Friday, 13 September 2013 12:46

የአዲስ ዓመት እርድ ቢሉ፣ አደን ትዝ አለኝ!

Written by  ፍፁም ገ/እግዚአብሔር
Rate this item
(1 Vote)

                        ከ1997 ዓ.ም መጨረሻ፣ ከ1998 ዓ.ም የዘመን መለወጫ ጀምሮ የኑሮ ውድነት ያለ ቅጥ እያሻቀበ ሲመጣ፣ የእነ ዶሮ፣ በግ፣ ፍየልና በሬም ዋጋ እንደዛው ማሻቀቡ አልቀረም፡፡ በተለይ ከሁለት ሺኛ ዓመታችን (ከሚሊኒየማችን) ዋዜማና መባቻ ጀምሮ፣ የኑሮ ውድነት እንዴት ለመለካት (ለመመዘን) አስቸጋሪ መሆኑን ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ የታሰበ እስኪመስል፣ ጣራ እየነካ ነው። ለነገሩ ከ2002 በኋላ ግን የኑሮ ውድነት ጣራ እንደሌለው በሚገባ ያረጋገጠ ይመስላል፡፡ ስለዚህ፣ የኑሮ ውድነት ጣራው በመበሳቱ፣ ኧረ እንደውም ጣራው በመቦደሱ “ውደነት” ብቻው ሽቅብ እንደ ሮኬት እየተተኮሰ ነው ቢባል፣ ተጋነነ የሚል ያለ አይመስለኝም፤ ካልሆነ ሽቅብ ከሚተኮሰው የኑሮ ውድነት ያለ ቅጥ የሚያተርፍ ባለ ጊዜ ሰው መሆን አለበት!
የዘንድሮው ማለቴ የ2005 ዓ.ም በዓላት ላይ የእርድ እንስሳት ዋጋ ከጣሪያ በላይ ስለመሆኑ የገበያ መረጃ እንዳጣቅስ መቼም አትጠይቁም፤ “አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው” ሀቅ ነበረና፡፡ ታዲያ 2005 ዓ.ም መቋጫ ወይም የ2006 ዓ.ም አዲስ ዓመት መባቻ ላይ የእርድ ዋጋ እንደተለመደው ያለ ቅጥ ባያሻቅብ እንኳ ቢያንስ እንደማይቀንስ ግን ይታወቃል፤ እሺ “ይታወቃል” የምትለዋን ቅድመ ፍርጃ አገላለጽ፣ ለስለስ ባለ ትሁት ቋንቋ መግለጽ ካስፈለገ ወይም ከተገባ፣ “ቢያንስ እንደማይቀንስ ይገመታል” ልንል እንችላለን፡፡
እናም የአዲስ ዓመት መባቻው ዕለት ሳይቀርብ፣ በጳጉሜ የመጀመሪያ ቀናት ወደ ገበያ ወጣ ብዬ የዶሮና የበግ ዋጋ ስጠይቅ የማይቀመስ ነው። በነገራችን ላይ ይቺ ጳጉሜ የምትባል የወር ደመወዝተኛን የምታጐሣቁል ወር በሏት የማትቆጠር ቀናት አትመቸኝም! ሆድ፣ ለአምስት ቀናት፣ ከአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ለስድሥት ቀናት እረፍት ያደርግ ይመሥል፣ እየሠሩ ክፍያ አለማግኘት ፍትሐዊ ነው!? ለአምሥት ወይም ለስድሥት ቀናት ወደ ሥራ ቦታ ለመጓዝ የታክሲ ወጪ ብቻ አሁን አሁን የማይቀመሥ እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ ጳጉሜ በነፃ ልታሥፈጋን በየዓመቱ ሥትመጣ፣ “እንቁ”ን ትተን “ጣጣሽ” መጣች ብንላት የሚፈረድብን አይመሥለኝም፡፡
ታዲያ የጳጉሜ የወር ገቢያችንን የማፋለሷ ጣጣ እያለብን፣ የልጆች የትምህርት ወጪዎች እያፏጩብን፣ የአዲስ ዓመት በዓል እርድ ወጪ ሲታከልበት ኑሮ፣ “ንሮ፣ ንሮ…እሮሮ” ብቻ ሆነብን። በዚህ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር ተመካከርንና “የዘንድሮ የአዲስ ዓመት እርድ ቢቀርስ?” ወደሚል አቅጣጫ አዘመምኩ፡፡ ባለቤቴም፣ “ለወትሮው ዶሮውም፣ በጉም አይቅር እያልሽ፣ ከመሥሪያ ቤት ብድር ሁሉ ታስጠይቂኝ ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ሁሉም እርድ ይቅር ነው የምትይ? ልጆቹስ? ባይሆን በጉ ይቅርና ዶሮ እንገዛለን፤ በዓሉ ደግሞ እሮብ ላይ ስለሚውል ጥሩ ማሳበቢያ ይሆነናል…” በማለት መለሰልኝ፤ “ማሳበቢያ ይሆነናል…” የሚለው ገለፃው በርግጥም በጣም አስቆኛል፡፡
በሚቀጥለው ቀን በሾላ ገበያ፣ የዶሮዎችን ዋጋ ስጠይቅ ውዬ ሳልገዛ ተመለስኩ፡፡ ሰፈራችን፣ ፈረንሳይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጥግ ላይ ስለሆነ፣ መጠነኛ ጫካ ማየት ብርቅ አይደለም። ከገበያ መልስ ወደ ቤት ልገባ ስል ከቤታችን በላይ ያለው በባህር ዛፍና አልፎ አልፎ በጽድ የተሸፈነ ተራራ ታየኝ፡፡ በዚህ ተራራ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ የጅብ ጩኸት መስማት የተለመደ የአካባቢው የተፈጥሮ ገፀበረከት ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ወይም በኑሮው ሁኔታ ስንጨናነቅ መፍትሔ ፍለጋ ለማሰላሰል፣ ለመጠሞን (ጥሞና ለማድረግ) ወይም ለመናፈስ በጫካው ውስጥ መንጐራደድ የተለመደ ነው፡፡
እኔም የቤታችንን አጥር አልፌ ወደ ተራራው ሳቀና ባለቤቴ፣ “ከገበያ መልስ ወደ ጫካ ምን ያስኬዳል?” በማለት በፈገግታ ጠየቀኝ፡፡ “በገበያው መናር ተስፋ ቆርጬ፣ ልታነቅ ነው አልልህም፡፡ ባይሆን የእርዱ ዋጋ ስላልቻልን ወደ አደን እየወጣሁ ነው…” ስለው በመልሴ እግሩን አንስቶ ሳቀ፡፡ እኔም ሳቅሁና ወደ ቤት ገባን፡፡
ጫካው ግፋ ቢል ጅብ ይገኝበት እንደሆነ እንጂ የእርድ እንስሳት አይታሰብም፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ዶሮ እንኳ በጫካው ትርው አይሉም፤ ያውም ዓመት ባዕል ሲደርስ፡፡ በርግጥ ዶሮ ባይኖር፣ ዶሮ አራጅ (ሙጭልጭላ) አይጠፋ ይሆናል፡፡ በእውነት ግን ዶሮን የሚተካ የሚበላ የአሞራ ዘር ባድን ምን ይለኛል? የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ አባታችን የቆቅና የዝግራ ሥጋ እንዴት እንደሚጣፍጥ ሲተርክልን የነበረው ትዝ አለኝ፡፡ ዛሬ ቆቅና ዝግራ ያውም በዚህ ጫካ ማደን ቀርቶ ማየት የሚከብድ ይመስለኛል። ሌሎች የወፍ ወይም የአሞራ ዘሮችም ሥጋቸው ስላልተቀመሰ እንጂ ከዶሮም ሊበልጡ ይችላሉ የሚል ሃሳብ መጣብኝ፤ ወዲያው የምግብ ምርጫ ማህበራዊ ህጋችን ወይም በአጠቃላይ አነጋገር የአመጋገብ ባህላችን ችግር እንዳለበት፣ ለችጋር የሚያጋልጥ እንደሆነ መጠየቅ፣ መመራመር ወይም መፈላሰፍ አሰኘኝ፡፡
ኧረ ለመሆኑ፣ የሚታደኑ እንስሳት ቢገኙ እንኳን እንዴትና በምን ማደን እንደሚቻል አላውቅም…መቼም የሽንኩርት ቢላዋ ወይም የድስት ማማሰያ ይዤ ለአደን አልወጣም፡፡ ባለቤቴንና ልጆቼን አስከትዬ ብሄድም፣ የሚሳካ አይመስለኝም ወዘተ…እያልኩ ከራሴ ጋር ማውጋት ጀመርኩ፡፡ መቼም፣ “ሳይጠሩት ዘማች” የሚል ምሣሌ የሚጠቅሱብኝ አይመስለኝም፡፡ እኔ ወደዚህ ሁሉ ጣጣ የገባሁት፣ የአዲስ ዓመት እርድ ገበያ፣ ከጳጉሜ የኪሣራ ቀናትና ከልጆች የትምህርት ወጪ ጋር አብሮ ስለ ኑሮ ሁኔታ ስላሳሰበኝ ነው፤ “ስላሳበደኝ ነው” እስከማለት ግን አልደፈርኩም፡፡
ምንም ሆነ ምን ግን “ለእርድ የሚሆኑ እንስሳትን ማደን” የሚል አማራጭ የኑሮ ዘዴ ፖሊሲ በመንደፌ ቢያንስ ባለቤቴን አስቄበታለሁ፡፡ ከፍ ሲልም፣ የሥራ ፈጠራ ጥረቴን ለማሳየት አስችሎኛል…ባለቤቴም በእቅዴ እየተገረመና እየሳቀ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አነሳብኝ፤ “ለመሆኑ ለአዲስ ዓመት የሚሆኑ የእርድ እንስሳትንም ቢሆን ለማደን ፈቃድ አያስፈልግም? የምር ግን ማንም እንደፈለገው ማደን ይችላል? …ህግ፣ ፍቃድ ምናምን የሚባል ነገር ባይኖር እኮ ሰው ሁሉ የጐረቤቱን ዶሮና በግ ‘ያደንኩት ነው’ እያለ ያርድ ነበር…” አለ፡፡ እኔ ግን ንግግሩን ሳይጨርስ፣ ሼልፍ ላይ ወደተቀመጡ መጻሕፍት አመራሁ፡፡ አንድ ትልቅ ሀገርኛ መጽሐፍ አውጥቼ፣ ማገላበጥ ጀመርኩ፡፡
ባለቤቴም፣ ልጆቼም ወደ “እኔ ቀርበው አይናቸውን ከመጽሐፉ ገፆች ላይ ተከሉ፡፡ “ብራቮ! ‘ስለ ዱር አውሬ አደን’ የሚል ጽሑፍ” ስል፣ ባለቤቴ ፈጠን ብሎ፣ “ይነበብልና” አለኝ፡፡ ወዲያው፣ “የአውሬ አደን በኢትዮጵያ የጨዋ ልጆች ዋና ሞያ ሆኖ ክብርም ደረጃም ያስገኝ እንደነበረ እኔም ከደረስኩ ተመልክቼዋለሁ” የሚለውን የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል ጽሑፍ አነበብኩ። እንደቀልድ የተጀመረው የአደን ጉዳይ ብዙ እንድንጠይቅና እንድናነብ አነቃቃኝ፡፡
“በቀድሞ ዘመን ገና ጠመንዣ ባገራችን ሳይገባ፣ ጐበዞቹ አውሬ ያድኑ የነበሩት በጦርና በጐራዴ ስለነበረ፤ ይኸም ዐይነት አደን ከበሽታው ሌላ ለሕይወት የሚያሰጋ ነገር ያመጣባቸው እንደነበር ማንም ሊገምተው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ዠግኖቹ ከክንዳቸው መጠንከርና ከልባቸው ሙሉነት የተነሳ የሚያስፈሩትንና የሚያሰጉትን አውሬዎች በድፍረት በጦር እየወጉ መግደላቸውን ያዩ ሽማግሌዎች ያረጋግጣሉ” የሚለውን በጋራ አነበብነው፡፡
አንዷ ልጄ፣ “የጨዋ ልጆች” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላነሳችብን ድንገተኛ ጥያቄ፣ ወደ አባቷ “ሪፈር” በመላክ እኔ ንባቤን ቀጠልኩ፡፡ ጥያቄው ብዙ ታሪካዊና ባህላዊ ዳራዎችን እያወሱ ማስረዳትን እንደሚጠይቅ እኔም ባለቤቴም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ትንሹ ልጄ፣ “የባለጌ ልጅ ያልሆነ ማለት ነው?...” ብሎ በጥያቄ የመለሰውን ድፍረት አባቱን ቅር ያሰኘው መሰለኝ፤ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ “የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል በቀላል አቀራረብ” የሚል መጽሐፍ ለማዘጋጀት በሚያነቃ ደረጃ በወጉ ማስረዳቱን የተያያዘው፡፡
እኔ አሁንም፣ ዐይኔን ከመጽሐፉ አንቀፆች መንቀል አልተቻለኝም፡፡ ቀድሞ ከሚታወቁ ስመጥር አዳኞች መካከል፣ ዝሆን በጦር በመግደል ተደጋጋሚ ጀብዱ የፈፀሙትን “ፊታውራሪ ቡራዮ የሚባሉትን የወለጋ ሰው” የመጽሐፉ አዘጋጅ፣ ደራሲ ማኅተመሥላሴ እንደደረሱባቸውና በአካል እንዳዩዋቸው የገለፁበትን አንቀጽ እያነበብኩ ተደመምኩ፡፡ በአፄ ምኒሊክ የመካከለኛ ዘመን መንግሥታቸው ወዲህ የተለያዩ የአደን መሣሪያዎች እንደ ዛሬው ዘመን ባይበዙም ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበረ፣ እነዚህ የአደን መሣሪያዎቹም የጦር ወይም የውጊያ መሣሪያዎች እንደሆኑ እያነበብኩ፣ እኔ በሽንኩርት ቢላዋና በድስት ማማሰያ ለአደን መውጣት እንዳሰብኩ አድርጐ ባለቤቴ ያሳቀብኝ ወሬ ትዝ አለኝ - ሳቅሁ፡፡ ባለቤቴና ልጆቼ ውይይታቸውን አቁመው የሳቅሁበትን ምክንያት ለማወቅ ወደ እኔ ዞሩ፡፡ ትንሹ ልጄ የሳቅሁበትን እንድናገር በጥያቄ ወተወተኝ፡፡ “በሉ ሁላችሁም የሽንኩርት ቢላዋና ማማሰያ እየያዝን ወደ ጫካ እንውጣ፤ ለአደን ተዘጋጁ፤ የአመት ባዕል ሥጋ ቁጭ ብሎ አይገኝም!” ሥል ቤቱ ሁሉ ጥርስ በጥርስ ሆነ፡፡
ባጋጣሚ የተጀመረው የአደን ወሬና ንባብ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን አሳወቁን፡፡
በአገራችን በነበረው የአደን ባህል፣ አንበሳ ከገደለ ግስላ የገደለ የበለጠ ክብርና ሞገስ እንደሚያገኝ፣ በጀግንነቱም የበለጠ እንደሚደነቅ አነበብኩ፡፡ የአራዊቶች ሁሉ ንጉስ አንበሳ ነው እያለ በሚናገር ህብረተሰብ ውስጥ አድገን፣ ከአንበሳ የበለጠ ግስላ ወይም ቀጭኔ ያደነ ትልቅ ክብርና ሞገስ እንዳለው በማወቃችን እኔና ባለቤቴም ተገርመናል፤ ልጆቻችንም ከአንበሳ በላይ የሚያስከብሩ ሌሎች አራዊቶች መኖራቸውን ለመቀበል ሁሉ ተቸገሩ፡፡ ስለዚህ ስለ አደን ባህላችን ብዙ እያነበብን ብዙ ለመወያየት ተስማማን፡፡
እናም፣ ስለ አደን ህግ፣ አዋጅ፣ ስለሚታደኑ እንስሳትና ስለሚገኘው ክብርና ሞገስ…የማኅተመሥላሴን መጽሐፍ እያጣቀስን በቤታችን የምናደርገውን ውይይት “ለአዲስ አድማስ” አንባቢዎችም ለማካፈል እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያው ግን፣ በእኔ ቤት የአዲስ ዓመት መዋያ እርድ ባይታረድ እንኳ፣ ብዙ አያስጨንቀንም፤ ቢያንስ ስለ አደን ባህላችን እያነበብንና እየተወያየን ቤት ባፈራው ምግብና መጠጥ በደስታ እንደምናሳልፍ ማረጋገጫ አግኝቻለሁ፡፡ በርግጠኝነት ግን የምነግራችሁ፣ አላስፈላጊ ብድር ውስጥ ገብተን እርድ ወደ ማረድ እንደማንገባም ይታወቅልን፡፡ እኔና ቤተሰቤ በአዲስ ዓመት ዋዜማም በሉ መባቻ በግና ዶሮ ባናርድ እንኳ፣ መጻሕፍትን እያነበብን አዳዲስ መረጃዎችንና እውቀቶችን በመበለት በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ያረቀቅሁትን የኑሮ ዘዴ አያችሁልኝ? አያዋጣም? “የአዲስ ዓመት እርድ ቢሉ፣ አደን ትዝ አለኝ” ማለት እንዲህ ነው፡፡

Read 2307 times