Print this page
Monday, 16 September 2013 08:27

ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከማን ልትገናኝ ነው?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ከአልጄርያ፤ከቱኒዚያ፤ ከጋና፤ ከናይጄርያ ወይስ ከአይቬሪኮስት
በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን በመወከል የሚሳተፉ 5 ብሄራዊ ቡድኖች የሚለየው የጥሎ ማለፍ ምእራፍ የጨዋታ ድልድል የፊታችን ሰኞ የሚወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ ከማን ጋር ልትገናኝ ትችላለች የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል ለዓለም ዋንጫ የምታልፍበትን እድል በ180 ደቂቃዎች ትወስናለች፡፡
የጥሎ ማለፉ ድልድል አስቀድሞ ካይሮ ውስጥ በሚገኘው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ዋና ፅህፈት ቤት እንደሚደረግ ቢገለፅም በከተማዋ ባለው አለመረጋጋት በደቡብ ግብፅ በምትገኘው ሉክሰር ከተማ ለማውጣት መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ለዚሁ የጥሎማለፍ የጨዋታ ድልድል የሚያስፈልገው ወርሃዊው የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ የታወቀ ሲሆን ለጥሎ ማለፍ ምዕራፉ የበቁት 10 ብሄራዊቡድኖች በእጣ አወጣጥ ስነስርዓቱ በሁለት ማሰሮዎች የሚመደቡበት ሁኔታ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይፋ ሆኗል፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ ከ10ሩ ብሄራዊ ቡድኖች አንዷ የነበረችው ኬፕቬርዴ በምድቧ ከቱኒዚያ ጋር ባደረገችው የመጨረሻ ጨዋታ ተገቢ ያልሆነ ተጨዋች በማሰለፏ ውጤቷ ሲሰረዝባት በምትኳ ቱኒዚያ ለጥሎ ማለፉ ከደረሱት 10 ብሄራዊ ቡድኖች አንዷ እንድትሆን መወሰኑንም ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ አስታውቋል፡፡ ከኬፕቨርዴ መባረር በኋላ በወርሃዊው የፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ መሰረት በሁለቱ የእጣ ማውጫ ማሰሮዎች የሚመደቡት አምስት አምስት ብሄራዊ ቡድኖች በከፍተኛ ደረጃቸው በማሰሮ 1 አይቬሪኮስት ፤ ጋና፤ አልጄርያ፤ ቱኒዚያ እና ናይጄርያ ሲቀመጡ በዝቅተኛ ደረጃቸው በማሰሮ 2 ግብፅ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ካሜሮን፤ ሴኔጋል እና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ከትናንት በስቲያ በወጣው የፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ ባለፈው ወር ከነበረችበት ደረጃ ዘጠኝ እርከኖችን በማሻሻል በአፍሪካ 25ኛ በዓለም 93ኛ ደረጃ ላይ ነች፡፡ አይቬሪኮስት በአፍሪካ 1ኛ በዓለም 19ኛ፤ ጋና በአፍሪካ 2ኛ በዓለም 24ኛ፤አልጄርያ በአፍሪካ 3ኛ በዓለም 28ኛ፤ ናይጄርያ በአፍሪካ 4ኛ በዓለም 36ኛ፤ ቱኒዚያ በአፍሪካ 7ኛ በዓለም 46ኛ ፤ ግብፅ በአፍሪካ 8ኛ በዓለም 50ኛ ፤ ቡርኪናፋሶ በአፍሪካ 9ኛ በዓለም 51ኛ እንዲሁም ሴኔጋል በአፍሪካ 11ኛ በዓለም 66ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን በ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የደርሶ መልስ ትንቅንቅ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአራት የአፍሪካ ግዙፍ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር መገናኘቱ በከፍተኛ ደረጃ በማነጋገር ላይ ይገኛል፡፡ በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በጥሎ ማለፍ የደርሶ መልስ ትንቅንቁ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ቡድን ጋር ተደልድላ የመጀመርያውን ጨዋታ ከሜዳ ውጭ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በሜዳዋ ላይ እንድታደርግ እየተመኙ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኑ ለጥሎ ማለፉ ሁለት ጨዋታዎች በከፍተኛ ትኩረት እና በሙሉ አቅም እንዲዘጋጅ እና ቢያንስ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለአቋም መፈተሻ ማድረግ እንደሚኖርበትም ይመክራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሰኞ በሚወጣው የጥሎ ማለፍ የጨዋታ ድልድል በማሰሮ 1 ከሚገኙት አምስት ግዙፍ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የሚፋጠጥበት እድል ሲኖረው ተጋጣሚዎቹ አይቬሪኮስት ፤ ጋና፤ አልጄርያ፤ ቱኒዚያ እና ናይጄርያ ናቸው፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በጥሎ ማለፍ ድልድሉ ከግብፅ ጋር ላይገናኝ መቻሉ ያስደሰታቸው ቢሆንም ከሁለቱ የሰሜን አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች አልጄርያ እና ቱኒዚያ ጋር የምትገናኝበት እድል መኖሩ አስግቷቸዋል። ከሰሜን አፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ባሻገር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በርካታ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ስብስብ ከሚይዙት የምእራብ አፍሪካ ተወካዮች ጋና እና አይቬሪኮስት ጋር መገናኘቷን በስጋት የሚመለከቱ ስፖርት አፍቃሪዎች ደግሞ ከምእራብ አፍሪካ ቡድኖች በተለይ ከናይጄርያ ጋር ብትገናኝ ምርጫቸው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ምእራፍ መብቃቱ በራሱ ታላቅ ታሪክ እንደሆነ የሚያሰምሩበት አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ከሚሳተፉት የዓለም ምርጥ 32 ብሄራዊ ቡድኖች መሆኑ ካልቀረ ከአፍሪካ 10 ምርጥ ቡድኖች አንዱን አሸንፎ ማለፉ ተገቢ ፈተና ነው በማለት ሰኞ የሚወጣውን ድልድል በጉጉጉት ይጠባበቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ በጥሎ ማለፍ የጨዋታ ድልድሉ ልትገናኛቸው ከምትችላቸው አምስት የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያላት የውጤት ታሪክ ተቀማጭነታቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ባደረጉ የእግር ኳስ ታሪክ እና ስታስቲካዊ መረጃዎች አሰባሳቢ ባለሙያዎች ተቋም በሆነው ኤኤፍኤስ ተሰርቶ 11v11.com በተባለ ድረገፅ የተቀመጠው መረጃ ከዚህ በታች የቀረበውን ይመስላል፡፡
ኢትዮጵያ ከአልጄርያ - በ4 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ተገናኝተው እኩል አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጨዋታዎቹ በ1968 እኤአ ላይ ኢትዮጵያ 3ለ1 ያሸነፈችበት፤ በ1982 እና በ1994 እኤአ ለሁለት ጊዚያት ያለምንም ግብ አቻ የተለያዩበት እና በ1995 እኤአ ላይ አልጄርያ 2ለ0 ያሸነፈችበት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከጋና - በአንድ የአፍሪካ ዋንጫ እና በሌላ ኢንተርናሽናል ግጥሚያ ለሁለት ጊዚያት ተገናኝተው እኩል አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል፡፡ በ1963 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ጋና 2ለ0 ስትረታ በ1996 ደግሞ በኢንተርናሽናል ግጥሚያ ኢትዮጵያ 2ለ0 አሸንፋለች፡፡
ኢትዮጵያ ከናይጄርያ - በታሪካቸው 6 ጊዜ ተገናኝተው ናይጄርያ አራቱን ስታሸንፍ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ አሸንፋ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ናይጄርያ ድል ያደረገችባቸው ጨዋታዎች በ2013 እኤአ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ 2ለ0፤ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች በ2011 እኤአ 4ለ0 ፤ በ1993 እኤአ 6ለ0 እንዲሁም በ1982 በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ 3ለ0 የተመዘገቡት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ብቸኛ ጨዋታ በ1993 እኤአ ላይ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ 1ለ0 ያስመዘገበችው ሲሆን በ2011 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ደግሞ 2ለ2 አቻ ተለያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአይቬሪኮስት - በታሪካቸው በ3 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ተገናኝተው ሁለቱን አይቬሪኮስት ስታሸንፍ ኢትዮጵያ አንዱን ድል አድርጋለች፡፡ በ1968 እኤአ ላይ ኢትዮጵያ 1ለ0 ስታሸንፍ በተመሳሳይ ወቅት አይቬሪኮስት 1ለ0 ረትታለች፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በሰፊ የግብ ልዩነት ሽንፈት ተብሎ በሪከርድ የተመዘገበው ሌላው ግጥሚያ በ1970 እኤአ አይቬሪኮስት 6ለ1 ያሸነፈችበት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ - በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ዋና ውድድር እና የማጣርያ ጨዋታዎች እንዲሁም በተለያዩ ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታዎች 9 ጊዜ ተገናኝተው ቱኒዚያ 4 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ 3 ጊዜ ሲያሸንፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያሸነፈችባቸው ሶስት ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ በ1962 እኤአ ላይ 4ለ2፣ በ1963 እኤአ ላይ 4ለ2 እንዲሁም በወዳጅነት ጨዋታ በ1967 እኤአ ላይ 2ለ1 ያሸነፈችባቸው ነበሩ፡፡ ቱኒዚያ የረታችባቸው 4 ጨዋታዎች ደግሞ በ1964 እኤአ ላይ በወዳጅነት ጨዋታ 3ለ2፣ በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በ1965 እኤአ 4ለ0፣ በ1990 እኤአ 2ለ0 እንዲሁም በዓለም ዋንጫ የማጣርያ በ1993 እኤአ 3ለ0 በሆነ ውጤት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በአቻ ውጤት የተለያዩባቸው ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ በ1992 እኤአ 0ለ0 የተለያዩበት እና በ2013 እኤአ ላይ በወዳጅነት ጨዋታ አንድ እኩል አቻ የወጡበት ናቸው፡፡

 

Read 2385 times