Print this page
Friday, 13 September 2013 12:50

“ከሁሉም በላይ ስኬታችን ቻምበር አካዳሚ ማቋቋማችን ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን (የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት)

በ2005 ዓ.ም በግል ህይወቴ ትልቁ ፈተና የነበረው የእናቴ መታመም ነው፡፡ ህመሟ ከባድ ነበር፤ አሁን ግን ተሽሏታል፡፡ በስራ ቦታ ባሉ እንቅስቃሴዎች እንቅፋት የሚሆንብሽ ብዙ ነገር አለ፡፡ የአገር ስራ ስትሰሪ ለግልሽ የምትሰሪ ይመስል በተሳሳተ ግንዛቤ እንቅፋት የሚፈጥሩብሽ ሰዎች ያጋጥሙሻል፡፡ ደግነቱ ጉዳዩን ሲረዱ መመለሳቸው ነው፡፡ እንዲህ አይነት ፈተናዎች የተለመዱ ናቸው፤ ግን በጥሩ ሁኔታ ተወጥቶ መፍታቱ ጥሩ ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ከገጠሙኝ ፈተናዎች ውስጥ እኔ ፕሬዚዳንት ሆኜ ስመጣ ብዙ ማህበራት ተጣልተው ስለነበረ እነሱን ማስማማት አንዱ ነበር፤ ምክንያቱም በሰላማዊ የስራ ድባብ ውስጥ ካልተሰራ የትም አይደረስምና፡፡ በኋላ ግን ሁሉንም በማስታረቅ ተወጥቼዋለሁ፡፡ ይህ እንደስኬት የምቆጥረው ነው፡፡
ሌላው ስነ-ምግባር ያለው የንግድ ማህበረሰብ እንዲፈጠር እዚህም ሆነ በክልል በብዛት እየተንቀሳቀስን ስለሆነ ይህም ስኬት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ስነ-ምግባር ያለው የንግድ ማህበረሰብ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት በራሱ ጥሩ ነው፡፡
በግሌ ብዙ ያቀድኳቸው ነገሮች አሉ፤ የተጀመሩና መጠናቀቅ ያለባቸው፡፡ ከንግድ ም/ቤቱ እቅድ ደግሞ የመጪውን የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ በዚህ ሳምንት አፅድቀናል፡፡ በመጭው አምስት አመት እኛም ብንቀጥል ሌሎችም ቢተኩ የሚሰራው ሰው አቅጣጫ ይዞ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ነው፡፡ ሌሎችንም የንግድ ምክር ቤት አደረጃጀትና ቻምበር ሲስተሙን አስመልክቶ እንደዚሁ ያፀደቅናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ትልቁ ስኬታችን ቻምበር አካዳሚ ማቋቋማችን ነው፡፡ በየጊዜው በድንገት ተመርጠው ስልጣን ላይ የሚቀመጡ የም/ቤቱ ሀላፊዎችም ሆኑ ማህበራት ስለ አስተዳደር እና ስለ ጉዳዩ ሳያውቁ ስራው ላይ ይጋፈጣሉ፡፡ የቻሉትን ያህል ሲሰሩ ስህተት ነው ተብለው ይተቻሉ። ጥሩም ቢሰሩ ጥሩ ስራቸው በአንዳንድ ስህተት ይሸፈንባቸዋል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ቻምበር አካዳሚ ወይም “ኢንተርፕረነርሺፕ፣ ሊደርሺፕ ኤንድ ማኔጅመንት” ማዕከል አቋቁመናል፡፡ ይህ ማዕከል ወደፊት በአለም አቀፍ ደረጃ ነው የሚሰራው። ለጊዜው ግን “ቻምበር አካዳሚ” ብለነዋል፡፡ በአጠቃላይ ይህን ይመስላል፤ ችግሮችም ስኬቶችም አሉ፡፡ አብዛኛውን ፈተና ግን በድል ተወጥተናል፡፡
በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአለም ህዝብ የምመኘው ከስስት ተላቀን ሁሉንም ሰው በፍቅር እንድናገለግል ነው፡፡ በራሳችን ሊደረግ የማንፈልገውን በሌሎች ላይ ባለማድረግ፣ ለራሳችን የምንፈልገውን መልካም ነገር ለሌሎችም በማድረግ፣ ይህች አለም በሰላምና በፍቅር የተሞላች ትሆን ዘንድ እንድንጥር እመኛለሁ፡፡ አለምን ለመቀየር ስናስብ ራሳችንን ለመቀየር እንሞክር እላለሁ፡፡ ከፈለግን ደግሞ እንችላለን፡፡ አዲሱ አመት የጤና፣ የሰላም፣ የፀጋና ያሰብነውን የምናሳካበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡

Read 2780 times