Saturday, 21 September 2013 09:58

ሁለት ተጨማሪ ነጋዴዎች በሙስና ተጠርጥረው ፍ/ቤት ቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ለወራት በእስር የቆዩት አቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ በዋስ ተለቀቁ

የተለያዩ ሃሰተኛ የንግድ ፍቃዶችን በማውጣት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ ሸቀጦችን ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተዋል እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ የራሳቸው አስመስለው ይዘዋል የተባሉ ሁለት ነጋዴዎች በቁጥጥር ስር ውለው በትናንትናው እለት ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን የ14ቀን የምርመራ ጊዜም ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በፌደራሉ የስነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ ታደለ ብርሃኑ እና አቶ ወ/ሚካኤል ሃለፎም የተባሉት ተጠርጣሪዎች በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውንና የተጠረጠሩበትን ወንጀል የፈፀሙት ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ ካሉት የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሃላፊዎች ጋር በመመሳጠርና ጉቦ በመቀባበል ነው ተብሏል፡፡

የመርማሪ ቡድኑ እስካሁን በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ንብረት የራስ አድርጐ መጠቀም ከሚለው የወንጀል ፍሬ ጋር በተያያዘ ንብረቶቹ የሚገኙበትን ቦታ ማግኘቱን ለፍ/ቤቱ አመልክቶ፤ ይቀሩኛል ያላቸውን ተግባራትም አስረድቷል፡፡ ከሚቀሩ የምርመራ ስራዎች መካከልም የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበል፣ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ማሰባሰብ እንዲሁም የምስክሮችን ቃል መቀበል ይገኙበታል፡፡

እነዚህን ስራዎች ለማጠናቀቅም የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ የየግል ምክንያቶቻቸውን አቅርበው ጉዳያቸውን በዋስ ሆነው እንዲከታተሉ የጠየቁ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ14 ቀን ቀጠሮ ፈቅዶ ጉዳዩን ለመስከረም 23 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ዳኞች ተሟልተው ባለመቅረባቸው በፅ/ቤት በኩል በሁለት ዳኞች በተስተናገደው በእለቱ ችሎት ከኦዲት ምርመራ ጋር በተያያዘ ክስ ሳይመሰረትባቸው ጉዳያቸው ወደ ጊዜ ቀጠሮ ከተመለሱት 4 ተጠርጣሪዎች መካከል በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአዋሽ ቅርንጫፍ ሠራተኛ በነበሩት በአቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ ላይ የሚካሄደው ምርመራ በመጠናቀቁ በ20ሺህ ብር ዋስ ተለቀዋል፡፡

በእነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መዝገብ ተካተው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የነበሩት አቶ ምህረተ አብ አብርሃ እና አቶ በእግዚአብሔር አለበል ላይ የሚካሄደው የኦዲት ምርመራ ስራ አለመጠናቀቁን ለፍ/ቤቱ ያመለከተው የመርማሪ ቡድኑ፤ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 14 ቀን የጠየቀ ቢሆንም ፍ/ቤቱ የ8 ቀን ጊዜ ብቻ ለመጨረሻ ጊዜ በመፍቀድ መዝገቡን ለመስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡ የሌላኛው ተጠርጣሪ የአቶ ፍፁም ገ/መድህን መዝገብ በእለቱ ባለመቅረቡ ጉዳያቸው በአዳሪ እንዲሰማ ብይን ተሰጥቶበት ለሰኞ መስከረም 13 ቀን 2006 ተቀጥሯል።

Read 18830 times