Print this page
Friday, 13 September 2013 13:10

አርቲስቶች ለአዲስ ዓመት

Written by  መልካሙ ተክሌ ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

“እወድሃለሁ” የአስቴር አዲስ አልበም ወጣ
የታዋቂዋ ድምፃዊ አስቴር አወቀ “እወድሃለሁ” የተሰኘ አዲስ አልበም ሰኞ ዕለት ለገበያ ቀረበ፡፡ አስራ ሁለት ዘፈኖች የያዘው አልበም፤ የድምፃዊቷ ድርጅት በሆነው ካቡ ሪከርድስ ኤክስኩዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የተሰራ ሲሆን የሚያከፋፍለው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ነው፡፡የአብዛኛዎቹ ዘፈኖች ግጥም እና ዜማ ደራሲ ራሷ ድምፃዊቷ ስትሆን ቅንብሩን የሰሩት አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ፣ሄኖክ ነጋሽ እና ካሙዙ ካሳ ናቸው፡፡

===============

የአርቲስት ስለሺ የአዲስ ዓመት ስጦታ

“ኢትዮጵያዊነት ጥበብ ነው”

ባለፈው አርብ አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) “ያምራል ሀገሬ” የተሰኘውን የሙዚቃ አልበም በሂልተን ሆቴል አስመርቋል፡፡ የምረቃ ስነስርዓቱን ያዘጋጀው የማስተርስ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ፤ አልበሙ ከሁለት ዓመት በላይ የተለፋበት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አርቲስት ስለሺ ለአንድ ሰዓት ያህል ስለ አዲሱ ሥራውና ስለ ኢትዮጵያዊነት ሠፊ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን በዕለቱ ካቀረበው ንግግር ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረውን እንደሚከተለው ቀንጭበን አቅርበነዋል፡፡
“ሜታዎች ሙዚቃህን ሊያዳምጡ የሚችሉት እነማን ናቸው አሉኝ፡፡ እኔም ‘ለየት ያሉ ናቸው፤ ቤታቸው ያሉ፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በደንብ ያላገኙ ናቸው፡፡ አድማጮቼ የራሳቸው ምስጢር ያላቸው ናቸው ስላቸው’ ያለንን ገንዘብ ሁሉ ውሰድ ብለውኛል፡፡
“የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ለዐይን ይቀፍ የነበረ ከተማ ብዙ ባይሆንም የፀዳው በእናንተ ጭምር ነው፡፡ ንፁሕ አመለካከት ቢኖረን ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም፡፡ እኛ ግን የማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል፡፡ ሰው ራሱን ያጣ ጊዜ የመጨረሻ ውድቀት ነው፡፡ እስቲ ፈረንጅ ነኝ ብዬ ልቅረብ፤ ለእናንተ እንደ ፈረንጅ ላወራ እችላለሁ፡፡ ሰውነቴን መለወጥ እችላለሁ፡፡ ግን ፈረንጅ ነኝ? አይደለሁም፡፡ መሆንም የለብኝም፡፡ እያመራን ያለንበት አቅጣጫ ያሳፍራል፡፡ እንግሊዝኛ የምንጠቀመው የእናት የአባታችን ቋንቋ ጠፍቶን ነው? እንግሊዝኛ ማጣፈጫ የእውቀት ምልክት ስለሚመስለን ነው?
“የዛሬው የሙዚቃ ሥራ የኢትዮጵያን የባሕል መሳሪያዎች ይዞ የተሰራ ነው፡፡ ተረቶቻችንን፣ ፍልስፍናችንን፣ ጥበብን … ይዞ ማንነታችንን ይበልጥ የምናወጣበት ነው፡፡ ብዙ የውጭ ሰዎች ተስፋ ቆርጠውብናል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ናት ብለን ስንመጣ ጣራው፣ ግድግዳው፣ ምግቡ … ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የለም። እንግሊዝኛ ሳይችሉ አማርኛ የጠፋባቸው ብዙዎች አሉ ተባብለናል፡፡
“ፈረንሳዊቷ እዚህ መጥታ ካፌ ስትገባ ወንዶቻችን ነይ እዚህ ጋ ተቀመጭ አሏት፤ በእንግሊዝኛ፡፡
እርሷ ግን በአማርኛ “አይ እዚህ ጋ ነው መቀመጥ የምፈልገው” አለቻቸው፡፡
“አማርኛ ትችያለሽ እንዴ?”
“አዎ”
“የት ተማርሺው?”
“ፈረንሳይ ሀገር ሶርቦር ዩኒቨርሲቲ” አለች፡፡
ጀርመኖች፣ ፈረንሳዮችና ሌሎች እኛን ግእዝ፣ የግእዝ ቅኔ፣ አማርኛ … ያስተምራሉ፡፡ እኛን አማርኛ፤ እኛን ኦሮምኛ፤ እኛን ወላይትኛ የሚያስተምሩ ገና ይመጣሉ፡፡ እንኳን ደስ አለን …
ኢትዮጵያዊነት ጥበብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ነው፡፡ ሥልጣኔ ነው … አንድ ቦታ ከራሳችን ጋር መጋጨታችን መቆም አለበት፡፡ የልጆቻችንን ሥም የኢትዮጵያዊነት ሥም እንስጥ፤ ቆንጆ ቆንጆ ስሞች አሉን፡፡ ለምሣሌ የአንድ ሰው ስም ቶሚ እና ምናምን ከሚባል ደንድር ቢባል ራሱን የቻለ ሙዚቃ ነው፡፡ ኒውዮርክ ካፌ ከሚባል ቀበሪቾ ወይም ጤና አዳም ቢባልስ? ስንት ሥም አለን፤ አፀደ፣ ምንትዋብ፣ ሳልሳዊት፣ ዳግማዊት … እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ሥሞች ናቸው፡፡ ይኼ እንቅልፍ ይነሳችኋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የራሳቸው ማንነትና ሐይማኖት አላቸው፡፡ ማንነታችንን ግን አሳልፈን እየሰጠን ነው። አስራ ሦስቱ ሙዚቃዎቼ ሥዕላዊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ “አይ ምንትዋብ” በሚለው ምንትዋብን ታያላችሁ…”


=========================

“ጥረቴን ወደ ስኬት የቀየርኩበት ዓመት ነው”
በ2005 መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ፈተናዎች ነበሩብኝ፡፡ ሁለተኛ አልበሜን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና የምልበት ወቅት ነበር፡፡ 

እጅግ ውጥረት ነበረብኝ፡፡ በአመቱ መጨረሻ ላይ ግን ድካሜ፣ ውጥረቴና ጥረቴ ፍሬ ያፈራበት በመሆኑ ለእኔ የስኬት ዘመን ሆኗል፡፡ ስለሆነም ፈተናውን ስኬቱ ሸፍኖታል፡፡ በጤናም በማህበራዊ ግንኙነቴም በጣም ጥሩ ነበርኩኝ፡፡ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡
በ2006 አዲስ አመት ብዙ እቅዶች አሉኝ። በእቅድ የመመራት ልምድ አለኝ፡፡ አልበሜን በመስከርም ወር መጨረሻ ማለትም መስከረም 23 ቀን በሸራተን ጋዝ ላይት አስመርቃለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ በአዲስ አበባና በክልሎች ኮንሰርቶችን ለመስራት እቅድ አለኝ፡፡ የውጭ አገር ጉዞዎችም ይኖሩኛል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሳካል የሚል እምነት አለኝ፡፡
አዲስ አመት የደስታ፣ የጤናና የስኬት እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እመኛለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት ይሁንልን፡፡

=============

እውቋ ድምፃዊ ሐመልማል አባተ “ያደላል” በሚል መጠሪያ ለአዲስ አመት አዲስ አልበም ሰርታ ያሳተመች ሲሆን አልበሟ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚሸጥ ብቸኛው የአልበሙ አከፋፋይ ሮማሪዮ ሪከርድስ ገለፀ፡፡
አልበሙ ጎጃምኛ፣ ጉራግኛ፣ ሙዚቃው ትግርኛ የሆነ እና የአማርኛ ዘፈን ኦሮምኛና ባህላዊ ዜማዎች የተካተቱበት ሲሆን በዛ ያሉ የፍቅር ዘፈኖችን እንደያዘም ታውቋል፡፡ ድምፃዊቷ ለአዲሱ አመት ዋዜማ በሚሌኒየም አዳራሽ በሚቀርበው የሙዚቃ ድግስ ላይ ከአዲሱ ሥራዋ የተወሰኑትን እንደምታቀነቅን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ድምፃዊ ሀመልማል አባተን ስፖንሰር በማድረግ አልበሟን ያሳተመው ሞሃ የለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ ሲሆን ለአልበሙ ከ500ሺ ብር በላይ እንዳወጣ ተገልጿል፡፡
ሮማሪዮ ሪከርድስ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣በደብረ ማርቆስና በባህርዳር በከፈታቸው ቅርንጫፎቹ በርካታ የሙዚቃ ስራዎችን እያሳተመ በማከፋፈል ላይ ሲሆን ለአዲስ አመትም የሐመልማልን ስራ ጨምሮ አራት ስራዎችን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የድርጅቱ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ በቀለ ገልፀዋል፡፡

 

Read 4554 times