Monday, 16 September 2013 08:28

የታላላቅ አትሌቶች የግማሽ ማራቶን ትንቅንቅ በኒውካስትል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(5 votes)

ነገ በእንግሊዝ ኒውካስትል በ2013 ‹ቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን› ላይ የዓለማችን ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች በግማሽ ማራቶን ከባድ ትንቅንቅ ሊያደርጉ ነው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች በዋናነት የኢትዮጵያ ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ተፎካካሪነት ሲጠበቅ በርቀቱ አዳዲስ የዓለም ሪከርዶች የሚመዘገቡበት እድል የሰፋ መሆኑ እየተገለፀ ነው፡፡ በወንዶች የግማሽ ማራቶን ውድድሩ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ቀነኒሣ በቀለ እና የእንግሊዙ ሞፋራህ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በግማሽ ማራቶን ውድድር በመገናኘት አስደናቂ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡ በግማሽ ማራቶን ውድድሩ ኃይሌ ገብረስላሴ ካለው ልምድ አንፃር ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት እንዳለው ቢገለፅም፤ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን የወሰደው የእንግሊዙ ሞ ፋራህ ዓመቱን በስኬት ለመደምደም ማቀዱ እና በግማሽ ማራቶን ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፍው ቀነኒሣ በቀለ በውጤታማነት ወደ ጎዳና ሩጫዎች ለመሸጋገር ተስፋ ማድረጉ ፉክክሩን ያጠናክረዋል፡፡ በሴቶች ምድብ በተለይ በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ባላቸው ተቀናቃኝነት ዓለም የሚጓጓላቸው ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር በግማሽ ማራቶን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ መገናኘታቸውም ትኩረት ስቧል፡፡ በግማሽ ማራቶን ውድድር ጥሩነሽም ሆነ መሰረት ያን ያህል የዳበረ ልምድ እንደሌላቸው የገለፀው የአትሌቲክስ ዊክሊ ዘገባ፤ እርስ በራስ ለመሸናነፍ የሚያደርጉት ትንቅንቅ ግን ምናልባትም ክብረወሰን እንዲሰበር ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡
ግማሽ ማራቶን በአጠቃላይ 21.0 975 ኪ.ሜ የሚሸፍን ውድድር ነው፡፡ በወንዶች ግማሽ ማራቶን የዓለም ሪኮርድን የያዘው ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ በ2010 እ.ኤ.አ በፖርቱጋል ሊዝበን ባስመዘገበው 58 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች ሲሆን ፤ በሴቶች ደግሞ የኬንያም ማሪ ኪታኒ በ2011 እ.ኤ.አ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ 1 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ50 ሰኮንዶች ርቀቱን በማጠናቀቅ ሪከርዱን አስመዝግባለች፡፡ በኖቫ ኢንተርናሽናል የሚዘጋጀው ‹ቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን› ከዓለማችን ግዙፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን ነገ ከ56ሺ በላይ ስፖርተኞችን እንደሚያሳትፍ ሲታወቅ ራን› በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ በሆነውና የቢቢሲ ኮሜንታተር በነበረው ብሬንዳን ፎስተር ከ32 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ነው፡፡ የቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ ስኬት ያላቸው ሲሆን በወንዶች ሶስት በሴቶች ደግሞ አራት አትሌቶች አሸናፊዎች ነበሩ፡፡ በወንዶች የግማሽ ማራቶን ውድድር በ2004 እኤአ ደጀኔ ብርሃኑ፤ በ2008 እኤአ ፀጋዬ ከበደ እንዲሁም በ2010 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ ሲያሸንፉ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ በ2006 እና በ2010 እኤአ ላይ ብርሃኔ አደሬ ሁለቴ ማሸነፏ ሲታወስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ደራርቱ ቱሉ፤ በ2008 እኤአ ላይ ጌጤ ዋሚ እንዲሁም ባለፈው አመት ጥሩነሽ ዲባባ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡
ኃይሌ ከቀነኒሳ ከሞ ፋራህ
የ40 ዓመቱ አንጋፋ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በነገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ በከፍተኛ የውድድር ደረጃ በተፎካካሪነት የመሰለፍ ብቃት እንዳለው ሲገልፅ ሁለቱን ተቀናቃኞቹን ቀላል አልፈትናቸውም ብሏል፡፡ በ2010 እኤአ ላይ በተመሳሳይ ስፍራ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን በ59 ደቂቃ ከ33 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመጨረስ ያሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ በግማሽ ማራቶን የዳበረ ልምድ ቢይዝም በሞ ፋራህ እና ቀነኒሳ ላይ ብልጫ ለማሳየት ከግዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣው አሯሯጡ እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ኃይሌ ገ/ስላሴ በ2006 እ.ኤ.አ በአሪዞና ግዛት አሜሪካ በ58 ደቂቃ ከ55 ሰኮንዶች ርቀቱን በመሸፈን ሪከርድ አስመዝግቦ ነበር፡፡ የ38 ዓመቱ ቀነኒሣ በቀለ ነገ በግማሽ ማራቶን የሚሮጠው በሩጫ ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በ‹ቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን› ተሳትፎው ወደ ማራቶን ሯጭነት የሚሸጋገርበትን አዲስ ምእራፍ እንደሚከፈት የተናገረው ቀነኒሣ፤ ከ10 ዓመት በፊት የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ ውድድር በኒውካስትል በተዘጋጀ አገር አቋራጭ ተሳትፎ ማሸነፉን አስታውሶ በነገው ግማሽ ማራቶን መሳተፉን እንደታላቅ ክብር እንደሚቆጥረው አስታውቋል፡፡ ኃይሌ እና ሞ ፋራህ በርቀት አይነቱ ከእሱ የተሻለ ልምድ እንደሚኖራቸው ያመነው ቀነኒሣ፤ከትራክ ውድድር ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች የሚሸጋገርበትን ሁኔታ በሚያስመዘግበው ውጤት ለማነቃቃት እንደሚያስብም ተናግሯል፡፡ ቀነኒሣ በቀለ ከነገው የግማሽ ማራቶን ተሳትፎው በኋላ ወደ ማራቶን ፊቱን እንደሚያዞር ከመግለፁም በላይ በሚቀጥለው ዓመት በለንደን ማራቶን የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው እና ዋና እቅዱ እና ዓለማው በ2016 እኤአ ላይ በሚደረገው 31ኛው የብራዚል ኦሎምፒያድ በማራቶን መወዳደር መሆኑን አስታውቋል፡፡ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ በነገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ለማሸነፍ እና ዓመቱን በስኬት የመዝጋት ፍላጎት እንዳለው ሲናገር ሰንብቷል፡፡ በሩጫ ዘመኑ ሶስተኛውን የግማሽ ማራቶን ውድድር የሚያደርገው ሞ ፋራህ ምናልባትም የኃይሌ እና የቀነኒሳ ተፎካካሪነት በመቋቋም ካሸነፈ በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን የውድድር ታሪክ ከ28 አመታት በኋላ ያሸነፈ እንግሊዛዊ ይሆናል፡፡ እንደ አትሌቲክስ ዊክሊ ሀተታ ሞ ፋራህ ለመጀመርያ ጊዜ የግማሽ ማራቶን ውድድር የሮጠው ከ2 ዓመት በፊት በኒውዮርክ ሲሆን በርቀቱ ፈጣን ሰዓቱን በዚሁ ውድድር በ60 ደቂቃ ከ23 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበ ነው፡፡
ኃይሌ፤ ቀነኒሣ እና ሞ ፋራህ ባለፉት 20 ዓመታት በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገቡ የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ናቸው፡፡ በሞስኮው 14ኛው የዓለም ሻምፒዮና የእንግሊዙ አትሌት ሞ ፋራህ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ደርቦ በማሸነፍ ከተሳካለት በኋላ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሐናት የረጅም ርቀት ንጉስ መሆኑን የተናገሩት በሁለት ዓመት ልዩነት በአንድ ኦሎምፒክና ሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰቡ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱንም ርቀቶች ክብረወሰን ባለመስበሩ አትሌት ሞ ፋራህ የእንግሊዝ አትሌቲክስ ንጉስ እንጅ የዓለም ሊሆን አለመቻሉ ግልፅ ይሆናል፡፡ ሞ ፋራህ ይህን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ለረጅም ጊዜ አተኩሮ ሲሰራ የኖረው በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረኮች የወርቅ ሜዳልያዎችን ለማግኘት መሆኑን ገልፆ በቀነኒሣ በቀለ ለበርካታ ዓመታት ተይዘው የቆዩ የ10ሺ እና የ5ሺ ሜትር ሪከርዶችን የማሻሻል አቅም እንደሌለው በይፋ ተናግሯል፡፡ ከሦስቱ አትሌቶች የረጅም ርቀት ንጉስ የመባል ተፎካካሪነት ሊኖራቸው የሚችሉ ኢትዮጵያውያኖቹ ኃይሌ ገ/ስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ናቸው፡፡
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባለው ልምድ 23 ዓመታትን ያስቆጠረው ኃይሌ ገብረስላሴ ቀዳሚው ሲሆን ቀነኒሳ የ21 ዓመት እንዲሁም ሞፋራህ ከ10 ዓመት ያነሰ ልምድ በመያዝ ይከተሉታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናዎች፤ በኦሎምፒክ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከ25 በላይ የወርቅ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ቀነኒሣ ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበ ሲሆን ኃይሌ ገብረስላሴ እስከ 15 የወርቅ ሜዳልያዎች በማስመዝገብ ሞ ፋራህ ደግሞ ከ7 የማይበልጡ የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ በሰፊ ርቀት ይከተላሉ፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በትራክ እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች፤ ኃይሌ ገብረስላሴ በትራክ እና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች እንዲሁም ሞፋራህ በትራክ ውድድር ብቻ ባላቸው ውጤታማነት ይታወቃሉ፡፡ ኃይሌ ገብረስላሴ በሩጫ ዘመኑ ከ2 ማይል እስከ ማራቶን በ17 አይነት የውድድር መደቦች ከ27 በላይ ክብረወሰኖችን በማስመዝገብ ከፍተኛ ለውጥ በስፖርቱ ላይ መፍጠር ችሏል፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ5 የውድድር መደቦች ስድስት ክብረወሰኖችን ያስመዘገበ ሲሆን በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የያዛቸው ሪከርዶች ለረጅም አመት ሳይሰበሩ በመቆየታቸው ተደንቆበታል፡፡ ሞ ፋራህ በአውሮፓ ደረጃ የተመዘገቡ ሪከርዶች እንጅ ዓለም አቀፍ ክብረወሰን የለውም፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ ከመሰረት ደፋር
ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር በ5ሺ ሜትር ባላቸው ትንቅንቅ ከፍተኛ ትኩረት በመላው ዓለም ያገኛሉ፡፡ ነገ ግን ብዙ የዳበረ ልምድ በሌላቸው የግማሽ ማራቶን ውድድር የሚገናኙት ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ባለፈው ዓመት በቡፓ ግሬት ኖርዝ ራን በግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ በሩጫ ዘመኗ ለመጀመርያ ጊዜ ስትሳተፍ ያሸነፈችው ርቀቱን በ1 ሰዓት ከ07 ደቂቃ ከ35 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ ነበር፡፡ አትሌት መሰረት ደፋር በበኩሏ ዘንድሮ በኒውኦርሊዬንስ በሮጠችው የግማሽ ማራቶን ያሸነፈቸው ከጥሩነሽ ሰዓት በ10 ሰከንዶች ፈጥና በመግባት ሲሆን ያስመዘገበችው 1 ሰዓት ኮ7 ደቂቃ ከ25 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ ነው፡፡
የጥሩነሽ እና የመሠረት አስደናቂ ፉክክር በሩጫ ዘመናቸው ባስገኙት ስኬት በማነፃፀር መታዘብ ይቻላል፡፡አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምፒክ መድረክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች 3 ወርቅና 2 ነሐስ በመሰብሰብ ሲሳካለት መሰረት ደፋር በኦሎምፒክ 2 ወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያ ብቻ አላት፡፡ ለዓለም ሻምፒዮና ጥሩነሽ ዲባባ 5 የወርቅ ሜዳልያዋን ስትሰበስብ መሠረት ደፋር 2 ወርቅ፣ 2 ነሐስ አስመዝግባለች፡፡ መሠረት በዓለም የአትሌቲክስ ፍጻሜ ውድድር 9 ወርቅ እና 1 የብር ሜዳልያ በመሰብሰብ ሲሳካለት ጥሩነሽ ያላት1 የወርቅ 3 የብር 1 የነሐስ ነው ፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር መሠረት 4 ወርቅ 1 ብርና 1 ነሐስ ሜዳልያ ስትወስድ ጥሩነሽ በዚህ ውድድር ብዙም ውጤት የላትም፡፡ ጥሩነሽ በሩጫ ዘመኗ 7 የዳይመንድ ሊግና 7 የጐልደን ሊግ ሩጫዎችን ስታሸንፍ መሠረት ደፋር በበኩሏ 6 የዳይመንድ ሊግና 6 የጐልደን ሊግ ውድድሮችን አሸንፋለች፡፡ ጥሩነሽ በ5 ሺ ሜትር እና በ15 ካ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ ሁለት የዓለም ክብረወሰኖች ሲኗሯት መሠረት በቤት ውስጥ ውድድር የ3ሺ እና የ5ሺ ሜትር ክብረወሰኖችን ይዛለች፡፡ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም አትሌቲክስ በ10ሺ ሜትር በ1360 ነጥብ ከዓለም አንደኛ፣ በጐዳና ላይ ሩጫ ለ1260 ነጥብ 1ኛ፣ በ5ሺ ሜትር በ1360 ነጥብ 2ኛ እንዲሁም በሁሉም የአትሌቲክስ ውድድር በ1392 ነጥብ ከዓለም 11ኛ ነች፡፡ አትሌት መሠረት ደፋር በ5ሺ ሜት በ1392 ነጥብ 1ኛ፣ በ10ሺ ሜትር በ1271 ነጥብ ዘጠነኛ እንዲሁም በሁሉም የአትሌቲክስ ውድድር በ13 ነጥብ ከዓለም 9ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡

Read 4282 times