ገድሎም ቢሆን የስራ ባልደረባችንን ለማዳን ጥረት ተደርጐ ነበር” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ “ከዚያ በኋላ ሊመጡ የሚችሉትን አለም አቀፍ የእንስሳት መብት ጥያቄዎችና ሌሎች ጉዳዮችን እንመልሳቸው ነበር” ብለዋል፡፡ በፅዳትና በመጋቢነት ለሶስት አመታትን የሰሩት አቶ ምትኩ ጭብሳ፤ ከሌላ የስራ ዘርፍ ወደ መጋቢነት ሲዛወሩ የወሰዱት ስልጠና ስለመኖሩ ጠይቀናቸው፤ ስልጠና ሳይሆን በመ/ቤቱ የሚሰጡ መመሪያዎችና ማስጠንቀቂያዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ስራው ከአንበሳ ጋር የሚሰራና ህይወትን እስከማጣት ለሚያደርስ አደጋ የተጋለጠ በመሆኑ መዘናጋት እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

“ሁሌም በአዕምሯችን ስጋት መመላለስ አለበት፤ በንቃትና በጥንቃቄ የሚሰራ ስራ ነው፤ ከአንበሶች ጋር የሚውል ሰው ለሰከንድ እንኳን መዘናጋት የለበትም” ሲሉም ምክራቸውን ይለግሳሉ፤ አቶ ምትኩ፡፡ በተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችና ድረገፆች የአቶ አበራ በአንበሳ መገደል ሲዘገብ የሰነበተ ሲሆን “ቀነኒሳ መጋቢውን ገደለ” የሚሉ እና መሰል አዘጋገቦችን በተመለከተ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን መምህር “አዘጋገቡ ከሙያ ስነ-ምግባር እጅግ ያፈነገጠ ነው፤ ታዋቂውን አትሌት ቀነኒሳንም የሚያስከፋና በመልካም ዝናው ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ “በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚዘገቡ በርካታ ዘገባዎች ሙያው ከሚፈቅዳቸው አካሄዶች ያፈነገጡ ናቸው” ያሉት መምህሩ፤ ሙያው በባህሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ ሙያተኞቹ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት መስራት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ሌላው የግቢው ሰራተኛ የሆኑና ለ13 ዓመታት እንደሰሩ የገለፁ ግለሰብ “የአንበሶቹን ያህል ለእኛ ለሰዎች ጥንቃቄ አይደረግልንም” ያሉ ሲሆን የጓደኛቸው የአቶ አበራ አሟሟት ዘግናኝ እንደነበርና ነገ በራሳቸው ላይ ሊደርስ እንደሚችል ገልፀው፤ በጤና፣ በደሞዝና አደጋን በሚከላከሉ መሳሪያዎች ልንታገዝና መንግስት ከአቶ አበራ ሞት ትምህርት ወስዶ ሌሎች ሰራተኞችን ከአደጋ መታደግ አለበት ብለዋል፡፡

“ያለበለዚያ ግን አንበሶቹ ይወገዱ” ብለዋል - እኚሁ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰራተኛ፡፡ የአንበሶቹ ዝርያ ለየት ያለ መሆኑ ከጀርመኑ “ላይፕ ዚክ” እህት ከተማ ጋር በመተባበር በተካሄደ የደም ምርመራ መረጋገጡን ዶ/ር ሙሴ ይናገራሉ። በኬጅ ውስጥ የሚኖር አንበሳ ከ20-25 ዓመት የመኖር እድል እንዳለው የገለፁት ባለሙያዎች፤ በዱር የሚኖር አንበሳ ግን በአማካኝ 14 ዓመት ብቻ በህይወት እንደሚቆይ ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱም በጫካ የሚኖር እንስሳ ምግብ ለማግኘት ብዙ ከመድከሙም በላይ ከሌሎች ጋር የሚያደርገው ተጋድሎ እድሜውን ያሳጥረዋል፡፡ በኬጅ የሚኖረው እድሜው የተሻለ የሚሆነው የተመረመረ ምግብ ከማግኘቱም በላይ ጤንነቱ በባለሙያ ክትትል ይደረግለታል፣ ከዚያም በላይ ከየትኛውም አቅጣጫ ትግልና ድካም አይኖርበትም ይላሉ- ባለሙያዎቹ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ ዙ ፓርክ ውስጥ 8 ወንድና ሴት አንበሶች፣ አምባራይሌ የተባለ እንስሳ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ኤሊዎች፣ ንስር፣ ጦጣና የተለያዩ አዕዋፋት እንደሚኖሩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባለፈው ሰኞ በአንበሳ ተነክሰው ለህልፈት የተዳረጉት ሟች አቶ አበራ ሲሳይ፤ ባለፈው ማክሰኞ በገርጂ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፅሟል፡፡ ሰበተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎችና ድረገፆች የአቶ አበራ በአንበሳ መገደል ሲዘገብ የሰነበተ ሲሆን “ቀነኒሳ መጋቢውን ገደለ” የሚሉ እና መሰል አዘጋገቦችን በተመለከተ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን መምህር “አዘጋገቡ ከሙያ ስነ-ምግባር እጅግ ያፈነገጠ ነው፤ ታዋቂውን አትሌት ቀነኒሳንም የሚያስከፋና በመልካም ዝናው ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል ነው” ሲሉ ተችተዋል፡፡ “በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚዘገቡ በርካታ ዘገባዎች ሙያው ከሚፈቅዳቸው አካሄዶች ያፈነገጡ ናቸው” ያሉት መምህሩ፤ ሙያው በባህሪው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ ሙያተኞቹ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት መስራት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

Read 8952 times