Print this page
Friday, 13 September 2013 12:36

የወንደላጤው የአዲስ ዓመት ፀሎት!

Written by  ነ.መ
Rate this item
(2 votes)

አምላኬ ሆይ!
በዚህ አዲስ ዓመት
ምነው ያንዷን ድምጿን
ምነው ያንዷን ሳቋን
ምነው ያንዷን ሽንጧን
ምነው ያንዷን ባቷን
ምነው ያንዷን ጡቷን
ምነው ያንዷን ዓመል
ምነው ያንዷን አንጐል
ያንዷን ጨዋታዋን
የሚጥም ለዛዋን
ከየአካሏ ነጥቀህ
ከገላዋ ሰርቀህ
ሁሉን ማግኘት ብችል ነጥዬ ለብቻ
ሙሉ ሴት ለማግባት፣ አዋህዶ አንድ አርጐ፣ የህይወትን አቻ
ይሄ ነው ፀሎቴ
ንጥሩ ምኞቴ
በሌት - ቀን ጐዳና
እንዲህ ነው እምወድ ‘ራሴን በጠና!
ያው እንደምታውቀው፤
ራስ ወዳድነት
ሌላውን ካልነካ፣ ምን ክፋት አለበት?!
አሜን…አሜን…አሜን…ለወንደላጤነት፡፡
ለዚህ ነው እስካሁን ሚስት ያላገባሁት፡፡
አምላክ ሆይ አድምጠኝ፡፡
ወይ ማረኝ፤
ወይ ዳረኝ፡፡
ወይ እኔኑ አጽድቀኝ፣ ወይ ምርጫዬን ስጠኝ!
አምላክም መለሰ፡-
አዳም ወንደላጤው ስማ መስሚያ ካለህ
ከግራ ጐንህ ላይ፣ አንድ ያጐደልኩብህ
ሙሉ እንደማትሆን፣ ነበረ ልንገርህ፡፡
ስንት ዘመን ኖረህ፣ አሁንም አልገባህ፡፡
ምኞት ብቻኮ ነው፣ ፍፁምነት ማለት
ይህ ገብቶህ አግባና፣ ያቅምህን አንዲት ሴት
ተዳምራችሁ ሙሉ፣ ይሄን ያንተን ፀሎት
አለዛ እርግማኔ
በብቸኝነት እጅ፣ በቅን ፍቅር ጠኔ
ስትመርጥ እንድትኖር ነው፣ ያላንዳች ውሳኔ፡፡
ኩነኔ ማለት ነው፣ የወላዋይ ወኔ!!
ማነብነቡን ተወው፣ አይጠቅምህም ፀሎት
ይልቅ ዝቅ ብለህ፣ እጅህን ዘርጋላት
የህይወት እኩያህ፣ እንድትመጣ አንዲት ሴት
ሂጂም አትበላት፣ ነይም አትበላት
የእንቁጣጣሿ’ለት፣ አበባ አዙርላት!
ሰኔ 1998 ተጀመረ ሰኔ 2005 አለቀ)
(ለብኩን ወንደላጤ)

Read 4407 times