Saturday, 07 September 2013 10:59

፭ቷ …

Written by  ዋሲሁን በላይ (አዋበ)
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ ነሐሴ ፴ ነው፡፡
ቀኑ ይበራል አይገልፀውም፡፡
ቀኑን እየተጉመጠመጠ የሚውጠው ወር ከመቼው ከተፍ እንደሚል እንጃ! እንዴት ነው “እሚገፋው … ህይወት … ያለ ምንም ለውጥ? … ጊዜው ሽምጥ ይጋልባል፡፡
እትዬ ንጋቷ በራቸው ላይ ተቀምጠው ሶስት ነገር እያከናወኑ ነው፡፡ በመዘፍዘፊያ ሙሉ የተላጠውን ሽንኩርት ሰተቴ ድስት ውስጥ ከተው የልጅ ልጃቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ ተርከክ ብሎ የሚነደው ከሠል ላይ በሸክላ ድስት የጣዱት ሽሮ ወጥ ሙያቸውን ለማሳበቅ ሽታው ሳያንኳኳ ቤቴ ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ ገርበብ ብሎ ከተከፈተው አገልግላቸው ጥጥ መዘዝ እያደረጉ ይፈትላሉ፤ ሳውቃቸው አንድ ሥራ ብቻ ይዞ መቀመጥ አይሆንላቸውም፡፡
በስንጥቁ የቤቴ ቀዳዳ ስመለከታቸው … ወጣቸውን እያማሰሉ … ቀመስ … አድርገው ማማሠያውን ሸክላው ጆሮ ላይ እንደ ጉትቻ አስቀምጠው … መልሰው ወደ ጥጣቸው ተጋቡ፡፡ እሚመጣ እሚገባውን ለመቃኘት ይመስል … ዓይናቸው ከወዲያ ወዲህ ከብለል ይላል፡፡
አቀማመጣቸው በሁለት ተቃኝቷል … እንዝርቱን ለማሾርና ከፍሙ ለመሞቅ በመጠኑ ገለጥለጥ ከፈተፈት ብለዋል፡፡
“ስሚ እንጂ ህብስቴ …” ስሜት ውስጥ ሆኗ ድምጿን ከሳቅ ጋር አሽታ ጠለዘችላቸው … የልጅ ልጃቸው ናት፡፡ “ኩበት እንዲህ የተወደደው ከብቶቹ ተደራጁ እንዴ…? ምነው እቴ … እኔ’ኮ ጨሰስ … ሸተት ሲል ነው ዓውዳመት ዓውዳመት የሚመስለው ብዬ ነው እንጂ በዚህ በኤሌክትሪኩ መጋገር አቅቶኝ አይደለም … የምን ችጋር ማቀንቀን ነው!” የምር ተማረዋል፡፡
“ደግሞ ህብስቴ … የመብራትና የውኃውን መልስ አልሰጠሽኝም፣ እምረሳ መስሎሽ …?” እንደ ስሟ የውኃ ዳቦ የመሠለ ሳቋን እየደወለች ወጣች፡፡
“እማ! ለአለቃ መልስ አይሠጥም እኮ!” ሳቋ ይገርማል፡፡
“ሞኚት… መልስ የማይሠጠው ለገንዘብ ሳይሆን ለአፍ እላፊ ነው፡፡ እኔ ንጋቷ ገንዘብ በዋልጌ ሜዳ ላይ ሲወድቅ አልወድም … ያንገበግበኛል፡፡” ወጣቸውን ጐብኝተው ወደ ጥጣቸው ተመለሱ፡፡
“እማ እንዴት ነው አዲሱን ዓመት በሽሮ እያጨበጨብሽ ልትቀበይው ነው…?”
“እስቲ አምስቷን ቀን ልፁም… ከዚህ በኋላ በላሁ አልበላሁ ለምኔ…! ይልቅ አንቺም ከቻልሽ ፁሚ…”
“ማ… ምን በወጣኝ … ኑሮ ራሱ ፆም አይደል…!” መንቀርቀር አለች፡፡
“አይ ሞኝት … ሳይጐድልበሽ መፆም መፀለይ ያልቻልሽ… ላንድ ሳምንት ብትቸገሪ … ጌታችንን ድጋሚ ትሰቅይዋለሽ፡፡”
“ኧረ በስመዓብ በይ እማ!”
“ይሁን እስቲ … በይ ከኛ ጓሮ ካለው ኮባ ሁለት ቁረጭና ለሸንኮሬ ውሰጅላቸው… እንዳትረሺ! አሁን ይሔን ሽንኩርት ቶሎ አስፈጭተሽ ነይ …”
“እማ!” ተገርማለች፡፡
“ፍሪጅ ውስጥ ይቀመጣል … የምን ሲደርስ መንደፋደፍ ነው … ዶሮዎቼንም ገለታ ባርኳቸው አጣጥቤ እከታለሁ”
በረጅም ገመድ የታሰሩት ሁለት ቀያይ ድምድም ዶሮዎች የሰሙ ይመስል በተራ በተራ ኩኩሏቸውን አስነኩት፡፡
አንገቴን ብቅ አድርጌ ሳያቸው … “አጅሬው ምነው ሰጐን ይመስል አንገትህን አሠገግህ…?” አሉኝ፡፡
“ደህና አደሩ እትዬ ንጋቷ …” ሙሉ በሙሉ ወጥቼ በሬ ጋ ቆምኩ፡፡
“ደህና አረፈዱ በሚለው ይታረም!” ቀይ ፊታቸው ላይ ፀሐይ የወጣች ይመስላል … አንገታቸው በንቅሳት ስቋል … ግራና ቀኝ እጃቸው አይበሉባው ላይ ወደል ወደል መስቀል አለ፤ ነጭ ሻሽ የመሠለው ጥርሳቸው በአረንጓዴ ከተወቀረው ድዳቸው ጋር ተዳምሮ እንኳን ስቀው ፈገግ ሲሉ ልብ ወከክ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዕድሜአቸው ገፍቶም ቀሽት ናቸው፤ ይብላኝ ልጅ እያሉ…!
“እንደምን አረፈዱ …” ስህተቴን ሳልረሳ ማረም ነበረብኝ፡፡
“እናትና ልጅ ክብር ይግባቸው፡፡ ከዘመን ዘመን እንደ አደይ አበባ ያልዘለለኝ አንድዬ ምስጋና ይድረሰው”
ማርያምን ሲወዷት አይጣል ነው፡፡ “ልጅም፣ አምላክም የወለደች ብቸኛ!!” እያሉ ይገረሙባታል፤ በመታደሏ፡፡
“አሜን” ዋናው እሱ ነው፤ ይመስላል አባባሌ - መሬት መሬቱን እያየሁ፡፡
“ምነው አቀረቀርህ …?”
“እ…ምንም”
“ደግሞ ምንድነው ከወንድምህ ጋር የምትናቆሩት…?”
“ኧረ እትዬ ንጋቷ ሊደፋኝ ነው…! ተሳስቼ ኪሴ ውሰጥ ሳልደብቀው ገንዘብ ካደረ … ገላውን ቀዶ ነው መሠለኝ የሚደብቀው አላገኘውም፡፡ ማታ ለዛ ነው የተጣላነው … በዛ ላይ ጥምብዝ ብሎ መጣ፡፡”
“ስማ ሃምሣ ብር ጠፋብኝ ብለህ ነው እንደዚህ አንድ ክፍለ ከተማ የተቀማህ ይመስል የምታቅራራው?!” በሩን በርግዶ ገፍቶኝ ወጣ፡፡ እትዬ ንጋቷ ጥሎባቸው ይወዱታል፡፡ “የህብስትን አባት ያስታውሠኛል፤ እንደሱ ቦጅቧጃ ነው” ስለሚሉ እሱም አይፈራቸውም፡፡
“ለምን አርፈህ አትወጣም … የተሰረቅሁት እኔ፣ የምትቆጣውና የምትሳደበው አንተ…” ታላቁ ነኝ፡፡
“አታካብዳ…!”
“ሠይጣን አሚር ጠጣ እሺ!”
“አፈር ብላ አንተ ቀውላላ፣ አማረብኝ ብለህ ነው ወንድምህን አሚር ጠጣ ብለህ የጋበዝከው … የኔ ሾላ እኔ ጉሽ ጠላ እሠጥሃለሁ…” በስስት ተመለከቱት፡፡
“ለነገሩ ሾላዬ ላንተኮ ዐፈር በጥብጠው ቢሠጡህ ትጋተዋለህ…”
ወንድሜ አቀረቀረ፡፡
“እየው ሾላዬ እንደው ስሞትልህ… እቺ ማታ እያመሸህ፣ በዛ ላይ ያማረብህ መስሎህ እያላዘንክ የምትመጣውን አቁም!” እንዳቀረቀረ … እራሱን በአዎንታ ነቀነቀላቸው፡፡
“ስጠኛ…?” ቀስ ብዬ ጠየኩት፡፡
“ምንድነው የምሠጥህ…?!” እሳቸው እንዲሠሙት ይመስላል አጯጯሁ፡፡
“ሌላው ቢቀር ለምንድነው የማታግዘኝ?”
“ምን ተሸከምክና?”
“አንተን መሸከም በራሱ … ሙሉ መጋዘን ብረት መሸከም እኮ ነው!”
“ታቅራራለህ እንዴ …” መላጣውን እያሻሸ … በቆረጣ እትዬ ንጋቷን ይመለከታል፡፡
“አትቀልድ! የትምህርት ቤት ክፍያ አለ … ቀለብ … ጋዝ አልቋል … እንዳየኸው አምስት ኪሎ ቲማቲም ሁለት ቀን ሳንጠቀምበት ተበላሽቶ ተጣለ፡፡ አንተ ፀሐይ ላይ ማውጣት ሰንፈህ አምስት ኪሎ ሽንኩርት በቀለ፣ በሰበሠ፣ ይሄ ሁሉ ብክነት አያሳዝንህም?” እትዬ ንጋቷ ዝም ብለው ጥጣቸውን እየፈተሉ ይሠማሉ፡፡
“እሺ አሁን ለምሣ ሰላሣ ብር ሥጠኝ?”
“አላበዛኸውም… እዚህ መጥተህ አትበላም … ወይ ቋጥረህ አትወጣም!”
“ማታ ስታላዝን መች ሰራህ!”
“ተው! ተው! እንተጋገዝ… አሁን በአስር የቤት ኪራይ አለ … ይሔ ሁሉ እኔ ጫንቃ ላይ ነው ያለው፡፡” ጆሮው ጋ ጠጋ ብዬ … ቀስ ብዬ ነበር በእርጋታ …
“እና መቻል ካልቻልክ ለምን አመጣኸኝ?!”
“ሰው ትሆናለህ ብዬ ነዋ! ኑሮን የምታግዘኝ መስሎኝ … ተምረህ እንድትለወጥ ጓጉቼ …” ተወራጨሁ፡፡ በጣም ተሠማኝ … ድግግሞሽ ህይወት ያስጠላል፡፡
“አገር እንደሚቀልብ ሰው አቅራራህ!”
“አሚር ጠጣ!” በጣም አናደደኝ፡፡
“ቱ… አፈር ብላ! አፈር ያስበላህ …! ምነው አንተ … እርጐ የጋበዝከው መሠለህ እንዴ … አስር ጊዜ አሚር ጠጣ የምትለው፤ ደግሞ ከየት ያመጣኸው ስድብ ነው … ያለወትሮህ …”
“ምን ላርግ እትዬ ንጋቷ … ሊያሳብደኝ ነው … አቃጠለኝ እኮ!”
“ቢሆንም ቀስ አድርገህ ምከረው…”
“ይሔ ብነክረውም አይርስ…!”
“አትሠልች… እንዳንተ ስራ እንዲወድ … እንዲያነብ … ቀስ እያልክ …”
“ኧረ ይሔ መጽሐፍ ገልጦ ከሚያነብ … የሴት ቀሚስ መግለጥ ይቀለዋል…!”
“እሱስ ተወው … ከማን ያየውን…”
ቀስ ብሎ ሳቀ፡፡ ህብስትም ለምን እንደሳቀች ሳላውቅ ከውስጥ እየተፍነከነከች ወደ እኛ መጣች፡፡ ወንድሜ መላጣውን እያሻሸ ሊወጣ ሲል … “ገለታ… መታጠፊያው ድረስ አግዘኝ…?” ድስቱን ጆሮና ጆሮውን አንጠልጥለው እንደ ባለጌ ህፃን ወጡ፡፡
“አየኸው የዋህ እኮ ነው…” እባኮት ሥለሚወዱት ነው … አልኩኝ በሆዴ፡፡ ቤት ገባሁና ቁልፍ ይዤ … በሩን ቆልፌ ልወጣ ስል…
“እ…እየውልህ… አምስቷን ቀን መስከረም አስር እምትሠጠኝ ላይ ደምረህ ሥጠኝ…!” ወገቤ ለሁለት የተከፈለ መሠለኝ፤ እንደ ማቅለሽለሽም አደረገኝ፡፡
“ማለት … ጳጉሜን ደምረዋት ነው…?”
“አዎ… አስራ ሶስት ወር ያላት ሐገር እያላችሁ ትፎልሉ የለም እንዴ”
“አምስት ቀን እኮ ናት”
“አንድም ቀን እድሜ ነው”
“እሱማ አዎ … ግን … የትም ቦታ እኮ ሒሳብ ላይ አይደመርም…”
“እንግዲህ የእኔን ቤት ከየትም ቦታ ጋር ከደመርከው ስህተት እየሰራህ ነው”
“አይደለም እኮ እትዬ ንጋቷ … መንግስት መስሪያ ቤትም ቢሆን እኮ አምስቷ ቀን ሒሳብ ላይ አትደመርም…”
“መንግስትን ተወው! ሌባ ስለሆነ ነው፡፡” ሊሆን ይችላል አልኩ በሆዴ፡፡
“እግዜርም ቢሆን እድሜአችን ላይ መች ይደምረዋል…” ለማራራት አስቤ ነበር፡፡
“እሱ ሞልቶት ስለተረፈው ነው”
“ምን…?”
“አንድዬ የእድሜ ካዝናው ሙሉ ስለሆነ እኛ ጉዳይ ውስጥ አትጥራው፡፡”
“ለዚህ ከባድ ጉዳይ እሱን ያልጠራን ማንን እንጠራለን?”
“እንግዲህ ተናግሬአለሁ … አምስቷን ቀን ደምረህ እንድታመጣ ብሬን! አይ የለኝም … የምትል ከሆነ … አምስቷን ቀን ከወዲሁ ብትቀንስ … ከወዲያ መስከረም አምስት ቤቴን ለቀህ እንድትወጣ!” ጭው አለብኝ፡፡ በዚህ የኑሮ ግለት … በዚህ የቤት እጦትና የኪራይ መወደድ ከዚህ ቤት ወጥቼ የትስ አገኛለሁ … እንዴትስ ከአቅሜ ጋር የሚመጣጠን ቤት ይገጥመኛል፡፡ አንገቴ ተቀንጥሶ ሊወድቅ መሠለ …
“አንተ ቀውላላ…”
“አቤት…”
“ምነው ተለጐምክ… ሥራ እየሰራሁ ነው አላልከኝም?… ይሔ ቲያትር ነው … ደግሞ ሩጫም ሮጣለሁ … አላልከኝም…? ሁለቱም እኮ ብራሞች ናቸው፡፡”
“አዎ” ቃላቱን መዘዝኩት፡፡
“እና… እምትሮጠውና ቲያትርህንም ደግሞ የደበቅኸኝ ፊልምም፣ ሴቶቹ ላይ ነው እንዴ የምትሠራው…? ልጄ መንገድ ላይ ባየሁህ ቁጥር ሴት አቅፈህ ነው፣ ትከሻህ አለመገንጠሉ … ትገለፍጣለህ … ጥርስህ አለመርገፉ፣ ህልምህን እየተገበሩልህ ይመስል ደግሞ … በየመንገዱ የተለጠፈው ፎቶህ ሳይቀር … ሴቶቹን አቅፈህ ነው … ምን አቅፈህ ብቻ … እያፈስክ ነው የሚመስለው፡፡” መሳቅ አማረኝ … ግን ከሳቅሁ እንባዬም እንደሚመጣ ገባኝ … አፈርኩ፣ ጥጣቸውን አስቀምጠው … በአነጋገራቸው የጠወለገውን ፊቴን ተመለከቱ…
“እህ… ምን አሠብክ…? የአምስቷን ቀን?”
“ኧረ… ፈጣሪም አይወደው … ምነው… ጠበል እንኳ በነፃ አይደለም እንዴ የምንጠመቀው…”
“እስቲ ሩፋኤልን በል…?” እሚያላግጡም መሠለኝ … ግን አይደለም፡፡
“እግዚአብሔርን…” አሁንም አተኩረው ተመለከቱኝ… ከምስኪን ፊቴ ላይ የሚያነቡት የሐዘን ደብዳቤ ያለ ይመስል፡፡
“እና አሁን ኑሮውን አልቻልኩም … ሥለዚህ የለኝም ነው የምትለው?!”
“አ…ዎ…” ቃላት ከጉሮሮዬ መውጣት አቃታቸው፡፡
“ምነው በከተማው ፎቶህን ከተለያዩ ሴቶች ጋር ተለጥፎ አየው የለም!”
“ምን… ያው… እያሰሩ እኮ አይሠጡንም…! እስክንሠራላቸው እንጂ ከዛማ … እኛ መለመን ሲገባን … እኛው ለማኞች ሆንን”
“ስራውንም የለማኝ አስመሰላችሁት … ቢሆንም … ህሊናህ ውስጥ ብስለት ካለጠፍክ … የከተማው ፎቶ ዋጋ የለውም፡፡ ጠዋት ያንተ ተለጥፎ ከሠዓት ደግሞ እንዳንተ ሴት ያቀፈ እላይህ ላይ ይለጠፋል፡፡ ምነው እንደዛ ባናት ባናቱ ከምትለጣጠፉ … አጠገብ ላጠገብ ብትሆኑ…”
“ያው… ሥሥታሞች አይደሉ … አንዱ ባንዱ ትከሻ ላይ መበልፀግ ይመኛል”
“አትሞኝ ላብህ የትም አትቀርም … በላብህ ያላገኘሀትን ገንዘብ ደግሞ ከሥር ከሥር በይ ያዝበታል” እኚህ ሴትዮ አንዳንዴ የሚያስደነግጥ ሐሳብ ይሠነዝሩብኛል … የቡጢ ያህል፡፡ እኔ ለራሴ ጭው እያለብኝ ነው፡፡ ሐሳባቸውን ሳላስጨርስ ልወጣ ስል …
“እና ምን ወሠንክ…?”
“እትዬ ንጋቷ … እስከዛሬም … ፍቅርዎትን … ነፃነትዎን ብለን የተቀመጥነው ኪራዩን ስለቻልነው ሳይሆን እናትነትዋ በልጦብን ነው፤ ስለዚህ … በቃ … እግዚአብሔር ያውቃል … ሌላ ቤት እፈልጋለሁ…” መራመድ ጀመርኩ፡፡
“ና…ና…” አይናቸው ውስጥ እንባ ይዋኛል፡፡ አቀረቀሩ… ደግሞ ቀና አሉ …
“ልጄ… ይሔ ልብስ እና እቃ ስትገዙ … የሚለጠፈው ታናሽ ታላቅ ነው… ምንድን ተብሎ የሚለጠፈው?”
“ታላቅ ቅናሽ?” ፊቴን ዘፍዝፌዋለሁ፡፡
“እህ … ላንተም ልዩ ታላቅ ቅናሽ አድርጌልሐለሁ” ልቤ ሆያ ሆዬ ደለቀች … አብዝቼ ፈራሁ… እንደ ፍቅር የሚያስፈራ ነገር የለም፡፡
“ኧረ እትዬ ንጋቷ … የምርዎን ነው?…”
“ስቀልድ ነው የኔ ልጅ … እኔ ክው ልበል … የእኔ ፊት ማድቤት ይምሠል… ልጄ ባዲሱ ዓመት ከምትሰጠኝ ላይ መቶ ሃምሣ ብር ቀንሼልሃለሁ … አንተ ደግሞ … መልካም ሥራህና ጥሩነትህ ይብዛ…! እምታንጠለጥላቸውን ሴቶች ደግሞ ቀነስ አድርግ! ካላወክበት አንዷም ሸክም ናት!”
በርከክ ብዬ ለእንዝርትና እና ለፍሙ የተገለጠውን ጉልበታቸውን ሳምኩ፡፡ ጣታቸውን ሰደው … ፀጉሬን ዳበሱኝ፣ እንባዬ አመለጠኝ… ጉልበታቸውን ለብ ያለ ነገር ሲዳብሳቸው …
“ምነው ልጄ … እንድታለቅስ እኮ አይደለም … የወንድምህን አመል ስለማውቅ፣ ኑሮውም ስለሚገባኝ … በዛ ላይ ስንት አመት ሙሉ አንገትህን ደፍተህ ትወጣለህ፣ አንገትህን ደፍተህ ትገባለህ … በሚገባ አክብረኸኛል … የማርያም ልጅ ያክብርህ፡፡ ለልጄም ወንድሞቿ እንጂ ሌላ ምኗ ነበራችሁ … እሰልል ነበር እኮ … የደረሠች ሴት ያለው መች እንቅልፍ ይተኛል። እዚህ ጊቢ መኖራችሁ በራሱ ለእኔ ክብር ነው፤ ለዛ ነው ልጄ እንደልቤ የምሆንባችሁ … እስቲ ያንዱን ችግር እንደራስ ችግር አድርገን እንተጋገዝ … እኔ ሞልቶኝ … እኔ ስቄ ስኖር … የሌላው ርሃብና እንባ … ድሎት ይሆነኛል…? አይሆነኝም፡፡ ልባችን አደይ አበባን ይሁን … ወቅት ጠብቆ ብቻም ሳይሆን ተኝተን ስንነሳ በነጋ ቁጥር ሁሌም ንፁህ ልብ ይኑረን … ማነው ‘አቤቱ ንፁህ ልብ ፍጠርልኝ’ ያለው … እንዲህ ነው ህይወትን መለመን፤ እምንካፈለው ችግር እና እምናካፍለው አያሳጣን ፈጣሪ … ያኔ መድኃኒያለም ጉልበቱን አይነፍገንም፡፡ አብሮ መሳቅማ በደስታህ ጊዜ ማንም መንገደኛ ያጫፍርሃል … እና ልጄ የምሬን ነው፡፡ በህይወት እስካለሁ ሲከፋችሁ ይከፋኛል … ሲርባችሁ ይርበኛል፡፡ አንተ በርትተህ ካየሁህ … የወንድምህን ነገር ለኔ ተወው… እቀይረዋለሁ… ምንም የተሻለ ነገር ሳይኖር “ተው! ተው!” ከአድርግ አይተናነስም”
በደንብ ቀና ስል … እንባዎቼን በቀኝ እጃቸው አበሱልኝ … ዶሮዎቹ … እኩል በሉ የተባሉ ይመስል … “ኩኩሉ” አሉ፡፡
በዶሮኛ … “እድሜዎት ይርዘም” መሠለኝ፡፡

Read 3199 times