Monday, 16 September 2013 08:02

ኢትዮጵያዊው ባለሀብት በሞስኮ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

አቶ ተፈራ የኋላወርቅ በባህርዳር አካባቢ በሚገኝና “መሸንቲ” በተባለ የገጠር መንደር የተወለዱ የገበሬ ልጅ ናቸው፡፡ በቴክስታይል እና በማይኒንግ ኢንጅነሪንግ ሁለት ዲግሪ ያላቸው አቶ ተፈራ፤ በሞስኮ ከተማ “አቬኑ አፍሪካ” በተባለ የራሳቸው ባርና ሬስቶራንት ማናጀር ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ግሩም ሠይፉ 14ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመዘገብ ወደ ሞስኮ በሄደበት ጊዜ አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ቃለምልልሱን እነሆ:-

ራሺያ ከመግባትዎ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ሰርተዋል?
ራሺያ ከመጣሁ እነሆ 27 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በ1986 እ.ኤ.አ በደርግ ስርዓት የመጣሁት፡፡ በግሌ ባገኘሁት የነፃ ትምህርት ዕድል ከባህርዳር ፖሊቴክኒክ በቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተመርቄያለሁ፡፡ ይህን ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ በአዲስ አበባ ለስድስት ወራት ያህል እንደሰራሁ ለኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ተከላ ከተመረጡ ሠራተኞች አንዱ ነበርኩ፡፡ የባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ፣ የተግባረዕድና የዊንጌት ተማሪዎችም ለተመሳሳይ ተግባር ተመድበው ነበር፡፡ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካው መሣሪያዎች ከውጭ የገቡ ሲሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን በመትከል ልምድ ካላቸው አፍሪካውያን ጋር ሆነን ሰርተናል፡፡ የደርግ ባሰስልጣናት የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካን ለ10ኛው አብዮት በዓል አድርሱ የሚል ትዕዛዝ ሰጥተውን ነበር፡፡ በአስቸኳይ ትዛዝ ውስጥ ሆነን ሙሉ ፈረቃ ስንሰራ ሽንት ቤት ለመሄድ እንኳን በተራ ነበር፡፡
የፋብሪካውን ተከላ ለመጨረስ የተሰጠን ጊዜ አራት ዓመት ነበር፡፡ በዚያን ሰዓት በዲፕሎም ከቴክኒክ ትምህርት ቤት የተመረቀ ለመንግስት አገልግሎት ለሁለት ዓመት የመስራት ግዳጅ ነበረበት፡፡ እኔ ደግሞ ትምህርቴን በውጭ አገር ለመቀጠል ፍላጐት ነበረኝ፡፡ ግዳጁን ባለመጨረሴ ግን አልቻልኩም፡፡ ነፃ የትምህርት ዕድል ለማግኘት የግዴታ የአኢወማ አባል መሆን እንዳለብኝም ተነገረኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የዩኒቨርስቲ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ምሩቃን የአኢወማ አባል መሆን አለባቸው የሚል ግዳጅና ብዙ ጭቅጭቅ ነበረ፡፡
ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ተብለን የተመደብነው 56 የፖሊ ቴክኒክ ምሩቃን ነበርን። ምደባው እንደአገራዊ ግዴታ ይታይ ነበር፡፡ ያኔ ደሞዙ 357 ብር ነበር፡፡ ከወጭ ቀሪ ተጣርቶ ወደ 290 ብር ይደርሰናል፡፡ በካምፕ ውስጥ ነበር የምንሰራው፡፡ በኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ ስሰራ ለመጀመርያ ጊዜ ከቤተሰብ ተለያይቶ መኖር እና የብቸኝነት ህይወት ያየሁበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ የረሃብ ነው፡፡ አይኔ እያየ ሰው የሚሞትበት ወቅት ነበር፡፡ ጠዋት ቁርስ ሰጥተናቸው ማታ ስንመለስ ሞተው የምናገኛቸው ሰዎች ነበሩ፡፡
የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ በቶሎ እንዲደርስ የተፈለገው ለምንድነው?
የአብዮቱ ፍንዳታ 10ኛ ዓመቱ ስለሆነ፣ ታላላቅ ፋብሪካዎች ግንባታቸው አልቆ ለበዓሉ ጊዜ ስራ እንዲጀምሩ በመፈለጉ ነው፡፡ ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ብቻ አልነበረም፡፡ ሙገር ሲሚንቶ፣ የናዝሬት ትራክተር ፋብሪካ፣ በአጠቃላይ አስር ትልልቅ ፕሮጀክቶች በዚያን ጊዜ ስራ መጀመር ነበረባቸው፡፡ የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ጣቃዎችን የሚያመርት ነበር፡፡ ፋብሪካው ለምርት ሙሉ ለሙሉ ሳይዘጋጅ ነበር ከአገሬ የመጣሁት፡፡
ከአገር ሊወጡ የሚችሉበት ምን አይነት አጋጣሚ ተፈጠረ?
ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ተከላ ላይ ለአንድ ዓመት እንደሰራሁ የነፃ ትምህርት ዕድል መጥቶ ስለነበር መውጣት ፈልጌ ነበር፡፡ ለወሎ ክፍለሀገር በመጣው ኮታ መስፈርቱን የሚያሟላ ተወዳድሮ ዕድሉን ማግኘት ይችላል ተባለ፡፡ ለመወዳደር ስንመዘገብ ማሟላት የሚገባን ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ከቀበሌ፣ ከወረዳ፣ ከአውራጃና ከክፍለሀገር ከሚመጡ ዕጩዎች ጋር ነበር ውድድሩ። ሆኖም በወረዳና በክፍለሀገር ደረጃ የነበሩት የአኢወማ መሪዎች የፓርቲ አባል ስለነበሩ ቅድሚያ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ስለዚህ እኛ በትምህርት ደረጃ ከፍተኛ ነጥብ ቢኖረንም ዕድሉን ዘጉብን፡፡ እናም በመጀመሪያው ዓመት የመጣ ዕድላችን ተበላሸ። በሚቀጥለው ዓመት የነጻ ትምህርት የምትፈልጉ ሠራተኞች የአኢወማ አባል ካልሆናችሁ መሄድ አትችሉም ተባለ፡፡ ይህንኑ መስፈርት ለማሟላት በአኢወማ አባልነት ተመዘገብንና እኛው ራሳችን ምርጫ አካሄድን፤ በዲፕሎማ የነበረን 2.6 ነጥብ ውጤትና የምንሰራበት መ/ቤት የአገልግሎት ምስክር ወረቀትም ነበረን፡፡ በመጨረሻም የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተሳካ፡፡ በመጀመሪያ ጀርመን የመሄድ እቅድ ነበረኝ፡፡ ያኔ ግን ብዙ የነፃ ትምህርት ዕድል የነበረው በሶቭየት ኅብረት ነው፡፡
የነፃ ትምህርት ዕድሉ በሶቪየት ኅብረት ግዛት የት ዩኒቨርሲቲ/ኮሌጅ ነው የተገኘው?
ተወዳድሬ ባሸነፍኩት የነፃ ትምህርት ዕድል መሠረት፣ ከሌሎች ዕድሉን ካገኙ 3ሺ ተማሪዎች ጋር ራሽያ ገባሁ፡፡ ተቋሙም በትልቅነቱ በ2ኛ ደረጃ የሚታወቀው ድሮ “ፓትሪስ ሉቡምባ” ዩኒቨርሲቲ ይባል የነበረው ነው፡፡ ፓትሪስ ሉቡምባ የመጀመሪያውን የኮንጐ ኮምኒስት ፓርቲ ያቋቋመ መሪ ስለነበር ነው የዩኒቨርሲቲው ስያሜ ለእሱ መታሰቢያ ተደርጐ የነበረው፡፡ እኛ በዩኒቨርሲቲው መማር ስንጀምር፣ ከተለያዩ አገሮች በተለይ ሶሻሊስት ከነበሩት የሚመጡ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነ ደቡብ አፍሪካ፣ ኩባ፣ ምስራቅ ጀርመን የመሳሰሉት አገራት ተማሪዎችን ይልኩ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሶሻሊዝም ስርዓትን ከሚከተሉ አገራት የሚመጡ ተማሪዎችን የማስተናገድ ትኩረት ነበረው፡፡ ዛሬ ግን ዩኒቨርሲቲው ያኔ የነበረው ኮሚኒስታዊ ትኩረት ተቀይሮ ከመላው ዓለም በርካታ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስተምር ሆኗል፡፡ እዚያ ዩኒቨርሲቲ ያለምንም ችግር ገባሁ፡፡ ለመማር የመረጥኩት ትምህርት ማይኒንግ ኢንጂነሪንግ ነበር፡፡
ለመሆኑ ራሽያ ስትገቡ የአገሪቱ አጠቃላይ ገጽታ ምን ይመስል ነበር?
ራሽያ እንደገባሁ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጋጨሁት ከአየር ፀባዩ አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የኮምኒስት ስርዓት ስለነበር፣ የአገሬው ሰው የውጭ ዜጋ ሲያይ ብርቁ ነበር፡፡ አቀራረባቸው እና እንክብካቤያቸው የተለየ ነበር፡፡ የፀጥታ ኃይሎች እኛን የሚተናኮል ሰው ካለ መብታችንን በማስከበር ይደግፉን ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ዘረኝነትም ብዙ አልነበረም፡፡ ግን አንዲት ራሽያዊት ሴት ከጥቁር ሰው ወይንም ከሌላ አገር ዜጋ ጋር ግንኙነት ቢኖራት ያባርሯት ነበር፡፡ የራሽያ ሴቶች ከእኛ ጋር ጓደኛ የሚሆኑት ተደብቀው ነበር፡፡
ከቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ሙያ ወደ ማይኒንግ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ለመቀየር ለምን ወሰኑ?
ይገርምሃል ያን ጊዜ የቴክስታይል ኢንጂነሪንግ ተምሬ ከተመረቅሁና ከዚያም በኋላ ስራ ስጀምር በዚህ የሙያ ዘርፍ በብዛት የተሰማሩት ሴቶች ነበሩ፡፡ እናም የሴቶች ሙያ እየመሰለኝ ለምን ይሄን የትምህርት መስክ አጠናሁኝ እያልኩ እቆጭ ነበር፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽንና ሌላ ዓይነት መሠረተ ልማት ላይ የሚያሰማራ ሙያ እፈልግ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሰው ኃይል የሌለበትና አዲስ የሆነ የትምህርት መስክ ባገኝ እያልኩ አስብ ነበረ፡፡ እናም በማይኒንግ ኢንጅነሪንግ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የተማረ ሰው እንደሌለ በመገንዘቤ፣ በራሽያ ያገኘሁትን የነፃ ትምህርት ዕድል በዚህ የሙያ መስክ አድርጊያለሁ፡፡
ትምህርቴን የጨረስኩት ከ5 ዓመታት በኋላ ነው፡፡ አንድ ዓመት የራሽያ ቋንቋ መማር ግድ ነበር፡፡ የተመረቅኩት በማስተር ኦፍ ሳይንስ¸ኤንድ ኢንጅነሪንግ የዲግሪ መርሐግብር ነው፡፡ ትምህርቱን እንደጨረስኩ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ፡፡
ያን ጊዜ በአገር ቤት ያለው ሁኔታ ምቹ ነበር?
ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በጠቅላላው የአገሪቱ ሁኔታ እየተቀያየረ ነበር፡፡ የኑሮው ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ራሽያ ተመልሼ ለመስራት ወይም ለመኖር ወሰንኩ፡፡ ተመልሼ ወደ ራሽያ ስገባ ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ በኪሴ የነበረው ይገርምሃል 20 ዶላር ብቻ ነበር፡፡ ዋናው የተማመንኩበት ነገር ትምህርቱን እንደጨረስኩ ሚስት ማግባቴ ነው፡፡ ባለቤቴ ራሽያዊት ናት። እሷን ከማግባቴ በፊት እንግሊዝ አገር ለመሄድ የምችልበትን ዕድል አግኝቼ ቪዛ ሁሉ አስመትቼ ነበር፡፡ ራሽያዊቷን ባለቤቴን ትቼ ወደ እንግሊዝ መሄዱን ስላልፈለግሁት በራሽያ ኑሮዬን ለመቀጠል ወሰንኩ፡፡ በርግጥ በዚያን ወቅት በራሽያ የነበረው አጠቃላይ ሁኔታና አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡
የራሽያና የኢትዮጵያ ግንኙነት የቀዘቀዘበት ጊዜ ስለነበር ያ ሰአት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ትምህርቴን ብጨርስም በራሽያ ለመኖር የመኖሪያ ፈቃድ የለኝም፡፡ በሌላ በኩል የዘር ልዩነት ከፍተኛ ተጽእኖ ያስከትል ጀምሮ ነበር፡፡ የሚገርምህ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ የምበላው ነገር እንኳን አልነበረኝም፡፡ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡
የመጀመርያው አማራጭ ያደረግነው በመንገድ ላይ ዕቃዎችን የመቸርቸር ንግድ ውስጥ መግባት ነበር፡፡ በወቅቱ ሚክሲድ ኢኮኖሚ ተጀምሮ ነበርና እንደሩስያዎቹ መንገድ ላይ መነገድ መስራት ጀመርኩ፡፡ የሽግግር ጊዜ ስለነበር ከቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ እና ከሌሎች አገራት የሚገቡ ዕቃዎች ነበሩ፡፡ የራሽያዊቷ ሚስቴ ጓደኞች ነጋዴዎች ነበሩና ከእነሱ ዕቃዎችን እያመጣሁ በመንገድ ላይ መቸርቸር ጀመርኩ፡፡ የማልሸጠውና የማልቸረችረው የዕቃ አይነት አልነበረም፡፡ ሱሪ፣ ካልሲ፣ ካኔታራ፣ የሴቶች ልብሶች በቃ በያይነቱ ዕቃዎችን እቸረችር ነበር። ገበያው ልክ እንደመርካቶ ነበር፡፡ መንገድ ላይ በመለስተኛ ጠረጴዛ ዕቃዎችን ደርድሬ በችርቻሮ ስነግድ ቆይቼ፣ መጨረሻ ላይ የራሴን የችርቻሮ መደብር ከፈትሁ፡፡ በጐዳና ላይ የችርቻሮ ንግድ ለ4 ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በእነዚያ ጊዜያት ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን ቀጥሬ ማሰራትም ችያለሁ፡፡ ይህን የችርቻሮ ንግድ የምሰራው ፓታሮቭባ በተባለ አካባቢ ነበር፡፡ አሁን ይህ የገበያ ቦታ ተዘግቷል፡፡
ሩስኪዎች ቮድካና ኮኛክ እየጠጡ ሲሰሩ፣ እኔ ምንም ሳልጠጣ በበረዶ ላይ ቆሜ በረዶ ፊቴ ላይ እየደረቀና እየተሰበረ፣ ከብርድ የሚከለክል “ቫሌንኮ” የተባለ ቦቲ ጫማ አድርጌ እሰራ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት እከፍል የነበረው ለራሺያዊቷ ባለቤቴ ፍቅርና ለትዳራችን አክብሮት ስል ነው፡፡ እሷን ትቼ መሄድ አልፈለግሁም፡፡ ያንንም በተግባር አስመሰከርኩኝ፡፡ ለ4 ዓመታት በጐዳና ንግድ ስሰራ ቆይቼ የራሴን ኩባንያ አቋቋምኩ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ስለነበር ኩባንያውን ያቋቋምኩት ብዙም ገንዘብ ሳይኖረኝ ነበር፡፡ ግን ምንም ተስፋ የቆረጥኩበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ መጀመሪያ የከፈትነው የኢትዮጵያ ሬስቶራንትን ነበር፡፡
የስራ መስክዎን ወደ ሬስቶራንት የለወጡት በምን ምክንያት ነው?
ዋናው ምክንያት የንግድ ስራው መቀዝቀዝ ነው፤ ብዙም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ በጐዳና ላይ ንግድ እሠራ በነበረበት ጊዜ በከፍተኛ ብርድ እና አስቸጋሪ አየር ሁኔታ ያሳለፍኩት ህይወት ለጤንነቴም አሳሳቢ ሆኖ ስለነበር ሃኪሞች ይህ ዓይነቱ ስራ አይበጅህም ብለው ከመከሩኝ በኋላ ነው ሬስቶራንት የመክፈት ሃሳቡን ያኘሁት፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተመካክሬ በመጀመሪያ የተለያዩ ምግቦችን የሚሸጥ መለስተኛ ሬስቶራንት ከፈትኩ፡፡ በምሠራበት ሬስቶራንት አካባቢ ደግሞ አንድ የውጭ ሬስቶራንት ነበር፤ እሱንም ተከራየሁኝ፡፡ ቦታው ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ብዙም አይርቅም ነበር፡፡ ሬስቶራንት ስጀምር ስለራሽያ ምግቦች አሰራር ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህም ራሽያውያን ምግብ አብሳዮችን ቀጠርኩ፡፡ እነሱን ቀጥሬ በማሰራት ምግቦቹን እንዴት እንደሚሠሩና እንደሚያዘጋጁ ማጥናትና መማሬን ቀጠልኩ፡፡
ከተፈጥሮም፣ ከቤተሰቦቼም ሊሆን ይችላል፤ ተስፋ መቁረጥ እና መሸነፍ አልወድም፡፡ ወላጆቼ ሲያሳድጉኝ ደጅ ቆይቼ በሆነ ነገር ተሸንፌ ወደ ቤቴ ብመጣ እንደ ልጅ አይቆጥሩኝም፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት አስተዳደጌ በእልህ እንድሰራ አድርጐኛል። የምግብ አሰራሩን በደንብ ከተማርኩ እና ካወቅሁ በኋላ ተከራይቼ እሠራ የነበረውን ቤት በመተው በሌላ ስፍራ ሰፋ ያለ ቦታ አፈላለግሁ፡፡ ፓትሪስ ሉቡምባ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ ሄጄ ቦታ ጠየቅሁ፡፡ ያንን ያደረግሁት ለተማሪዎች የሚያገለግል ምግብ ቤት በዩኒቨርሲቲው አካባቢ መክፈት ያስፈልግ እንደነበር ስለማውቅ ነው፡፡ በተለይ ለአፍሪካውያን የተለየ ሬስቶራንት አልነበረም፡፡ እናም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተመካክረን አብረን መስራት ጀመርን፡፡ ዶ/ር የዝናወርቅ ይባል ነበር፡፡ ከእሱ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ውላችን ፈረሰ፡፡ መጨረሻ ላይ ፓትሪስ ሉቡምባ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ የተከፈተውን ትልቅ ሬስቶራንት ሙሉ ለሙሉ ጠቅልዬ ያዝኩት፡፡ አሁን ይህ ሬስቶራንት “አቬኑ አፍሪካ” ይባላል፡፡ የአፍሪካ ጐዳና እንደማለት ነው፡፡
ባርና ሬስቶራንቱ በቀን ቢያንስ 50 ቢበዛ እስከ 100 ሰው ያስተናግዳል፡፡ የመላው ዓለም ምግብ አለ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ምግቦች፤ የብዙ አፍሪካ አገራት ምግቦችም በሬስቶራንቱ ይገኛሉ፡፡ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ምግቦችም ይሠራሉ፡፡ ለአፍሪካዊያን ተማሪዎችና ዲፕሎማቶች ዋነኛ መመገቢያ ሬስቶራንት ሆኗል፡፡ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮ ሲገቡ በቅድሚያ የሚጎበኙት የእኛን ሬስቶራንት ነው፡፡ “አቬኑ አፍሪካ ሬስቶራንት” በአሁኑ ጊዜ 15 ሠራተኞች አሉት፡፡ ሶስት አፍሪካዊ፣ ሁለት ራሽያዊና አንድ ኢትዮጵያዊ ምግብ አብሳዮች አለ፡፡ የእኔ ስራ ማኔጅመንት ነው፡፡ ባርና ሬስቶራንቱ በእኔና ሚስቴ ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡
ከአቬኑ አፍሪካ ባርና ሬስቶራንት በተለየ ኢንቨስትመንት ሊንቀሳቀሱ አቅደዋል? ብዙውን ጊዜ በውጭ አገር የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ በእርስዎ በኩልስ?
በአገሬ ኢንቨስት ለማድረግ የመጀመሪያ ሙከራ አድርጌ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ተወልጄ ያደግሁት ባህርዳር ነው፡፡ በአንድ ወቅት በትውልድ ቦታዬ ኢንቨስት ለማድረግ መጥቼ ለከተማው ባለስልጣናት የኢንቨስትመንት ዕቅዴን ሰጥቼ ነበር። የት እንዳስገቡት አላውቅም፡፡ በተወለድኩበት፣ ባደግኩባትና በተማርኩባት ከተማ ላይ በተለይ ትራንስፖርትን በተመለከተና የከተማዋን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዤ ነበር የሄድሁት። የከተማ ቆሻሻዎችን ለማጥፋት የሚችል ልዩ ቴክኖሎጂ ነበር፡፡ ይህን እቅድ ወደፊትም የምተወው አይደለም። ሌላ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በቱሪዝም መስክ ለመንቀሳቀስ በነበረኝ እቅድ የጀመርሁትም ስራ ነበር፡፡
ከአንድ ሰው ጋር ለመስራት የቱሪዝም መኪና ሁሉ አስገብቼ ባለመግባባት እና እምነት በማጉደል ልሠራበትና ውጤት ላመጣበት አልቻልኩም። በክስ የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ግን በአገሬ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ያለኝን እቅድ አይቀይሩትም፡፡ ተስፋም አላስቆረጡኝም፤ እናም ወደ ኢትዮጵያ እመለሳለሁ፡፡ ስመለስ ግን ባዶ እጄን አይደለም፡፡ ያስተማረኝን ህብረተሰብ በጭራሽ ልረሳው አልፈልግም፡፡ በሞስኮ ነዋሪ ሆኜ በተለያዩ የንግድ መስኮች ስንቀሳቀስ ጊዜ ፈተናዎች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ በአንድ አገር የውጭ ዜጋ ሆኖ በሚሰራ ማንኛውም ሰው ላይ ፈተናዎች መኖራቸው በየትኛውም የዓለም ክፍል የተለመደ ነው፡፡ በሞስኮ ስሰራ የእኔና የባለቤቴን መኪና፣ የምንሰራበትን ቦታ፣ ልጆቼ ምን እንደሚለብሱና የት እንደሚማሩ እየተከታተሉ የሚበሳጩ አሉ፡፡ ይህ አንዱ ፈተና ነው፡፡ ይሄ ጥቁር ሰው እንዴት አገራችን ገብቶ ሃብት አካበተ ብለው ሊናደዱ ይችላሉ፡፡ እኔና ባለቤቴ ሃቀኛ እና ቁርጠኛ ሰዎች ነን፡፡ የሰው አንነካም፤ የራሳችንንም አናስነካም፡፡
እስቲ ስለራሽያዊቷ ባለቤትዎ ይንገሩ…?
ባለቤቴ ማርቼንኮ ትባላለች፡፡ የ3 ልጆች እናት ናት፡፡ ለሦስቱም ልጆቼ ኢትዮጵያዊ ስም አውጥቼላቸዋለሁ፡፡ የመጀመሪያ ልጄ 20 ዓመቷ ሲሆን ማርያ ትባላለች፡፡ በማይኒንግ ኢንጂነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ሌሎቹ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው አስቴር እና የ5ኛ ክፍል ተማሪዋ ኤልሳ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ወገኖቼ ራሽያዊ ሚስቴን ጐጃሜ ይሏታል፡፡
ያለምክንያት አይደለም። የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችን መስራት ትችላለች፡፡ የሬስቶራንቱን የምግብ አሰራር የምትቆጣጠረው እሷ ነች። የምግብ ባለሙያነቷ ጐጃሜ ያስመስላታል፡፡ ልጆቼን በኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ነው አስተዳደግ የማሳድጋቸው፡፡ አማርኛ መናገር ብዙ አይችሉም። ቋንቋውን መማር አለባቸው፡፡ ለመግባቢያ እንግሊዝኛ እና ራሽያኛ ብንጠቀምም አማርኛ ማወቅ አለብን እያልኩ እየመከርኳቸው ነው፡፡

Read 3768 times