Print this page
Monday, 16 September 2013 07:59

የአዲስ ዓመት አስገራሚ ገጠመኜ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(7 votes)

2005 ሊገባ ሁለት ቀን ሲቀረው ነው፤ ጳጉሜ 3 ቀን 2004 ዓ.ም፡፡ ጊዜው ወደ አስር ሰዓት ገደማ ይሆናል፡፡ የቢሮ ስራዬን አጠናቅቄ ለበዓል ዝግጅት ወደ ቤቴ በመጓዝ ላይ ነበርኩ፡፡
ከ22 በታክሲ ተሳፍሬ ፒያሳ ደረስኩኝ፡፡ ወደ ሰፈሬ የሚወስደኝን ታክሲ ለመያዝ “መኮንን ባር” ፊት ለፊት ልደርስ ጥቂት ሲቀረኝ “የኔ እህት” የሚል የትልቅ ሰው ድምፅ ተሰማኝ፡፡ ዞር አልኩኝ። መጀመሪያ ሰውየውን የማውቃቸው መስሎኝ ነበር። ግን አላውቃቸውም፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን።
“ከየት ነው? ከስራ ነው ከትምህርት?” ጠየቁኝ። ከስራ እየተመለስኩ መሆኔን ገለፅኩ፡፡
ሰውየው እድሜያቸው በግምት በ60ዎቹ መጀመሪያ ይሆናል፡፡ አለባበሳቸውና ኮፍያቸው የወጣት አይነት ነው፡፡ ዘንጠዋል፡፡ “እባክሽ ሻይ ልጋብዝሽ” ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እንደምቸኩል ገለፅኩላቸው፡፡ የእውነትም ቸኩዬ ነበር፡፡
“በዓልን እንዴት ልታሳልፊ አስበሻል?” ጥያቄው ቀጠለ፡፡
ሰውዬው ለምን ያደርቁኛል ስል ተበሳጨሁ። ሆኖም ትልቅ ሰው በመሆናቸው ታግሼ ጥያቄያቸውን ከመመለስ ያለፈ ምንም ላደርግ አልቻልኩም፡፡
“ቀለል አድርጌ ነው የማሳልፈው” አልኳቸው። መንገድ ላይ ቆመን ስናወራ አላፊ አግዳሚው በትኩረት ይመለከተን ነበር፡፡ “ሹገር ዳዲዋ ይሆናል” ብለው የገመቱ እንደነበሩ ቅንጣት አልተጠራጠርኩም፡፡
“ከቤተሰብ ጋር ነው ለብቻሽ የምትኖሪው?” ቃለ-ምልልሱ ቀጥሏል፡፡
“ይሄ ጥያቄ ይለፈኝ” አልኳቸው፡፡ ብቻዬን ነኝ ካልኩኝ መጥተው ተከርቸም የሚገቡ ስለመሰለኝ ነው፡፡
“ለምን መሰለሽ? እኔ በበዓል አንድ ልምድ አለኝ” አሉኝ፡፡
“ምንድነው ልስማዋ” አልኳቸው፡፡ ወደ ቤቴ የምገባበት ጊዜ በጣም ናፍቆኛል፡፡ እንዲህ መቆሜ ካልቀረ ምናለ የሻይ ግብዣውን ተቀብዬ ትንሽ አረፍ ባልኩኝ ስል ተቆጨሁ፡፡
“ላለፉት 20 ዓመታት ካናዳ ቶሮንቶ ነው የኖርኩት፤ የካናዳ ዜግነትም አለኝ፤ እዚህ መኖር ከጀመርኩኝ አራት አመታትን አስቆጥሬያለሁ” በማለት ጥቂት ስለራሳቸው ነገሩኝ፡፡ እኔ ደግሞ ልምድ አለኝ ያሉትን ነገር ቶሎ ነግረውኝ ወደ ቤቴ ብሄድና የበዓል ዝግጅቴን ባካሂድ ምኞቴ ነበር፡፡
“እስኪ ልምድዎትን ይንገሩኝ” አጣደፍኳቸው፡፡
“በዓመት ሁለት ጊዜ ለአዲስ አመትና ለፋሲካ ለሁለት ለሁለት ሰዎች የበግ ስጦታ አበረክታለሁ” አሉኝ፡፡
“በጣም ጥሩ ልምድ ነው፤ ግን በጉን ለመስጠት መስፈርትዎ ምንድነው?” ስል ጠየቅኋቸው፡፡
“በቃ እየሄድኩኝ ድንገት አጠገቤ ያገኘሁትን ሰው አናግሬ እሰጣለሁ፤ አንቺም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነሻል” ብለውኝ አረፉት፡፡
“ሰውየው ይቀልዳሉ እንዴ?” አልኩኝ በሆዴ። እውነት ለመናገር አላመንኳቸውም፡፡ ሰውዬው አገባባቸውን አሳምረው ምን ሊጠይቁኝ ነው እያልኩ መብሰክሰክ ጀምሬአለሁ፡፡
“ምነው ቅር አለሽ እንዴ? ደስ አላለሽም?” ዝም አልኳቸው፡፡ “ለማንኛውም አንቺንም አላቆይሽ፤ እኔም አይምሽብኝ ስልክሽን ስጭኚና ነገ ዋዜማው ነው ከሰዓት በኋላ በጉን አመጣልሻለሁ” አሉ ኮስተር ብለው፡፡
“እንዴ የምርዎትን ነው እንዴ?” ስላቸው ከት ብለው ሳቁ፡፡ ነገሩ የባሰ ግራ አጋባኝ፡፡
“ስልኬን እንኳን አልሰጥም በጉ ይቅርብኝ እንጂ” አልኳቸው፡፡ “ግዴለሽም የእኔ ልጅ፤ ስልክሽን ስጪኝ ጥርጣሬሽና ፍራቻሽ ይገባኛል ግን በእኔ ይሁንብሽ” በማለት እንደምንም አግባብተው ስልክ ቁጥሬን ተቀበሉኝና የእሳቸውንም ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡
የሰውየው ሁኔታ ሲያስገርመኝ አመሸ፡፡ በነጋታው የበዓል ስራዎቼን ስከውን ስለ ዋልኩ ጉዳዩን እረስቼው ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ 11 ሰዓት አካባቢ ሰውየው ደወሉ፡፡ እናም ሰፈሬን ፣የት ቦታ ቆመው እንደሚጠብቁኝ ጠየቁኝ፡፡ አሁን ፍርሃት ፍርሃት አለኝ፡፡ ሰውየው የሆነ ነገር አስበው ነው እንጂ እንዴት እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ እያልኩ ከሰፈሬ ራቅ ያለ ቦታ እንዲጠብቁኝ ምልክት ሰጠኋቸው፡፡
ከዚያ በኋላ አንድ ፖሊስ ዘመዴ ጋ ደውዬ ቶሎ እንዲመጣልኝ ነገርኩት፡፡ ዘመዴም የሆነ ነገር ገጥሟት ነው በሚል ፈጥኖ መጣልኝ፡፡ የጓደኛዬ ወንድም በቅርቤ ስለነበረ ፖሊሱ ዘመዴና ይህ የጓደኛዬ ወንድም ከኋላ ከኋላዬ በቅርብ ርቀት እንዲከተሉኝ ነግሬያቸው፣ ሰውየውን ወደቀጠርኩበት ቦታ አመራሁ፡፡ ጥቁር ፒክ አፕ መኪና ይዘዋል፡፡
ጥቁር መነፅር አድርገዋል፡፡ ነገሩ ጥቁር በጥቁር ሲሆንብኝ የባሰ ፍርሃት ለቀቀብኝ፡፡ ሆኖም የኋላ ደጀኖቼን በመተማመን ወደ ሰውየው ቀረብኩ፡፡ ከመኪና ወርደው የሞቀ ሰላምታ ከሰጡኝ በኋላ “ስጦታዬን ትወጂዋለሽ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እስኪ እይው” በማለት መኪናው ላይ እግሩን ተጠፍሮ ታስሮ የተጋደመውን ነጭ በግ አሳዩኝ፡፡ በጣም ትልቅና ግርማ ሞገስ ያለው በግ ነው፡፡ በጣም ተገረምኩ፡፡ ምንም የምናገረው ነገር አጣሁ፤ አንደበቴ ተለጎመ፡፡ “ቤትሽ ቅርብ ከሆነ የሚሸከምልሽ ሰው ጥሪ፤ የተሸከመበትን እከፍልልሻለሁ” አሉ፡፡ ተሸካሚ ተጠራ፡፡ ተሸካሚው እስኪመጣ እንዲህ አጫወቱኝ፤
“ላለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ከጀመርኩ አንስቼ ይህን አደርጋለሁ፤ የዘንድሮው ባለዕጣዎች የፒያሳ አካባቢ ሰዎች ናቸው” አሉኝ፤ “በመጀመሪያው ዓመት መርካቶ እና አብነት አካባቢ፣ በሁለተኛው ዓመት ኮተቤና ጎተራ፣ሶስተኛው ዓመት ላይ ፈረንሳይና ጦር ሀይሎች፤ አራተኛው አመት አሁን ፒያሳ በአንቺ ጀምሬአለሁ፤ የፋሲካው ተረኛ የትኛው ሰፈር እንደሆነ ገና አልወሰንኩም” አሉኝና ሳቁ፡፡ እኔም ተገረምኩኝ፡፡ ከዚያም ባለ አንድ ሺህ ስድስት መቶ ብር የጠገበ በግ ሰጥተውኝና፣ መልካም በዓል እንዲሆንልኝ ተመኝተው መኪናቸውን አስነስተው ተፈተለኩ፡፡ እኔም ከኋላ ያስከተልኳቸው የ“ደህንነት” ሰራተኞቼን ራቅ ብለው ከቆሙበት ጠርቼ እየተሳሳቅንና እየተገረምን ወደ ቤታችን ሄድን፡፡
እውነት ለመናገር ከዚያ በኋላ ይደውላሉ ብዬ ጠብቄ ነበር፤ ነገር ግን ይሄው አንድ አመት ሞላቸው፤ ደውለውም ደውዬም አላውቅም፡፡ የዘንድሮው የሰውየው የበግ ስጦታ የት ሰፈር ገብቶ ይሆን? የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
እኔ ግን በድጋሚ የበግ ስጦታው የሚደርሰኝ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ “ሰርፕራይዝ” የማድረግ ወይም የመደረግ ልምድ ያላችሁ እስቲ ገጠመኛችሁን አካፍሉን፡፡
መልካም አዲስ አመት!!

Read 4042 times