Monday, 16 September 2013 07:48

ጅግራ ያዝ፡፡ ሩጫ ከፈለክ ልቀቃት፣ ሥጋ ከፈለክ እረዳት!

Written by 
Rate this item
(8 votes)

በጥንት ጊዜ አንድ ሰው ወደ ጐረቤቱ ማሳዎች ተደብቆ በመዝለቅ እህል አጭዶ ሊሰርቅና ሊወስድ ወሰነ፡፡ “ከሦስቱም ማሳዎች ትንሽ…ትንሽ አጭጄ ብወስድ አይታወቅም፡፡” በማለት ራሱን አሳመነ፡፡ “ለእኔ ግን ከሁሉም ማሳዎች የምሰበስበው ብዙ ይሆንልኛል፤” በማለት አሰበ፡፡
ስለዚህ ሰውየው ቀኑ ሲጨላልምና ደመናው ሲከብድ ያሰበውን ስርቆት ተግባራዊ ለማድረግ ተነሳ፡፡ ደመናው ጨረቃዋን ሲሸፍናትና አካባቢው ሲልም ሴት ልጁን ይዞ፣ ከቤቱ ወጣና ተሹለክልኮ ከማሳዎቹ ዘንድ ደረሰ፡፡
“ትሰሚያለሽ…ልጄ…የሆነ ሰው ካየኝ ንገሪኝ፡፡ እዚህ ጋ በትጋት ቁሚና ጠብቂ” በማለት ትንሿን ልጁን አዘዛትና እርሱ ወደ አንዱ ማሳ እየተንሿከከ ገባ፡፡
ሰውየው በመጀመሪያው ማሳ ገብቶ እያጨደ ስርቆቱን ተያያዘው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ልጅቷ “አባቴ ኧረ እየታየህ ነው!” አለችው፡፡
ቆም ብሎ ዙሪያውን ሲመለከት ምንም ነገር የለም፡፡ የቻለውን ያህል አጭዶና ተሸክሞ ወደ ሁለኛው ማሳ ገባና ያጭድ ጀመር፡፡
“አባቴ አሁን ታይተሃል” በማለት ልጁ ተናገረች፡፡ ማጨዱን አቁሞ፣ አሁንም አካባቢውን ማተረ። ምንም ነገር ስላልታየው አጭዶ የሠረቀውን ሰበሰበና ወደ ሦስተኛው ማሳ ገባ፡፡ እዚያም ማጨድ እንደጀመረ፣ “አባቴ ኧረ እያዩህ ነው ታይተሃል!” እያለች ልጅቷ ጮኸች፡፡
ሌባው ሰውዬ አካባቢውን ቢቃኝም የሚታየው ነገር ስለሌለ ስርቆቱን ጨርሶ የሰበሰበውን አስሮ ተሸከመ፡፡ ወደ ልጅቷ ተጠግቶ “ማንም ሰው ሳያየኝ “አዩህ” እያልሽ ለምን ታስጨንቂኛለሽ?!” በማለት እየተናደደ ተቆጣት፡፡
“አባቴ፤ አንተ ግራና ቀኝ፣ ፊትና ኋላ እያየህ፣ ማንም የለም ትላለህ፡፡ የታየኸው ወይም ያየህ ከላይ ነበር፡፡ አንተ እኮ ወደ ሰማይ ቀና አላልክም” አለችው፡፡
* * *
አንታይም ብለን ያደረግነው ሁሉ የማታ ማታ የሚያየውን እጅ ላይ እንደሚጥለን አንርሳ፡፡ በዚያኛው ዘን ያደረግነው ወደዚህኛው ዘመን፣ በዚህኛው ዘመን ተደብቀን ሳይነቃብን ያለፍነው፤ በመጪው ዘመን ሊከሰትብንና ከላይ የሚያይ እንደሚያየን ልብ እንበል፡፡ የምናደርገው ክፉ ሥራ ሁሉ እንደጥቁር ጥላ ይከተለናል፡፡ ህሊናችንን ያመናል፡፡ እንቅልፍ እንደነሳን ይኖራል፡፡ “ሞት ላይቀር ማንቋረር” እንደሚባለው ነው፡፡ ከዚህም ከዚያም በዘረፍነው ገንዘብ ፎቅ ስንገነባ፣ ውድ ውድ መኪና ስንገነባ፣ ሰፋፊ ቢዝነስ ስንከፍት ወዘተ፤ ሌሎች ኑሯቸው እየቆረቆዘ፣ ሀገሪቱ ከነግ ሠርክ ቁልቁል እየወረደች መሄዷን የሚያይ ዐይን አለ፡፡
ከላይ ጂ ቤኔት “የማታየው ያይሃል” ብሎ የፃፈውና ደራሲ ገ/ክርስቶስ “ደወል” በሚለው መጽሐፉ ተርጉሞ ያስቀመጠው ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡ እንደ ሌባው አባት ሴት ልጅ “ኧረ እየታየህ ነው” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወል የሚያንቃጭል አመራር ያስፈልገናል፡፡
ጤናችን በታወከበት፣ ትምህርታችን እየተዳቀቀ በሄደበት፣ ኪነጥበባችን ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት፣ መቻቻላችን አጠያያቂ በሆነበት፣ ዲሞክራሲያችን አገም ጠቀም እየሆነ በሄደበት፣ መልካም አስተዳደራችን የብልጭ ድርግም ባህሪ በሚያሳይበት፣ ሰው ከዕለት ወደዕለት ራስ ወዳድነቱ ከሀገሩ ጥቅም እያየለ በተጓዘበት፣ ግብረ ገብነት የክፉ ቀን እርግማን በመሰለበት፤ የችግሮቻችን መፍትሔዎች “ጡቷን ስትሸፍን ታፋዋ ታየ፤ ታፋዋን ስትሸፍን ጡቷ ታየ” እየሆኑ ባሉበት፤ ሁኔታ ውስጥ የጉዳያችንን ጥልቀት አስተውለን የበለጠ ጥንቃቄ፣ የበለጠ ትጋት፣ የበለጠ ትግል እናደርግ ዘንድ የማስጠንቀቂያ ደወል ያሻናል፡፡ ይህን እንደበለጠ የጥረት መቀስቀሻ እንጂ እንደመርዶ ወይም እንደሟርት አንየው፡፡ እልህ ኖሮን እንነሳሳ!!
በእርግጥ ፒተር ዳያማንዲስ እንደሚለን፤ “የሚደማ ጉዳይ መሪ ዜና ይሆናል” የሚለው ጥንት ስለጋዜጦች የተነገረ ዕውነት ቢሆንም፤ ዛሬም ይሰራል፡፡
(If it bleeds, it leads እንዲሉ ፈረንጆቹ፡፡) “ዋሽንግተን ፖስት” ጋዜጣን አንሱና አሉታዊና አዎንታዊ፣ ደግና ክፉ፣ ዜናዎችን አወዳድሩ፡፡
ከዘጠና በመቶ በላይ ሐተታዎቹ ክፉ ወሬን የሚተርኩ ናቸው፡፡ በአጭሩ ደግ ደጉ ዜና ትኩረታችንን አይስብም፡፡ ምክንያቱም “አሚግዳላ” የተባለው የአንጐላችን ክፍል ሁሌም የሚያስፈራ’ንን ነገር ለመፈለግ ይገፋፋናል፡፡ ባጭሩ አንጐላችን አንዴ ክፉ ወሬን ፍለጋ ከተሰማራ፤ ክፉ ወሬ ያገኛል” ይኸው ፀሐፊ አጠንክሮና አበክሮ እንዲህ ይለናል፡፡ “የዛሬ ጊዜ አደጋዎች ከሞላ ጐደል የምናልባቴ ጉዳዮች ናቸው (Probabilistic)፡፡ ኢኮኖሚ ባፍንጫው ወይም ባፍጢሙ ሊደፋ ይችላል (nose-dive)፡፡ በማናቸውም ሰዓት የአሸባሪዎች ጥቃት ሊከሰት ይችላል፡፡ የሚገርመው ፍርሃትንና ቁጣን የሚቆጣጠረው የአንጐላችን ክፍል (አሚግደላ) በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ላያውቅ ይችላል፡፡”
አዎንታዊ እንዳንሆን ሦስት ቅጣቶች አሉብን 1ኛ/ የአዕምሮአችን የማጣሪያ ነገረ-ሥራ ክፉ ክፉውን የሚመኝ ሆነ 2ኛ/ ሚዲያ ተነባቢ ለመሆን ክፉ ክፉውን ዜና መረጠ፡፡ 3ኛ/ ሳይንቲስቶችም የማንወጣበት ገደል ውስጥ ነን ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ለመውጣት ፈቃደ ልቦናው የለንም ማለታቸው ነው፡፡
ዓለም፤ የሚያስፈራ አደጋ እያሸተተና የማያስተማምን መሆኑን፤ ፀሐፍት እየነገሩን ነው፡፡ ይህንን እንግዲህ ወደ ሀገራችን ሁኔታ መመንዘር ነው፡፡ እንደ ነጋዴ ስንጥቅ እያተረፍን “ባመጣሁበት ውሰደው” ባንልም፤ አደጋውን በሙስናው፣ በኢፍትሐዊነቱ፣ በአስተዳደር ጉድለቱ፣ በኢኮኖሚ ዝቅጠቱና በመቻቻል መመናመኑ ወዘተ ውስጥ አስተውሎ ሁሌ ንቁ ሆኖ ማየት ነው፡፡
ምዕራቦቹ የሚጠጣ ንፁህ ውሃና የሚተነፈስ ንፁህ አየር እየጠፋ ነው እያሉ ሥጋቱ ሊገላቸው ነው። እኛ ጥያቄው ከነመኖሩንም አናውቅም፡፡
እነሱ እየተቆጣጠሩትም ፍርሃቱ ሊገላቸው ደርሷል፡፡ እኛ እርምጃቸውንም ከጉዳይ አልጣፍነውም። እነሱ “ዓለም ወዴት እየሄደች ነው” ብለው ተጨናንቀው ሊሞቱ ነው፡፡ እኛ የዘረፍነውን ዘርፈን “እቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው” እያልን በማላገጥ ላይ ነን! በዚህ ዓመት ምህረቱን ያምጣልን (If it bleeds it leads እንዳንል ይጠብቀን፡፡) ክፉ ወሬ ቀዳሚ ርዕሰ-ጉዳይ እንዳይሆን እንፀልይ፡፡
“በድህነቷ ላይ አገውኛ ጨመረችበት” የሚለው የትግሪኛ ተረት ያሳስባል፡፡ የሀገራችን አንዱ ችግር የጉዳዮች የአንድ ሰሞን ዘመቻ
መሆን ነው፡፡ ጨበጥነው፤ ተቆጣጠርነው ስንል፤ ተመልሶ እዛው ይዘፈቃል፡፡
ቢያንስ ለዘንድሮው ዓመት፤
“ጅግራ ያዝ፣ ሩጫ ከፈለክ ልቀቃት፤
ሥጋ ከፈለክ እረዳት” የሚለውን ተረት ልብ እንድንል ልብና ልቦና ይስጠን!!.

Read 4131 times