Saturday, 21 September 2013 10:28

የአዳማ ጉዞ ማስታወሻ!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(7 votes)

ማህደረ-ማህበራት “አንኳኩ ይከፈትላችኋል …

” “ኧረ ናዝሬት ናዝሬት፤ ረባዳው መሬት

ታበቅያለሽ አሉ፣ ሸጋ እንደ ሠንበሌጥ”

መምህር ምፅላለ-ድንግል ሙሉነህ

የዛሬው ትረካዬን እንደ መግቢያ ቁጠሩት፡፡

ሰሞኑን የተዟዟርኩት ደብረዘይት፣ አዳማ፣ እና አዋሳ ከዚያም ሻሸመኔ (አጄ) ነው፡፡ እንደተለመደው መንገድ ላይ ያጋጠመኝን ሁነት፣ ሰው፣ ተውኔትና በምናቤ የተቀረፀውን ስዕል ሁሉ ልተክርላችሁ አስቤያለሁ፡፡ በነዚህ ቦታዎች ብቻ የምወሰንም እንዳይመስላችሁ፡፡ ገና ደብረ-ብርሃን፣ ድሬዳዋ፣ ባሕር ዳር እና ዐውራምባ ድረስ እየተጓዝኩ የገጠመኝን ሁሉ፣ በራሴ ነፃነትና አካሄድ እተርካለሁ። ይህን ሁሉ እንድፈፅም ያስቻለኝን “የእየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅትን (JECCDO) አመሰግናለሁ፡፡ (በጉዞዬ ውስጥ ይህ ድርጅት ምን አረገ፣ ከማን ጋር ምን ሠራ? ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችስ ጋር ምን ምን ፈፀመ? ማለቴ አይቀርም) የጉዞዬን ማስታወሻ ለሶስት ወር በተከታታይ እተርክላችኋለሁ፡፡ መጓዝ ማወቅ ነው ብያለሁ - “የእኛ ሰው በአሜሪካን” ስፅፍ፡፡

አሁንም እላለሁ፡፡ ምናልባት የምጨምረው ነገር ቢኖር፤ መጓዝ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማሳወቅም ነው፤ የሚለው ነው፡፡ የናዝሬት ልጅ ነኝ - የአዳማ፡፡ እኛ ልጅ ሆነን በናዝሬት እጅግ ታዋቂ የሆነውና አንጋፋው ዕድር የአቶ ዓለሙ ወርቁ ዕድር መሆኑን ማንም ጅል አይስተውም፡፡ የዓለሙ ወርቁን ዕድር ያለዋዛ አላነሳሁትም። አንጋፋ ዕድር ነው፡፡ የአገር ጧሪ ቀባሪ ነው፡፡ የሚያውሰው ድንኳን፣ ሳህንና የብረት ኩባያው፣ አጋፋሪው፣ የዕድሩ ዳኛ፣ ሥርዓቱ፣ መቀጮው … ብዙው ነገሩ ዛሬም ውል ይለኛል፡፡ ድፍን ናዝሬት (አዳማ) አንቱ ያለው ዕድር ነው፡፡ እንደዚያ ዓይነቱ ዕድር ዛሬ ኋላ ቀር ነው ሲሉ ስሰማ ደንገጥ እላለሁ፡፡

የዛሬው የናዝሬት ጉዞዬን ልዩ የሚያደርገው፤ ያንን እኔ የማውቀውን ታላቅ ዕድር የሚበልጥ እጅግ ግዙፍ የዕድሮች ኅብረት አለ መባልን ሰምቼ የሚመለከታቸውን ሰዎች ላናግር መምጣቴ ነው፡፡ “የናዝሬት ልጅ ነኝ” አልኩት፤ ገና ስንተዋወቅ፡፡ “እኔም እዚሁ ነኝ” አለኝ፡፡ ይሄ ናዝሬት (አዳማ) ያገኘሁት ሰው ጠይም ነው፡፡ ረጅም ነው፤ መረመንጅ፡፡ የዱሮ ክቡር ዘበኛ ምልምል የመሰለ ቁመና ያለው፡፡ ዱሮ እኛ ሰቀቀሎ የምንለው ዛሬ 01 ቀበሌ የሚባለው ውስጥ ነው የተገናኘነው።

“የእንረዳዳ የዕድሮች ማኅበር” የሚባለው ቅፅር ግቢ ነው፡፡ ይሄ ሰው ከእኔ ላቅ ያለ ቁመትና ግዝፈት ይኑረው እንጂ ሲናገር ማራኪና አንደበተ - ቀና ነው፡፡ ዱሮ ደስኳሪ፣ ተናጋሪ የምንለው ዓይነት ነው፡፡ “እኔ ታምራት አስፋው ነኝ!” አለ፤ ኩራት ባለው፣ ግን ሣሣ ባለ ቅላፄ፡፡ ለስብሰባ የተዘጋጀ በሚመስል፣ ጠረጴዛና ስምንት ዘጠኝ ወንበሮች ያሉት ቦታ በጣም ተቀራርበን ተቀምጠን ነው የምናወራው፡፡ “ከአፄ ገላውዴዎስ ት/ቤት “አማርኛ አስተማሪያችንን ጋሽ ምፅላለን ታስታውሳለህ?” “ምፅላለማ አሁንም ወዳጄ ነው፡፡ ይገርምሃል ቁልጭ እንዳለ አለ!” “ዕውነትክን ነው? እኔ እሱን የማስታውስባት አንዲት የግጥም ስንኝ አለች፡- “ኧረ ናዝሬት ናዝሬት፣ ረባዳው መሬት ታበቅያለሽ አሉ፣ ሸጋ እንደሠንበሌጥ!” ተሳሳቅን፡፡ ስመ-ጥሩውን መምህራችንን በደስታ አስታወስነው፡፡

“እስቲ ስለኃላፊነትህ አውራኝ?” አልኩት፡፡ “የእንረዳዳ የዕድሮች ማህበር ሰብሳቢ ዳኛ ነኝ” ያው እኔ መቼም ከአቶ ዓለሙ ወርቁ ወዲያ ዕዳር ላሣር ነው የምል ነኝና ስለ ዱሮ ዕድሮች አነሳሁለት፡፡ “ያኛው የመሠረት ይሁን እንጂ ኋላቀር ነው፡፡ የሞተ - መቅበር፣ ማስተዛዘን፣ ድንኳን መስጠት ወዘተ ነው፡፡ “የእኛ ይለያል!” አለ ኮራ ባለ ቅላፄ፡፡ “በል እንዴት እንደምትለዩ ከዱሮው እድር (traditional) ግለጽልኝ?” አልኩት፡፡ “እዚህ ሠፈር ዕድር ውስጥ አመራር ነበርኩ። በዛን ወቅት ኤች አይ ቪ በጣም ተስፋፍቶ ነበር። ወላጅ እናት፣ ወላጅ አባት ይሞታል፡፡ ልጆች ሰብሳቢ የላቸውም፡፡ ለችግር ተጋለጡ፡፡ እነዚህ ልጆች ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ነው? አልን፡፡ የኛስ ሚና ምን መሆን አለብን? አልን፡፡ እንደራሳችን ልጆች አየናቸውና አዘንን፡፡ ሰቀቀን፡፡ (ታምራት ዛሬ 69 ዓመቱ ነው፡፡ የልጆች አባት ነው፡፡) የወላጅ አልባዎቹን ህፃናት ነገር አነሳንና ተወያየንበት፡፡

“በጋራ እነዚህን ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት ሊወሰድ ይገባል” አልን፡፡ ተስማማን፡፡ በዚህ መሠረት ለየዕድሩ አባላት የማስረዳት፣ የማሳመን ተግባር አስፈለገን፡፡ በነበረው በጥንቱ የእድር አደረጃጀት ሳይሆን ለየት ያለ ዓላማ የያዘ የዕድር ሂደት ነው፡፡ ዓላማችንን ግልጽ አርገን፣ ራዕያችንን ግልጽ አርገን፣ ተልዕኳችንን ግልጽ አርገን መተማመን ላይ ደረስን፡፡ እያንዳንዱ ዕድር በተናጠል የሚሠራው ሥራም መሆን የለበትም፤ አልን፡፡ አሥራ ሁለት ዕድሮችን አቀናጀን! አመራሩ አምኖበታል - አባሉም ማመን አለበት ተባባልን፡፡ መድረኮች ፈጠርን፤ እያንዳንዱ ዕድር 300፣ 400 አባላት አሉትና የማሳመን ሥራ ሠራን (awareness) ይሄ ችግር የእኛው ነው! ችግሩን ማቃለል ያለበት ሌላ አካል ሳይሆን እኛው ነን፤ አልን! ከዚያ በኋላ ከጠቅላላ ጉባዔው፣ ከህዝቡ፣ ይሁንታ አገኘን፡፡

ፕሮጄክት ዲዛይናችንን ቀረጽን፡፡ ህጋዊነት እንዲላበስ አደረግን፡፡ ከዛ ምኑ ቅጡ!...” ታምራት ሲናገር በስሜት ተጥለቅልቆ ነው። አሁን ድፍረቱ ሳይሆን ዕውነቱ ነው ፊቱ ላይ እያበራ የሚታየው፡፡ በረድ ይበል ብዬ፤ “ይሄ ማለት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ነው?” አልኩት፡፡ “በትክክል! ከ1996 - እስከ 99ማለት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሥራ ስንሰራ የከተማ መስተዳድሩንም፣ የሆስፒታል አኪሞችንም፣ መድረክ ላይ እየጋበዝን እንዲናገሩ አድርገናል፡፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሠራተኞችን ጋብዘናል፡፡ ሁኔታው በመንግሥትም በህዝብም ፋይዳው ምን እንደሆነ ግንዛቤ አስጨብጠናል፡፡ አየህ ብቻችንን መሥራት አንችልም

1ኛ/ ህብረተሰቡን ለማንቀሳቀስ ከመንግስት ጋር ጥሩ የሆነ የሥራ ግንኙነት መፍጠር አለብን

2ኛ/ ከግብረ ሠናይ ድርጅቶች ለምሳሌ እንደ የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ጄክዶ/Jeccdol)፣ ፎረም ኦን ስትሪት ቺልድረን፣ አክሽን የባለሙያዎች ማህበር፣ ኸልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ወዘተ ዓይነቶቹ ጋር ተቀራርበን፣ ተጣጥመን መሥራት አለብን፡፡

3ኛ/ ከባለሀብቶች፣ ከዕምነት ተቋሞች ጋር ወዘተ አብረን ለመሥራት ሙሉ ግንዛቤ ወስደናል፡፡” “ከዛስ ምን አረጋችሁ? “ከዛማ በር የማንኳኳት ሥራ ነው የቀጠልነው። አንኳኩ ይከፈትላችኋል! እሹ ታገኛላችሁ!” ይላላ መጽሐፉ፡፡ በር የማንኳኳትና ዓላማችንን የማስረዳቱን ሥራ ተያያዝነው፡፡ ለየድርጅቱ፣ ለየተቋሙ፣ ለየባለሀብቱ አስረዳን፡፡ በሩ ተከፈተ! ብዙ ድጋፍ አገኘን! ሥራው እያደገ መጣ፡፡ ሥራ ክፍፍሉም በዛው መጠን ሰፋ፡፡ “መንግሥትስ እንዴት ነው? መቼም ከዕድሮች ጋር የመሥራት ፍላጐት ሳይኖረው አይቀርም?” “መጠርጠሩስ! እጅግ እጅግ ከፍተኛ ትብብር ነው ያደረገልን፡፡

አባዱላን የመሰለ ባለሥልጣን ሁለቴ ጠርተናቸው ሁለቴ ነው የመጡት፡፡ ትልቅ ድጋፍ ነው የሰጡን፡፡” “የመንግስት መሥሪያ ቤቶች በራቸው ክፍት አይደለም የሚባለውስ?” “ለእኛ? የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በራቸው ብቻ ሳይሆን ልባቸውም ክፍት ነው፣ ነው የምንለው። ዕውነትም ክፍት ነው፡፡ እናንኳኳለን፤ እንገባለን፤ እናገኛለን! ዓላማችን ግልጽ ነው - ህፃናትንና አረጋውያንን መርዳት! እነዚህ እንዲረዱ የማይፈልግ ማነው?” አንኳኩ ይከፈትላችኋል! ነው፡፡ “አስረድተን ይሳካልናል፡፡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይም አስተያየት እንድንሰጥ ይጋብዙናል። ጥሩ ግብብ አለን፡፡ ይሄን የ01 ቀበሌ ጽ/ቤትኮ እንድንሠራበት በነፃ ነው የተሰጠን፡፡” “መርሆዎቻችሁስ፣ መሪ መፈክሮቻችሁ ምን ይመስላሉ?” ግድግዳው ላይ የተለጠፉትን እይ:- “ያገሩን ሠርዶ ባገሩ በሬ!” “ድር ቢያብር አምበሳ ያሥር!” “ጋን በጠጠር ይደገፋል!” “50 ሎሚ ላንድ ሰው ሸክሙ፣ ለ50 ሰው ጌጡ!” “ዋናው ነገር ግን “አንኳኩ ይከፈትላችኋል” ነው” አለኝ በግርማ - ሞገስ፡፡ (ዝርዝሩንና ውጤቱን ሳምንት እናያለን)

Read 2952 times