Friday, 13 September 2013 12:49

እንቁጣጣሽ

Written by  በኃይሉ ገ/እግዜር
Rate this item
(0 votes)

ልጅ እያለሁ እንቁጣጣሽን የሚያህል ደስ የሚለኝ በዓል አልነበረም፡፡ የአበባ ስዕል መሳል አልወድም። የማልወደው ግን ስዕል መሳል ስለማልችል ብቻ ነው፡፡ እቤታችን ሌሎች ልጆች የሚያመጡአቸውን ስዕሎች ወስጄ እንድሸጥ ስለሚፈቀድልኝ ባለመሳሌ ብዙም አልቆጭም፡፡ በዚህ በልጅነት ህይወት ውስጥ ከሌሎች ጐልተው ትዝ የሚሉኝ፣ አክስቴ እና ክርስትና አባቴ ናቸው፡፡
አክስቴ ስዕል ማማረጥ ትወዳለች፡፡ እኔ ባልሳልኩት ስዕል ሁልጊዜ ማብራሪያ ስለምትጠይቀኝ በጣም እናደድ ነበር፡፡
“አክስቴ እንኳን አደረሰሽ!”
“እንኳን አደረሰህ! ጐሽ አምጣው እስቲ”
እሰጣታለሁ፤ ትኩር ብላ ታየዋለች፡፡
“ሰይጣኑን ስለህ ቅዱስ መልዓኩን ያልሳልከው ለምንድነው?”
“እሱ እኮ ሰይጣን አይደለም ብሩስሊ ነው፡፡”
“ማነው ብሩስሊ?”
“ካራቲስት ነው፤ ካራቴ የሚችል፡፡”
“እግሩን እዚህና እዚያ የከፈተው ታዲያ ምን ሆኖ ነው?”
“ወደ ላይ ዘሎ ሌቦቹን ሲማታ ለማሳየት ነዋ። አይታዩሽም እንዴ ሌቦቹ ተመተው ሲወድቁ?” በጣም እየተናደደች፣ “ይሄን ወደዛ ውሰድልኝ! የመልዓክ ስዕል ካለህ አምጣ!” ትለኛለች
“እሺ እንቺ” ሌላ ስዕል እሰጣታለሁ፡፡
“ይሄ ነው መልዓክ? አንተ እርኩስ! ይሄ ነው? ግራና ቀኝ ወገቡ ላይ የኮባ ቅጠል የበቀለበት አስመስለህ ሰርተህ መልዓክ ትለኛለህ?... ዓይኖቹንስ እንዲህ አድበልብለህ ያፈጠጥከው ምን አድርጐህ ነው አንተ?”
አክስቴ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር እንደተጨቃጨቀች ነው፡፡ ደስ የምትለኝ ግን እንዲህ ተጨቃጭቃም እንኳን አንዱን ስዕል ከወሰደች በኋላ የምትሰጠኝ ድፍን አንድ ብር ነው፡፡
ክርስትና አባቴ ደግሞ እንደ አክስቴ ስዕል የሚያማርጥ ሰው አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ገንዘብ የማይወጣው ቆጥቋጣ አይነት ስለሆነ፤ ከእርሱ ሳንቲም ተቀብሎ ለመሄድ የሚገጥመኝ ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡
“ጌታሁን!”
“አቤት”
“እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል አደረሰህ፤ ና እስኪ ሳመኝ”
“እሺ” አበባውን ይዤ ወደ እርሱ እቀርባለሁ፡፡
ቀረብ ስል ጉንጬን በሁለት እጆቹ ይዞ አገላብጦ ይስመኛል፡፡ ልቤ “ስንት ሳንቲም ይሰጠኝ ይሆን?” በሚል ጥያቄ ስለሚያዝ የሚስመኝን ጉንጬን እንኳ አስተካክዬ አልሰጠውም፡፡
“ማነሽ ጌጤ …” ስሞኝ ሲጨርስ ትልቋን ልጅ ይጣራል፡፡
“አቤት”
“ለጌታሁን እስቲ ዳቦ ስጪው”
“እሺ”
ዳቦ በሰሀን ይዛ መጥታ ትሰጠኛለች፡፡ ቶሎ ሣንቲሜን ተቀብዬ ለመሄድ ትንሷን ዳቦ መርጬ ሳነሳ “እንዴ! ምነው አንተ! ያባትህ ቤት እኮ ነው፤ ጌጤ፤ ተለቅ ያለውን ዳቦ ጨምሪለት” ይላል፡፡ ጌጤ ትመጣና ትልቁን ዳቦ ያለአቅሜ ታሸክመኛለች፡፡ በቃ መከራዬ የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡ ዳቦውን ካልጨረስኩ ሳንቲሙ አይሰጠኝም፡፡ ሳንቲሙ ካልተሰጠኝ ደግሞ አልሄድም፡፡ ቶሎ ካልሄድኩ ደግሞ ሌሎች ዘመዶቼ ቤት ለመሄድ ይረፍድብኛል።
ዳቦውን ቶሎ ለመጨረስ ስጣደፍ ካየ፣ “ጌጤ ርቦታል መሰል ጨምሪለት!” ይላል፡፡ በጣም እናደድና፣ “በቃኝ! ኧረ በቃኝ!” እላለሁ፤ አፌ ላይ ያለውን ዳቦ በቅጡ ሳልጨርስ፡፡ ጌጤ እግዜር ይስጣትና ፍላጐቴ ገብቷት ምልስ ትላለች፡፡
ዳቦውን ጨርሼ፣ ላመጣሁት ስዕል ሳንቲም ሰጥቶኝ ምናለ ቶሎ በሄድኩ እያልኩ ስቁነጠነጥ፣
“አባትህ ደህና ነው?” ይለኛል፡፡
“ደህና ነው፡፡” እየተናደድኩ እመልሳለሁ፡፡
“እናትህስ ተሻላት?”
“አዎ! ተሽሏታል፡፡ መድኃኒት እየዋጠች ነው፡፡” ሌሎች ዘመዶቼ ጋር መሄድ አለብኛና ስናገር ፈጠን ብዬ ነው፡፡
“ወንድምህ ትምህርቱን ጨርሶ መጣ?”
“አዎ! መጥቶ ነገ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ የሚቀጥለው ዓመት ትምህርቱን ይጨርሳል” ስመልስ ለጠየቀኝ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚጠይቀኝም ጭምር ነው፡፡
ጥያቄውን ምነው በጨረሰ እያልኩ በሆዴ ስፀልይ፣
“ለመሆኑ ስንተኛ ክፍል ደረስክ?” ይለኛል፡፡
“አምስት” ድምፄ መቸኮሌን ይናገር ነበር፡፡ እርሱ ግን ግድ የለውም፡፡
“ጐብዘሃልና ለመሆኑ ለምንድነው እየመጣህ የማትጠይቀኝ?”
“እ?”
“እኔ አባትህ አይደለሁም? ዘመድ አይጠየቅም?”
ዝም፤ ዳቦዬን በፍጥነት እያላመጥኩ፡፡
“እኔ አንተን ከጌጤ ከትንሷ ልጄ ነጥዬ አያለሁ ወይ? ከወንዱ ልጄስ አሳንሼ የማይህ ይመስልሃል?”
ዝም፤ መጨረሻውን በመናፈቅ፡፡
“‘አባቴ አምስተኛ ክፍል ደርሻለሁ፤ ደብተር መግዣ ቸገረኝ፣ እስኪብርቶ ግዛልኝ’ ብትለኝ እንቢ እላለሁ”
በሆዴ እያጉረመረምኩ ፀጥ፡፡
“ሰማህ ወይ?”
“አቤት”
“ላንተ ለልጄ የሚሆን ሳንቲም የማጣ ይመስልሃል?”
የተሰጠኝን ዳቦ ጨርሼ፣ እጁን ወደ ኪሱ የሚከትበትን ሰዓት በመናፈቅ ዓይኔን እያቁለጨለጭኩ ነው፡፡
“እኔ አባትህ ቀላል ሰው አታድርገኝ! እ! ይመስገነው፤ ላንተ ለልጄ የሚሆን ገንዘብ የማጣ አይደለሁም፡፡”
በመከራ እጁን ወደ ኪሱ ከተተ፡፡ ሳንቲም ሰጥቶ ሊሸኘኝ ነውና ደስ አለኝ፡፡ ድንገት እጁን ሰብሰብ አድርጐ፤
“ኧረ ለመሆኑ ያቺ እህትህ ከቤት እንደወጣች ቀረች ወይስ ተመለሰች?”
“መጥታለች፡፡ አጐቴ ነው ይዟት የመጣው፡፡”
“ጐሽ!”
“እሰይ! ጥያቄውን ጨረሰ” ብዬ በረጅሙ ስተነፍስ፣
“እንዴ! እንዴ! ያ አጐትህ እንዲህ የጠፋው በደህና ነው?”
“እ?”
“ያ አጐትህ እንዲህ የጠፋው በሰላም ነወይ?”
ማን ይሙት ያጐቴን አጠፋፍ እኔ በምን አውቃለሁ? አጐቴ ትልቅ፤ ያውም ያባቴ ታላቅ፡፡ እኔ ደግሞ...
“ሁልጊዜ እየመጣ ይጠይቃችኋል?”
“አልፎ አልፎ”
“ይገርማል! ምናለ እኔንስ ብቅ እያለ ቢጠይቀኝ እ...”
“የመጣሁበትን እረሳው እንዴ?” እያልኩ በሆዴ ሳጉተመትም፣ እጁን በድጋሚ ኪሱ ከተተ፡፡ አሁንም ደስ አለኝ፡፡ ሳንቲሞች ተቃጨሉ፡፡ እንዴ ይሄን ያህል አስለፍልፎ ዝርዝር ሳንቲም ብቻ ሊሰጠኝ ነው እንዴ? ተነጫነጭኩ፡፡ ሳንቲሞቹን አወጣቸው፡፡ አይኔ ከእጆቹ ጋር አብረው ተንከራተቱ፡፡
አዎ! እጁ ላይ ድፍን ስሙኒና ድፍን ሃምሳ ሳንቲም ይታዩኛል፡፡
“ማነሽ ጌጤ!”
ደግሞ ምን ሊል ነው፡፡ “እንዴ ዳቦ በቃኝ! አሁንስ ዳቦ በቃኝ! ወሬም በቃኝ! እንዴ ሌላ ቦታ የማልሄድ አደረገኝ እንዴ? ዘመዴ እሱ ብቻ የሆነ መሰለው እንዴ?” ንጭንጩ ለሌላ ሰው ባይሰማም ለሚመለከተኝ ሰው ያስታውቅብኝ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ክርስትና አባቴ እንደሆነ ምንም ሊገባው አልቻለም፡፡
“ጌጤ!”
“አቤት”
“ያንን ኮፖርት አቀብ’ኝ”
እፎይ አልኩ፡፡ የጌጤ መጠራት ለዳቦ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኔ ብር ለመስጠት ታስቦ ጭምር በመሆኑ ተደሰትኩ፡፡ ጌጤ ካፖርት አምጥታ ሰጠችው፡፡ ወዲያው የክርስትና አባቴ እጆች በየካፖርቱ ኪሶች ውስጥ መንከራተታቸውን ተያያዙት፡፡
“እዚህ ውስጥ ዝርዝር ሳንቲም አልነበረኝም እንዴ ጌጤ?”
“እኔ እንጃ ፈልገዋ”
እንደተባለው ፈለገ፡፡ የሆኑ ሳንቲሞች አገኘ፡፡ ያሰብኩት ድፍን ብር ባይሰጠኝም፣ ከሱሪው ኪስ ውስጥ ከተገኘው ሰባ አምስት ሳንቲም ጋር አብሮ ከሰጠኝ ያው ነው ብዬ ተዝናናሁ፡፡
የሆነው ግን ይህ አልነበረም፡፡
“ና ጌታሁን” አለኝ በኩራት ብዙ ብር እንደሚያሸክመኝ ሁሉ፤ ሄድኩ፡፡
“ዝርዝር ሳንቲም አጥቼ አቆየሁህ አይደል!?”
“ኧረ ችግር የለም”
“በል ይቺን ያዝ ይኸውልህ፡፡ ስዕሉን ሌላ ቦታ ወስደህ ስትሸጠው ብዙ ሳንቲም ይሆንልሃል እሺ ያዝ!” አዘንኩ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ ክርስትና አባቴ የሰጠኝ አስራ አምስት ሳንቲም ብቻ ነበር፡፡ ሃምሳ ሳንቲም ላለመስጠት፤ ሃምሳው ይቅርብኝ፤ ስሙኒ ላለመስጠት ካፖርታ አስመጥቶ እንደዛ መልፋቱ አበሳጨኝ፡፡ ከእጁ ላይ የመመንጨቅ ያህል ተቀብዬው ልወጣ ስል፣
“ጌታሁን” ጠራኝ፡፡
“አቤት” ተመለስኩ ወደ ኋላ፣ ድንገት ተፀፅቶ ሳንቲም ቢጨምርልኝ ብዬ፡፡
“ሰማኸኝ፤ እናትህን እንደምትላት ‘እንዴት ነሽ? ተሻለሽ ወይ? መጥቼ እጠይቅሻለሁ ስል ሳይመቸኝ ቀረ’ በልልኝ፡፡”
“እሺ” እያልኩ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡
እሱ ግን አልጨረሰም፡፡
“አባትህንም፣ ‘እንኳን ለቅዱስ ዮሐንስ አደረሰህ’ በለው፡፡ ያ ተማሪ ወንድምህንም ሰላም በልልኝ፤ ‘አንተ ወመኔ ምን ሆነህ ነው መጥተህ የማትጠይቀኝ’ በለው...”
ክርስትና አባቴ እንቁጣጣሽ በመጣ ቁጥር ይኸው ነበር ባህሪው፤ ሲያናድድ!

Read 1831 times