Print this page
Saturday, 07 September 2013 11:24

የጉድ አውደ አመቶች!

Written by  አቡኪያ - ከአዳማ
Rate this item
(1 Vote)

አዲሱ አመት ከእሳት ጋር ሳይሆን ከሳቅ ጋር ----
ድንገተኛ ጩኸት… ያልተጠበቀ ዋይታ… ድብልቅልቅ ያለ እሪታ…
በ1997 ዓ.ም ወርሃ ጥር፡፡ ከወሩ ሌሊቶች በአንደኛዋ፡፡
መነሻው ያልታወቀ ጉድ፣ በእኩለ ሌሊት ከተፍ ብሎ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢን አናወጠው። በእንቅልፍ እረፍትን ሊጎናጸፍ ወደየአልጋው የገባው፣ በየዶርሙና በየላይብረሪው መሽጎ ደብተሩ ላይ ያቀረቀረው፣ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማራው… ሁሉም በድንገተኛው ጩኸት ደነበረ፡፡
ተኝተው የነበሩ ደንብረው ተነሱ፡፡ ህልምን ከእውን በሚለየው ድንበር ላይ ቆመው በተምታታ ስሜት እየተርገፈገፉ ጠየቁ፡፡
“ምንድን ነው?”
“ማን ነው የሚጮኸው?”
“ምን ተፈጠረ?”
ሁሉም ግራ በመጋባት ይጠይቃል እንጂ፣ ለጥያቄው እርግጠኛ የሆነ ምላሽ የሚሰጠው አላገኘም፡፡ የደነገጠ ልብ የተረጋገጠ ምላሽ እስኪያገኝ አይጠብቅም፡፡ ይገምታል… መላ ይመታል…
እሳት… አውሬ… መደርመስ… እንዲህ ያለ ሌላ ሌላ አደጋ!
አንዳንድ እማኞች ጩኸቱ የመጣበትን አቅጣጫ ጠቆሙ፡፡ 308 ተብሎ ከሚጠራው የሴት ተማሪዎች የመኝታ ህንጻ አካባቢ አመለከቱ፡፡ ይሄን የሰሙም፣ በእሳት የሚጋይ ህንጻ በአይነ ህሊናቸው እየታያቸው ወደዚያው ጎረፉ፡፡
ጩኸቱ ግን እንደተባለው ከ308 ህንጻ ብቻ አይደለም የሚሰማው፡፡ ከየአቅጣጫው ነው የሚደመጠው፡፡ እዚህም እዚያም እሪታ ሆነ፡፡ የሆነ ቦታ ላይ በሆነ ሰበብ የጀመረው ጩኸት፣ ስጋትና ጭንቀት የወለደው ሌላ ጩኸትን እየፈጠረ ዙሪያ ገባውን አናወጠው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ግቢ በእኩለ ሌሊት በዋይታ ተደበላለቀ፡፡ ጨለማ ውስጥ ሽብር ነገሰ፡፡ ሁሉም በጭንቅ ተውጦ ተተራመሰ፡፡
ሁሉም በድንጋጤና በፍርሃት እየተንቀጠቀጠ፣ ከወዲያ ወዲህ ተራወጠ፡፡ ምድረ ተማሪ የመጣውን ጉድ ለማየት ይሁን ከመጣው ጉድ ለማምለጥ በማይለይ መልኩ ደመነፍሱ ወደመራው አቅጣጫ ሮጠ፡፡
ጩኸቱ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ አልፎ፣ ባሻገር ወዳለው መንደር ዘልቆ፣ ወደ ከተማዋ ተሻግሮ ተሰማ፡፡ ከተራራ እስከ ተራራ…ከታቦር እስከ አላሙራ፣ ከመንደር እስከ መንደር… ከሰፈረ ሰላም እስከ አረብ ሰፈር ዙሪያውን ይሰማ ጀመር፡፡ ይሄን የውድቅት ዋይታ የሰማው የአዋሳ ህዝብ፣ ተማሪው በሆነ አደጋ ከመጥፋቱ በፊት ፈጥኖ ደርሶ ሊታደገው ወደ ግቢው ተመመ፡፡
ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሶችን የጫኑ መኪኖች ሳይረናቸውን እያሰሙ፣ በተሸከርካሪ መብራት ጨለማውን እየከተፉ ወደ ግቢው ከነፉ፡፡ ከውጭም ከውስጥም ጭንቅና ትርምስ ሆነ፡፡ ከብዙ ግርግርና ትርምስ፣ ከብዙ ድብልቅልቅና ውዥንብር፣ ከብዙ ስጋትና ፍርሃት በኋላ… ተማሪው ለማምለጥና ለመዳን፣ ፖሊስና ህዝቡ ለመድረስና ለማዳን በጨለማ ውስጥ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ከሮጡ በኋላ… ድንገት የጀመረው ጩኸት፣ ድንገት ቆመ፡፡
“ምንድን ነው ነገሩ?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ምላሽ አገኘ፡፡
“የኒው ይር ሴሌብሬሽን ነው!” ተባለ፡፡
ይህቺ ናት ‘ኒው ይር ሴሌብሬሽን’!!... በሰው ድግስ አስረሽምቺው!!...
ሁሉም የሰማውን ለማመን ተቸገረ፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የፈረንጆች አዲስ አመት የጠባው ከደቂቃዎች በፊት ነው፡፡ ይህቺን ሌሊት በጉጉት ሲጠብቁ የከረሙ፣ ወር ሳምንት… ቀን ሰዓት… ደቂቃና ሰከንድ ሲቆጥሩ የቆዩ፣ በአገራቸው ሆነው የሰው አገር ዘመን መለወጥ ያስፈነደቃቸው የአንድ ዶርም ‘ሞደርን ተማሪዎች’ ነበሩ ጩኸቱን የጀመሩት፡፡
የ‘ሞደርኖቹ’ የ‘ሴሌብሬሽን’ ጩኸት ከዶርም ዶርም፣ ከህንጻ ህንጻ እንደሰደድ እሳት እየተዛመተ፣ ብዙዎችን በፍርሃት ካንቀጠቀጠ፣ ፖሊስን ካተራመሰ፣ የአዋሳን ህዝብ ካላቀሰ በኋላ ተቋጨ!! የአዲስ አመት መጥባትን ምክንያት በማድረግ የተፈጠረ ጩኸት መሆኑ የተነገራቸው አንዳንዶች፣ በነገሩ ግራ ተጋቡ፡፡
“ደሞ በጥር የምን አዲስ አመት መጣ?” በማለት ጠየቁ፡፡
“የፈረንጆች አዲስ አመት ዛሬ ነው የሚገባው” የሚለው ማብራሪያም አላረካቸውም፡፡
“ታዲያ እነሱን በፈረንጅ አውዳመት ምን ጥልቅ አረጋቸው?... ቢሆንስ ደሞ፣ አመት በአል በጩኸት ነው እንዴ የሚከበረው?” አሉ በንዴትና በግራ መጋባት፡፡
እርግጥ ይህን ጩኸት ያሰሙት የአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሆናቸው ቀርቶ አየርላንዳውያን ቢሆኑ ኖሮነ ነገርዬው እምብዛም ባላስገረመ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዓሉ በዓላቸው፣ ጩኸቱም ባህላቸው ነውና!! አየርላንዳውያን የአዲስ አመትን አከባበር የሚጀምሩት፣ በዋዜማው ምሽት በየቤታቸው ግድግዳና በር ላይ ዳቦ በማንጠልጠል ነው፡፡ ዳቦው የተትረፈረፈ ጸጋን እንደሚስብና መጥፎ መንፈስንና ክፉ እድልን ከቤታቸው እንደሚያስወጣ ያምናሉ፡፡ በዚህም አያበቁም፡፡ ከቤታቸው በዳቦ ያባረሩት መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል ከደጃፍ እንዳይጠብቃቸው በመስጋት በእኩለ ሌሊት ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ ጆሮ የሚበጥስ ሃይለኛ ጩኸትም ያሰማሉ፡፡
ሁሉም በየደጃፉ ቆሞ አቅሙ በፈቀደው መጠን እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡ ህጻን አዋቂው ጉሮሮው እስኪደርቅ በመጮህ፣ ከደጃፉ ያደፈጠውን መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል ከአገር ምድሩ ጠራርጎ ያስወጣና፣ አዲስ አመትን “በል እንግዲህ ሰተት ብለህ ግባ!!” ብሎ ይቀበላል፡፡
የአዲስ አመትን መምጣትና የዘመንን መለወጥ እንዲህ በአስገራሚ አኳኋን የሚያከብሩ አገራትን ህዝቦች ተሞክሮ በጥቂቱ እንካችሁ…
አንዲት ብራዚላዊት የወርቅና የአልማዝ ጌጣጌጦቿን አወላልቃ ወደ ባህር ስትወረውር ቢያዩ፣ ጤንነቷን ሊጠራጠሩ ይችላሉ፡፡ አይጠራጠሩ! ጤነኛ ናት፡፡ ጌጣጌጦቿን ወደ ባህር የምትወረውረውም፣ ያለፈውን አመት በሰላም በጤና እንዳሳለፈችው ሁሉ፣ አዲሱ አመትም የሰላምና የጤና እንዲሆንላት አምላኳን ለመለመን ነው፡፡
ኮፓካባና ተብሎ የሚጠራው የብራዚል ባህር ዳርቻ፣ አመቱን ሙሉ በቱሪስቶች የሚጥለቀለቅ ታዋቂ የመዝናኛ ስፍራ ነው፡፡ ኮፓካባና ከአመት አመት የመዝናኛ፣ ከአመት አንድ ቀን ደግሞ የአውዳመት የማክበሪያና የመማጸኛ ባህር ነው፡፡ ብራዚላውያን በዘመን መለወጫ ዋዜማ በሚያከናውኑት ‘ፌስታ ዲ ኢማንጃ’ የተባለ ባህላዊ ክብረበዓል፣ ወደ ባህሩ አቅንተው ‘ኢማንጃ’ የተባለችዋን የባህር አምላክ ይለማመናሉ፡፡ አዲሱን አመት መልካም እንድታደርጋቸው ይጸልያሉ፡፡ በስተመጨረሻም ወደ ባህሩ እጅ መንሻ ይወረውራሉ፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ ወደ ባህሩ የሚወረወሩት ጌጣጌጦች ብቻም አይደሉም፡፡ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ሽቶዎች፣ አበቦችና ፍራፍሬዎች ጭምር እንጂ፡፡
ወደ አገራችን መጥቶ በጥምቀት በኣል የታደመ እንግዳ ዴንማርካዊ፣ ኮበሌው ወደ ልጃገረዷ ደረት ሎሚ ሲወረውርና ጡቷን ሲመታ ቢያይ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡ ወደ ዴንማርክ አቅንቶ የዘመን መለወጫ በዓላቸውን የታደመ የኛ አገር ሰው በተራው ፣ ስኒ እንደ ድንጋይ ወደየቤቱ ደጃፍ ሲወረወር ቢያይ በተመሳሳይ ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡
ዴንማርካውያን በአዲስ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ የማጀት እቃዎቻቸውን ለቃቅመው ወደ ጎዳና ይወጣሉ፡፡
በጨለማ ውስጥ ተደብቀው ወደመረጡት ጎረቤት ወይም ወዳጅ ዘመድ ቤት በማምራትም የማጀት እቃዎቻቸውን እንደ ድንጋይ ይወረውራሉ፡፡ በዚህች ምሽት ብርጭቆ፣ ትሪ፣ ሰሃን፣ ጭልፋ፣ ማንኪያ፣ ድስትና ሌላ ሌላው የቤትእቃ በሙሉ ከየመደርደሪያው ወርዶ ወደየቤቱ ደጃፍ ይወረወራል፡፡ ከግድግዳ እየተጋጨ፣ ከመስኮት እየተፋጨ፣ በየበሩ ሲሰባበር፣ በየደጃፉ ሲነካክት ያመሻል፡፡
ንጋት ላይ… ሁሉም ከቤቱ በመውጣት በየራሱ ደጃፍ የተጠራቀመውን ስብርባሪ የማጀት እቃ በማየት ደስታን ይጎናጸፋል፡፡ የተሰባበረው እቃ የመልካም ነገሮች ምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ምሽቱን ወደቤቱ ብዙ እቃ ሲወረወርበት ያደረ፣ሲነጋ ከደጃፉ ብዙ ስብርባሪ ተጠራቅሞ ያገኘ ቤተሰብ፣ በሌሎች ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ እንደሆነና መጪው አመትም በተለየ ሁኔታ የደስታ፣ የብልጽግናና የጤና እንደሚሆንለት ይታሰባል፡፡ ዴንማርካውያን ከዚህ በተጨማሪም በአዲሱ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ ወንበር የመዝለል ባህል አላቸው፡፡ ይህም ከአሮጌው አመት ወደ አዲሱ አመት፣ ከችግር ወደ ስኬት በሰላማዊ ሁኔታ የመሸጋገር ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
“ቺሊያውያን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር ነው የሚያከብሩት” ብዬ ስነግርዎት፣ “ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል?… እኛስ ከዘመድ አዝማድ ጋር አይደል እንዴ የምናከብረው?!” እንደሚሉኝ አውቃለሁ፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው…
የቺሊያውያንን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር የማክበር ባህል ከኛ የሚለየው ዋናው ነጥብ፣ ወደዘመዶቻቸው የሚሄዱት በዋዜማው ምሽት መሆኑ አይደለም፡፡ በህይወት ወዳሉ ዘመዶቻቸው አለመሄዳቸው እንጂ!! ቺሊያውያኑ በዋዜማው ምሽት በሞት የተለዩዋቸው ዘመዶቻቸው ወዳረፉበት መካነ መቃብር ያመራሉ፡፡ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠው መቃብር ውስጥ አረፍ ብለውም፣ ካረፉ ዘመዶቻቸው ጋር በዓሉን በዝምታ ጨዋታ ሞቅ ደመቅ አድርገው ያከብራሉ፡፡
አዲሱ አመት የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የሚመኙ የላቲን አሜሪካ አገራት ዜጎች ደግሞ፣ በዋዜማው ምሽት ቀይ ወይም ቢጫ የውስጥ ሱሪ የማድረግ ልማድ አላቸው፡፡ ቀዩ ለብልጽግና፣ ቢጫው ደግሞ ለፍቅርና ለሰመረ ትዳር ይመረጣል፡፡
በአዲስ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳርን ስለመሻት ካነሳን አይቀር፣ የአየርላንዳውያን ሴቶች ልማድ እንመልከት፡፡ በአዲሱ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳር ይገጥማት ዘንድ የምትመኝ አየርላንዳዊት ሴት፣ በበዓሉ ዋዜማ ሚስትሌቶ የሚባል የተክል አይነት በትራሷ ስር ሸጉጣ ታድራለች፡፡
በአገራችን ስራ ተፈትቶና ዘና ተብሎ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል፣ በኮሎምቢያና በሜክሲኮ ከዋዜማው እኩለ ሌሊት አንስቶ ከባድ ሸክም በመሸከም እንደሚከበር ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን?
የአሮጌው አመት የመጨረሻ ዕለት ተጠናቅቃ የአዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን ስትጠባ፣ ስኮትላንዳውያን ቤተሰቦች ማልደው በር በሩን ማየት ይጀምራሉ፡፡ ቀጣዩ የበዓል አከባበር የሚደምቀውና የሚሞቀውም ሆነ የቤተሰቡ የአዲስ አመት እጣፈንታ የሚወሰነው በጠዋት ነው፡፡ በዚህች ማለዳ ቀድሞ ወደ ቤታቸው የሚመጣው ሰው ነው ሁሉንም የሚወስነው፡፡
ደጃፋቸውን ቀድሞ የረገጠው ሰው፣ ቁመተ ሎጋና መልከመልካም ወንድ ከሆነ ደስታ ነው፡፡ እሱ የአዲሱ አመት መልካም እድል ምልክት ነው፡፡ ቀይ ጸጉር ያላት ሴት አልያም ህጻን ልጅ ከሆነ ደግሞ አመቱ ለቤተሰቡ ይዞት የሚመጣው አንዳች መከራ አለ ተብሎ ይታመናል፡፡
የሚመጣውን አዲስ አመት ወደቤታቸው በሚመጣው ሰው የሚተነብዩት ስኮትላንዳውያን ወንዶች፣ የዘመን መለወጫ በአልን በአጉል ጨዋታ ነው የሚያከብሩት - በእሳት እየተጫወቱ፡፡ ነበልባል እሳት እንደ ኳስ እያንጠባጠቡና በሰራ አካላቸው ላይ እያሽከረከሩ በመንገድ ላይ እየተደሰቱ በመጓዝ፡፡
አዲሱ አመት ከእሳት ጋር ሳይሆን ከሳቅ ጋር እየተደሰቱ የሚጓዙበት ይሁንልዎት!!

 

 

Read 2587 times