Saturday, 07 September 2013 10:35

የተሻለ አዲስ ዓመት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁማ!
ምን መሰላችሁ…ደግነቱ እንደ ድሮ “በአዲሱ ዓመት ዕቅድህ ምንድነው?” ምናምን ብሎ የሚጠይቅ ሰው ቁጥሩ በጣም ቀንሷል፡፡፡ ልክ ነዋ…ለሳምንት እንኳን ማቀድ ባልተቻለበት…“ለከርሞ ገንዘብ አጠራቅሜ ሶፋ እለውጥና…” ምናምን ብሎ ነገር ያስቸግራላ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ እኮ፣ አይደለም ‘ሶፋ ተለውጦ’ የተቀደደ ብረት ድስት ሲበየድ ከታየ አንዳንዱ አከራይ (አሁን፣ አሁን… “አብዛኛው አከራይ…” ልንል እየቀረብን ነው) “እነኚህ ደልቷቸዋል ማለት ነው…” ብሎ ኪራይ ይጨምራል፡፡
አዲሱ ዓመት… ለቤት ኪራይም ይሁን ለሌሎች አገልግሎቶች ተገቢ ክፍያ ከመጠየቅ ይልቅ …አለ አይደል… ከተገልጋዮች የወር ገቢ በ‘ፐርሰንት መካፈል’ አይነት ተመን የሚያወጡትን ልብ ይስጥልንማ!
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን የመልካም ምኞት መግለጫ ስሙልኝማ…“አዲሱን ዓመት ይቺን ወሬኛ ምላስህን የምትሰበስበበት እንዲያደርግልህ እመኛለሁ፡፡” አሪፍ አይደለች! የእውነት እኮ ግን…ዘንድሮ ‘ጦር ከፈታን፣ ወሬ የፈታን’ ቁጥራችን የበዛንበት ዘመን ነበር፡፡ አንዱ ወሬ ገና እውነትነቱንና ውሸትነቱን ለማረጋገጥ እየሞከርን ሌላ አንድ መቶ ወሬ ይፈለፈላል። እናላችሁ…“ታማኝ ከሆኑ የወሬ ምንጮች እንዳገኘነው…” ለመባባል እያቃተን ነው፡፡ ‘ኦፊሻል’ በሉት ‘አንኦፊሻል’ በሉት…አለ አይደል…እያንዳንዱ ወሬ በ‘ሀምሳ ምናምን አይነት’ እየቀረበ…የግል አመለካከትና ‘ጠጣር እውነት’ የሚሉት ነገር እየተደበላለቀ...በአንድ ቋንቋ እንኳን እየተነጋገርን መግባባት አቅቶናል፡፡
አዲሱ ዓመት እረፍት ያጣ እንደሚመስለው ‘መናገሪያ አንደበታችን’ ሁሉ ‘ማዳመጫ ጆሯችንም’ የሚከፈትበት ዓመት ይሁንልንማ! ከ‘ምላሳችን ጫፍ’ ሳይሆን ከ‘ልባችን ጥልቀት’ መልካም ምኞት የምንለወዋወጥበት አዲስ ዓመት ይሁንልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ እኛ ዘንድ በዓል ማለት… አለ አይደል…ምግብ፣ ምግብና ምግብ ብቻ እየሆነ በእንቁጣጣሽ ለየጎረቤቱ የአበባ ስዕል መሰጣጣት እንኳን ‘ጊዜ እያለፈበት’ ነው፡፡
የሚሰጡ ቢኖሩ እንኳን በመልካም ምኞት መግለጫነት ሳይሆን በቤት ለቤት የሽያጭ ሥራ አይነት ነው፡፡ እግረ መንገዴን… አንዳንድ አገሮች አዲስ ዓመትን እንዴት እንደሚቀበሉ የሆነ ቦታ ያነበብኩትን ስሙኝማ…ኢኳዶር በምትባል የደቡብ አሜሪካ አገር ያለ የአዲስ ዓመት አከባበር እንዴት መሰላችሁ… የፖለቲካ መሪዎችና ሌሎች በህዝብ የሚጠሉ ሰዎችን ምስሎች በአሻንጉሊት መልክ ይሠሯቸዋል፡፡ እነኚህ አሻንጉሊቶች በአሮጌ ጋዜጦች፣ በጭድና በአሮጌ ልብሶች የሚሠሩ ሲሆን ተቀጣጣይ ርችቶች ይውሸቁባቸዋል፡፡ የየአካባቢው ነዋሪዎች እነኚህኑ አሻንጉሊቶች ይዘው ሌሊት ላይ ይሰበሰባሉ፡፡ ከዛ ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው… አሻንጉሊቶቹን ዶጋ አመድ ያደርጓቸዋላ! ይህ ልማድ እንዲሁ የሚደረግ ሳይሆን ትርጉም አለው። ይኸውም የመጪውን ዓመት መጥፎ መናፍስት መቃጠልና የአዲሱን ዓመት መቀበል ተምሳሌት ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛ አገር እንዲህ አይነት ባህል ቢኖር ኖሮ ለአሻንጉሊቶች መሥሪያ የሚበቃ አሮጌ ልብስ ይኖራል! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እዛው ደቡብ አሜሪካ ፑዌርቶ ሪኮ በምትባለው አገር ደግሞ ምን ይደረጋል መሰላችሁ… አሮጌውን ዓመት አጥቦ ለማባረር ነዋሪዎቹ መስኮቶቻቸው ላይ በባድሊ ውሀ ይደፋሉ፡ ቤቶቻቸውንም አጽድተው በጌጣ ጌጥ ያንቆጠቁጧቸዋል፡፡
እዚህ እኛ ዘንድ፣ አይደለም መስኮቶቻችን ላይ ውሀ ልንደፋ…ብዙ ቦታ ውሀ እንደ ማግኘት…አለ አይደል… የደሞዝ እድገት ከማግኘት የበለጠ ‘አንገብጋቢ ጉዳይ’ ሆኗል፡፡ በተለይ ይሄ እየወጣ ያለው ዓመት በውሀና በመብራት ማዳረስ በኩል አሪፍ አልነበረም፡፡ ውሀ ተርፎን በመስኮት ላይ እንድንደፋ የምንበቃበት ዘመን መምጫው ይፍጠልንማ!
የአየርላንድ ተወላጆች የአገራቸውን የወደፊት ፖለቲካዊ አካሄድ ለማወቅ በአዲስ ዓመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት የነፋሱን አቅጣጫ ያያሉ፡፡ እናም በነፈሰበት አቅጣጫ መሠረት በአዲሱ ዓመት የአገራቸው ፖለቲካ ‘እኩይ’ ይሁን ‘እርጉም’ ይተነብዩበታል፡፡ (እኔ የምለው… ባለፉት ብዙ ዓመታት የእኛው ደመራ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነበር እንዴ የሚወድቀው! አሀ… ዘመንም አንዱ ሄዶ ሌላው በተተካ ቁጥር…አለ አይደል… ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ሲመስል አሪፍ አይደለማ!)
በአሜሪካ ደግሞ ምን አይነት ባህል አለ መሰላችሁ… በአዲስ ዓመት እኩለ ሌሊት ላይ ከፍቅረኛ ወይም ደግሞ ከማንኛውም ሌላ ሰው ጋር የመሳሳም ልማድ አለ፡፡ ይህ መጪውን ዓመት እጅግ ውብ ያደርገዋል ተበሎ ይታሰባል። እውነተኛ ፍቅር ያመጣል ተብሎ ይታመናል፡፡ ያለፉትን መጥፎ ትውስታዎችና ዕጣ ፈንታዎች አስወግዶ አዲሱን ዓመት በአዲስ ፍቅርና በአዲስ ህይወት ለመጀመር ያስችላል ይባላል፡፡ እናላችሁ… እንደውም ይህንን የአዲስ ዓመት ልማድ ተከትሎም ‘ኢን ሰርች ኦፍ ኤ ሚድናይትስ ኪስ’ የሚል ታዋቂ ፊልም ተሠርቷል፡፡
እዚች ላይ እንኳን እኛ ባንወዳደራቸው ነው። አዲስ ዓመት የለ…ምን የለ ይኸው ‘ወጣት የነብር ጣት’ በሉት፣ ‘ጎልማሳ’ በሉት…በጠራራ ፀሀይ በየአደባባዩ ‘ኪሶሎጂ’ እያጦፈላችሁ አይደል! ‘አማሪካኖቹ’ ይቺን እንኳን ‘ከእኛ ቢማሩ’! አሀ…365 የ‘ኪሶሎጂ’ ቀናት እያሉላቸው ምን ዓመት ያስጠብቃቸዋል! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…እንቁጣጣሽ አንዱ በጣም ደስ የሚለው ሰዎች ከልባቸው ለአዲሱ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹላችሁ ነው፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤናና የደስታ ይሁንልህ መባል በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡
ብቻ መጪውን ዓመት በሁሉም በኩል ‘የወሬ’ ሳይሆን ‘የእውነት’ አዲስ ዓመት ያድርግልንማ!
“ከብረው ይቆዩ ከብረው
በዓመት ወንድ ልጅ ወልደው
ሠላሳ ጥጆች አስረው
ከብረው የቆዩ ከብረው”
እያሉ ወጣት ሴቶች ከልብ የመነጨ ምኞት የሚያሰሙበትን ዘመን ያምጣልንማ!
“የእማምዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት
የአባብዬን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት”
እያሉ ወጣት ወንዶች ከልብ የመነጨ ምኞት የሚያሰሙበትን ዘመን ያምጣልንማ!
ከዓመት ዓመት “ሊነጋ ሲል ይጨልማል…” እያልን ራሳችንን የምንሸነግልበት ዘመን አልቆ የእውነትም ለሁላችንም ‘እኩል የሚነጋበትን’ ዘመን ያምጣልንማ!
እናላችሁ…ከአንጀታችን፣ ከልባችን ሎሬት ጸጋዬ ከዘመናት በፊት እንደጻፈው…
“ነጋ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ፣ ፀደይ አረብቦ
ሌሊቱ እንደ ጎሕ ቀደደ፣ ጨለማው እንደ ቀን ጠራ
እንደ ውቅያኖስ ዕፅዋት፣ እንደ ጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ስጋጃ ለበሰ፣ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በዕልልታ ተቀባ
እዮሀ መስከረም ጠባ፡፡”
እንድንል የምንበቃበት… በኑሯችንም፣ በእርስ ለእርስ ግንኙነታችንም፣ ለዚች መከረኛ አገር ባለን ራዕይም ፅንፍ ለጽንፍ ከመሆን ይልቅ ይበልጡኑ የምንቀራረብበትን ዘመን ያምጣልንማ!
“ከሳሽን ጠቆርሽን ይለኛል ባላገር
የሆዴን አውጥቼ ለስንቱ ልናገር”
ከሚሏት እንጉርጉሮ ነጻ የሚያወጣን ዘመን ይምጣልንማ!
“መሄዴ ነው መልቀቄ ነው ከአገር
እንቅቡም ሰፌዱም ነካካኝ በነገር”
እያልን በር ዘግተን የምንቆዝምበት እስከዘላለሙ በማይመጣ መልኩ ይጥፋልንማ! (‘ሰባኪ’ ነገር መሰልኩ እንዴ!)
መልካም የዋዜማ ቀናት ይሁኑልን፡፡
መልካምና የተሻለ አዲስ ዓመትም ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4902 times Last modified on Saturday, 07 September 2013 10:41