Print this page
Saturday, 07 September 2013 11:02

ፅናት ላይ ያነጣጠረው “በርናባስ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“በርናባስ” በ2005 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ ለአንባቢያን የቀረበ ረጅም ልቦለድ ታሪክ ነው፡፡ በደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በ353 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እና በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ተዟዟሪ ፈንድ የታተመ ነው፡፡
ጽናት፤ የመጽሐፉ ማዕከላዊ መልዕክትና ጭብጥ ነው፡፡ ከዋና ገፀ ባሕሪያት የአንዱ ሥም ነው የመጽሐፉ ርዕስ የሆነው፡፡ “የመጽናት ልጅ” የሚል ትርጉም ያለው ይሄ ስያሜ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ነው፡፡ እምነቱ፣ ጽናቱና ታማኝነቱ ተረጋግጦለት “የመጽናት ልጅ” የተባለው የመጽሐፍ ቅዱሱ በርናባስ፤ የእርሻ መሬቱን የሸጠበትን ገንዘብ በሙሉ ለሐዋርያት ወስዶ በመስጠቱ ምክንያት ነበር ዮሴፍ የሚለው ቀዳሚ መጠሪያው ተቀይሮ በርናባስ የተባለው፡፡
“በርናባስ” የረጅም ልቦለድ ታሪክም ተመሳሳይ መልዕክት የያዘ ነው፡፡ ጽኑ ሆኖ ያሰቡት ግብ ላይ ለመድረስ ግን የሚታለፈው ችግርና መከራ ጥልቅና ሰፊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ ጽናት ምንድነው? መጽናትና አለመጽናትስ በምን ይመዘናል? መጽናት ምን ያስገኛል ምንስ ያሳጣል? በተቃራኒው አለመጽናትስ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ ይጋብዛል፡፡
የአንድ ዘመን ልጆች በአንዱ መንደር አድገው፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ተምረው …ከጊዜ በኋላ አንደኛው ገበሬ፣ ሌላኛው የጐዳና ተዳዳሪ፣ ከፊሎች ሴተኛ አዳሪ፣ የቢሮ ሠራተኛ፣ መምህር፣ ነጋዴ፣ ባለስልጣን….እንዲሆኑና በደረጃ እንዲለያዩ ምክንያቱ ከመጽናት አለመጽናት ጋር ይያያዛል ወይ? በዓላማው፣ በመርሁና በአቋሙ ፀንቶ የቆየውስ ጽናቱ የጉዳቱ ምክንያት ለምን ይሆናል? ዓላማ በሌለበትስ ጽናት ሲታይ ምን ማለት ይቻላል? ልቦለድ መጽሐፉን ያነበበ እነዚህን ጥያቄዎች ሊያነሳ ይገደዳል፡፡
መጽሐፉ ከሁለት አቅጣጫ እየፈሰሱ መጥተው በአንድ ወንዝ እንደሚገናኝ ውሃ አብረው መጓዝ የቻሉ ታሪኮችን አጣምሮ ይዟል፡፡ አንደኛው በልጅነታቸው የፍቅር ቃል ኪዳን የገቡ ሁለት ወጣቶች፤ ከአስር ዓመት በኋላ አንደኛቸው በሌላኛቸው ዘንድ ያኖሩትን አደራ የማግኘት ፍለጋን ያሳያል፡፡ ሌላኛው፤ በ1960ዎቹ ፖለቲካ ምክንያት ከአገር የወጡ ኢትዮጵያዊያን፤ በስደት ላይ እያሉ ተምረው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ምሁር ከሆኑ በኋላ፤ የማንነት ጥያቄ ሲያታግላቸው ቤተሰባቸውን ፍለጋ ወደ አገር ቤት ቢመጡም መሻታቸው ፈጣን መልስ ሊያገኝ አለመቻሉን የሚጠቁም ነው፡፡
ልቦለዱ የምልሰት ትረካዎቹን ዘመን ሳይጨምር ከ1991 እስከ 1997 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚያካልል ሲሆን ገፁ ባሕርያቱ በዋነኛነት የሚንቀሳቀሱት በደብረ ማርቆስና በአዲስ አበባ ከተሞች ነው፡፡ የደብረ ማርቆሱ ገፀ ባሕሪያት የልጅነት ታሪክ ብዙ የሚያስደምሙ ጉዳዮችን ይዟል፡፡
በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወንዶቹ በረባሶን፣ ሴቶቹ ደግሞ ኮንጐ ጫማን እንደ ብርቅ ያዩ ነበር። በዲጂታል ቁጥሮች የሚሰራም “ዲስኮ” ሰዓት ያለው ልጅ፣ ጓደኞቹን ያስደንቃል፡፡ በከፋይ ጨርቅ የሚሰራው የቻይናዎች የካራቴ ጫማ መጫማት ከፋሽን ተከታይነት በላይም ያስከብራል። ልጆቹ የሽቦ መኪና ሰርተው የሚነዱበት፣ ጭቃ አድበልቡለው ብይ የሚጫወቱበት፣ ተጠራርተው በሸርተቴ ጨዋታ የሚዝናኑበት የተለያዩ ጊዜያት አሏቸው፡፡
ፍሬን፣ ፍሪሲዮንና ነዳጅ መስጫ “ማርሽ ነው”፣ “አይደለም” ብለው በልጅነታቸው በደብረ ማርቆስ ሆነው ከተከራከሩት ጥቂቶቹ በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በዕድሜም ጨምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይገባሉ፡፡ የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪ በርናባስ አንዱ ነው፡፡ የዩኒቨርስቲው ጨዋታና ቀልዳቸው ግን እንደ ትምህርት ተቋሙ ከፍ ያለ ሆኗል፡፡
“ምትኩ ለማቲማቲክስ ልዩና ጥልቅ ፍቅር፣ ረቂቅ ችሎታ አለው፡፡ የሚነገረውን ማንኛውንም ነገር “ማቲማቲካሊ” ነው የሚረዳው፡፡ የሚያስበውም በዚያው በማቲማቲክስ ነው፡፡ ለምሳሌ በዓይን ፍቅር ወድቆላት “ዩቲሊቲ ማክሲማይዘር” ብሎ የሰየማት የአካውንቲንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ፍሬሰላም፤ እዚያው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ በር ላይ ታጥፋ መገናኛ ወደሚገኘው ሰፈራቸው ለመሄድ አንዳንዴ የምትይዛትን 64 ቁጥር አውቶብስ ካየ፣ የአውቶብሷን ቁጥር “Two to the power of six” ብሎ ጭንቅላቱ ውስጥ ይመዘግበዋል፡፡”
በቀልድ ፈጣሪነቱ በዩኒቨርስቲው ግቢ ዝነኛ መሆን የቻለው ሸዋፈራሁ ደግሞ “የ R kellyን I Believe I can fly” ዘፈን ወደ አማርኛ ተርጉሞ “አልበር እንዳሞራ ሰው አርጐ ፈጥሮኛል” እንዳለው በሰፊው ተወርቶበታል፡፡ History of Economic Thought ደግሞ “ሥነ ስስታዊ እሳቤ” በሚል ሀገር በቀል ትርጓሜ አስተዋውቋል፡፡”
በደብረ ማርቆስ በአንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ ከነበሩት ተማሪዎች ጥቂቶች ለዩኒቨርስቲ በቅተው ወደ ታላቅ ደረጃ የሚያደርሳቸውን መስመር ሲይዙ፣ ከፊሎቹ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነዋል፡፡ ትምህርቱን አቋርጦ ገበሬ የሆነ አለ፡፡ ሌላኛዋ በአዲስ አበባ ከተማ በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርታ፣ ደብረ ማርቆስ የሚገኙ ቤተሰቦቿን ትረዳለች፡፡ የልጆቹ ዕጣ ፈንታ፣ ከመጽናትና አለመጽናት ጋር የተያያዘ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ይገፋፉናል፡፡
“ሸሌ ተንኮለኛ ካልሆነች ክፉ ወንድ አይገጥማትም” የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሰችው ዊንታ የምትባል ገፀ ባሕሪ፤ በችግር ምክንያት ከደብረ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሴተኛ አዳሪ ለመሆን ያሰበች ጓደኛዋን ለማዳን ብዙ ትለፋለች፡፡ ጥረቷ እንዳልተሳካ ስታይ፤ ጓደኛዋ መልካም እንዲገጥማት ለወንዶች ክፉ እንዳትሆን ትመክራታለች፡፡
ዊንታ በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በኤችአይቪ (ኤድስ) እስከ መያዝ የደረሰ ብዙ ችግርና መከራ ቢገጥማትም አገር፣ ትውልዱንና ሕብረተሰቡን በመታደግ ሥራና ተግባር ላይ እንደተሰማራች የምታስብበት ጊዜም አለ፡፡ በየቤቱ ብዙ ጉድ አለ የምትለው ዊንታ፤ የሚወዳቸው ሚስትና ልጆች ያሉት አባወራ፤ ከቤቱ ያጣውን እኛ ዘንድ ለማግኘት ይመጣል ትልና “በቃ ሰላሙን አግኝቶ ይመለሳል፡፡ ለምን ቢባል፤ ለጊዜያዊ ሰይጣን፣ ለሚያልፍ ስሜት ኑሮውን ይበጠብጣል? እንዲያውም ባይገርምሽ በኛ ምክንያት የስንት ሰው ትዳር ከመፍረስ እንደዳነ?” ትላለች፡፡ እስከዳር ሌላኛዋ የደብረ ማርቆስ ልጅ ናት። በትምህርቷ እስከ ኮሌጅ ዘልቃ በመመረቅ፣ በሙያዋ ተቀጥራ ትሰራለች፡፡ ለወንዶች ያላት አመለካከት፤ ከሴተኛ አዳሪዋ ዊንታ ጋር ሲነፃፀር መቶ በመቶ ፐርሰንት ተቃራኒ ነው፡፡ “የገጠሟትና በቅርበትም የምታውቃቸው ወንዶች ሁሉም ማለት ይቻላል ክፉዎች፣ ራስ ወዳዶች፣ ከጊዜያዊ ደስታ አርቀው ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ፣ ልብ አውልቆች” ብላ ነው የደመደመችው፡፡
እነዚህ ታሪኮች ስለ መጽሐፉ አስተኔ ገፀ ባሕሪያት የተነገሩ ናቸው፡፡ ዋናው ባለታሪኮች በርናባስና እሌኒ ናቸው፡፡ ሁለቱ ወጣቶች በልጅነታቸው የፍቅር ቃል ኪዳን ገብተው ከተለያዩ ከ10 ዓመት በኋላ ሲፈላለጉና ተገናኝተውም በመሟገትና በመካሰስ ቃላቸውን ስለመጠበቃቸውና በጽናት ስለመቆየታቸው በብዙ ገፆች ይተረክላቸዋል፡፡ ደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም፤ ስለ ጽናት ምንነት ለማሳየት የሞከሩት የዋናና አስተኔ ገፀ ባሕሪያትን ሕይወት፣ ዓላማና ግብ በንጽጽር በማቅረብ ነው፡፡
የጽናት ምንነት ማሳያ ሆነው የቀረቡት ሌላኛው ባለታሪክ ቤተሰባቸውን ፍለጋ ከባህር ማዶ ወደ አገራቸው የመጡት ምሁርና በዙሪያቸው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ባለታሪኩ በአንድ ወቅት በጽናት የታገሉለትና ለስደት የዳረጋቸው አመለካከትና አቋም ነበራቸው፡፡ ከስደት ተመልሰው ቤተሰባቸውን ሲያፈላልጉ እና ለአገር ይጠቅማል ባሉት የልማት ሥራ ላይ ሲንቀሳቀሱም ጽናት ይታይባቸዋል፡፡ ያለፈውን ዘመን በሚተቹበት ሃሳብ “ከጥቂት ወራት በኋላ እንዳረጀ ልብስ አውልቀን ልንጥለው በምንችልው ፍልስፍናችን ምክንያት ስንለያይ እንታያለን፡፡
ከዚያም እርስ በእርሳችን መደማመጥ፣ መታገስና መቻቻል እየተሳነን ሄዷል፡፡ ለዚህ ነበር ስንገዳደልና ስንሞት፣ ስንተላለቅ መቆየታችን” እያሉ ያዝናሉ፡፡ ይህ ደግሞ የዛሬ ሀዘናቸውንና የቀድሞ ዘመን ጽናታቸውን እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? ማስታረቅ ካልተቻለስ ጽናት ምንድነው? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡
ሀንፍሬ የሚባሉት እኚህ ገፀ ባሕሪ ካለፈው ትውልድ በተሻለ በአሁኑ ዘመን ወጣቶች ላይ የተሻለ እምነት ያሳደሩ ይመስላል፡፡ የእውነተኛ ጽናት ማሳያ ምሳሌ ሆነው የቀረቡት በርናባስና እሌኒን የሚያግዙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም፤ በሕብረተሰባችን ውስጥ ያለውን ጽናትና በተቃራኒው ጽናቱን የሚፈታተኑ ብዙ ማሳያና ትርክቶችን አቅርበዋል፡፡ ዋናው ገፀ ባሕሪያት (በርናባስና እሌኒ) ከ10 ዓመት በኋላ ሲገናኙ አንዳቸው ሌላኛቸውን ቃል ኪዳን አፍርሷል በሚል የተፈጠረባቸውን ጥርጣሬ ለማጥራት በምክንያታዊ ክርክር፣ በግልጽ ውይይት፣ በይቅርታና ንስሀ የደረሱበት እውነት ጽናታቸውን አረጋግጦላቸዋል፡፡ የደራሲ ትዕግሥቱ ተክለማርያም እምነትና ተስፋም በዚህ ተንፀባርቋል፡፡ የዛሬ ወጣቶች ለጽናትም ሆነ ለኃላፊነት ተስፋ የሚጣልባቸው ትውልዶች ናቸው ከሚለው በመነሳት መጽሐፋቸውን ያዘጋጁት ይመስላል፡፡

Read 2687 times
Administrator

Latest from Administrator