Print this page
Saturday, 07 September 2013 11:54

ዋልያዎቹ በሞት ሽረት ምዕራፍ ላይ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዛሬ የምድብ 1 የሞት ሽረት ፍልሚያዎች በኮንጎ ብራዛቪል ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ደርባን ላይ ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና በሚገናኙባቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በምድብ 1 የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በ5 ጨዋታዎች ምንም ሳትሸነፍ በ1 ጨዋታ በቅጣት 3 ነጥብ ተቀንሶባት በ10 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ ምድቡን ትመራለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ8 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ቦትስዋና በ7 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው መካከለኛው አፍሪካ በ3 ነጥብና በ6 የግብ ዕዳ መጨረሻ ነች፡፡
ዛሬ ከመካከለኛው በአፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በኮንጎ ብራዛቪል የሚፋለመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ሐሙስ ምሽት በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል አሸኛኘት ሲደረግለት የአግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ‹‹የፈፀምነውን ታሪካዊ ስህተት በታሪካዊ ድል በመመለስ ድሉን ለህዝባችን የአዲስ አመት ስጦታ እናደርገዋለን ›› ብለው የተናገሩ ሲሆን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ቡድናቸው ወሳኙን ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት የሚያስፈልገውን ዝግጅት እንዳደረገ፤ ተጨዋቾቻቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አምበል የሆነው ደጉ ደበበ ‹‹የህዝብ አደራ ተቀብለን እንደምንጓዝ እናውቃለን በድል አድራጊነት የተጓዝንበትን የ2005 ዓ.ም በድል እንደምናጠናቅቀው እምነቴ ነው›› ብሏል፡፡ ዋልያዎቹ ሞቃታማ የሆነውን የኮንጎ ብራዛቪል የአየር ጠባይ ለመላመድ በአዳማ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡ ዋልያዎቹ በዛሬው ጨዋታ የሚኖራቸው ውጤታማነት አዲሱን ዓመት በታላቅ ተስፋ ለመጀመር ከማስቻሉም በላይ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ስፖርት አፍቃሪው ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የዓለም ዋንጫ የምታልፍበትን እድል በስፋት እንዲነጋገርበት ምክንያት ይሆናል፡፡
ጎል የተባለው የስፖርት ድረገፅ ከምድብ 1 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጨረሻ ትንቅንቆች በፊት ከአንባቢዎቹ ድምፅ በማሰባሰብ ባወጣው ትንበያ በኢትዮጵያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ጨዋታ ሙሉለሙሉ የአሸናፊነቱ ግምት ለዋልያዎቹ አድልቷል፡፡ ኢትዮጵያ ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክን 3ለ1 ታሸንፋለች ያሉት 30.1 በመቶ፤ 2ለ1 ያሉት 15.53 በመቶ እንዲሁም 2ለ0 ያሉት 14.56 በመቶ ናቸው፡፡ ለሌላው የምድቡ ጨዋታ በተሰጠ ግምት ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና 1ለ1 አቻ ይወጣሉ ያሉትቨ 13.04 በመቶ ያህሉ ሲሆኑ 17.39 በመቶው 2ለ0 እንዲሁም 21.74 በመቶ 3ለ1 ደቡብ አፍሪካ እንደምትረታ ተንብየዋል፡፡
ዋልያዎቹ እና
የምድባቸው ቡድኖች ዝግጅት
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው 1 ዓመት በዓለም ዋንጫው የ3 ዙር ማጣሪያዎች ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች አልተሸነፈም፡፡ በተጋጣሚዎቹ ላይ 11 ጐል አግብቶ የቆጠረበት 5 ነው፡፡ በእያንዳንዱ ተጋጣሚው ላይ በአማካይ 1.57 ጐል ያገባል፤ 0.71 ጐል ይገባበታል፡፡ በማጣሪያዎቹ በአጠቃላይ 12 ቢጫ ካርዶች የዋልያዎቹ ተጨዋቾች ተቀጥተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርግበት ግብዣ ከወር በፊት ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ብዙዎቹ ተጨዋቾች እረፍት ላይ በመሆናቸው እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንፌደሬሽን ካፕ ከነበረው ተሳትፎ በተያያዘ እድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ለአቋም መፈተሻ የሚሆኑትን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከሱዳን እና ብሩንዲ ጋር ለማድረግ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም፡፡ የመካከለኛው አፍሪክ ሪፖብሊክ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ለአቋም መፈተሻ የሚሆነውን ግጥሚያ ከሊቢያ ጋር በማድረግ 0ለ0 ተለያይቷል፡፡ ዛሬ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር ለሚደረገው ወሳኝ ፍልሚያ ለዋልያዎቹ 23 ተጨዋቾች ተመርጠዋል፡፡ ከተለያዩ አገራት ለብሄራዊ ቡድኑ የተመረጡ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ሳላዲን ሰኢድ ከስኬርቴ ክለብ ቤልጅዬም፤ ጌታነህ ከበደ ከዊትስ ክለብ ደቡብ አፍሪካ፤ሽመልስ በቀለ ከአሊትሃድ ክለብ ሊቢያ እንዲሁም አስራት መገርሳ ከራህማት ክለብ እስራኤል ናቸው፡፡8 ተጨዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኑ ያስመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ነው ሲሆን ሳምሶን አሰፋ ፣ ሳላዲን በርጌቾ ፣አበባው ቡጣቆ ፣ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ምንያህል ተሾመ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ አዳነ ግርማና ኡመድ ኡክሪ ናቸው፡፡ ከዘንድሮው የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ደደቢት አምስት ተጨዋቾች ሲመረጡ እነሱም ሲሳይ ባጫ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ ፣ስዩም ተስፋዬ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ማይክል ጆርጂ ናቸው፡፡ ቶክ ጀምስና ፋሲካ አስፋው ከኢትዮጵያ ቡና፤መድሃኔ ታደሰና ሽመልስ ተገኝ ከመከላከያ ፤ዮናታን ከበደና ደረጀ ዓለሙ ከዳሸን ቢራ፤ ሙሉዓለም መስፍንና አንተነህ ተስፋዬ ከአርባምንጭ ተመልምለዋል። የተቀሩት ሞገስ ታደሰ ከመድን፤ በረከት ይስሃቅ ከመብራት ሃይል፤ ተክሉ ተስፋዬ ከንግድ ባንክ ናቸው፡፡ባፉና ባፋዎቹ ለመጨረሻው የሞት ሽረት ትንቅንቅ በፕሮፌሽናል ቡድናቸው ተጠናክረዋል። 4 ተጨዋቾች ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ ሁለት ወጣት አማካዮች ከሆላንዱ ኤር ዲቪዜ፣ ከፍተኛ ልምድ ያለው የቀኝ ተመላላሽ ከቤልጅዬም ክለብ እና ምርጥ የመሀል ተከላካይ ከሩስያ ፕሪሚዬር ሊጋ በመጥራት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ቦትስዋና በአመዛኙ በደቡብ አፍሪካ አብርሣ ፕሪሚዬር ሊግ በሚወዳደሩ ክለቦች ውስጥ ያሉ ከ10 በላይ ተጨዋቾች አሰባስባለች፡፡
የደቡብ አፍሪካው አሰልጣኝ ጐርደን ሌጀንሰንድ ከቦትስዋና ጋር በሚደረገው ጨዋታ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ማናቸውንም ነፍስ የምንዘራበት ውጤት እና ሂሳባዊ ስሌትን ከቡድኔ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ ከአጀማመር ይልቅ አጨራረስን ማሰብ ይሻላል ብለው የሚሰሩ አሰልጣኝ መሆናቸውን ሱፐር ስፖርት በዘገባው ገልጿል፡፡ ጎርደን ሌጀሰንድ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ቦትስዋናን ካሸነፈን በተከታታይ ካደረግናቸው 4 ጨዋታዎች 3 አሸንፈን ማለት ነው፡፡ ይህ በውድድር አንድ ብሔራዊ ቡድን ሊያገኝ የሚቻለው ከፍተኛ ውጤት ነው። ዋናው ነገር ቦትስዋን እንደምናሸንፍ እርግጠኞች መሆናችን ነው፡፡ በተቀረ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ኢትዮጵያን በማሸነፍ ትረዳናለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን በሞግዚት አሰልጣኙ ስታንሌ ቶሶሄኔ የሚመራው ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸው ያልተጠበቀ ድል ማስመዝገቡ እንደማይቀር እምነቴ ነው ብለው ተናግረዋል፡፡አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በጨዋታው ላይ አስተያየት ሲሰጡ‹ የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድናችን በፊፋ ቅጣት 3 ነጥብ በተቀነሰበት ሰሞን ከሩዋንዳ ጋር ለቻን ውድድር ለማለፍ የደረሰውን የደርሶ መልስ ትንቅንቅ በማሸነፍ ጥንካሬው ታይቷል፡፡ በተቀነሰብን ነጥብ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በማጣርያው የማለፍ ተስፋን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና በኛ ተጨዋቾች ያለው ጠንካራ መንፈስ ሙሉ ለሙሉ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን በማሸነፍ ላይ የሚያተኩር ነው። ሙሉ 3 ነጥብ በመውሰድ እናሸንፋለን። በማለት ተናግረዋል፡፡ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ አሰልጣኝ የሆኑት ሄርቬ ሉጁዋንጂ‹‹ ብራዛቪል የገባነው ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ነው፡፡ በምድቡ ሁሉም የሚገርፈው ቡድን የእኛ መሆኑን የሚያስቡ አሉ፡፡ ይህን አስተሳሰብ ፉርሽ ማድረግ እንፈልጋለን። በሁሉም የምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ነበርን፤ ውጤት ያጣነው በእድለቢስነት ነው። ኢዮጵያን እናከብራታለን እንጅ እንፈራትም፡፡›› በማለት ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አስሩ ምድቦች ያሉበት ሁኔታ
በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪካቸው እስከ ሩብ ፍፃሜ በመድረስ የአፍሪካን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ጋና እና ሴኔጋልን ጨምሮ 5 አገራት ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ግጥሚያዎች ምድቦቻቸውን በመሪነት ጨርሰው ለማለፍ አንድ ነጥብ ብቻ የሚፈልጉ ናቸው። ጋና፤ ናይጄርያ፤ ሴኔጋል፤ ካሜሮንና ቱኒዚያ ምድቦቻቸውን በመሪነት ለመጨረስ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አቻ ውጤት ይበቃቸዋል፡፡ በምድብ 1 ኢትዮጵያ ለማለፍ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን ማሸነፍ ግድ ይሆንባታል፡፡ የኢትዮጵያ አቻ መውጣት ለደቡብ አፍሪካ ቦትስዋናን አሸንፎ የማለፍ እድል የሚፈጥር ሲሆን መሸነፍ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን ማሸነፍ ከቻለች ለቦትስዋናም ማለፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በምድብ 2 ከፍተኛ የማለፍ እድል ያላት በ11 ነጥብና በ6 የግብ ክፍያ የምትመራው ቱኒዚያ ነች፡፡ ከምድብ 3 አይቬሪኮስት ማለፉ አረጋግጣለች፡፡ በምድብ 4 ጋና በ12 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ መሪነቱን ብትይዝም ዛምቢያ በ1 ነጥብ ብቻ ተበልጣ በተመሳሳይ የግብ ክፍያ እየተከተለች ነው፡፡ በምድብ 5 ኮንጐ በ10 ነጥብ 5 በ1 የግብ ክፍያ እየመራች ነው፡፡ ቡርኪናፋሶ በ9 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ እንዲሁም ጋቦን በ7 ብር በ5 የግብ ክፍያ የማለፍ ዕድል እንደያዙ ናቸው፡፡ በምድብ 6 ናይጄሪያ በ9 ነጥብና 3 የግብ ክፍያ ብትመራም ማላዊ በ7 ነበር በ3 የግብ ክፍያ እንዳደፈጠች ነው፡፡ ግብጽ ከምድብ 7 ከመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች በፊት ማለፏን ያረጋገጠችው በ15 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ነው፡፡ አልጀሪያ ደግሞ ምድብ 8ን በ12 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ ከ6ኛው ጨዋታ በፊት በመቆጣጠር ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ በምድብ 9 መሪነቱን ካሜሮን በ10 ነጥብና በ3 በግብ ክፍያ ብትይዘውም ሊቢያ በ9 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ ትከተላታለች፡፡ በመጨረሻም በምድብ 10 ሴኔጋል በ9 ነጥብና 4 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ ኡጋንዳ በ8 ነጥብና 5 የግብ ክፍያ ተናንቃለች፡፡ በማጣሪያው የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር በ5 ጐሎቻቸው ሦስት ተጨዋቾች ሲጠቀሱ፤ እነሱም ኢስማን ሱሊማን በ5 ጨዋታዎች 293 ደቂቃዎች በመጫወት፣ ጌታነህ ከበደ በ5 ጨዋታዎች 312 ደቂቃዎች በመጫወት እንዲሁም የግብፁ መሃመድ ሳላህ በ5 ጨዋታዎች 450 ደቂቃዎች በመጫወት ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሳላዲን ሰይድ በ4 ጨዋታዎች 347 ደቂቃዎችን ተጫውቶ ባስመዘገበው 4 ጐል ከሌሎች 7 ተጨዋቾች ጋር በማጣሪያው የኮከብ ግብ አግቢው ፉክክር የደረጃ ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡
የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ
የዓለም ዋንጫው የመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ የማጣሪያው 3ኛ ዙር ምዕራፍ ነው፡፡ በ2ኛው ዙር በምድብ ድልድል ላለፈው 1 ዓመት ሲደረግ በቆየው ፉክክር በአስሩ ምድቦች አንደኛ ደረጃ የያዙት 10 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸውን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ይወስኑበታል፡፡ ከምድብ ማጣሪያው የመጨረሻ 6ኛ ግጥሚያዎች በፊት ከምድብ 3 አይቬሪኮስት ከምድብ 8 ግብጽ እንዲሁም ከምድብ 9 አልጀሪያ ወደ 3ኛው ዙር ጥሎ ማለፍ መሸጋገራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ለቀሩት የ7 ብሔራዊ ቡድኖች ኮታ ዛሬና ነገ በሚደረጉ የምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ፍልሚያዎች ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዛሬው ጨዋታ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ከበቃች በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ ትልቅ ውጤት ይሆናል፡፡ በታሪካዊው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ሲሆን ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኝበት እድል ያመዝናል፡፡ ከአይቬሪኮስት፣ ከጋና ወደ ከናይጀሪያ ወይም ከአልጀሪያ፣ ከግብፅ ወይም ከቱኒዚያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሊገናኝ ይችላል፡፡ የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ ድልድል ለ10ሩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወጣው ከሳምንት በኋላ በካይሮ ነው፡፡ አስሩ ብሔራዊ ቡድኖች ለጥሎ ማለፍ ድልድል የሚወጣላቸው በሁለት ማሰሮዎች ሆነው አምስት አምስት ሆነው በመቧደን ሲሆን በሁለቱ ማሰሮዎች የሚገቡት ቡድኖች ማንነትን የሚወስነው በሚቀጥለው ሰሞን በፊፋ ይፋ በሚሆነው ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ነው፡፡የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ከወር በኋላ በኦክቶበር 11-15 የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች እንዲሁም ኖቬምበር 15-19 ላይ የመልስ ጨዋታዎቹ ይደረጋሉ። አፍሪካን ወክለው በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ወደምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የማያልፉ 5 ብሔራዊ ቡድኖች በ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡

Read 4118 times
Administrator

Latest from Administrator