Saturday, 21 September 2013 10:37

የ“ሴቶች ለምን አይቀድሱም?”

Written by  ካሌብ ንጉሴ
Rate this item
(3 votes)

ጥያቄ አልተመለሰም፤ አቶ መልካሙ ዳር ዳሩን አይዙሩ!

              “ሴቶች ለምን አይቀድሱም?” በሚል ርዕስ ነሐሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም በዚሁ ጋዜጣ ላይ ለወጣ ጽሑፌ “መልካሙ ተክሌ” እና “አንዱዓለም ናስር” የተባሉ ጸሐፊዎች መልስ ነው ያሉትን ፈጥነው በመላካቸው ላደንቃቸው እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም ሁለቱም ሰዎች ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም በታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ሲጽፉ ሃሳቤን የመደገፍም የመንቀፍም አዝማሚያ በማየቴ ጉዳዩ ጥርት ብሎ እስኪታወቅ ድረስ መጻፍ ያስፈልጋል ብዬ አመንሁ፡፡ አንባቢያን ግራ እንዳይጋቡ ሁለቱ ጸሐፊዎች ያተኮሩባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በየተራ እያነሳሁ መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ የአቶ መልካሙ ተክሌን ላስቀድም፡፡

አቶ መልካሙ ጽሑፋቸውን ሾርኔ በሚመስል ነገር ጀምረው የመጀመሪያዋ በደለኛ ሴትሔዋንመሆንዋን ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ ምንም እንኳ ይህን አባባል እስኪሰለቸን የሰማነውና የምንሰማው ዘወትራዊ ቃል ቢሆንም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ደፈር ያሉ ጥያቄዎች ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ የእውቀት መነሻ ጥያቄ ነዋ! [“አዳምና ሔዋን ተፈጠሩ” በተባለበት ወቅት ከሁለቱ ሌላ ሰብአዊ ፍጡር አልነበረም፡፡ እነሱም የተማሩ አልነበሩም፡፡ ታዲያ ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መጣሷን ማን ቆሞ ተመልክቶ ነው እንዲህ ዘላለም ስትወቀስ የምትኖረው? ወንድ በነበረው አስተሳሰብ መሠረት ችግሮቹን ሁሉ በሴቶች ላይ የመጫን አባዜ ተጠናውቶት ይሆን ይህ አይነት አስተምሕሮ ሊቀጥል የቻለው? ኦሪት ዘፍጥረትን የጻፈውስ ማን ነው? ሴት ወይስ ወንድ? ወይስ ፈጣሪ ጻፈው? ሔዋን በደለች ብንል እንኳ ከአዳም ይልቅ እውቀትን ቀድማ የሻተች ናትና ልትወቀስ ይገባል? በእውቀት ላይ የተመሠረተ መልስ ያሻው ይመስለኛል፡፡ “ቅዱሳት ስለሆኑ፤ ሴቶች መቀደስ አለባቸው ብሎ መሟገት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም” ሲሉም አቶ መልካሙ ሃሳቤን ለመተቸት ሞክረዋል። ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች እንዳይቀድሱ የሚከለክልበትን ህግ አላሳዩንም፡፡

ያ ቢሆን ኖሮ በሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሁሉ ሴቶች እንዲቀድሱ አይፈቀድም ነበር፤ ለሃሳባቸው ክብደትም እጅ በነሳኋቸው ነበር፡፡ ግን ትችታቸው “ሾላ በድፍኑ” ሆነብኝ፡፡ እንዲያውም “ልክ መውለድ ለሴቶች እንደ ተሰጠ ሁሉ ቅዳሴ የወንዶች ድርሻ ነው፤ ቅዳሴ ተፈጥሯዊ የሥራ ክፍፍል ነው” ብለው የሌለና የማይመስል ነገር በጽሑፋቸው አስፍረዋል፡፡ እዚህ ላይ ነው አቶ መልካሙን “እንግባባ እንጂ” የምላቸው፤ አርግዞ መውለድንና ማገልገልን ምን አገናኛቸው? “ሕግን ያወጣው አምላከ እስራኤል እግዚብሔር እንጂ ሙሴ አይደለም” ሲሉም አቶ መልካሙ ለሙሴ ጥብቅና ለመቆም ሞክረዋል፡፡ በመሠረቱ እግዚብሔር ለሙሴ እንደሰጠው የሚታመነው አስርቱን ትእዛዛት ብቻ ነው - በጽላቱ ላይ ጽፎ የሰጠው፡፡ (ኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ 20) ሕግጋቱን ሁሉ እግዚአብሔር ለሙሴ ሰጠው ብለን ብንቀበል እንኳ ዛሬ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ጉዳዮች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ባሪያ እንደ እንስሳት እንዲሸጥ እንዲለወጥ (ዘጸአት 21፡1-11) የሙሴ ሕግ ይፈቅድ ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መከራከር አስፈላጊ አይሆንም፡፡

በጊዜው ሙሴ ሕግ አድርጐ አወጣው፤ እስከ 20ኛው መቶ ክ.ዘመን ድረስ ይህ ዘግናኝ ድርጊት በመላ ዓለም ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል፡፡ የማህበራዊ ህግጋት ባህርይ ከተፈጥሮ ህግጋት የሚለየው በሰዎች ተዘጋጅቶና ሥራ ላይ ውሎ መልሶ በሰዎች መሻሻል መቻሉ ነው፡፡ አንድ ሰብአዊ ሕግ ለሰዎች ህይወት ይጠቅማል ተብሎ ይዘጋጃል፤ እስከተወሰነ ጊዜ ሲያገለግል ይቆይና አላሰራ ሲል ይሻሻላል፤ ወይም ከነአካቴው ሊሰረዝ ይችላል። የተፈጥሮ ህግ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ የጨለማና ብርሃን፣ የሞትና ሕይወት፣ የክረምትና በጋ ወዘተ ህግጋት በሰው ሊሻሻሉ ወይም ሊቀየሩ አይችሉም፡፡ በመሆኑም የኦሪት ህግጋት የእግዚአብሔር ህግጋት ቢሆኑ ኖሮ፣ ዛሬም ሰው እንደ እንስሳት እንዲሸጥ፣ ዐይን ያጠፋ ዓይኑ እንዲጠፋ፣ የገደለ ሁሉ እንዲሞት፣ እናት አባቱን የሰደበ በሞት እንዲቀጣ፣ ዝሙት የፈፀመም በድንጋይ ተወግሮ እንደሚሞት አግባብ ነበር፡፡

እነዚህና መሰል ጉዳዮች ወንጀልነት ቢኖራቸውም ዛሬ ሙሴ ይቀጣበት በነበረው ዘግናኝ መንገድ አያስቀጡም፡፡ እንዲያውም እንደ ዝሙት ያሉት አንዳንድ ጉዳዮችማ የመንግሥታት እውቅና ሁሉ ተሰጥቷቸው የገቢ ማስገኛ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ ታዲያ አቶ መልካሙ ዛሬም የኦሪት ህግጋት ተግባራዊ መደረግ አለባቸው እያሉን ይሆን? መቸም በኦሪትኛ እንደማያስቡ እርግጠኛ ነኝ፡፡ “ቅዳሴ የመብትና የዲሞክራሲ ጉዳይ ሳይሆን የአገልግሎት ጉዳይ ነው” ሲሉም አቶ መልካሙ ድፍን ያለ መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ እኔ በመነሻ ጽሑፌ ላይ የገለጽሁት “ፍሬ ነገሬ ነገረ ሃይማኖት ነው” ብዬ ነበር፡፡ ምኑን ከምን ሊያነካኩት እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም፡፡ ማነካካት ደግሞ ጤናማ መንገድ አይመስለኝም፡፡ ግን ወዳጄ ቅዳሴ የአገልግሎት ጉዳይ ከሆነ የእኔም ጥያቄ እኮ ይኸው ነው፡፡ ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ በሌሎች አብያተክርስቲያንም እያገለገሉ ነው፤ እኛ አገርስ ለምን አያገለግሉም ነው፡፡

አቶ መልካሙ እንኳንስ የእኔን ጽሑፍ የራስዎንም ልብ አላሉትም እንጂ መጀመሪያ ላይኮ “ቅዳሴ የተፈጥሮ ድልድል ነው” ብለው ነበር፡፡ መልሰው ደግሞ “መብት አይደለም አገልግሎት ነው” አሉ፡፡ በእርስዎ ሃሳብ ለተወሰኑ ሴኮንዶች ልመራና መቀደስ የተፈጥሮ ስጦታ ከሆነ የመብት ጥያቄም ሊነሳ ግድ ይላል፡፡ ግን እነ አዳም “ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ቀደሱ” የሚል ማስረጃ ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ቅዳሴ የተጀመረውም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው። ተፈጥሮአዊ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ወይም ከፍጥረተ ሰብእ ጀምሮ መከናወን ነበረበት፡፡ “አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስራ ሁለት ሐዋርያት ሲመርጥ ሁሉም ወንዶች ነበሩ (ሐዋርያነት የጾታ ጉዳይ ባይሆንም) ሰላሳ ስድስት ቅዱሳት እንስትም መርጧል ከሴቶች” ሲሉ የሰጡት ሃሳብ ደግሞ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አንዴ ሐዋርያት ወንዶች ነበሩ፤ እንደ ገና ደግሞ 36 ቅዱሳት አንስትንም መርጧል ብሎ ማደናገር ምን ይሉት ፈሊጥ ነው፡፡ “ቅዱሳት” መባላቸው የሚያሳየው ትልቅ ጉዳይ አለ፡፡ በኢየሱስ መመረጣቸውና ለሐዋርያዊ አገልግሎት ብቁ በመሆናቸው ነው፡፡

ታዲያ በኢየሱስ የተመረጡ መሆናቸውን የሚቀበሉ ከሆነ አቶ መልካሙ ሰው ሰራሹ ቤተ መቅደስ ነው ወይስ ኢየሱስ ይበልጥ ቅዱሱ? “ማርያም መቅደላዊት ረቡኒ (መምህር) ብላ ስትጠጋው … አትንኪኝ ብሏታል” ሲሉ የተረኩልን ጉዳይም የተዛባ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “ማርያም መግደላዊት” እንጂ “መቅደላዊት” አትባልም። መቅደላ ያለው እኛ አገር ደቡብ ወሎ ምዕራብ ወረዳዎች ውስጥ ነው፡፡ መግደላዊት የኖረችው ደግሞ ከገሊላ አካባቢ “መጌደል” ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው፡፡ በመሠረቱ ማርያም መግደላዊት ከትንሣኤው በኋላ ከሐዋርያቱም ሆነ ከሌሎች ቅዱሳት አንስት ቀድሞ በአትክልት ቦታ- ኢየሱስ የተገለጠላት ቅድስት ሴት ናት፡፡ “አትንኪኝ” ያላትም ከማረጉ በፊት ማንም እንዳይነካው መለኮታዊ ሃይሉ ስለወሰነ እንጂ ማርያም መግደላዊት ቅድስና፣ ንጽህና ጐድሏት አይደለም፡፡ “ካልዳሰስሁ አላምንም” ያለው ቶማስ እጁ የተኮማተረውም ትዕዛዙን አላከብር ብሎ ነው፡፡

ስለሆነም ሴቶችም ሆኑ ወንዶች እንዳይነኩት ፈለገ ነው የሚባለው ወይስ “ሴቶችን ከልክሎ ለወንዶቹ ፈቀደ?” ክብደት ያጣ መከራከሪያ ነው፡፡ እስዋን ከልክሎ ቶማስ ቢዳስሰው ኖሮና በጤናው ቢቀር አባባልዎ ትክክል ሊሆን ይችል ነበር፡፡ በነገራችን ላይ አቶ መልካሙ የቅዳሴን ሥርዓት የደነገጉት ወንዶች ተሰብስበው እንጂ እግዚአብሔር ወይም እርስዎ እንዳሉት የተፈጥሮ ድልድል አይደለም። በአንድ ወቅት ስብሰባ ላይ የተቀመጡ ጳጳሳት፤ ከኢትዮጵያ ፓትርያርክ እንዳይሾም ህግ አቁመው ነበር፡፡ እስከ 1950ዎቹ ድረስ ይህ ህግ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፤ ጳጳሳት ከግብጽ እየመጡ የሁከት ስራ ጭምር ሲያከናውኑ እንደነበር መገንዘብ ያለብዎ ይመስለኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ጳጳስ እንዳይሾም የሚከለክለው ህግ በአባ ባስልዮስ ሹመት ምክንያት ውድቅ ተደርጓል፡፡

የቅዳሴ ሥርዓትም ልክ እንደ ፓትርያርክነቱ ሁሉ ሰው ሰራሽ ህግ ነው፡፡ ለዚህም ሲኖዶስንና ፍትሐ ነገሥቱን ቢያዩ እውነቱን ይገነዘቡታል፤ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ሴት እንዳትቀድስ የሚያግድ አንድም አንቀጽ አያገኙም ወዳጄ! “ኢየሱስ ምስጢረ መለኮቱን በደብረ ታቦር ሲገልጥ ሴቶች አልነበሩም” በማለት ሊያስረዱን የደከሙበት ነጥብም ጭብጥ አይሞላም፡፡ ደጋግሜ እንደገለጽሁት ትንሣኤውን ቅዱሳት አንስት እንዲያዩ ሲመረጡ አንድም ሐዋርያ አልነበረም፡፡ ታዲያ ሴቶች ከወንዶች ስለሚበልጡ? ወይስ ኢየሱስ ተአምራቱን ሊገልጥለት ለፈለገው ብቻ ስላደረገ? መከራከሪያዎን ደግመው ቢያዩት ከስሜት ይልቅ ሚዛናዊነት ጠቃሚ መሆኑን ሊገነዘቡ ይችላሉ፡፡

ከኢየሩሳሌም አጠገብ ከሚገኘውና “ቢታንያ” ተብሎ በሚታወቀው ቦታ ነዋሪ የነበረችው የማርታና የአልአዛር እህት ሌላዋ ማርያምንና ቤተሰቦችዋን ኢየሱስ ወደቤታቸው እየሄደ ይጠይቃቸው ነበር፡፡ ቃሉን ስለሰማችም ኢየሱስ አመስግኗታል (ሉቃስ 10፡39-42) ወንድሟ አልአዛር ከሙታን በተነሳ ጊዜም ከኢየሱስ ጋር በሰፊው ተነጋግራለች (ዮሐንስ 11)፡፡ ኢየሱስ እንደሚሞት ስለተረዳችና በጣም ትወደውም ስለነበር የናርዶስ ሽቱ እግሩን ቀባችው (ዮሐንስ 12፡1-8) የታናሹ ያዕቆብና የዮሳም እናት ማርያም ለክርስቶስ ስቅለትና መቀበር ምስክር ነበረች፡፡ (ማር. 15፡40-47፤ 16፡1፤ ሉቃስ 24፡10) ማርያም የቀለዮጳ ሚስትም ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ከመስቀሉ አጠገብ ቆማ ነበር (ዮሐንስ 19፡25)፡፡ ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም አቶ መልካሙ ጌታ የፈቀደውን ያደርጋል እንጂ አንድን ተአምር ሲፈጽም የግድ የጾታ ስብጥር ያስፈልጋል አላለም፡፡ በደብረ ታቦር መለኮቱን ሲገልጥ ከነቢያትም ከሐዋርያትም ለተወሰኑት ታየ እንጂ ለጠቅላላው ነቢያትና ሐዋርያት አልተከሰተም፡፡

በኦሪት ዘመን ሐናን የመሰሉ በርካታ ሴት ነቢያት እንደነበሩም አይዘንጉ፤ “የእግዚአብሔር ወኪል ነበር” ያሉትን ሙሴን ከባህር ላይ አንስታ ያሳደገችው ሴት መሆኗንም አይዘንጉ፤ በቅዳሴ ሴቶቹን ማራቅ የተጀመረው ወንጌል ከተሰበከ ወዲህ ነው፡፡ “አንዱዓለም ናስር” የተባሉት ጸሐፊ ባነሷቸው ነጥቦች፤ በተለይ የወር አበባን አስመልክቶ ባቀረቧቸው መከራከሪያዎች ላይ በአብዛኛው እስማማለሁ፡፡ ሆኖም አንድ የዘለሉት ዋና ጉዳይ አለ። “ሴቶች ለምን አይቀድሱም?” ለተባለው ጥያቄ ቀጥ ያለ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ልክ እንደ ወር አበባው ሁሉ ሴቶች ቢቀድሱ ምን ችግር (ካለ) ሊፈጠር እንደሚችል፤ ሳይንሳዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ጥቅምና ጉዳት ካለውም እንዲሁ መረዳት እንችል ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ የወር አበባ በኦሪት ዘመን የርኩሰት ምልክት እንደ ነበር ከክርስቶስ ልደት በኋላ ግን የርኩሰት ምልክትነቱ እንደ ቀረ፣ ሆኖም የወንዴ ዘር ካላገኘና የሚወጣ ከሆነ እድፍ እንደሚሆን የገለጹልን ጠቃሚ ሐሳብ ይመስለኛል፡፡ ግን የወር አበባ ጊዜያቸው ሳይደርስ፣ ወይም ከወር አበባቸው በኋላ ለምን አይቀድሱም? ርኩሰት አይደሉማ! እድፍ ከሆነ በውሃ ይነፃላ! እንወያይ፡፡

Read 3484 times