Print this page
Friday, 13 September 2013 12:26

የሚሊኒየም አዳራሽ የዋዜማ ሙዚቃ ለሳምንት ተራዘመ

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

በውጭ ምንዛሬ እጥረት ክፍያ በጊዜ አልደረሳቸውም

ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ የ”ፒስኩዌር” ሙዚቀኞች በክፍያ መጓተት ሳቢያ ዛሬ በአዲስ አመት ዋዜማ በሚሊዬኒም አዳራሽ ሊያቀርቡት የነበረው የሙዚቃ ድግስ ለሚቀጥለው ሳምንት መሸጋገሩን አዘጋጆቹ ገለፁ። ለዘፋኞቹና ለሙዚቃ ቡድናቸው በጥቅሉ 200ሺ ዶላር ገደማ በጀት ተይዞ እንደነበር ምንጮች የገለፁ ሲሆን
የዘፋኞቹ ክፍያ በዶላር እንደሆነ አዘጋጆቹ ጠቅሰው፤ ከባንክ የውጭ ምንዛሬ ለማስፈቀድ ጊዜ እንደፈጀባቸው ተናግረዋል፡፡
ዘግይቶም ቢሆን ክፍያው ለዘፋኞቹ ደርሷቸዋል፤ ነገር ግን፣ በአንድ ቀን ውስጥ ፈጣን ትራንስፖርት እንዲያገኙና እንዲመጡ ብዙ ጥረት ብናደርግም አልተሳካለንም ያሉት አዘጋጆቹ፣ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ደርሶብናል ብለዋል፡፡
ከናይጄሪያዊያኑ ዘፋኞች ጋር በዋዜማው የሙዚቃ ድግስ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞችም እንደሚቀርቡ የሚታወቅ ሲሆን፤ ደንበኞች ትኬት የገዙት ሁሉንም ዘፋኞች ለማየት ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞችን ብቻ ማቅረብ አንችልም ሲሉ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ለደንበኞቻቸው መረጃ ለማቅረብና ይቅርታ ለመጠየቅ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ የተናገሩት አዘጋጆቹ፣ የሙዚቃ ድግሱን ለመስከረም 11 ቀን እንዳሸጋገሩት ገልፀዋል፡፡
የዝግጅቱ ዋና ስፖንሰር ሜታ ቢራ ብዙ ወጪዎችን እንደሚሸፍን ምንጮች የገለፁ ሲሆን፣ የቲኬት ዋጋ እራትን ጨምሮ አንድ ሺ ብር ነው። በኮንሰርቱ አመልማል አባተ፣ ዘሪቱ ጌታሁን፣ ናቲማን፣ ጃሉድ፣ ታደለ ገመቹ፣ ፍቅርአዲስ ነቅአጥበብ፣ አብርሃም በላይነህ (ሻላይ) እና ተስፋዬ ታዬ ከመሃሪ ብራዘርስ ባንድ እና ከኩል ባንድ ጋር ይሳተፋሉ፡፡

Read 10529 times