Print this page
Friday, 13 September 2013 12:22

የአየር ኃይል ቬቴራንስ አሶስዬሽን የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም አዘጋጀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

የአየር ኃይል ቬቴራንስ አሶስዬሽን እያስገነባ ላለው ባለ 4 ፎቅ ሕንፃ ማስጨረሻና የአየር ኃይሉን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ማሳተሚያ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የአሶስዬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት መግለጫ፣ መስከረም 23 ቀን 2006 ዓ.ም ለሚደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ፣ ክቡር ዶ/ር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲ፤ ከ800 ሰዎች በላይ የሚይዝ አዳራሾችና እራት እንዲዘጋጅ መፍቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥቂት ሰዎችና አውሮፕላኖች በ1937 ዓ.ም የተመሠረተው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አኩሪ ታሪክ እንዳለው የጠቀሱት የአሶስዬሽኑ ሊቀመንበር ብ/ጀኔራል ተጫነ መስፍን፤ የአየር ኃይሉን የ68 ዓመት ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ለማሳተም፣ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎችና የአየር ኃይሉን የውጊያ ታሪክ በተንቀሳቃሽ ምሥል ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ በቢሾፍቱ ከተማ እየተገነባ ላለው ባለ 4 ፎቅ ሕንፃ ማጠናቀቂያ የገንዘብ ችግር ስለገጠመው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ምሽት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያዋ አውሮፕላን በ1921 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስታርፍ ብዙዎች ተደንቀው እንደነበርና ሥራቸውም መልዕክት ማስተላለፍ፣ አለቆች፣ ደጃዝማቾችና ራሶችን ማመላለስ እንደነበር የጠቀሱት ጀኔራል ተጫነ፤ ፋሲስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረች ጊዜ ቁጥራቸው 16 ቢደርስም የውጊያ ብቃት ስላልነበራቸው ሁሉም ማለቃቸውንና ዘመናዊ የአየር ኃይል በ1937 ዓ.ም በስዊድናውያን አሠልጣኝነት መቋቋሙን አብራርተዋል፡፡
አየር ኃይል ዘመናዊ ጄት አውሮፕላኖች ቢገዛም፣ የመጀመሪያዎቹ አብራሪዎች የአድዋ ድል የቀሰቀሳቸው ጥቁር አሜሪካውያን እንደነበሩ አንድ የአሶስዬሽኑ አባል ገልጸዋል፡፡ አየር ኃይሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙንና የውጊያ ብቃቱን በማሻሻሉ፣ ሁለት ጊዜ የሶማሊያን ወራሪ ኃይል ድባቅ በመምታት የአገሩን ሉዓላዊነት ማስከበሩን ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡
አፍሪካዊያን ስለ አውሮፕላን በቂ እውቀት ባልነበራቸው በ1950ዎቹ ዓመታት አየር ኃይሉ በነበረው የውጊያ ብቃት በተባበሩት መንግሥታት ተመርጦ፣ በኮንጐና በታንዛኒያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መወጣቱን፤ የሱዳን፣ የናይጄሪያና የደቡብ የመን አየር ኃይል አባላት ማሠልጠኑን ሊቀመንበሩ አውስተዋል፡፡
በ1985 በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ የነበሩ የአየር ኃይል አባላት የመረዳጃ ማኅበር አቋቁመው ላለፉት 17 ዓመታት በከተማዋ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ1ኛ-3ኛ ለሚወጡ እንዲሁም ከ10ኛና ከ12ኛ ክፍሎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተማሪዎች ሲሸልሙ መቆየታቸውን አንድ የአሶስዬሽኑ አባል ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም መረዳጃ ማኀበሩና የከፍተኛ መኮንኖቹ ተልዕኮ ተመሳሳይ ስለሆነ፣ አንድ ላይ ሆነው የአየር ኃይል ቬቴራንስ አሶስዬሽኑን መሥርተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ብ/ጄኔራል ተጫነ መስፍን ተናግረዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም የተመሠረተው የቬቴራንስ አሶስዬሽን በአሁኑ ወቅት 600 አባላት ሲኖሩት፣ አየር ኃይሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አገልግለው በተለያዩ ምክንያቶች በጡረታ የተገለሉ አሁንም በማገልገል ላይ ያሉና ወደፊትም የሚሰናበቱ አባላትን እንደሚይዝ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

 

Read 7561 times