Friday, 13 September 2013 12:15

አየር መንገድ ከፒቲኤ ባንክ ጋር የ22 ሚ.ዶላር ስምምነት ተፈራረመ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያስገነባ ላለው የሠራተኞች መኖሪያ ቤት ከፒቲኤ (ከፕሪፈረንሻል ትሬድ ኤርያ ወይም ከምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድና የልማት ባንክ) ጋር የ22 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ወ/ማርያም እንደጠቀሱት፣ አየር መንገዱ የሚያሰለጥናቸው ሙያተኞች የቤትና ትራንስፖርት አገልግሎት ወደሚሰጣቸው መካከለኛው ምስራቅ አገሮች መፍለሳቸውን ለመቀነስ 1‚192 ቤቶች እያስገባ መሆኑንና ለትራንስፖርት አቅርቦትም እያሰበበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለሰራተኞቹ እየተሰሩ ያሉት ቤቶች ግንባታ 30 በመቶ መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡
የፒቲኤ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አድማሱ ታደሰ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ የመጣ ስምና ዝና ያለው በመሆኑ ብድሩን እንደሚከፍል በመተማመን የዳሬክተሮችና የማኔጅመንት ቦርዱ ብድሩን መፍቀዱ ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ፣ባንኩ 29ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን በኢትዮጵያ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉባኤው እዚህ እንዲሆን የተወሰነው ኢትዮጵያ የባንኩ መስራችና ከፍተኛ ባለአክሲዮን በመሆኗና እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚ ከሚያስመዘግቡ 10 የዓለም አገሮች አንዷ በመሆኗ ኢኮኖሚውና የንግዱን ማህበረሰብ ለማነሳሳትና ለመደገፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባንኩ እስካሁን በኢትዮጵያ ያደረገው የፋይናንስ ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የባንኩ ካፒታል እያደገ በመምጣቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ካለችው ኢትዮጵያ ጋር መስራት የሁሉንም ወገኖች ዕድገት ከፍ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡
ፒቲኤ እስካሁን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 22 ሚ.ዶላር፤ ለሀበሻ ሲሚንቶ 50.5 ሚ.ዶላርና ለግሪን ኮፊ ኢንተርፕራይዝ 2.4 ሚ.ዶላር ብድር መስጠቱን ጠቅሰው፣ ወደፊት በአስመጪና ላኪ ዘርፍ ከተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

Read 7061 times