Monday, 16 September 2013 08:05

ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ የዘለቀው ሸዋ ዳቦ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(10 votes)
  • በአዲስ አበባና በአዳማ 20 ቅርንጫፎችና 52 ማከፋፊያዎች 
  • በቃሊቲ ትልቅ የዳቦ ማምረቻ ኢንዱስትሪ 
  • በአዳማ የዱቄት ፋብሪካ 
  • ሴንትራል ማተሚያ ቤት - እህት ኩባንያ

              በአዲስ አበባ ሆነ በክልል ከተሞች እያወቅን የማናውቃቸው (ስማቸውን እያወቅን አመሠራረትና ታሪካቸውን የማናውቅ) ብዙ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱ ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ነው፡፡ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ቢጓዙ፣ ሸዋ ዳቦን ወይም ማከፋፈያውን አያጡም ማለት ይቻላል፡፡ አባ ኮራን፣ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ቃሊቲ፣ ወይራ ሰፈር፣ አየር ጤና፣ ቦሌ፣ ገርጂ፣ ጀሞ፣ ቄራ፣ … ሸዋ ዳቦን ወይም ማከፋፈያውን ያገኛሉ፡፡
ሸዋ ዳቦን ከ54 ዓመት በፊት በ1951 ዓ.ም (ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ማለት ነው) በተለምዶ አባኮራን በመባል በሚጠራው ሰፈር፣ የመጀመሪያዋን ዳቦ ቤት በመክፈት ሥራ የጀመሩት፤ የዛሬው የ83 ዓመቱ አረጋዊ አቶ ዘሙይ ተክሉ ናቸው፡፡ ሸዋ ዳቦ የግል ቢዝነስ ቢሆንም መሥራቹ በጡረታ ተገልለው፣ በእግራቸው ልጆቻቸው ተተክተዋል፡፡ አሁን ድርጅቱን የሚመሩት ልጆቻቸው ናቸው፡፡ አቶ ዘሙይ እንደቀድሞው ተሯሩጠው ባይሰሩም፣ በረዥም ዘመን ያካበቱትን ልምድ ልጆቻቸውን በማማከር እውቀታቸውን እያካፈሉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ኃ.የተ.የግ.ማኅበርን፣ በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት የአቶ ዘሙይ የበኩር ልጅ አቶ ፀሐይ ዘሙይ ናቸው፡፡ አቶ ፀሐይን ሸዋ ዳቦ እንዴት እንደተመሠረተ፣ በስንት ብር ካፒታልና ሠራተኛ ሥራ እንደጀመረ፣ አሁን ካፒታሉ ስንት እንደደረሰ፣ እንዴት እየሠራ እንደሆነና የወደፊት ዕቅዱን ማወቅ ፈልገን፣ ሸዋ ዳቦ እንዴት ተመሠረተ? አልናቸው፡፡
አሁን በተለምዶ ጎጃም በረንዳ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር ዝቅ ብሎ፣ አባ ኮራን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ካለው ቤንዚን ማደያ አጠገብ፣ የአንድ ኢጣሊያዊ ትንሽ ዳቦ ቤት ነበረች፡፡ አባቴ ከአሥመራ እንደመጡ፣ እዚያች ዳቦ ቤት በኃላፊነት ተቀጥረው ይሠሩ ነበር፡፡ ጣሊያኑ አርጅቶ መሥራት ሲያቅተው፣ አቶ ዘሙይ ያቺን ዳቦ ቤት ከጣሊያኑ ገዝተው ማምረት ጀመሩ፡፡

በምን ያህል ነበር የገዙት?
ከ5ሺህ ብር ጥቂት ከፍ ባለ ትንሽ ካፒታል ነበር የገዙት፡፡ እሳቸው ሥራ በጀመሩበት ጊዜ፣ ዳቦ ቤቷን ከገዙበት በተጨማሪ ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ ሥራ ማካሄጃው፣ ከዘመድ ከወዳጅ፣ በብድር የተገኘ ነበር፡፡ ሥራ ለመጀመር፣ ለዱቄት መግዣ የሚሆን ገንዘብ ስለቸገራቸው፣ አቶ ሰይድ አህመድ የተባሉ ወዳጃቸው ነበር ያበደሯቸው፡፡ ከዚያም ያለ ዕረፍት ሌት ተቀን ጥርሳቸውን ነክሰው በመሥራት ዕዳቸውን ከፈሏቸው፡፡
አባቴና እናቴ ወ/ሮ ውቧ ሀብተየስ፣ ከወዳጅና ከዘመድ የወሰዱትን ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጠንክረው በመሥራት ፒያሳ፣ ከማዘጋጃ ቤት የኋለኛ በር በታች አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት አካባቢ፣ 2ኛውን የሸዋ ዳቦ ቅርንጫፍ ከፈቱ፡፡ ከዚያም አምስት ኪሎ ከቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት 3ኛውን ቅርንጫፍ፣ 4ኛውን ደግሞ በደጃዝማች በላይ መንገድ ወደ አዲሱ መንገድ አካባቢ እያሉ ቀጠሉ፡፡ እንደዚያ እያደረጉ፣ የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር 7 አደረሱ፡፡
ሥራ ሲጀምሩ ምን ያህል ሠራተኛ ነበራቸው? አሁንስ ስንት አሉ?
እርግጠኛ ባልሆንም ከ20 የሚበልጡ አይመስለኝም፡፡ ዳቦ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜ ሰው ይቀያየራል፡፡ ምርት ላይ፣ በማከፋፈል፣ በጉልበት ሥራ፣ … የተሰማሩ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይለዋወጣሉ፡፡ ይህ የዳቦ ቤት ባህርይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየጊዜው የሠራተኛ መቀያየር ዛሬም አለ፡፡
በዚያን ጊዜ ከሸዋ ዳቦ ቤት ሌላ አልነበረም እንዴ?
በወቅቱ የተከፈቱ ሌሎች ዳቦ ቤቶችም ነበሩ፡፡ ግን በውድድሩ እየተሸነፉ ወጡ፡፡ እውነት ለመናገር በዚያን ጊዜ ከተጀመሩ ዳቦ ቤቶች በአሁኑ ወቅት ያሉት አንድ ወይም ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ውጤታማ የሆኑ አይመስለኝም፡፡
ከዚያስ የአቶ ዘሙይ ጥረት ምን ደረሰ?
ቀጠለ፡፡ እንደዚያ እየሠሩ ሀብት፣ የሠራተኞች ቁጥርና የቅርንጫፎች ብዛትም እየጨመረ ሄደ፡፡ እስካሁን ያወራነው በንጉሡ ዘመን የነበረውን ነው፡፡ ከዚያም ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በ47/67 አዋጅ ብዙ ንብረታቸው ተወረሰ፡፡
ምን ምን ተወረሰባቸው?
ያው፣ እንደማንኛውም ዜጋ ነበር የተወረሰው፡፡ በዚያን ጊዜ አዳማ ላይ የዱቄት ፋብሪካ አቋቁመው ነበር፡፡ በቀላጤ ነው የተወረሰባቸው፡፡
ቀላጤ ምንድነው?
በትንሽ ደብዳቤ ማለት ነው፡፡ በቦሌ መንገድ ከኦሎምፒያ ፊት ለፊት አሁን ጌቱ ኮሜርሻል ሕንፃ ካለበት ፊት ለፊት ያለው ዳቦ ቤትና ሕንፃው የእሳቸው ነበር፤ ተወረሰ፡፡ እዚያ ያለው ዳቦ ቤት ሲመለስላቸው ሕንፃው ግን እንደተወረሰ ቀረ፡፡ አባ ኮራን ያለውም ሕንፃ ተወረሰ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። ሌሎች በርካታ ንብረቶችም ተወርሰውባቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ፈተናዎች ተደቀነባቸው፡፡ የባንክ ዕዳ ነበረባቸው፤ ብዙ ችግር ወደቀባቸው፡፡
ታዲያ ምን አደረጉ? ተስፋ ቆርጠው ተቀመጡ?
እንዲያውም! ያ ሁሉ ችግር አልበገራቸውም፡፡ በዚያ ሁሉ በደል ሞራላቸው ሳይወድቅና ሳይጨናነቁ ሥራውን ቀጠሉ፡፡ ከአንድ እናትና ከአንድ አባት የተወለድነው 13 ልጆች በሙሉ የምንኖረው ውጭ አገር ነበር፡፡ ዕድሜአችን እየጨመረ ለሥራ ስንደርስ ወደ አገር ቤት ተመለስን፡፡ በዚያን ጊዜ የአባታችን ዕድሜ እየገፋ ነበር፡፡ ስለዚህ እሳቸውን አሳርፈን እኛ በእግራቸው ተተክተን መሥራት ቀጠልን። እሳቸውም በረዥም ዘመን ባካበቱት ልምድ እየመከሩንና እየመሩን እስካሁን ዘልቀናል፡፡
የአዳማው የዱቄት ፋብሪካ እንደተወረሰ ቀረ?
አይ! ተከራክረን አስመልሰናል፡፡ አሁን ለራሳችን የሚያስፈልገንን ዱቄት የምናስፈጨው እዚያ ነው። ፋብሪካው የሚፈጨው ዱቄት ብቻ ስለማይበቃን መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ከውጭ እየገዛ የሚያመጣውን ስንዴ ገዝተን እያስፈጨን እንጠቀማለን፡፡
የውጭ ስንዴ የምትጠቀሙ ከሆነ ዋጋችሁ ውድ ነው ማለት ነው?
አይደለም፡፡ መንግሥት፣ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮው እንዳይከብደው ለመደጐም ብሎ ያመጣው ስለሆነ በስንዴዉም በዱቄቱም በዳቦውም ላይ የዋጋ ጣሪያ (Price Cap) ተቀምጧል፡፡ ከዚያ አስበልጠን መሸጥ አንችልም፡፡ በዚያ ነው እየተሠራ ያለው፡፡
አከፋፋይ የተባሉት ፍራንቻይዝ ያደረጋችሁት ነው?
እንደሱ አይደለም፡፡ ከእኛ ጋር በኮሚሽን የሚሠሩ ማለት ነው፡፡ እነዚህ በኮሚሽን የሚሠሩ ሰዎች የራሳቸውን የዳቦ መሸጫ ያዘጋጃሉ፡፡ ቤቱ የግዴታ ሰፊና የእኛን ቅርንጫፎች መስፈርት ማሟላት የለበትም፡፡ ዓላማው ምንድነው? ብትል፣ ኅብረተሰቡ በየአቅራቢያው ትኩስ ዳቦ ማግኘት አለበት ከሚል የመጣ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እኛ ያደረ ዳቦ አንሸጥም፣ አያድርምም፡፡ ምናልባት መሽቶ ካደረም፣ እናደርቀውና ለኮተሌት መሥሪያ እንጠቀምበታለን፡፡)
አንድ ሰው አከፋፋይ መሆን ከፈለገ፣ ቤት ይከራያል፣ ሠራተኛ ይቀጥራል፣ ካውንተሮች ያዘጋጃል፡፡ ከዚያም ለእኛ ያሳየናል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ከሆነ ከእኛ ዳቦ ወስዶ ይሸጣል፤ እኛ 10 በመቶ ኮሚሽን እናስብለታለን፡፡ ይህ አሠራር ብዙ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው በሁለትና በሦስት ሺህ ብር ተቀጥሮ ከሚሠራ፣ ከእኛ ዳቦ እየወሰደ ቢሸጥ የበለጠ ይጠቀማል፡፡ በአገራችን የቤት አስተዳዳሪው ይሠራል፣ ሌሎች የእሱን እጅ ይጠብቃሉ፡፡
የቤት እመቤት የሆኑት ሴቶች ግቢያቸው ወይም በአቅራቢያቸው ፅድት ያለ ቤት ሠርተው ወይም ተከራይተው ከእኛ ዳቦ ወስደው ይሸጣሉ። በዚህ ዓይነት ገቢ ይፈጥራሉ፡፡ ከአባወራው ጋር ተደጋግፈው ቤተሰብ ያስተዳድራሉ፡፡ ብዙዎች በዚህ ዓይነት ይተዳዳራሉ፤ እኛም ከችርቻሮ ንግድ መውጣት እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ አከፋፋዮች እስካሁን ችግር ስላላገኘንባቸው ቀጣይ ዕቅዳችን ከችርቻሮ ንግድ ወጥተን ወደ ዳቦ ኢንዱስትሪ መግባት ነው፡፡
አከፋፋዮች የሚሸጡበት ዳቦ የእናንተን የጥራት ደረጃ ማሟላቱን እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት?
እንደገለጽኩት እነሱ ዳቦ አይጋግሩም - ከእኛ ወስደው ነው የሚሸጡት፡፡ እየተዘዋወሩ የሚቆጣጠሩ ሱፐርቫይዘሮች አሉን፡፡ የሌላ ዳቦ ቤት ዳቦ እንዳያስገቡና ከዳቦ ጋር የማይስማማ ነገርም ጨምረው እንዳይሸጡ ይቆጣጠራሉ፡፡ ለምሳሌ ከእኛ ዳቦ ጋር ወተት እንዲሸጡ አንፈቅድላቸውም። ምክንያቱም በፆም ጊዜ ወተት መኖሩን ከሃይማኖት ጋር የሚያያይዙ ሰዎች ስላሉ ደስ ላይላቸው ይችላል። ሌላው ደግሞ ወተት ዝንብ የመሳብ ባህርይ አለው። በዚህ ረገድ ወተት ታሽጐ ስለሚቀርብ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ዳቦ ግን እንዲሁ ነው የሚሸጠው፡፡
ለምን እናንተ ዳቦ አሽጋችሁ አታቀርቡም?
ልክ ነው፡፡ በውጭ አገር ዳቦ ታሽጐ ነው የሚቀርበው፡፡ እኛም ሞክረን ነበር፡፡ ሰው ግን የታሸገ ዳቦ የቆየ ስለሚመስለው እሺ አይልም፡፡ እኛማ የሚቀለን እሱ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት የተጋገረ ዳቦ አሸግንና እንዲሁ አቅርበን የታሸገውን ስንሰጠው አይገዛም፡፡ “ከዚያኛው ከትኩሱ ስጠኝ” ይላል። ዳቦ ሲታሸግ ከዝንብና ላዩ ላይ ከሚያርፍ ቆሻሻ ነገር ይጠበቃል፡፡ ሕዝቡ እንቢ አለ እንጂ ሞክረን ነበር፡፡ ወደፊት ኅብረተሰቡ የአመለካከት ለውጥ ያደርግና ሁሉም ዳቦ ቤቶች ዳቦ አሽገው ያቀርባሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ግን አሁንም ቢሆን አሽገን የምናቀርባቸው ምርቶች አሉን፡፡
ቁጥጥር ስናደርግ ከሌላ ቦታ ረከስ ባለ ዋጋ ጥራቱ አነሰ ዳቦ አስገብተው ሲሸጡ ያገኘናቸው አከፋፋዮች አሉ፡፡ እነሱን ዘግተናቸዋል፡፡ የዳቦ ጥራት የሚታወቀው በግብአቱ ነው፡፡ የማይሆን ርካሽ ዘይት ይጠቀሙና ጣዕሙን ያበላሹታል፡፡ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደግሞ እርሾ፣ ዘይት፣ … የሚቀንሱ አሉ፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ዱቄት ሳይቀር የሚጠቀሙ አሉ፡፡ እኛ ግን ትርፋችን የፈለገውን ያህል ይቀንስ እንጂ እንደዚህ አናደርግም።
ሸዋ ዳቦ ምን ያህል ሠራተኛ አለው?
ሲጀመር ከ20 እና ከ30 አይበልጡም ነበረ፡፡ አሁን ግን ከአንድ ሺህ በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉን - በዳቦና በዱቄቱ ማለት ነው፡፡
የሸዋ ዳቦ የስኬት ምስጢር ምንድነው?
ማንኛውም ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በተለይ ምግብ ነክ ሲሆን የበለጠ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ እኛ የምናመርተው ዳቦ የት ይሄዳል? ማን እጅ ይገባል? ብሎ ማሰብ ይፈልጋል፡፡ ሸዋ ዳቦ፣ በጥራት ጉዳይ ላይ በፍፁም ድርድር አያውቅም፡፡ ዱቄት ስንገዛ ተጠንቅቀን ነው፡፡ ስንዴም ከገዛን መጀመሪያ ሞክረን ነው፡፡ ትርፍ ለማብዛት ብለን ያገኘነውን አንገዛም፡፡ እርሾም ስናስመጣ ጥራቱ የተጠበቀና መጨመር ያለበት መጠንም መቀነስ የለበትም። ጨውም ሆነ ዘይት እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች ጥራታቸው የተጠበቀ ነው የምንጠቀመው፡፡ ለምሳሌ የምንጠቀመው ዘይት 1ኛ ደረጃ ነው፡፡ ጥራቱን ያልጠበቀ ዘይት በፍፁም አንጠቀምም፡፡
ዘይት ለባትራው (ለመጋገሪያው) ነው?
አዎ! ለባትራው ብቻ ሳይሆን በተወሰነ መጠን ላይ ይጨመራል፡፡ እህሉን እያየን ነው የምንጨምራቸውን ነገሮች ፐርሰንቴጅ የምንወስነው። ለምሳሌ ውሃ የማያነሳና የሚያነሳ እህል አለ፡፡ የሚያነሳው ላይ ጨው ስንጨምር ተጠንቅቀን ነው፡፡ ዝም ብለን ጥሬውን ጨው አንጨምርም፡፡ በውሃ አሟሙተንና አጣርተን ነው፡፡ ምክንያቱም ዝቃጩ አሸዋና ሌላም ነገር ስለማያጣ ተጠንቀቀን ነው፡፡
የዳቦ ዋጋ ከጫማ ማስጠረጊያ ዋጋ በታች ነው። ከእንጀራ ጋር ካየነው ደግሞ አንድ እንጀራ ከዳቦ ዋጋ ከሦስት እጥፍ በላይ ይበልጣል። ሁለቱን ስናስተያይ ግን ምንም የጥራት ለውጥ የለም፡፡ እንዲያውም ዳቦ የሚበልጥበት ጊዜ አለ፡፡ ስለዚህ የእኛ የስኬት ምስጢር ታማኝነት፣ ጥራትና አቅርቦት ነው፡፡ አቅርቦት ካልተሟላ ገንዘብ እያለህ መግዛት አትችልም፡፡ የአባቴ የዳቦ ባለሙያነት፣ ሥራ ወዳድነት፣ ጥንካሬና ታታሪነት ሳይዘነጋ ማለቴ ነው፡፡ አቶ ዘሙይ ዳቦውን በማየት ብቻ ይኼ ነገር ጐድሎታል የሚሉ ባለሙያ ናቸው፡፡ እኛም ከእሳቸው ተምረን የማንኛውንም ዳቦን ጥራትና ደረጃ በማየት ብቻ እንለያለን፡፡ በዓመት 365 ቀናት እየሠራን ነው፡፡ ሱቆቻችን ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ለሸማቾች ክፍት ናቸው-በዓል ሆነ አልሆነ ሸዋ ዳቦ ከተከፈተበት ዕለት ጀምሮ በር ዘግተን አናውቅም፡፡
ሠራተኞቻችሁ በአስተዳደሩ ምን ያህል ደስተኞች ናቸው?
ሠራተኞቻችን ዋነኞቹ የስኬታችን ምንጮች ናቸው፡፡ ሠራተኞቻችን ደከመን ሰለቸን ብለው አያውቁም፡፡ ሌሊትም ቀንም እንሠራለን፡፡ ሌሊት ሽያጭ የለም እንጂ ከተለያዩ ድርጅቶች (ከሆስፒታሎች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጦር ካምፖች…) ትዕዛዝ እንቀበላለን፡፡ እኛም ሠራተኞቻችን ምስጋና ይግባቸውና አናሳፍርም፤ በትዕዛዙ መሠረትና በተጠየቅነው ጊዜ እናቀርባለን-የቱንም ያህል ትዕዛዙ ብዙ ቢሆን፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ የሠሩ ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህን ያህል ጊዜ አብረውን የቆዩት በአስተዳደራችን ደስተኛ ስለሆኑ ይመስለኛል።
የአንድ ሠራተኛ ትንሹና ትልቁ ደሞዝ ምን ያህል ነው?
የተለያየ ደረጃ አለ፡፡ ገና ምንም የማያውቅ ሰው ሲቀጠር (Starting Salary) ከ700 ብር በላይ ነው። ትልቁ ደግሞ ከ8ሺህ በላይ ነው፡፡ ከሙከራ ጊዜ በኋላ ደግሞ ይጨመርለታል፡፡ በዋጋ ግሽበቱ የተነሳ ኑሮ ስለተወደደ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከ200 ፐርሰንት በላይ የደሞዝ ማስተካከያና ጭማሪ አድርገናል፡፡ ከትርፍ ጋር የተያያዘ ሳይሆን በኅብረት ስምምነታችን መሠረት በዓመቱ መጨረሻ ቦነስ እንሰጣለን፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
አሁን በጀመርነው የዳቦ ኢንዱስትሪ መቀጠል ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ ኩኪስ መግባት እንፈልጋለን። ፓስታና ማካሮኒም ለማምረት ዕቅድ አለን፡፡ የስንዴ እርሻም ለመጀመር ሐሳቡ አለ፡፡ አረማመድን በጥንቃቄ ካልመሩ በስተቀር እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ጥሩ ስለማይሆን ከአቅማችን በላይ አንሄድም፡፡ ሁሉንም ባይሆን ከ95 በመቶ በላይ ሠራተኞቻችንንና ደንበኞቻችንን ያስደስት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ እስካሁን አብረውን የተጓዙትን እናመሰግናለን፤ እናከብራለን፡፡
ለዱቄት የምንጠቀምባቸው ሁለት የጭነት መኪኖች፣ ውስጣቸው በሞላ በአሉሚኒየምና በደረቅ ስፖንጅ የተሸፈነ ዳቦ በየቦታው የምናመላልስባቸው 8 መኪኖች አሉን፡፡ እነዚህን ረዥም ጊዜ አንጠቀምባቸውም፡፡ በሁለትና በሦስት ዓመት እንቀያይራቸዋለን፡፡ ሸዋ ዳቦ የራሱ ሪል እስቴትም ብዙ አለው፡፡ በአዳማም ብዙ ንብረቶች አሉን፡፡
በአሁን ሰዓት ሸዋ ዳቦ ካፒታሉ ምን ያህል ነው?
ቁጥሩ በእጄ የለም፡፡ ግን እጅግ ብዙ ነው ብዬ ብደመድም ጥሩ ነው፡፡ የተሳሳተ ቁጥር ባልናገር ይሻላል፡፡

Read 6917 times