Print this page
Friday, 13 September 2013 12:56

“የአዲሱ ዓመት እቅዴ በማዕድን ፍለጋ ላይ መሰማራት ነው” አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ለእኔ 2005 ዓ.ም በአጠቃላይ ሲታይ መጥፎ አመት አልነበረም፡፡ ያሰብኩትን ያህል ባልሄድም ያቀድኳቸውን ነገሮች ከሞላ ጐደል ሳላሳካቸው አልቀረሁም፡፡ በቴፒና በሚዛን መካከል በሚገኝ ማሻ በተባለ ቦታ ላይ የቡና እርሻ ለመጀመርና ሁለት መቶ ሄክታር ቡና ለመትከል አቅደን ነበር፤ እሱን አሳክተናል፡፡ ሁለተኛው ስኬት የሻሸመኔው ሆቴሌ መጠናቀቅ ነው፡፡ ሆቴሉ “ኢ-ላይት” ይባላል፡፡ በ“ማራቶን ሞተር” ድርጅታችን በኩልም ውጤታማ ነበርን፡፡ “በሀይሌ አለም ሪል ስቴት” አማካኝነት ባለፈው አመት ያቀድነውን በርካታ ቤቶች ገንብተናል፡፡ ቤቶቹ ሀያት አካባቢ የሚገኙ ናቸው፡፡ በሀይሌ አለም ኢንተርናሽናል ቢሯችን በኩል ግን እንሰራለን ብለን ያልሰራናቸው ነገሮች አሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳኩ ማለት ነው፡፡ ለስራው አለመሳካት እንደ እንቅፋት የሆነብን የውጭ ምንዛሬ ችግሮች ነበሩ፡፡ ያው ነጋዴ ስትሆኚ አንዴ ከፍ፣ አንዴ ዝቅ ማለት ያጋጥማል፡፡ አንድ ሚሊዮን አተርፋለሁ ብለሽ ግማሽ ሚሊዮን የምታተርፊ ከሆነ ከእቅድ በታች ነው ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሀይሌ አለም ኢንተርናሽናል በ2005 ዓ.ም ከ2004 ዓ.ም ብዙ የተለየ እንቅስቃሴ አላሳየም ማለት ይቻላል፡፡
በ2006 ብዙ ነገሮች አቅጃለሁ፡፡ ዋናው ግን በማዕድን ፍለጋ ዘርፍ ልሰማራ ነው፡፡ ትልቁ እቅዴም እርሱ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የጀመርኳቸው ሂደቶችም አሉ፡፡ በቡና እርሻው በኩል በዚህ አዲስ አመት ሶስት መቶ ሄክታር ቡና ለመትከል እቅድ አለን፡፡ ይሄ ሁለተኛው እቅድ ነው። ሶስተኛው እቅድ በ2005 ከገነባናቸው ሪል እስቴቶች በተጨማሪ በአዲሱ ዓመት ከ55-60 አፓርትመንቶችን ለመገንባት አቅደናል፡፡ በሪል እስቴቱ በኩል አጠቃላይ ልንገነባ ያቀድነው ወደ 220 አፓርትመንቶችን ነው፤ አብዛኞቹ በ2005 ዓ.ም ተገንብተዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ዋና ዋናዎቹ እቅዶች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ጥቃቅኖቹ ደግሞ ይቀጥላሉ፡፡ በተረፈ በቤተሰብ፣ በጤናና በመሳሰሉት አመቱ ጥሩ ነበር፡፡
2006 ዓ.ም የምናቅድበት ብቻ ሳይሆን ያቀድነውን የምንከውንበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ምክንያቱም አንድ አመት ጥሩ ነው የሚባለው የምንፈልገውንና የምናቅደውን ስናሳካበት ነው፡፡ አመቱ የጤና፣ የሰላምና የብልፅግና እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እመኛለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት፡፡

Read 4026 times