Saturday, 21 September 2013 10:34

የ‘ፌስቡክ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ስሙኝማ…‘የፌስቡክ ሪቮሉሽን’ በአጠቃላይ ‘ፍሬንድ በፍሬንድ’ አደረገን አይደል! ወዳጅ እያጣን በእድርና እቁብ እንኳን መግባት ያቃተን ሁሉ ዕድሜ ለ‘ፌስቡክ’! ለምሳሌ አንዳንዱ፣ የሰፈሩ ህዝብ ሁሉ ልጆቹን ከእሱ ጋር እንዳይገጥሙ ስሙ እየተጠቀሰ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥበት አይነት አለላችሁ፡፡ “አንተ ልጅ ከእሱ ጋር ትገጥምና ነግሬያለሁ። የስንት ሰዎችን ልጅ ያበላሸ ነው…” ወይም ደግሞ “አጠገቡ ድርሽ ትልና ውርድ ከራሴ፡፡ የእሱ ቤተሰቦቹ እንደሆኑ መተተኞች ናቸው፣ ልጄን ፉዞ እንዳያደርጉብኝ” ይባላል፡፡ እናላችሁ… ይህ የአምስት እድር ሰው በጠቅላላ… አለ አይደል… ‘እንትን የነካው እንጨት’ ያደረጉት ሰው በፌስቡክ ስንት ‘ፍሬንድስ’ ቢኖሩት ጥሩ ነው…ሦስት ሺህ አምስት መቶ! ይሄኔ እኮ በቱ ተዉአቸው፣ ድሮም ቢሆን ሀበሻ ምቀኛ፡፡

እኔ እንደሁ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ፍሬንዶች አሉኝ…” ብሎ ቤተሰብ ጉባኤ ላይ ይፎክር ይሆናል፡፡ ደግሞላችሁ…ይቺ ‘ላይክ’ የምትባል ነገር አለች። እናላችሁ… “እግሮቿን አይቼ ነው የወደድኳት...” ብሎ ነገር የለ… “ቁመናው ደስ ሲል…” ብሎ ነገር የለ… (“እጥረቱ ደስ ሲል” የሚል የ‘ፌስቡክ ግሩፕ’ ሲቋቋም አስገቡኝማ!)…በቃ ‘ላይክ’ የምትለዋን ጠቅ በማድረግ ‘መውደድ’ ይቻላል፡፡ ታላላቆቹ መጻሕፍት ላይ ‘ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ… ምናምን የሚሉ ነገሮች አሉ። እናላችሁ…ዘንድሮ የመፋጠጥ ዘመን ሆነና…አለ አይደል… “እኛን ውደዱን ብሎ…” ነገር ፌስቡክ ያመጣብን ነው፡፡ (ያው “ላይክ አድርጉን” ማለት “ውደዱን…” ማለት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡) እናላችሁ…የእኔ ቢጤዎች… አይደለም ሰዉ ተጠግቶ ወዳጅ ሊያደርገን…ቢተነኩሱት እንኳን የማይተነፍስ ‘ጭምት’ ውሻ ገና እንዳየን የሚጮህብን በሺህ የሚቆጠሩ ፍሬንዶች አሉን እላችኋለሁ፡፡

ደስ አይልም! እናላችሁ… ዘንድሮ የፌስቡክ ገጼን ‘ላይክ’ አድርጉ ማለት ያው በተዘዋዋሪ ‘ላይክ’ አድርጉኝ ማለት ነው፡፡ እናላችሁ… ‘መወደድ’ በማመልከቻ የሆነበት ፌስቡክ የማንወድሳ! ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኔ እንደውም ወደፊት “የፌስቡክ ውሽምነት” በመጀመር ፌስቡክ ከተፈጠረ ጊዜ በኋላ (“ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” እንደሚባለው…) የመጀመሪያዎቹ የምንሆን ይመስለኛል፡፡ ልክ ነዋ! ከዛማ… መቼም እኛ የያዝነው ነገር ሁሉ ‘ሲያልቅ አያምርብንም’ አይደል…በየቤቱ ፍልሚያው ይጀመራል፡፡ “አጅሬ በአንተ ቤት አልታወቀብህ መሰለህ፡፡ እንደው ዝም ብዬ ጫካ ውስጥ ምናምን የተፈጠርኩ ይመስልሀል!” “ምንድነው የምታወሪው?” “እባክህ ተወው…ደርሼበታለሁ ነው የምልህ!” “ምኑን ነው የምትደርሺበት?” “ፒያሳ ኢንተርኔት ካፌ ሆነህ ከፌስቡክ ውሽማሀ ጋር ምን ነበር ‘ቻት’ ስትደራረጉ የነበረው! በአንተ ቤት አታውቅብኝም ብለህ ነው፡፡” “በቃ…ስለ አንድ አዲስ የግጥም መጽሐፍ ነዋ…ሌላ ምን ‘ቻት’ አደረገ አሉሽ?” እናላችሁ…እዚህ አገር የማይሆን ነገር የለም፡፡

ደግሞላችሁ ሌላው አለ… “ስሚ… ይሄ ፌስቡክ ላይ ‘ቻት’ የምታደርጊው ሰውዬ ግን…ቢያርፍ አይሻለውም!” “የቱን ነው የምትለው?” “ያ ‘ፕሮፋይል ፒክቸሩ’ን ቢዮንሴ የሀበሻ ልብስ ለብሳ ያለችበትን ያደረገው…” “ታዲያ እሱ ምን አደረገ ነው የምትለው?” “ምንሽ ነው?” “የፌስቡክ ፍሬንዴ ነዋ!” “የፌስቡክ ውሽማዬ ብትይ አይሻልም!” “ማነው ደግሞ እንዲህ ያለህ?” “ብቻ… ማንነቱን ደርሼበት እንደ አዲስ አበባ መንገዶች ቆፍሬ፣ ቆፋፍሬ ገደል በገደል ሳላስመስለው አንፍሬንድ ብታደርጊው ይሻልሻል!” (ውሽማ ተብዬው ያለው እኮ ያለው ቱርክሜንስታን ሊሆን ይችላል! እናላችሁ…እንደውም አላማረብን…የፌስቡክ ውሽምነት ከተጀመረ ‘ትራጂ–ኮሜዲዎች’ የሚስማሙ መአት ታሪኮች ይኖራሉ፡፡ ስሙኝማ…ለምን ይዋሻል…እስካሁን ሀያ ‘ፌስቡክ ፍሬንድስ’ አሉኝ፡፡

ከእነሱም አንድ ስምንት፣ አሥሩ ሰሞኑን ‘አንፍሬንድ’ ይደረጋሉ፡፡ (እንትናዬ…ምን ያህል ‘ሻይ’ እንደሆንኩ በ‘ፌስቡክ ፍሬንዶቼ’ ብዛት አየሽ አይደል! እናማ… ዝምታ ማብዛቴ የፍላጎት አለመኖር እንዳልሆነ ግንዛቤ ይግባልኝማ! ቂ…ቂ…ቂ…) ለነገሩማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል……የ‘ፌስቡክ ኩኪንግ’ ምናምን አለ ይባላል፡፡ ግን እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ ልክ ነዋ… ለምሳሌ እሷዬዋ “ብረት መዝጊያ የሚሆን ተገኘ…” ትልና ያላትን ፎቶ ሁሉ ‘ሼር’ ታደርገዋለች፡፡ እናላችሁ… ቢዘገይም መቼም መጣላት አይቀርም አይደል… በእነዛው ኩክ በተደራረጉባቸው ‘ፌስቡክ’ ገጾቻቸው ላይ ይጣላሉ። እንግዲህ በእውነተኛው ዓለም ሲጣሉ “ፎቶዎቼን መልስልኝ…” ይባል የለ፡፡ ‘ፌስቡክ’ ላይ ሲጣሉ እሷ ምን የምትል ይመስለኛል መሰላችሁ… “‘ሼር’ ያደረኩህን ፎቶዎቼን ሁሉ ዲሊት አድርግልኝ!” ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ኮሚክ ዓለም እኮ ነች…ኦባማ ፑቲንን ‘አንፍሬንድ አደረጓቸው’ ሲባል በሳቅ አልተንፈራፈራችሁም! ለካስ… እነኚህ በ‘ሪሞት ኮንትሮል’ እጣ ፈንታችንን የሚወስኑት አንዳንዴ እንደ እኛ ያደረጋቸዋልና! እናላችሁ…‘ፌስቡክ’ ነገሮችን እየለወጠብን ነው፡፡ ደግሞላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺ ‘ፕሮፋይል ፒክቸር’ የሚሏት ነገር አለች፡፡

…እንትና ‘ፕሮፋይል ፒክቸሩን’ ለውጧል ይባልና አዲስ የተለጠፈውን ስታዩት…ምን አለፋችሁ ግራ ነው የሚገባችሁ፡፡ አሀ…ልክ እሱን የሚመስል ቢያንስ በአሥራ ሰባት ዓመት የሚያንስው ወንድም እንዳለው አታውቁም ነበራ! ቂ…ቂ…ቂ… እናማ…የዚች ‘ከሠላሳ አንድ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈች’ አገር ኑሮ እንኩሮ ያስመሰለው ሰው… ምን አለፋችሁ…ፌስቡክ ገጹ ላይ አበባ መስሎላችሁ ቁጭ፡፡ ዕድሜ ለፎቶሾፕ! (“አንዳንዴ ሳይህ ትራስ ከሆነ የምርጫ ዘመናት ያሳለፈ አሮጌ ካናቴራ ቢጤ ትመስላለሀ…” ብለህ በሞራሌ ጢብ፣ ጢብ የተጫወትከው ወዳጄ…በፎቶሾፕ ብራድ ፒትን ሆኜልህ ቁጭ ስል ምን እንደምትሆን ብቻ አይቼ! “ለዓይን አትሞላም…” “ፊትህ ምግብ አይበላም…” ምናምን ማለት የለ…በነገራችን ላይ “ቦይፍሬንድ ምናምን አይወጣላትም…” ያልከኝ ‘ሲሱ’ እዚሁ ነች!) የ‘ፌስቡክ ፕሮፋይል ፒክቸር’ ልጠፋ አሪፍነቱ ምን መሰላችሁ…“ከስድስት ወር ያልበለጠ ፎቶ…” የሚል መመሪያ አለመኖሩ! እናላችሁ… ፌስቡክ ነገሮችን ሁሉ እየለወጠብን ነው፡፡

ደግሞላችሁ… ‘ፋይንድ ፍሬንድስ’ የሚላችሁ ነገር አለ አይደል…“እንትና ሠላሳ ሰባት ‘ፍሬንድስ’ አግኝታለች…” ምናምን ይላል፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ “‘ፍሬንድስ’” አግኝቷል የሚባል ሰው ላገኘው ሰው እንደገና “‘ፍሬንድ’ እንሁን…” የሚል ጥያቄ ማቅረቡ። ደግሞላችሁ…‘ሼር’ መደራረግ የሚሏት ነገር አለችላችሁ፡፡ ይቺ አገር ከሠላሳ አንድ ዓመት በፊት… (ይሄ ነገር ደጋገመኝሳ! በ‘ናይጄርያ እጅ ላይ ስለጣሉን’ ይሆን እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…) ‘ሼር’ መደራራግ የ‘ፌስቡክ አካውንት’ አያስፈልገውም ነበር፡፡ “የጩኒ እናት እባክዎ አንድ ኩባያ ሹሮ ካለዎት…” “አቶ አስጨናቂ፣ እስቲ መጥረቢያህን አውሰኝ፣ ይሄ ዛፍ እኮ አስቸገረኝ…” ምናምን እየተባባለ ‘ሼር’ ይደራረግ ነበር፡፡ አሁን “‘ፌስቡክ’ን ክፈቺ ሼር ያደረግሁሽ ነገር አለ…” ምናምን ይባልና ሲከፈት ምን ቢሆን ጥሩ ነው… ማይሊ ሳይረስ ‘እንትኗን ገልባ’ ስትቀብጥ! እና ‘ፌስቡክ’ ብዙ ነገር እየለወጠብን ነው፡፡ ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 6623 times