Print this page
Friday, 13 September 2013 12:59

ኢትዮጵያዊው የሬይልዌይ ኢንጂነሪንግ ተማሪ በሞስኮ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ስም ምሩፅ ገ/እግዚአብሔር ይባላል፡፡ በራሽያዋ ከተማ ሴንቲ ፒተርስበርግ የባቡር ዝርጋታ ምህንድስና (ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ) ተማሪ ነው፡፡ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት መምህር ሆኖ በማገልገል ላይ ሳለ በመጣ የነፃ ትምህርት ዕድል አሸንፎ ራሽያ የገባ ኢትዮጵያዊ ነው። ከጋዜጠኛ ግሩም ሰይፉ ጋር በሞስኮ ከተማ ተገናኝተው ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

ትውልድህ የት ነው? የተማሪ ቤት ቆይታህስ?
የተወለድኩት በትግራይ ክልል ግሎማህደር በተባለ ስፍራ ነው፡፡ በአዲግራት ውስጥ የምትገኝ የገጠር መንደር ናት፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት እዚያው አዲግራት በሚገኘው አጋዚ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ጥሩ የማትሪክ ውጤት ስለነበረኝ ጥሩ ትምህርት ለመማር እድል አገኘሁ፡፡ ኢንጂነሪንግ የመማር ፍላጐት ነበረኝ፡፡ እናም ሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ገብቼ ሲቪል ኢንጂሪነግ ለ4 ዓመት ተምሬ በጥሩ ውጤት ተመረቅሁ፡፡ የምረቃ ውጤቴ ለዩኒቨርስቲ አስተማሪነት የሚያበቃ ነበር፡፡ ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት በአስተማሪነት ተመደብኩ፡፡ እዚያ ለሁለት ዓመት ካስተማርኩ በኋላ፣ የነፃ ትምህርት ዕድል ከሁለት አቅጣጫዎች መጣልኝ፡፡ አንደኛው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሃይዌይ ኢንጂነሪንግ ሲሆን ሁለተኛው ከራሽያ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የምማርበት እድል ነው፡፡ የሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ትምህርት በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት እንቅስቃሴ አዲስና ተፈላጊ ሆኖ የመጣ ዘርፍ ቢሆንም በዘርፉ ብዙ የተማረ ሃይል የለም፡፡ በአገራችን ከባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክቶች መጀመር ጋር በተያያዘ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ በራሽያ የተማሩ የመጀመሪያ ተመራቂዎች አገራቸው ተመልሰው መስራት የጀመሩት ባለፈው ዓመት ነበር፡፡ እኔ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም በዚሁ ዘርፍ በራሽያ ለመማር እድል አገኘ፡፡
የነፃ ትምህርት ዕድሉን ያገኘኸው እንዴት ነው?
የራሽያ የነፃ ትምህርት ዕድል እንደሌሎች የአውሮፓና ያደጉ አገራት በግልህ በመፃፃፍ አይደለም የምታገኘው፡፡ የራሽያ እና የኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር መ/ቤቶች በሚያደርጉት ስምምነት የሚገኝ ዕድል ነው፡፡ እኔ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ እያስተማርኩ ከትምህርት ሚኒስቴር ለራሽያ የነፃ ትምህርት ዕድል ተወዳደሩ የሚል ማስታወቂያ መጣ፡፡ መስፈርቶቹን ለማሟላት በመቻሌ፣ የነፃ ትምህርት ዕድሉን ካገኙት ኢትዮጵያውያን አንዱ ሆንኩኝ። ዕድሉ የመጣልኝ ራሽያዋ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ ከሚገኘው ስቴት ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው በዓለም ላይ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ከሚያስተምሩ ዩኒቨርስቲዎች ታዋቂና በጥራቱ የሚጠቀስ ነው። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያዊ የለም። ከእኔ ጋር ከሚማሩት ኢትዮጵያውያን አንዱ፣ ከሌላ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ መንገድ የመጣ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የላካቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዩኒቨርስቲው ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ እየተማርን ያለነው ኢትዮጵያውያን አስር ነን፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንድም ተማሪ የለም፡፡
ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ምን አይነት የትምህርት ዘርፍ ነው? ትምህርቱ እንዴት ነው? ከባድ ነው እንዴ?
መማር የጀመርኩት በራሽያኛ ቋንቋ ነው። በመጀመሪያ ቋንቋውን ማጥናት ነበረብኝ፡፡ በኢትዮጵያ በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የሚያስተምር አንድም ተቋም አለመኖሩም የትምህርቱን አጀማመር ከባድ ያደርገዋል፡፡ ቋንቋውንና የሬልዌይ ኢንጂሪነግ የጀማሪ ኮርሶች ለማጥናት አንድ ዓመት ያስፈልግ ነበር፡፡ በኋላ በቀጥታ ወደ ዋናው የሬልዌይ ኢንጂሪነሪግ ትምህርት ገብተናል፡፡ ሬልዌይ ኢንጂነሪንግ የባቡር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት የሚያጠና ዘርፍ ነው፡፡ እኛ የምንማረው “ዲዛይን ኤንድ ኮንስትራክሽን ኦፍ ሬልዌይ” ይባላል። የባቡር መስመር ግንባታና ቅየሳን የሚመለከት ነው፡፡ ጥሩ እና ደስ የሚል አጀማመር ነው፡፡ ትምህርቱን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ጨርሼ ወደ አገሬ እገባለሁ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ እየተማርን ያለነው በቀጥታ ወደ አገር ቤት ተመልሶ ለመስራት ነው፡፡ ትምህርቱን ስንጀምር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውል ፈፅመን ነው፡፡ ሆኖም የሚያዝህ የውል ወረቀት ሳይሆን ህሊናህ ነው፡፡ ተምረህ ስትጨርስ አገርህ ላይ ነው የምትሠራው፡፡ በራሽያ በዘርፉ የምናገኘውን የላቀ ትምህርትና ክህሎት ምንም ባልተሠራባት ኢትዮጵያ፣ መጠቀም መቻል በራሱ የሚያጓጓ ነው፡፡
እስቲ ስለሞስኮ ሜትሮ ንገረን…
አስደናቂው የሞስኮ ባቡር ትራንስፖርት ሜትሮ እ.ኤ.አ በ1935 ሲመሰረት፣ በሁለት ሃዲዶችና በ13 ጣቢያዎች 11 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚሸፍን ነበር፡፡ ዛሬ የሞስኮ ሜትሮ 185 ጣቢያዎች፤ ከ12 በላይ ሀዲዶች ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ 305.5ሺ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ የሜትሮ ሲስተሙ የሞስኮን ከተማ ከአጓራባቾቿ ትንንሽ ከተሞች ክራስኖጎርስክ እና ሬውቶቭ ጋር ያገናኛል፡፡ የሞስኮ ሜትሮ በሰዓት ከ45 በላይ ባቡሮች ይመላለሱበታል፡፡ የጉዞ ፍጥነታቸው በአማካይ 41 ኪሎ ሜትር በሰዓት ነው፡፡ የባቡር አገልግሎቱ በቀን ተሳፋሪዎች ብዛት ከቶኪዮ እና ከሴኦል ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን በቀን እስከ 8 ሚሊዮን ህዝብ ይገለገልበታል። በየ90 ሰከንዱ በየጣቢያው ባቡሮች ማግኘት ይቻላል፡፡ በ28 ሩብል ወይም 1.5 ዶላር በመክፈል፣ የሜትሮውን ባቡሮች በየትኛውም ጣቢያ መሳፈርና ሞስኮን ምድር ለምድር መሽሎክሎክ ይቻላል፡፡
ከመሬት ስር የሚገኙ የባቡር መስመሩ መናሐሪያና መሳፈሪያ ጣቢያዎች በአስተማማኝ የግንባታ ግብዓት በተለያዩ የስነህንፃ ጥበቦች አምረው የተገነቡና እንደሙዚየም ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ እዚህ ሞስኮ ያለው የባቡር ትራንስፖርት መስመር ከተማ ውስጥ አንደር ግራውንድ (በመሬት ስር) የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ የባቡር ጣቢያዎች ከምድር 100 ሜትር ጥልቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ የቦታ ርቀትን ቀንሶ በፍጥነት ያደርሳል፡፡ በየቦታውም አይቆምም፡፡ በተለይ በክረምት ወራት በበረዶ የተነሳ ከጉዞ ከመስተጓጐል ያድናቸዋል፡፡ በፀጥታና ደህንነት በኩልም አስተማማኝ ነው፡፡ ከመሬት በላይ ባለው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅም ይቀንሳል፡፡ አጠቃቀሙ በጣም ቀላል ነው፡፡ ሜትሮ በከተማ ውስጥ በመሬት ስር በተዘረጉ መስመሮች የሚያገለግል ይሁን እንጂ ከከተማ ሲወጣ ከመሬት በላይ ነው፡፡
አሁን አንተ ከሴንት ፒተርስበርግ የመጣኸው በባቡር ነው?
በሞስኮ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼን ለመጠየቅ እና በተለያየ ጉዳይ ወደ ከተማዋ ስመጣ ሜትሮን ነው የምጠቀመው፡፡ ከሴንት ፒተርስበርግ ወደ ሞስኮ የመጣሁት በምቹ አገር አቋራጭ ባቡር ተሳፍሬ ነው፡፡ ከሴንት ፒተርስበርግ ሞስኮ የሚያመጡ የተለያዩ አማራጭ የባቡር ትራንስፖርቶች አሉ፡፡ በፍጥነታቸውና በክፍያቸው ይለያያሉ፡፡ 350 ኪ.ሜ በሰዓት በሚከንፈው ፈጣኑ የኤክስፕረስ ባቡር ከሴንት ፒተርስበርግ ሞስኮ ለመድረስ 3 ሰዓት ተኩል የሚፈጅ ሲሆን ክፍያው 7ሺ ሩብል (4ሺ ብር ገደማ) ነው፡፡ ከቸኮልክ ፈጣኑን ባቡር መያዝ ትችላለህ፡፡ ለመዝናናት እና ለሽርሽር ከሆነ ግን በ6 ሰዓት የሚደርሱትን ባቡሮች መጠቀም ይቻላል፡፡ ርካሽ ናቸው፤ 2ሺ ሩብል ቢሆን ነው፡፡
በኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት በምኒልክ ዘመን ቢጀመርም አላደገም፡፡ እድገቱ በጣም የዘገየ አይመስልህም?
ይህን ጥያቄ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብመልስልህ፣ በእርግጠኝነት በጣም ዘግይቷል ነው የምለው፡፡ ለምን ዘገየ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ብዙ ተጽእኖዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ያለፍንባቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚያ ችግሮች በመደራረባቸው የባቡር ትራንስፖርት እድገት በጣም ዘግይቷል፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ከአንድ አገር ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በአንድ አገር ውስጥ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የሲሚንቶ፣ የብረታብረት ፋብሪካዎች የሚንቀሳቀሱ ከሆነ፣ የባቡር ትራንስፖርት ያስፈልጋል፡፡ የእነዚያን ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ዕቃዎች በቀላሉ ለማመላለስ ያግዛል፡፡ በከተማ ውስጥ ያለውን የትራንስፖርት ችግር እና የትራፊክ መጨናነቅም በባቡር ትራንስፖርት መቅረፍ ይቻላል፡፡ ከአዲስ አበባ አዳማ፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ አሶሳ ወዘተ … በቀላሉ ለመጓዝ ባቡር የተሻለ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ከተሞችን ከከተሞች በቀላሉ ለማገናኘት ወሳኝ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት በዓለም ላይ ካሉት መጓጓዣዎች ሁሉ ተመራጭ ነው፡፡ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዛት ያለው ተሳፋሪ የሚያገለግል ሲሆን ለአደጋ ተጋላጭነቱ በጣም አነስተኛ ነው። ባቡር በተለይ ባደጉት አገራት ሰፊ አገልግሎት እና ጥቅም ይሰጣል፡፡ እንግዲህ በሞስኮ ከተማ የባቡር ትራንስፖርትን ጠቀሜታ እንዳየኸው ነው። የባቡር ትራንስፖርት እንደአየር ትራንስፖርት ብዙ የምትጉላላበትና የምትጨናነቅበት አይደለም። በጣም ቀላል ነው፡፡ ማንም የህብረተሰብ ክፍል በርካሽ ዋጋ ይጠቀምበታል፡፡ ከአደጋ የራቀ መጓጓዣ በመሆኑም አስተማማኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ ስፍራ ለመሄድ ስትፈልግ ዛሬውኑ ወደ አንዱ ጣቢያ በመሄድ የምትሳፈርበትን ትኬት መቁረጥ ትችላለህ፡፡ የአየር ትኬት ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በእኛ አገር እንግዲህ ገና የ5ሺ ኪሎ ሜትር የባቡር ትራንስፖርት ለመዘርጋት እቅድ ተይዟል፡፡ ግንባታው በተግባር የተጀመረው በ2ሺ ኪሎ ሜትር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለባቡር ትራንስፖርት አመቺ ናት ማለት ይቻላል?
የባቡር ትራንስፖርት ሜዳማ እና አስቸጋሪ ያልሆነ መልክዓ ምድር ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ መልክአዓ ምድር የባቡር ትራንስፖርት ለማስፋፋት አመቺ አይደለም፤ ፈታኝ ነው፡፡
የሬልዌይ ኢንጂነሪንግ መማር፣ ይህን አስቸጋሪ የመልክዓ ምድር ፈተናዎች ለመለወጥና በዘዴ ለመጠቀም የሚያስችል ዕውቀትን ያስጨብጣል። በእኛ አገር ተራሮች ስትወጣ፣ በውስጥ ለውስጥ ዋሻ ወይንም በድልድይ መሸጋገር ያስፈልግ ይሆናል። እነዚህ የመልክዓ ምድር ሁኔታዎች ከፍተኛ ወጭ ይጠይቃሉ እንጂ ለመስራት ይቻላል፡፡ ተራሮች፣ አስቸጋሪ ስፍራዎች እና ወንዞች ሲያጋጥሙ ዋሻዎች መስራትና ድልድዮችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በሬልዌይ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ አስቀድመው ተምረው እየሰሩ ያሉትና አሁን በመማር ላይ የምንገኘው ኢትዮጵያውያን፣ በአገራችን የባቡር ትራንስፖርትን ለማስፋፋትና ለመገንባት የሚያስችሉ ዕውቀቶችና ክህሎቶችን እየሰበሰብን ነው፡፡ ሁላችንም ተቀናጅተን ብዙም ወጭ የማይጠይቁ የባቡር ትራንስፖርት መሰረተልማቶችን በማቀድ እና በመገንባት ብዙ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ስለምትኖርባት ከተማ ፒተርስበርግ ንገረኝ…
ሴንት ፒተርስበርግ ለኑሮ ተመችታኛለች፡፡ ከተማዋ ልዩ ውበት ያላት ፀጥታ የሰፈነባት፣ የራሽያ የባህል መዲና ናት ማለት ይቻላል፡፡ ከተማዋ በታሪካዊ ስነ ህንፃዎች የተከበበች ናት፡፡ በታላቁ የራሽያ ንጉስ ፒተር ዘ ግሬት፣ በኔቫ ወንዝ ላይ ነው የተገነባችው፡፡ ጥንት የተመሠረቱ ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች አሏት፡፡
አሁን እኔ የምማርበት ዩኒቨርስቲ ከተመሠረተ ከ200 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የከተማዋ ልዩ መገለጫ ከምላቸው ነገሮች በቀዳሚነት የምጠቅሰው “ኤር ሚታዤ” የሚባለውን ዓለም አቀፍ ሙዚየም ነው፡፡
በዓለም ትልቁ ሙዚየም ነው፡፡ ሁሉንም የሙዚየሙን ክፍሎች በደንብ ተዘዋውሬ ልጐበኝ ካልክ 10 ዓመት ይፈጅብሃል፡፡ የኪነጥበብ፣ ቅርፃቅርጽ፣ ታሪካዊ ቁሳቁሶች፣ የየአገሩ… የየራሱ ክፍል ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክፍል አለ፡፡ በዚህ ክፍል የብራና መጽሐፍት፣ የታሪክ መዛግብት፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ቁሳቁሶች፣ የታሪካዊ ቦታዎች ምስሎች ይታያሉ፡፡ ሌላው የሴንት ፒተርስበርግ መገለጫ ወንዞቿ ናቸው፡፡ ራሽያውያን ከተሞቻቸውን በወንዞች ዙሪያ የሚያደርጉት ያለምክንያት አይደለም፡፡ አሁን ለምሳሌ በራሽያ ወንዝ ለትራንስፖርት አገልግሎት ያገለግላል፡፡ በሞቅታ መሬት የአየር ንብረቱን ለማቀዝቀዝ ይጠቅማል፡፡
ከወጣቱ ትውልድ ምን ይጠበቃል ትላለህ?
በግሌ የማስበው ምን መሰለህ? በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ጥሩ የሚባሉ ነገሮች እየታዩ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ትውልዱን ወደ መጥፎ አዝማሚያ የሚወስዱ ነገሮችን እየተመለከትኩ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ በብዙ ነገሮች አንድ ሆኖ፣ በብዙ ነገሮች ደግሞ የሚለያይበት ሁኔታ ይታያል፡፡ እኔ በበኩሌ ሰዎች በመረጃ ላይ የተመረኮዘ እውቀት እንዲያዳብሩ ነው የምመርጠው፡፡ አሁን ጊዜው በምትፈልገው መስክ በርካታ መረጃዎችን በቀላሉ የምታገኝበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የምታገኛቸውን ሁሉንም መረጃዎች በተገቢው መልኩ ተርጉመህና አውቀህ በራስህ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ መድረስና መጠቀም አለብህ፡፡ ትውልዱ ከአሉባልታ፣ እና በዕውቀት ባልዳበረ መረጃ መነሳት የለበትም፡፡ ስራ ሲሰራ፣ ማነው የሚሰራው ሳይሆን ምንድነው እየተሰራ ያለው ብሎ መደገፍና የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡ ያንድ ትውልድ ድርሻ የራሱን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ነው፡፡ ለአገሪቷ የሚጠቅማት የሚሰራውን እያየህ መደገፍ፤ የማይሰራውን ደግሞ ያለውን ክፍተት በችሎታህና በእውቀትህ እየሰራህ መሙላት ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ ትውልድ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ በዕውቀት እና በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ስራ ለአገሩ የሚያከናውን መሆን ይገባዋል፡፡

Read 4519 times