Friday, 13 September 2013 12:23

በዓመት በዓል ገበያ ሽንኩርት ከዓምናው በእጥፍ ጨምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“ከበዓሉ ይልቅ ለልጆች የት/ቤት ወጪዎች ትኩረት መስጠት ይገባል”
*በግ ከ900 እስከ 3ሺ ብር *ሰንጋ በሬ 18ሺ ብር *ማኛ ጤፍ 2ሺ ብር

የዘንድሮው የአዲስ አመት ገበያ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የበአል ግብይቶች ብዙም የተለየ አለመሆኑን የተናገሩ የበዓሉ ሸማቾች ፤ የሽንኩርት ዋጋ ግን አይቀመስም ብለዋል፡፡ በመዲናዋ ዋና ዋና ገበያዎች ሽንኩርት ኪሎው 16 ብር እየተሸጠ ሲሆን ካለፈው ዓመት ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የ8ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ባለፈው አዲስ ዓመት ሽንኩርት በኪሎ ከ8 – 10 ብር እንደተሸጠ ይታወሳል። የሽንኩርት ዋጋ በእጥፍ የጨመረው ሽንኩርት ወደሚመረትባቸው አካባቢዎች የሚወስደው መንገድ በክረምቱ የተነሳ በመበላሸቱ እንደሆነ ነጋዴዎች ይናገራሉ።
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ተዘዋውረን የአመት በዓል ገበያዎችን በቃኘንበት ወቅት የኑግ ዘይት አንደኛ ደረጃው በአማካይ 48 ብር በሊትር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃው 47 ብር ነው፡፡ ቅቤ አንደኛ ደረጃ በኪሎ 150 ብር ሲሸጥ ሁለተኛ ደረጃው 125 ብር፣ 3ኛ ደረጃው 120 ብር ይሸጣል፡፡ በርበሬ በአማካይ ኪሎው 65 ብር ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡ እንቁላል በኤልፎራ ማከፋፈያዎች አንዱ 1 ብር 60 ብር ሲሸጥ፣ በሾላ ገበያ በ2 ብር፣ በሣሪስ ገበያ ደግሞ በ2ብር ከ75 ሲሸጥ ሰንብቷል፡፡
በተዘዋወርንባቸው የገበያ ስፍራዎች ተለቅ ያለ ዶሮ እስከ 180 ብር፣ መካከለኛው እስከ 120 ብር ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡ በግ ትልቁ እስከ 3ሺ ብር ዋጋ የተቆረጠለት ሲሆን መካከለኛው 1700 ብር፣ አነስተኛ የሚባለው ደግሞ 900 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡ ስለዓመት በዓል ገበያ የጠየቅነው የበግ እና የበሬ ነጋዴው ዮሐንስ ዘሪሁን ፤ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ከክልል አካባቢዎች በጐችን ማምጣት አስቸጋሪ እንደነበረ ገልፆ፣ ዋጋው ግን የተፈራውን ያህል አልጨመረም ብሏል፡፡ አብዛኛው ማህበረሰብ በመስከረም ወር የበግ እርድ የመፈፀም ባህል እንዳለውና መጪው የመስቀል በዓል በመሆኑ የበግ ተፈላጊነት ሊጨምር እንደሚችል ነጋዴዎች ተናግረዋል፡፡
በአብዛኞቹ ገበያዎች ፍየል ለሽያጭ ያልቀረበ ሲሆን ፍየል ባገኘንበት የሳሪስ ገበያ ሙክት ፍየል በ5ሺ ብር ሲሸጥ እንደነበር አይተናል፡፡ ፍየል የሌለበትን ምክንያት የጠየቅናቸው አንዳንድ ነጋዴዎች፤ በአዲስ አመት ከፍየል ይልቅ ብዙ የሚፈለገው በግ ስለሆነ ነው ብለውናል፡፡
የዓመት በዓልን የበሬ ገበያ ለማወቅ ከከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን አቃቂ (ቄራ) የቃኘን ሲሆን ባለፈው ቅዳሜ በዋለው ገበያ፤ ሰንጋ በሬ እስከ 18ሺ ብር ሲሸጥ፣ መካከለኛው 12ሺ ብር፣ ወይፈኖች ደግሞ 7ሺህ ብር ተሸጠዋል፡፡ በሰሞኑ ገበያ የጤፍ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎችና ሸማቾች ይናገራሉ፡፡ ተዘዋውረን በቃኘናቸው የገበያ ስፍራዎች የማኛ ጤፍ ዋጋ በአማካይ ከ2000-2100 ብር በኩንታል ሲሸጥ የሰነበተ ሲሆን ስንዴ ኩንታሉ ከ800-950 ብር ይገኛል፡፡ በሣሪስ ገበያ ለዓመት በዓል ሲሸምቱ ያገኘናቸው ወ/ሮ የኔነሽ መንበሩ፤ ኪሎው እስከ 200 ብር ደርሶ የነበረው ቅቤ አሁን በ150 ብር መሸጡ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ አብዛኛው የወጥ አይነት የሚሰራበት ሽንኩርት 16 ብር በመግባቱ ለሌሎች ሸቀጦች የመደቡትን ገንዘብ ለሽንኩርት ለማዋል መገደዳቸውን ተናግረዋል። የሽንኩርት ዋጋ ለምን እንደተወደደ የጠየቅናቸው አንዳንድ ነጋዴዎች፤ የሽንኩርት ምርቱ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶች በክረምቱ በመበላሸታቸው አቅርቦቱ ላይ ክፍተት በመፈጠሩ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ የሽንኩርት ዋጋ በአብዛኛው ከክረምት ይልቅ በበጋ እንደሚጨምር አንዳንድ ሸማቾች ያለፈ ተመክሮአቸውን በመጥቀስ ይናገራሉ፡፡
የአዲስ ዓመት መጥቢያ የሆነው መስከረም ወር በአብዛኛው ቤተሰብ ዘንድ ወጪ የሚደራረብበት ወቅት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ወሩ የትምህርት መጀመሪያ በመሆኑ ከአውደአመቱ ገበያ በተጨማሪ ከትምህርት ቤት ጋር የተያያዙ ወጪዎች አቅምን ይፈታተናሉ፡፡
ለገሃር አካባቢ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከተዘጋጀው ባዛር ለልጆቻቸው ጫማ ሲገዙ ያገኘናቸው አባት፤ ከበአሉ ይልቅ የልጆቻቸው የት/ቤት ቁሳቁሶች ማሟላት ላይ እንዳተኮሩ ይናገራሉ፡፡ “በአሉ በየአመቱ የሚመጣ ነው፡፡ ሌሎች በአሎችም ገና ይጠብቁናል። እንደኔ ልጆች ያላቸው የቤተሰብ ሃላፊዎች ከበአሉ ይልቅ ለልጆቻቸው አስፈላጊውን የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ቅድምያ መስጠት አለባቸው” ሲሉ የመከሩት እኚህ አባት፤ ለበአሉም ቢሆን እንደ ጐረቤታቸው ሳይሆን እንደ ቤታቸው የአቅማቸውን ማዘጋጀታቸውን ነግረውናል፡፡

Read 10010 times